Skip to main content
x
የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይሰፋ ማደናቀፍ ነውር ነው!

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይሰፋ ማደናቀፍ ነውር ነው!

የአገር ሰላም አስተማማኝ ሆኖ የሕዝብ ደኅንነት የሚጠበቀው፣ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ሲነሳ ራሱ ሕግ አክባሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሕግ ማክበር የሚመነጨው ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበር፣ በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ አድራጊ ፈጣሪ ከመሆን በመቆጠብ፣ ባለሥልጣናት በገደብ የለሽ ሥልጣን ብልግና ውስጥ እንዳይገቡ በመቆጣጠር፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ከሕገወጦችና ከሥርዓተ አልበኞች በመከላከል፣ በዜጎች መካከል አንዳችም ዓይነት ልዩነት እንዳይኖር በማድረግና በመሳሰሉት ተግባራት ነው፡፡ መንግሥት ራሱን ከማናቸውም ህፀፆች በመጠበቅ ኃላፊነቱን የመወጣት ችሎታ ማዳበር የሚችለው፣ ጠንካራ የዴሞክራሲና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ግንባታ ሲያከናውን ነው፡፡ ይህንን ለማስፈጸም ደግሞ አንቱ የተባሉ የተመሰከረላቸው ባለሙያዎችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ማሰማራት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ዓይነቱ መንገድ መራመድ ሲችል የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ይሆናል፡፡ ጠንካራዋንና ዴሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያ መገንባት የሚቻለው በዚህ ሁኔታ የተደራጀ መንግሥት መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ሰፊ ምኅዳር እንዳይፈጠር ማደነቃቀፍ ነውር መሆኑ በግልጽ መነገር አለበት፡፡

ያለንበት ወቅት ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ የመጀመርያው የዘመናት ችግሮችን በተባበረና በተደራጀ መንገድ በመፍታት ወደፊት መራመድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዘመናት ችግሮችን ታቅፎ ማላዘን ነው፡፡ ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ሁለተኛውን አማራጭ አይፈልግም፡፡ ነገር ግን የዘመናት ጠባሳን እያከኩ ከዚያ የተረገመ የክፋት ጎዳና አንወጣም እያሉ የሚያስቸግሩ እንዳሉ ግን መዘንጋት አይገባም፡፡ በየምክንያቱ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ለማደናቀፍ የሚሯሯጡና ከግል ጥቅም በላይ የጋራ የሆነው የአገር ጉዳይ የማይሰማቸው አሉ፡፡ ለእነሱ አገር ማለት ጠበብ ያለ ስብስብ፣ ራዕይ ማለት የቡድን አጀንዳ፣ ሕዝብ ማለት የጥቅም ተጋሪ፣ ለውጥ ማለት የህልውናቸው መርገምት ነው፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከሕዝብ በተቃራኒ እየዘወሩ ግጭት መቀስቀስ፣ የንፁኃንን ደም ማፍሰስና ማፈናቀል፣ የአገር አንጡራ ሀብት ማውደምና ወጣቶችን በመማገድ ህልውናቸውን ማስቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በፓርላማ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ ‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሰፋ ረዥም ርቀት መሮጥ የማይችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትንፋሽ ያጥራቸዋል፤›› ያሉዋቸው ናቸው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ ኢትዮጵያን በተባበረና በተደራጀ መንገድ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሸጋገር፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ተሳትፎ የበለጠ አብቦና ጎምርቶ መታየት የሚችለው ግን በተናጠል በሚደረግ እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ በተደራጀ መንገድ ሲከናወን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ስብስቦች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ብቁ ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ ብቃት ደግሞ የፖለቲካ ጨዋታን ሕግ ከማወቅ ይጀምራል፡፡ የዴሞክራሲ መሠረታዊ አላባዊያንን ሳያውቁ ወይም ሆን ብለው ወደ ጎን እየገፉ፣ የፖለቲካ ፓርቲ መምራትም ሆነ መደራጀት ፋይዳ የለውም፡፡ አለው ቢባል እንኳ ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡ ስለሆነም የፖለቲካው ምኅዳር እንዲሰፋ በሩ ወለል ማለት ሲጀምር የነገዋ ዴሞክራሲያዊት አገር እንዴት እንደምትገነባ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ በተለመደው የአጥፍቶ ጠፊነት ጎዳና ላይ እየተንጎማለሉ በኋላቀር አስተሳሰብ ከመወጣጠር፣ በተቻለ መጠን ሥልጡኑን ጎዳና በፍጥነት መምረጥ ይገባል፡፡ ሕጋዊነትንና ሕገወጥነትን እያጣቀሱ አገር ማመስም ሆነ ሕዝብን ማተራመስ እንደማይቻል ማወቅ አለባቸው፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት ራሱ ሕግ አክብሮ ማስከበር ያለበት፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ ያሉ ወገኖችም ከምንም ነገር በላይ ሕግ እንዲከበር በፅናት መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከፈተው ምኅዳር ውስጥ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የሚቻለው፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ የጋራ ባህሪ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ባህሪ የጋራ ሆኖ በነፃነት መንቀሳቀስ ሲቻል በምርጫ ጊዜም ሆነ በአዘቦት ምንም ዓይነት ችግር አይፈጠርም፡፡ በአገር ውስጥ የነበሩም ሆነ ከውጭ የገቡ ፓርቲዎች በሙሉ እኩል ሆነው መወዳደር ወይም መፎካከር የሚችሉት ሕግ ሲከበር፣ ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፉክክር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ ሕዝብ የተሻለ ሐሳብ ወይም አጀንዳ ያለውን በነፃነት ይመርጣል፡፡ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደ መሆኑ መጠን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ልብ ለመማረክ ለሐሳብ የበላይነት መጨነቅና መጠበብ አለባቸው፡፡ የሐሳብ የበላይነት ሲጠፋ ነው ወንጀል ውስጥ የሚገባው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አንድ እግርን እዚህ አንድ እግርን እዚያ እያንፈራጠጡ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ሕገወጥነት ነው፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ በጣም ከባድ፣ ትልቅ ዕገዛ የሚፈልግ፣ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ የሚያሻውና ሙሉ ጊዜን መጠቀም የሚጠይቅ ነው፡፡ በተጨማሪም የትኛውም ዓይነት ችግር ውስጥ ቢገባ እንኳ ከሰላማዊ ይልቅ ወደ ኃይል ጎዳና በቀላሉ የማይገቡበት፣ ትዕግሥትና አርቆ አሳቢነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተከፍቶ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ዕድል ሲፈጠር፣ ከዴሞክራሲ ባህል አፈንግጦ አገር ማተራመስ በሕግ ማስጠየቅ አለበት፡፡ ከመጠን በላይ ትዕግሥት በማሳየት አንዳንዶች ደረታቸውን እንዲያሳብጡና እንደ መንደር ጎረምሳ እንዲያስቸግሩ መፍቀድ አይገባም፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልገው አንድነቷን፣ ሰላሟንና ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችል ፓርቲ ነው፤›› እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ በተቃራኒ የአገር ህልውናን የሚፈታተን ኃይልን በሕግ አደብ ማስገዛት የጊዜው ዓብይ ጥያቄ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳር እየሰፋ ጠበበኝ የሚሉ ካሉም የራሳችሁ ጉዳይ መባል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ድርጊታቸው ነውር ስለሆነ!