Skip to main content
x
የሕወሓት አመራር አባል የነበሩት ሹም ከድርጅቱ መልቀቃቸውን አስታወቁ
አቶ ዛዲግ አብረሃ

የሕወሓት አመራር አባል የነበሩት ሹም ከድርጅቱ መልቀቃቸውን አስታወቁ

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዴሞክራቲያዜሽን ማዕከል አስተባባሪ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት እንግሊዝ አገር በትምህርት ላይ የሚገኙት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አመራር አባል አቶ ዛዲግ አብረሃ፣ ከድርጅቱ በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ፡፡ ለሕወሓት ልዩ ዞን ጽሕፈት ቤት ባለ አምስት ገጽ የመልቀቂያ ደብዳቤም አስገብተዋል፡፡

አቶ ዛዲግ ለድርጅቱ ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳስታወቁት፣ ከድርጅቱ ለመልቀቅ የወሰኑት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው ሕወሓት በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለውን ለውጥ የሚቃወመው መሆኑን፣ ሁለተኛው ደግሞ የራያ ሕዝብ ከወንድሙ የአማራ ሕዝብ ጋር አንድ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ ላቀረበው የማንነት ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ አፈሙዝ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

እሳቸው ራሳቸው ከራያ ሕዝብ ውስጥ የመጡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በዚህም ምክንያት በጥርጣሬ ይታዩ እንደነበር ባቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ወጣትነት በሕወሓት ውስጥ ላለመታመን ምክንያት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አመራር ወቅት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዴሊቨሪ ዩኒት ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው ሲሠሩ ከሕወሓት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን አስታውሰው፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ሲወሰን እሳቸው በሚመሩት ተቋም ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ በመገለጹ ለምን የፖለቲካ እስረኞች ይባላል ተብሎ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደተፈጸመባቸው ጠቁመዋል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች በመፈታታቸውም የሕወሓት አመራሮች ደስተኛ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡ እሳቸው ግን አገሪቱን ወደ ትልቅ እስር ቤት እየቀየሩት የነበረው የአምባገነኖች ዕርምጃ መቆም እንዳለበት ያምኑ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

አቶ ዛዲግ በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው አፅንኦት የሰጡበት ሌላው ጉዳይ ሕወሓት በአገሪቱ እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጋር አብሮ ለመራመድ ፈቃደኛ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከለውጡ በተቃራኒ መቆሙ ድርጅቱን ለቀው ለመውጣት ዋናው ምክንያታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ለውጡ የትግራይንና የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጠቅም ሆኖ ሳለ፣ ሕወሓት በጥቂት ጠባብና ፀረ ለውጥ ኃይል በመጠለፍ ከአገራዊ ለውጡ ጎን ሊሠለፍ አልቻለም ብለዋል፡፡

‹‹ሕወሓት ለጥቂት ባለሥልጣናት ሲባል አፍራሽ ተግባር ውስጥ ገብቷል፤›› ሲሉ በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው ገልጸው፣ ሕወሓት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የገባበት የገዘፈ ስህተት ከድርጅቱ ለመለያየት እንዳስወሰናቸው አመልክተዋል፡፡

የራያን ሕዝብ ጥያቄ በተመለከተም ያለ ፈቃዱ በመካለሉ ምክንያት በሚያቀርበው ተቃውሞ ሲገደልና ሲሰደድ እንደነበር ገልጸው፣ ያልተደራጀው ተቃውሞው ለጥቃት አጋልጦታል ብለዋል፡፡ አሁን ግን የራያ ሕዝብ በተደራጀ ሁኔታ ወደ ትግል መግባቱን ጠቁመው፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከሕወሓት ጠቅልሎ ለመውጣት ሌላው ምክንያታቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከጥንት ጀምሮ ለነፃነት ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር አብሮ የተዋደቀውን የትግራይ ሕዝብ ዛሬ እንደ ሰብዓዊ ምሽግ ተጠቅመው ሊለያዩት ቢሞክሩም፣ ይህ የአክራሪ ወንጀለኞች የቀን ቅዠት እንደ ጉም መብነኑና መክሸፉ የማይቀር ነው፤›› ብለው፣ ኢትዮጵያዊነትን ከትግራይ ሕዝብ ልብ ላይ መፋቅ እንደማይቻልና ዛሬም ላዩ ላይ ተጋድመው የተጫኑትን ቀንበሮች ሰብሮ ለዳግም እኩልነትና ነፃነት እንደሚበቃ ጥርጥር የለኝም ብለዋል፡፡

‹‹ፀረ ለውጥና ፀረ ዴሞክራሲ ከሆነ ድርጅት ጋር ለመቀጠል ህሊናዬ ስላልፈቀደ በገዛ ፈቃዴ የለቀቅኩ መሆኑን አስታውቃለሁ፡፡ በቅርቡም ሊያታግለኝ ከሚችል ድርጅት ጋር በመቀላቀል ለራያና ለመላው የአገሬ ሕዝብ የሚጠቅመውን ለውጥ ለማገዝ እንደምሠራ አስታውቃለሁ፤›› በማለት የወደፊት ዓላማቸውን አሳውቀዋል፡፡

አቶ ዛዲግ ከመስከረም 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በእንግሊዝ መንግሥት ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡