Skip to main content
x

የጥር ወር የዋጋ ግሽበት በ10.9 በመቶ ጨመረ

በዚህ ዓመት ጥር ወር የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጋር ሲነፃፀር በ10.9 ከመቶ መጨመሩን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አደረገ፡፡

ኤጀንሲው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ዓመት ጥር ወር አኳያ በ10.9 በመቶ ከፍ ሲል፣ የምግብ ዋጋ ግሽበትም በዚህ ዓመት ጥር ወር ካለፈው ዓመት ጥር ወር አኳያ በ11.5 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ አስታውቋል፡፡ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮው ጥር ወር በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም የእህል ዓይነቶች ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡

የጤፍ ዋጋ በሁሉም ክልሎች ጭማሪ አሳይቷል፡፡  የስንዴ፣ የሩዝ፣ የማሽላና የዘንጋዳ ዋጋ ላይ ግን በተለይ በዋና ዋና ክልሎች ውስጥ መጠነኛ ቅናሽ ታይቷል፡፡ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በአትክልት ዋጋ ላይም በክልሎች መረጋጋት እንደሚታይ ኤጀንሲው ገልጿል፡፡ ይሁንና በሥጋ፣ በቅቤ፣ በወተት፣ በዓይብና በዕንቁላል እንዲሁም በቅመማ ቅመም ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ባልሆኑ የዋጋ ግሽበት መመዘኛ (ኢንዴክሱ) ክፍሎች አኳያም የዘንድሮው የጥር ወር ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጋር ሲነፃፀር የ10.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ምግብ ነክ ካልሆኑ የዋጋ ግሽበት መመዘኛው ክፍሎች ውስጥ ግሽበቱ ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ፣ የልብስና መጫሚያ፣ የቤት እንክብካቤና የኢነርጅ በተለይም የከሰል ዋጋ፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ የትራንስፖርት፣የሕክምናና በሆቴሎች የተወሰዱ ምግቦችና መጠጦች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት መሆናቸውን የኤጀንሲው ወርኃዊ መግለጫ አሳይቷል፡፡