Skip to main content
x
በተጓተቱ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሳቢያ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ አጋጥሟል ተባለ
አቶ ሐጂ ኢብሳ

በተጓተቱ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሳቢያ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ አጋጥሟል ተባለ

- በግማሽ ዓመቱ 98 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል

ገንዘብ ሚኒስቴር በግማሽ ዓመቱ የታየውን የበጀት አፈጻጸም በማስልከት ማክሰኞ፣ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ከ102 መሥሪያ ቤቶች የ1,000 ፕሮጀክቶችን ዝርዝር ሒደት የሚያሳይ መግለጫ ወይም ፕሮፋይል ተሰናድቶ ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የ43.1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውን አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ እንዳስታወቁት፣ በዚህ ዓመት ከተወሰዱ የማሻሻያ ዕርምጃዎች አንዱና የ100 ቀናት ዕቅድ አካል የሆነው የፕሮጀክቶችን ፕሮፋይል ማዘጋጀት ነው፡፡ በዚህም መሠረት 102 መሥሪያ ቤቶች 1,000 ፕሮጀክቶችን ፕሮፋይል ወይም የአፈጻጸም ወቅታዊ ሒደትን አመላካች ዝርዝር መግለጫዎች ቀርበዋል፡፡ አንድ ሺሕ ፕሮጀክቶቹ ምን ያህል በጀት እንደተመደበላቸው፣ መቼ ተጀምረው ማለቅ እንዳለባቸው ወይም እንደነበረባቸው፣ ከተጓተቱም ምን ያህል ወጪ እንዳስከተሉ በተደረገ ማጣራት፣ ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመታት የዘገዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ታይቷል፡፡ እነዚህ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችም 43.1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አስከትለዋል፡፡ እንደ አቶ ሐጂ ገለጻ፣ ይህ የገንዘብ መጠን ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዘንድሮ ከተመበደለት በጀት ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ በጀት 46 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ችግሮች ነበሩባቸው ያሉት አቶ ሐጂ፣ 113 ቢሊዮን ብር በዚህ ዓመት ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንዲውል መመደቡን፣ ሆኖም ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፕሮጀክቶች መግለጫና አፈጻጸም ሒደትን የሚያመላክት ዝርዝር የክንውን ሒደትን የሚያሳይ ሰነድ እንደማይቀርብ ይናገራሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ መቼ ጀምረው እንደሚያልቁ፣ በየዓመቱ ምን ያህል በጀት እንደተጠቀሙ፣ በአካል የሚታየውና በሪፖርት የሚቀርበው አፈጻጸም አለመጣጣም፣ የፕሮጀክት ክትትል ደካማነት፣ የፕሮጀክቶች ሒደት በማኅደር ተሰንዶ ክትትልና ወቅታዊ ግምገማ አለማድረግ የሰነበቱ ችግሮች ነበሩ፡፡ በዚህ ሳቢያም የጥራት፣ የመጓተት፣ ያለ በቂ ጥናትና አንዳንዴም ያለምንም ጥናት ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ሥራ ሲገቡ መቆየታቸው ተወስቷል፡፡ ፕሮጀክት እንዲገነቡ ከተቋራጮች ጋር የሚገባው ውል ደካማነትም ተጠያቂነት ሲያጓድል እንደቆየ ዋቢ የተደረገው ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የተገቢ ውሎች ይጠቀሳሉ ተብሏል፡፡

እንዲህ ያሉ የአፈጻጸም መጓተቶች የሚያስከትሏቸውን ኪሳራዎችና አላስፈላጊ ዕዳዎች ለመቀነስ የመንግሥትን ፕሮጀክቶች ሒደት፣ ትግበራቸውንና የተመደበላቸውን በጀት አጠቃቀምና ሌላውን ዝርዝር ጉዳይ የሚቆጣጠር ተቋም በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እየተቋቋመ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ይህም ሆኖ በዚህ ዓመት ከፀደቀው 346.9 ቢሊዮን ብር የዓመቱ በጀት ውስጥ ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም አቶ ሐጂ ተናግረዋል፡፡ ይህ በጀት ካምናው የ12.1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ወይም የ3.6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያስታወሱት ኃላፊው፣ በ2008 ዓ.ም. እና 2009 ዓ.ም. የተሰበሰበው ገቢ እንደታቀደው ስላልነበር የዚህ ዓመት በጀትም ብዙ እንዳይለጠጥ መደረጉንም አውስተዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ይሰበሰባል ከተባለው ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም፡፡ በ2009 ዓ.ም. ያልተሰበሰበው ገቢም ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡

ዘንድሮ ከተመደበው ውስጥ 91.7 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪዎች፣ 113.6 ቢሊዮን ብር ለካፒታል፣ 135.7 ቢሊዮን ብር ለክልሎች፣ ስድስት ቢሊዮን ብር ለዘላቂ ልማት ግቦች፣ በድምሩ 346.9 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት መመደቡ ይታወሳል፡፡ ለካፒታል ወጪዎች ከተመበደው ውስጥ 67 በመቶው ከመንግሥት ግምጃ ቤት ወጥቶ ሥራ ላይ እንደሚውል የዘረዘሩት አቶ ሐጂ፣ 16.4 ቢሊዮን ብር ከዕርዳታ፣ 18.5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከብድር እንደሚገኝ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ የካፒታል በጀት የሚመደብላቸው የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የከተማ ልማትና የመሳሰሉት መስኮች ሲሆኑ፣ ከመንግሥት ግምጃ ቤት ከሚመደበው በጀት ውስጥ አብዛኛው ከታክስ የሚሰበሰብ ነው፡፡

በስድስቱ ወራት 98 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲሰበሰብ፣ ይህ ገቢም ለበጀት ዓመቱ ከተያዘው 41 በመቶውን እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው ዓመት አኳያ የ7.5 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ የገቢ አፈጻጸሙ ሲታይም  በስድስቱ ወራት 85 ቢሊዮን ብር ወይም 87 በመቶ ከታክስ (ከ346 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 213 ቢሊዮን ብር ከታክስ የሚሰበሰብ ነው) ሲገኝ፣ 12 ቢሊዮን ብር ታክስ ካልሆነ ገቢ፣ አንድ ቢሊዮን ብር ከቀጥታ የበጀት ዕርዳታ ተሰብስቧል፡፡

እንደ አቶ ሐጂ ገለፃ፣ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ ከሚጠበቀው ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም፡፡ በ2010 ዓ.ም. እንዲሁ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ከታክስ አልተሰበሰበም፡፡ ለዚህም ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በታክስ ገቢው ላይ ጫና ሲያሳድር በመቆየቱ ነው ብለዋል፡፡ የታክስ ገቢ ከኢኮኖሚው ጥመርታ አንፃር በ2012 ዓ.ም. 17 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ዓመትም 15.9 በመቶ ይደርሳል ቢባልም፣ 10.7 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ግን 12.7 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን እየወረደ በመምጣት የታክስ አሰባሰቡ ደካማነት እያጎላው ይገኛል ተብሏል፡፡ የታዳጊ አገሮች የታክስና የኢኮኖሚ ሬሾ አማካይ 22 በመቶ ሲሆን፣ የአፍሪካ አማካይ 18 በመቶ ገደማ ነው፡፡ የኬንያ 18 በመቶ ነው ያሉት አቶ ሐጂ፣ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የታክስ ገቢ የምትሰበሰብ አገር ሆናለች ይላሉ፡፡

ታክስ እንደሚጠበቀው የማይሰበሰበውም በታክስ ማጭበርበርና ስወራ ምክንያት ነው ያሉት አቶ ሐጂ፣ የአገሪቱ ሰላም ዕጦትና ግጭቶች በታክስ አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመላክታል ብለዋል፡፡

ከገቢ መዳከም ባሻገር ያላግባብ የሚወጡ ወጪዎችም ለበጀት አጠቃቀም ችግሮች ትልቅ ድርሻ ስለነበራቸው፣ ዓምና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የወጣው የወጪ ቅነሳ መመርያ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት 600 ሚሊዮን ብር ወጪ ቅነሳ ምክንያት ማዳን ተችሎ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ በዚህ ዓመት የበጀት ዝውውር ተከልክሏል፡፡ ለሕትመት ወይም ለመሰል ወጪዎች የተመደበውን ለዚያው ለተመደበለት የወጪ ዘርፍ ከመጠቀም ውጪ ለሌላ ተግባር በጀቱ እንዲዛወር ማድረግ ተከልክሏል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት ተጨማሪ በጀት ሊመድብ እንደሚችል፣ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

በአገሪቱ በጀት ላይ ፈተና የሆነው ሌላው ጉዳይ የወጪ ንግድ መዳከም ሲሆን ይህም በአገሪቱ በጀት ላይ ለረጀም ዓመታት ጫና ሲያሳድር የቆየ ነው፡፡ እስከ ታኅሳስ መጨረሻ የነበረው የአምስት ወራት የወጪ ንግድ ገቢ 977.6 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሐጂ፣ ከ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 1.77 ቢሊዮን ዶላር አኳያ ሲነፃፀር ቅናሽ በ99.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም በ9.2 በመቶ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ የወጪ ንግድ ገቢው በተለይ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ በተለይም ከ2003 ዓ.ም. ይገኝ ከነበረውም ያነሰ ገቢ እየተመዘገበ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም. አራት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቶ ነበር፡፡

የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃላል በማለት በ2009 ዓ.ም. የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ እንደነበርና በዚያው ዓመትም አራት ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ዓምናም አራት ቢሊዮን ብር መለቀቁን፣ በዚህ ዓመት ደግሞ 950 ሚሊዮን ብር ወደ ክልሎች መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁንም ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 91.3 በመቶ መሠራጨቱ ተጠቅሷል፡፡ 875 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚቀርና አራት ክልሎች ግን ድርሻቸውን ሙሉ ለሙሉ መውሰዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አማራ፣ ደቡብ፣ ሐረሪና ድሬዳዋ የድርሻውን በሙሉ  እንደወሰዱ ሲገለጽ፣ ትግራይ ክልል 105 ሚሊዮን ብር ይቀረዋል ተብሏል፡፡ አፋር 123 ሚሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ 344 ሚሊዮን ብር፣ ሶማሌ 241 ሚሊዮን ብር፣ ቤንሻንጉል 133 ሚሊዮን እንዲሁም ጋምቤላ 15 ሚሊዮን ብር እንደሚቀራቸው ታውቋል፡፡  

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ለማዞር፣ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ማሰለፉ ይታወሳል፡፡ ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታ የሚዛወሩ የመንግሥት የልማት ድርጀቶች ዝርዝርም ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በከፊል ወደ ግል ይዞታ የሚዘዋወሩ ናቸው፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ላይ ዝርዝር ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ አራቱ ተራ በተራ ወደ ግል የሚዛወሩ ሲሆን፣ ቅድሚያውን የወሰደው ግን የቴሌኮም ዘርፉ ነው፡፡ ዘርፉ ላይ ወቅታዊ ጥናቶች መካሄዳቸውንና ሰነዶችም መዘጋጀታቸውን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የኩባንያውን ጠቅላላ ሀብትና ዕዳ የሚተነትን ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ይህንን ሒደት የሚያስተባብር ኮሚቴም ተዋቅሯል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የውጭ አማካሪዎች ከኢትዮ ቴሌኮም ባለሙያዎች ጋር በመሆን በሒደቱ እየተሳተፉ ነው፡፡

በተለይም ኢትዮ ቴሌኮም ወደፊት በከፊል ወደ ግል ሲዛወር የሚመራባቸው ሕጎችና አሠራሮች ስለመዘጋጀታቸውም ተጠቅሷል፡፡ የዓለም ባንክ ባለሙያዎች በሒደቱ ተሳትፈውበታል፡፡ የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ በሚመለከታቸው የመስኩ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል ያሉት አቶ ሐጂ፣ በተለይም የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት የሚደረግበትና የሚመራበትን አግባብ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሻሽሎና ፀድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለመላኩም ጠቅሰዋል፡፡