Skip to main content
x
የቬንዙዌላ ቀውስ
ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከግራ፣ ሚስተር ሁዋይን ጋይዶ

የቬንዙዌላ ቀውስ

በቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና በተቀናቃኛቸውና የሽግግር መንግሥትነትን ለራሳቸው ባቀዳጁት ሁዋን ጋይዶ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ቬንዙዌላውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ መንግሥታትንም ከፋፍሏል፡፡

ሁዋን ጋይዶ ራሳቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርገው ካሳወቁና ምርጫ እንዲካሄድ ከጠየቁበት ከ15 ቀናት በፊት አንስቶ አገሪቷ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡

ፕሬዚዳንት ማዱሮ የጋይዶን አካሄድ ‹‹ሕገወጥ›› በማለት ባይቀበሉትም፣ ተቃዋሚዎች በየጊዜው ሠልፍ በመውጣት ጋይዶን ሲደግፉ ተስተውለዋል፡፡ የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ለፕሬዚዳንት ማዱሮ ድጋፍ የሰጠ ቢሆንም፣ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ግን ለጋይዶ ድጋፍ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡

የቬንዙዌላ ቀውስ
100 ሺሕ ያህል ቬንዙዌላውያን በአሜሪካ የሚኖሩ ሲሆን፣ ብዙዎቹም ፕሬዚዳንት ማዱሮ ተቃውመዋል።

አሜሪካ ራሳቸውን ‹‹ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ነኝ›› ብለው ካወጁት ጋይዶ ጎን ተሠልፋለች፡፡ በአሜሪካና በቬንዙዌላ መካከል ያለው ግንኙነት ከዚህ ቀደምም የሻከረ ሲሆን፣ ሁለቱም አገሮችም ዲፕሎማቶቻቸውን ከየአገሮቹ እንዳስወጡ ይታወሳል፡፡

ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ ከአሜሪካ በተጨማሪ ሕጋዊ የምርጫ ሽግግር ባልተከናወነበት ‹‹ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ነኝ›› ላሉት ጋይዶ፣ ድጋፍ የሰጡ የአውሮፓ አገሮችም አሉ፡፡

ኦስትሪያ፣ ብሪታንያ፣ ክሮሺያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስፔን፣ ስዊድንን ጨምሮ 17 የአውሮፓ አገሮች ለሚስተር ጋይዶ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ የአውሮፓ አገሮች ለሚስተር ጋይዶ ድጋፍ የሰጡትም፣ ፕሬዚዳንት ማዱሮ የአውሮፓ ኅብረት በቬንዙዌላ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ይካሄድ ብሎ ያስቀመጠውን ሐሳብ ባለመቀበላቸው ነው፡፡

የላቲን አሜሪካ መንግሥታትም ቢሆኑ ለፕሬዚዳንቱ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ፣ ለሚስተር ጋይዶ ድጋፍ መስጠትን መርጠዋል፡፡ አብዛኞቹ የላቲን አሜሪካ አገሮችና ካናዳ የቬንዙዌላ መከላከያ ኃይል የተቃዋሚ መሪውን ሚስተር ጋይዶ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሚስተር ጋይዶም፣ ራሳቸውን የሽግግር ፕሬዚዳንት ነኝ በማለት አውጀው ከአሜሪካ፣ እስራኤልና ከበለጸጉ አገሮች ድጋፍ አግኝተዋል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ተመርጠው ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ማዱሮ ‹‹ሕጋዊ የአገሪቱ መሪ ነኝ›› ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ የእሳቸውን ሐሳብም የአሜሪካን በየቦታው ጣልቃ መግባት የሚቃወሙት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ቱርክ፣ ኩባ እና ኢራን ደግፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከወር በፊት ከፕሬዚዳንት ማዱሮ ጋር ተገናኝተው ነበር

አሜሪካና ተባባሪዎቿ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ጣልቃ መግባታቸውን የሚቃወሙትና በምድረ ሶሪያ ጎራ ለይተው የውክልና ጦርነት የሚያካሂዱት ኢራን፣ ሩሲያና አሜሪካ በቬንዙዌላ ጉዳይም ጎራ ለይተው ተሠልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ማዱሮ ግን የዓለም መንግሥታት በቬንዙዌላ ጉዳይ መከፋፈልና፣ በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን ላልያዘው ሚስተር ጋይዶ ድጋፍ መስጠት በቬንዙዌላ የእርስ በርስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንዳንድ አገሮች እየተገለሉ የመጡትን ፕሬዚዳንት ማዱሮ የምትደግፈው ሩሲያም፣ አሜሪካ ማንኛውንም ወታደራዊ ዕርምጃ እንዳትሰነዝር አስጠንቅቃለች፡፡ በቬንዙዌላ ሕጋዊ ያልሆነ የሥልጣን ሽግግርን አሜሪካ መደገፏንም አውግዛለች፡፡

ለተሽመደመደው የቬንዙዌላ ኢኮኖሚ መልካም አበዳሪ የሆነችው ሩሲያ፣ ለቬንዙዌላ መከላከያ ሠራዊት ትጥቅ የጀርባ አጥንትም ናት፡፡

ሩሲያ በቬንዙዌላ ትልቅ ኢንቨስትመንት ቢኖራትም፣ ቻይናም ለቬንዙዌላ አንድ ትልቅ አበዳሪ ናት፡፡ ቻይና ነዳጅን ጨምሮ የቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶችን በቬንዙዌላ ታንቀሳቅሳለች፡፡

የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም የምታራምደው ኩባ ከርዕዮተ ዓለም አቻዋ ቬንዙዌላ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ ላለፉት ሁለት አሥር ዓመታትም የጠነከረ ወዳጅነትን መሥርተዋል፡፡ ቬንዙዌላ ኩባን በነዳጅ ዘይት ስትደጉም፣ ኩባ ደግሞ ለቬንዙዌላ በሕክምና ዘርፉና በወታደራዊ አማካሪነት ትደግፋለች፡፡ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ቬንዙዌላና ኩባ በዚህ ቀውስ ወቅትም አልተለያዩም፡፡ ኩባ ለፕሬዚዳንት ማዱሮ ድጋፍ ከሰጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ናት፡፡

የረዥም ጊዜ የሶሻሊዝም አቀንቃኞቹ ኒካራጓ እና ቦሊቪያም ለፕሬዚዳንት ማዱሮ ድጋፍ ቸረዋል፡፡ ሜክሲኮ ገለልተኛ አቋሟን ስታንፀባርቅ፣ ቱርክ ለማዱሮ ደግፋለች፡፡ ኢራን የሚስተር ጋይዶን ድርጊት በማውገዝ ለፕሬዚዳንቱ ድጋፍ የሰጠች ሲሆን፣ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም ‹‹ኢራን የቬንዙዌላን ሕዝብ ትደግፋለች፡፡ ማንኛውንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ማንኛውንም ሕገወጥና ተቀባይነት የሌለው እንደ መፈንቅለ መንግሥት ያለውን አካሄድ ታወግዛለች፤›› ብለዋል፡፡

የቻይናው ፕሬዚዳንት
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢጂንፒንግ ቬንዙዌላን ለመርዳት ቃል ገብተዋል

ፕሬዚዳንት ማዱሮ ተቃውሞ የገጠማቸው ለምንድነው?

እ.ኤ.አ. በ2013 የአገሪቱን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሁጐ ቻቬስ ሞት ተከትሎ ሥልጣን የያዙት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በቅጡ ባለማስተዳደር ይተቻሉ፡፡

በአገሪቱ የምግብና የመድኃኒት እጥረት እንዳለም ይነገራል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በየ19ቀኑ በእጥፍ እየጨመረ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ከአገራቸው ተሰደዋል፡፡ ከ2014 ወዲህ ብቻ ሦስት ሚሊዮን ቬንዙዌላውያን ከአገራቸው መሰደዳቸውንም የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል፡፡

በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ቬንዙዌላ የሚመሩት ማዱሮም ተቃውሞው የጀመራቸው ከሥልጣናቸው ማግስት ቢሆንም፣ እንዲህ ፀንቶ የተገለጠው አሁን ነው፡፡

የውጭ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ ከአገሬውም ወጣቱን ጋይዶ ደግፈው ሠልፍ እየወጡ ነው፡፡ ሆኖም የወጣቱ ጋይዶ አመጣጥ ሕግን የጣሰና ሕጋዊ ምርጫን ያልተከተለ ነው፡፡ ራሳቸውንም የሽግግር ፕሬዚዳንት ነኝ ብለው ሹመዋል፡፡

መሪዎች በሕጋዊና በግልጽ ምርጫ ወደ ሥልጣን መምጣት አለባቸው የሚሉት አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ሌሎችም የሠለጠኑ አገሮች ሕግን ባልተከተለ መንገድ የሽግግር ፕሬዚዳንት ነኝ ለሚሉት ሚስተር ጋይዶ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ የአገሬው ሕዝብም ሆነ ሌሎች አገሮች ፕሬዚዳንት ማዱሮንና ሚስተር ጋይዶን በመደገፍ መከፋፈላቸው ፕሬዚዳንቱ ማዱሮ እንደፈሩት ቬንዙዌላን የእርስ በርስ ጦርነት መናኸሪያ ያደርጋት ይሆን?

(ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)