Skip to main content
x
ሥርዓተ ምግብ ላይ ያተኮረ ግብርና
አርሶ አደሩ ስለ ግብርናው መረጃ በቀጥታ የስልክ መስመር በመደወል ማግኘት ይችላል

ሥርዓተ ምግብ ላይ ያተኮረ ግብርና

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በግብርና እንደሚተዳደር በሚነገርላት ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና አሁንም ድረስ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው ግብርና ዜጎቿን እንኳ መመገብ አልቻለም፡፡ ለምለምና የተመቸ የአየር ንብረት አላት በምትባለው በኢትዮጵያ እስከ 72 ሚሊዮን ሔክታር የሚታረስ መሬት አለ፡፡ ይሁንና ከዚህ ውስጥ የሚታረሰው 20 ሚሊዮን ሔክታር አይሞላም፡፡ በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢ የገበሬው ጥያቄም በቂ የእርሻ ቦታ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡

80 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር የሚያርሰው 12 ሚሊዮን ሔክታሩን ብቻ ነው፡፡ አጠቃላይ ሊታረስ ከሚችለው መሬት ውስጥ አንድ ሦስተኛው ማንም ዞር ብሎ የማያየው ባክኖ የቀረ ሀብት ነው፡፡ ይህም ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ይውላል ማለት አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ ከሚያርሰው 12 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ከፊሉ የተራቆተና ፍሬ የመስጠት ዕድሉ የመነመነ ጪንጫ ነው፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተው ድርቅም የአገሪቱ ደጀን የሆነውን የአርሶ አደሩን ማሳ በከፍተኛ መጠን የሚያጠቃ ትልቅ ባለጋራ ነው፡፡ ይህም አገሪቱ ከባድ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ተዘፍቃ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው አመዛኙ አርሶ አደር ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ግብርናን ሙጥኝ እንዲል ያስገድዱታል፡፡ ይህም የአርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቹን ኢትዮጵያውያን የምግብ ዋስትና ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሀቅ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በ2.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ የሚለማው ስንዴ በቂ ባለመሆኑ 20 በመቶ የሚሆነው ስንዴ የሚገባው ከውጭ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ስንዴ በገፍ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል፡፡ ካላቸው ምርታማነት አኳያ በቆሎና ስንዴ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ተመርጠው እየተሠራባቸው ይገኛል፡፡ የበቆሎ ምርታማነት በምርምር ጣቢያዎች በሔክታር 134 ኩንታል፣ ስንዴም እንዲሁ በሔክታር 80 ኩንታል ደርሷል፡፡ በአርሶ አደሩ ማሳ እየተመረተ የሚገኘው ግን በቆሎ በሄክታር 34 ኩንታል፣ ስንዴ ደግሞ 24 ኩንታል ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እነዚህን ሒደቶች አልፎ የሚመረተው ምርት ከማሳ ተሰብስቦ ጎተራ እስኪገባ ባለው ሒደት ውስጥ እስከ 35 በመቶ የሚሆነው በድህረ ምርት ይባክናል፡፡ በየዓመቱ ከሚለሙ የእህል ምርቶች መካከል 18 በመቶ የስንዴ፣ 12 በመቶ የጤፍ፣ 12 በመቶ የማሽላ፣ 12 በመቶ የገብስ ምርት እንደሚባክን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡ የ2009 ዓ.ም. የምርት ሁኔታ ሲታይም 50,204,400.47 ኩንታል ጤፍ ተሰብስቧል፣ 6,024,528.06 ኩንታል ደግሞ ባክኗል፡፡ 20,249,216.76 ኩንታል ገብስ የተሰበሰበ ሲሆን፣ 2,429,906.01 ኩንታል ባክኗል፡፡ በአጠቃላይ በዓመቱ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መመገብ የሚችል ምርት እንዳይሆኑ ሆኗል፡፡

ከዚህ ሁሉ አልፎ ለምግብነት የሚውለውም ቢሆን ከችግር የፀዳ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት አኳያ የራሱ ክፍተት እንዳለበት ይነገራል፡፡ በተራቆተ ማሳ ላይ የሚበቅሉ የግብርና ምርቶች ለአካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በበቂ አይዙም፡፡ ይህም ማኅበረሰቡ ካለው የተመጣጠነ ምግብ አመጋገብ ችግር ጋር ተደምሮ ዜጎችን ለቅንጨራ ሲዳርግ የቆየ እውነታ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ 67 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች የቀነጨሩ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ 38.4 በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕፃናት የቀነጨሩ ናቸው፡፡ 9.9 በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትም የመነመኑ ናቸው፡፡

ይህንን አገራዊ ችግር እ.ኤ.አ. በ2022 ለመቅረፍ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ዕቅዱ ግቡን እንዲመታም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ግብርና ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ አርሶ አደሮች በማሳቸው ላይ በቋሚነት ከሚያለሟቸው የግብርና ምርቶች ጎን ለጎን በተለያዩ ለሰውነት ጠቃሚ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የተሞሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲያለሙ የሚያበረታታ ፕሮግራም ነው፡፡

ፕሮግራሙ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማግኘት እንዲችሉ እንዲሁም በምን ዓይነት መንገድ ማልማት እንደሚችሉ፣ የድህረ ምርት አያያዙንም በተመለከተ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት የሌላቸውና ተጋላጭ ለሆኑ አርሶ አደሮች ቅድሚያ ሰጥቶም ይሠራል፡፡ በዩኤስአይዲ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ሲተገበር የቆየው ይህ ፕሮጀክት እስከ 2021 የሚቆይ ይሆናል፡፡ ከስድስት ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከአምስት የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚከናወን ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆንም በ8028 ቀጥታ የስልክ መስመር አርሶ አደሩ ሥርዓተ ምግብ ተኮር የሆኑ የግብርና መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችለው አሠራር ባለፈው ሳምንት ይፋ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት በጋራ በመሆን የጀመሩት መረጃን በስልክ የማቅረብ ሥርዓት በንግግርና በጽሑፍ መልዕክት የሚተላለፍ ይሆናል፡፡

መረጃዎችን የሚያዘጋጀውና በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን የሚያሰናዳው ሴቭ ዘ ቺልድረን ይሆናል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሊድ ቦምባ መረጃ ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ግን ሌላ ወሳኝ ጉዳይ ነው በማለት ለአርሶ አደሩ የሚደርሰው ወቅታዊ መረጃ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሠራሩ በአንዴ ሚሊዮኖችን ለመድረስ ዓይነተኛ መንገድ ነው ያሉት በኢትዮጵያ የሴቭ ዘ ቺልድረን ዳይሬክተር ኤኪን ኦጉቶጉላሪ አርሶ አደሩ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚፈጠርበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 የተጀመረው 8028 የስልክ ጥሪ በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ እስካሁን አራት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተመዝግበው አገልግሎቱን እያገኙ ይገኛሉ፡፡ አገልግሎቱ በተጀመረ በመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ጥሪዎች ከ300 ሺሕ በላይ ከሚሆኑ አርሶ አደሮች ደርሶታል፡፡ ባለፈው ሳምንት በሂልተን አዲስ ሆቴል ኤጀንሲውና ሴቭ ዘ ቺልድረን ባከናወኑት የመግባቢያ ሰነድ ፍርርም አዲሱ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያተኮረው የግብር ስልክ መስመር ሥራ ጀምሯል፡፡