Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ስልክ ይደውልላቸዋል]             

 • ጋሼ እንዴት ነህ?
 • ዛሬ ከየት ተገኘህ ጎረምሳው?
 • አንተ እኮ ነው የጠፋኸው ጋሼ?
 • የእኛን ሥራ እያወቅከው?
 • አዎ ግን በጣም ነው የጠፋኸው፡፡
 • ስማ ሪፎርሙ ነዋ፡፡
 • ሪፎርሙ ምን ሆነ ጋሼ?
 • የቤት ሥራ አለብና፡፡
 • ትምህርት ጀመርክ እንዴ ጋሼ?
 • ሪፎርሙ በራሱ እኮ ከባድ ትምህርት ቤት በለው፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው የመቶ ቀናት የቤት ሥራ ተሰጥቶን ነዋ፡፡
 • እውነትህን ነው እንዴ ጋሼ?
 • እህሳ የመቶ ቀናት የቤት ሥራ የሚሉት ፈተና አምጥተውብናል፡፡
 • ታዲያ እናንተ በመድፈን የታወቃችሁ ናችሁ፡፡
 • መድፈን ስትል?
 • ማለቴ ምርጫውንስ ያው ከመቶ መቶ አይደል እንዴ ያመጣችሁት?
 • እሱ እኮ ድሮ ቀረ፡፡
 • እንዴት?
 • አሁን ዝም ብሎ መድፈን አይቻልም፡፡
 • አልገባኝም ጋሼ?
 • ማለፊያውን ራሱ ካገኘህ ጎበዝ ነህ ማለት ነው፡፡
 • ከመቶ 51 ማምጣት?
 • አዎን፡፡
 • አንተማ በመድፈን አትታማም ጋሼ፡፡
 • ይኼ እውነተኛ ፈተና ነው ስልህ፡፡
 • ምንም ቢሆን አንተ መቶ የምትለዋን ቁጥር እንደምትወዳት አውቃለሁ፡፡
 • ማን ነገረህ?
 • ይኸው ሀብትህ ራሱ መቶ ሚሊዮን እንደደረሰ ሰምቻለሁ፡፡
 • ኧረ ዝም በል፡፡
 • ይቅርታ ጋሼ፡፡
 • ዛሬ ግን የእውነት ከየት ተገኘህ?
 • እኔማ እንዴት ሳትነግረኝ ብዬ ነው የደወልኩት?
 • ምኑን?
 • መከፈቱን ነዋ፡፡
 • አገር ሁሉ ሆቴል መክፈቴን ሰምቶ አንተ አሁን ገና ሰማሁ ልትለኝ ነው?
 • የሆቴሉን መከፈትማ ሰምቻለሁ፣ እኔ ስለሌላ ነገር ነው የማወራው፡፡
 • ምንድነው የተከፈተው ታዲያ?
 • የሚኒስትሮች ምክር ቤት አለህበት አይደል እንዴ?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • ታዲያ የአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ለሁሉም ክፍት የሚያደርግ ሕግ እየተረቀቀ አይደል?
 • እያረቀቅን ነው ምነው?
 • አሁን በእርግጥ ሪፎርም ላይ እንደሆንን ገባኝ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በቃ ዘርፉ ክፍት ከተደረገ እኛም መሳቀቅ ልናቆም ነዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ጋሼ መቼ እንቅልፍ ተኝቼ የማድር መሰለህ?
 • ለምን?
 • ከነገ ዛሬ ተያዝኩ እያልኩ አይደል እንዴ የምኖረው?
 • በምን ምክንያት?
 • ጋሼ ባለፈው በኮንትሮባንድ ያስመጣህልኝ ዕቃ ትዝ አይልህም እንዴ?
 • አንተም የጦር መሣሪያ ንግድ ውስጥ አለህበት እንዴ?
 • አይ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡
 • ምን እየሠራህ ነው?
 • የዓለም አቀፍ ጥሪዎችን አስተናግዳለሁ እኮ?
 • አሃ… ጥሩ ገቢ ታገኛለህ ማለት ነው?
 • ኧረ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው ጋሼ፡፡
 • ከእጅ ወደ አፍ ስትል?
 • ይኸው ከሦስት መኖሪያ ቤት ውጪ ምን አለኝ? ሕንፃ እንኳን መገንባት አልቻልኩም?
 • እሱማ መገንባትህ አይቀርም፡፡
 • ይኼ አጋጣሚማ በደንብ ሊያስገነባኝ እንደሚችል ገብቶኛል፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ ቴሌ ሴንተሬን እቀይራለኋ፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ቴሌኮም ኦፕሬተር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር ይገናኛሉ]                

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ምነው ጣል ጣል አደረጉኝ?
 • አንተን እንዴት እጥልሃለሁ?
 • እኔማ ውለታዬን እንዴት ረሱት እያልኩ ነበር፡፡
 • እንዴት ይረሳል ወዳጄ?
 • ያን ሁሉ ነገር አሳልፈን ግን አሁን ዘነጉኝ፡፡
 • አንተ እንዴት ትዘነጋለህ?
 • ሙሉ ለሙሉ ነው እንጂ ፊትዎን ያዞሩብኝ፡፡
 • ኧረ ተው ወዳጄ፡፡
 • እውነት ተናገር ካሉኝ እንደዚህ ይሆኑብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡
 • ምን ሆንኩ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ የሚያምርብን እኮ ስንደመር ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እኛ እኮ ከዘመናት በፊት ነበር የተደመርነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • ወዳጅነታችን እኮ ከሪፎርሙም በፊት የነበረ ነው፡፡
 • እሱማ እውነት ነው፡፡
 • ስለዚህ እኛ የሚያምርብን እንደ ቀድሞአችን ስንደጋገፍና ስንተጋገዝ ነው፡፡
 • የእኔም እምነት እንደዚያው ነው፡፡
 • ስለዚህ ከሪፎርሙ በፊት የመደመርን ጽንሰ ሐሳብ ያመጣነው እኛ ነን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ልክ ነው ወዳጄ፡፡
 • ምን ልልዎት ነው ያን ሁሉ ድንጋይ የፈነቀልነው እርስ በርሳችን በመተጋገዛችን ነው ለማለት ነው፡፡
 • ሙሉ ለሙሉ እስማማለሁ፡፡
 • ታዲያ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ፊትዎን ያዞሩብኝ?
 • መቼ አዞርኩብህ?
 • ከሰው በታች አደረጉኝ እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን አድርጌ?
 • ይኸው ማንም እየተነሳ አይደል እንዴ አለቃችሁ ጋ የሚገባው?
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ታዲያ እኔ ከጓደኞቼ በምን አንሼ ነው የማያስገቡኝ?
 • መግባት ፈልገህ ነው?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለመሆኑ ምን ጉዳይ ገጥሞህ ነው?
 • ስንትና ስንት ፕሮጀክቶቼ እንደመከኑብኝ ያውቁ አይደል እንዴ?
 • እነሱማ ሕገወጥ እንደሆኑ ታውቃለህ?
 • እሱማ እኔስ መቼ ከሕገወጥ ነገር ውጪ ሠርቼ አውቃለሁ?
 • ታዲያ ሌላ ምን ጉዳይ ኖሮህ ነው መግባት የምትፈልገው?
 • እሱማ ለጉዳይ አይደለም መግባት የፈለግኩት፡፡
 • ታዲያ ለምን መግባት ፈለግክ?
 • ለማጎብደድ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]  

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰሞኑን በቴሌቪዥን ሳይህ ነበር፡፡
 • እንዴት አዩት ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም ነው ያዘንኩት፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለመሆኑ መቼ ነው የምትሻሻሉት?
 • አልገባኝም?
 • አንዳንዴ የአገሪቱን ፖለቲካ በቅጡ የምትረዱት አይመስለኝም፡፡
 • እንዲህ ማለት አይችሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን አልልም?
 • እኔ እኮ በፖለቲካ ነው ጥርሴን የነቀልኩት፡፡
 • አሁን የቀረውን ጥርሳችሁንም ፖለቲካው እንዲነቅለው ነው የምትፈልጉት?
 • ተመልሳችሁ አምባገነን የመሆን ሐሳብ አላችሁ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን ጠየቅከኝ?
 • የቀረችውን ጥርሳችሁን ፖለቲካው ይነቅልላችኋል ሲሉኝ ድጋሚ ልታስሩን ነው ወይ ብዬ ነዋ?
 • እናንተማ እሱን የምትፈልጉት ይመስለኛል፡፡
 • ለምን እንፈልገዋለን?
 • አሁን አጀንዳችሁን ተነጥቃችኋላ?
 • እኛ መቼ አጀንዳ ጠፍቶብን ያውቃል?
 • ዓየናችሁ እኮ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሪቱ በምን ዓይነት ሪፎርም እየሄደች እንዳለች እንኳን ማመን አትፈልጉም፡፡
 • እሱ ያጠያይቃል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ነገርኩህ እኮ፡፡
 • ምኑን?
 • እናንተ የተካናችሁበት ሥራ አንድና አንድ ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • ማጠልሸት፡፡
 • እንደዚያ አይበሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • በዚያ ላይ ደግሞ የእርስ በርሳችሁ መናናቅ ያሳፍራል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሲኒየሩም አዲስ መጪውም እኩል ነው እያሉ ነው?
 • ቢያንስ በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ መስማማት ያስፈልጋል እኮ?
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ሕዝቡ እኮ ከእናንተ ብዙ ነው የሚጠብቀው፡፡
 • ምንድነው የሚጠብቀው?
 • በቅርቡ ምርጫ እንደሚደረግ ረሳኸው?
 • ምርጫውንም ቢሆን ጥርሳችንን የነቀልንበት ነው፡፡
 • እንደተረዳሁት ግን እናንተም ውስጥ ሪፎርም መኖር አለበት፡፡
 • የምን ሪፎርም?
 • ሥልጣን መፈለግ ያለባችሁ ሕዝቡን ለማገልገል መሆን አለበት፡፡
 • እ…
 • እናንተን ግን ሳያችሁ ነጋዴዎች ናችሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በሕይወቴ የምጠላው ንግድና ነጋዴ ነው፡፡
 • የሚያሳዝነው ግን እናንተም ነጋዴዎች ናችሁ፡፡
 • የምን ነጋዴ?
 • የፖለቲካ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቤት ተገናኝተው እያወሩ ነው]    

 • ከቢሮ ስመጣ አንድ ነገር እያሰላሰልኩ ነበር፡፡
 • ምን?
 • አገሪቱ ውስጥ ያለውን ሪፎርም መቼም እየተከታተልሽው ነው?
 • ምነው?
 • ይኼን ሪፎርም እኛም ቤት ውስጥ አስገብተነው ሪኖቬሽን ማከናወን አለብን፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ቤታችንን ማደስ አለብን፡፡
 • በጣም ቅርብ ጊዜ ነው እኮ ያስመረቅነው?
 • አዎን ግን እድሳት ማድረግ እንዳለብን ተሰምቶኛል፡፡
 • ምን ዓይነት እድሳት?
 • ቤዝመንቱ መጋዘን መሆን የለበትም፡፡
 • የተሠራው ለዚያ ነበር እኮ?
 • አዎ ቢሆንም ቤዝመንቱ ውስጥ መዋኛ ማሠራት አለብን፡፡
 • እ…
 • ከዚያም ውጪ አሪፍ አሪፍ ክፍሎችን መገንባት አለብን፡፡
 • ኧረ ሰውዬ ተው?
 • ከመንግሥት የተሰጠውን አቅጣጫ ተከትዬ እኮ ነው እድሳት ለማድረግ የፈለግኩት፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • የእኔ ስም ከብዙ ወንጀል ጋር እንደሚነሳ ታውቂያለሽ አይደል?
 • ታዲያ ለምን አርፈህ አትቀመጥም?
 • አየሽ መጨረሻዬ እስር ቤት ሊሆን ይችላል፡፡
 • እና ምን ይጠበስ?
 • ስለዚህ እኔ መንግሥት እየቀለበ እንዲያስረኝ አልፈልግም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ወደፊት መታሰሬ የማይቀር ከሆነ ከአሁኑ ነው መገንባት ያለብኝ፡፡
 • ምንድነው የምትገነባው?
 • የግል እስር ቤት!