Skip to main content
x
የታሸጉ ውኃዎችና ተግዳሮቶቻቸው

የታሸጉ ውኃዎችና ተግዳሮቶቻቸው

የታሸገ ውኃ (ቦትልድ ዋተር) ለመጀመርያ ጊዜ የተመረተው በእንግሊዝ እ.ኤ.አ. በ1621 ነው፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች እየተስፋፉ የመጡበት ሁኔታ መኖሩ፣ የታሸገ ውኃ እንደ ፀበል በሽታን ይፈውሳል የሚል እምነት አሳድሮም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ መጠቀም ከተጀመረ ወደ ሁለት አሠርታት ቢሆንም በፍጥነት እያደገ የመጣ ዘርፍ ነው፡፡

አቶ ደሴ አበጀ የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የፓኬጂንግ ዳይሬክተር እንደተናገሩት፣ በ2006 ዓ.ም. 33 የነበሩት የውኃ ፋብሪካዎች አሁን ላይ 80 ደርሰዋል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራው፣ በቴክኖሎጂ ሽግግሩና ኅብረተሰቡን በማርካት ደረጃ ሲታዩ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታም አስገኝተዋል፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ በ1993 ዓ.ም. በትንሽ መሣሪያ ይገለገሉ የነበሩ ፋብሪካዎች፣ በአሁኑ ሰዓት እጅግ ትልልቅና በጣም ውስብስብ የሆኑ የውኃ ማምረቻ መሣሪያዎችን መጠቀም ጀምረዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፋብሪካዎችም በብዛት ተገንብተው በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከተወሰደው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው፣ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለበት አገር ውስጥ በቀን ለአንድ ሰው በአማካይ 100 ሚሊ ሊትር የታሸገ ውኃ ይመረታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ 3.5 ቢሊዮን ጠርሙስ ውኃ እንደሚመረት ይገመታል፡፡ ይህም ፍላጎትን እንደማያሟላ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የውኃ አምራች ተቋማት እያደጉና እየተስፋፉ ቢመጡም፣ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ይነገራል፡፡ ከችግሮቹም መካከል ደረጃ ባለማሟላታቸው የተነሳ የመታሸግ፣ ከተቆጣጣሪ አካላት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠት፣ የብሔራዊ ደረጃን ምልክት ሳይለጥፉ ማምረትና መሸጥ ተጠቃሾ ናቸው፡፡

የማምረቻ ቦታና አካባቢ ንፅህና ደረጃ አናሳ መሆን፣ የታሸገን ውኃ የምርት ደኅንትና ጥራት ሊያጓድሉ ከሚችሉ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ማከማቸትና ማጓጓዝ፣ በየሱቁ በታሸጉ ውኃዎች ላይ ኬሚካልና የፍሳሽ ሳሙና ተደርድረው መታየት፣ በሐሩራማና በጣም ከባድ በሆነ ፀሐይ አካባቢ የታሸጉ ውኃዎችን ማከማቸት እየተለመደ መምጣቱ፣ የውኃና የማሸጊያ ማምረቻዎችን በአንድ የሥራ ክፍል ውስጥ ማምረቱ ችግሮች ናቸው፡፡

ይህ ዓይነቱ የአመራረት ዘዴ ለብክለት ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡ በተለይ የፕላስቲኩ ብናኝ በቀጥታ ወደ ምርቱ ሊሄድ የሚችልበት ሁኔታም አለ፡፡

ቀጣይነት ያለው ምርት አለማምረት ማለትም አንድ ወጥ የሆነ ጣዕምና ጥራት ያለው ምርት አለማምረት፣ የአይኤስኦ ደረጃዎችን አለመተግበር፣ ሚኒራል ያልሆነውን ውኃ ከደረጃ ውጪ ሚኒራል ነው ብሎ መለጠፍ፣ በአንዳንድ አካባቢ የጉድጓድ ውኃ እጥረት መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኤሌክትሪክ መቆራረጥም ችግሮች ናቸው፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምርትን ያስተጓጉላል፣ ያበላሻል፡፡

የማስፋፊያ ቦታ ዕጦት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ ቤተሰብን መሠረት ባደረገ ማኔጅመንት መምራት፣ ከጅምሩ በባለሙያ ያልታገዘ ኢንቨስትመንት መሆን፣ በዚህም የሚፈለገውን ምርትና ጥራት አለማግኘት፣ ሌላው ዓብይ ችግር ነው፡፡

በኢትዮጵያ የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ በአብዛኛው ሰማያዊ ቀለም ሲሆን፣ የውጭ አገሮች ግን ነጭ ነው፡፡ ሰማያዊ ቀለም ቆሻሻን ለመደበቅ የሚችል ሲሆን፣ ነጩ ግን ንፁህና ቆሻሻ ቢኖረው እንኳን ሊታይ ይችላል፡፡

የታሸገ ውኃ ለፀሐይ ብርሃን ወይም ለሙቀት ከተጋለጠ አልጌ እንደሚፈጥር፣ በዚህም የተነሳ በመጋዘን ሲከማችና ከመጋዘን ወጥቶ በሚጓጓዝበት ጊዜ ቀዝቀዝ ባለና ጨለም ባለ ቦታ ቢሆን ጥሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የምግብ አምራቶች ኢንስፔክሽን አስተባባሪ አቶ ገረመው ጣሰው፣ ‹‹የውኃ ፋብሪካዎች መገንባት ያለባቸው ለብክለት የሚዳርጉ ነገሮች መራቢያና መከማቻ በማይሆን ቦታ ላይ ነው፡፡ የማምረቻውና የጥሬ ዕቃ ማስቀመጫ ክፍሎች ለየብቻቸውና ከሰው ንኪኪ ነፃ በሆነ መልኩ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆኑ ግን በኅብረተሰቡ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፤›› ብለዋል፡፡

በአንዳንድ የውኃ ማምረቻ ተቋማት ዘንድ የሠራተኞች የግል ንጽሕና አጠባበቅና በአጠቃላይ ልዩ ልዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች የመፀዳጃ ወይም ንፅሕና መጠበቂያ ክፍሎች የንፅህና አያያዝ ጉድለት እንደሚታይባቸው ገልጸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር ፀብ የሚፈጠረውም ከፍ ብሎ የተዘረዘሩ ጉድለቶችን ካለማስተካከል የተነሳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡   

እንደ አስተባባሪው፣ ባለሥልጣኑ ለውኃ ማምረቻ ተቋም የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጠው ተቋሙ የሚገነባበት አካባቢ ምርቱን ሊበክሉ ከሚችሉ ነገሮች መፅዳቱን፣ ግንባታው በሚመረተው ውኃ ላይ ተፅዕኖ አለመፍጠሩን፣ ማምረቻ መሣሪያዎች ዝገት የማይፈጥሩ መሆናቸውን፣ ውኃው ከተመረተ በኋላ ለመፈተሽና ለመቆጣጠር የሚያስችል ላብራቶሪ መኖሩንና መሣሪያዎቹ የሥነ ልክ አገልግሎት ማግኘታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የፕላስቲክ ውኃ ክዳኖች ትክክለኛና ለውኃ ማሸጊያ ተብለው የተፈቀዱ መሆናቸውን ማረጋገጥና ተቋሙን የሚመሩ የአካባቢና የሃይጂን፣ የጥራትና የምርት ክትትል ባለሙያዎች መመደባቸውን ማረጋገጥ ከባለሥልጣኑ የሥራ ደረጃ ተጠቃሾች መሆናቸውን አቶ ገረመው አመልክተው፣ አንድ የውኃ አምራች ተቋም ከፍ ብለው ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል 80 ከመቶ ያህሉን ካሟላ የብቃት ማረጋገጫ እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ የተጠቀሱትን ነጥቦች በማሟላቱ ብቻ ወደ ገበያ ይገባል ማለት እንዳልሆነና ገበያ ውስጥ ለመግባት የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃዎች የሚያወጣቸውን መሥፈርቶች ማሟላትና ለዚህም የብቃት ማረጋገጫ ሊያገኝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ገረመው፣ በውኃ ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ከጥበቃ ጭምር ጋዎን መልበስ፣ ፀጉራቸውን መሸፈን፣ የእጅ ጓንት ማጥለቅና አፍንጫቸውን መሸፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግሥቱ፣ ደረጃ ማለት በጋራ መግባባት የሚዘጋጅ ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰነዱም የሚዘጋጀው አምራቾች፣ መንግሥት፣ ኅብረተሰቡና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው በሚደርሱበት የጋራ መግባባት መሠረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የጋራ መግባባቱም ተቀባይነት የሚያገኘው በብሔራዊ የደረጃዎች ካውንስል ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመጠጥ ውኃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለት መልኮች አሉት፡፡ አንደኛው የቧንቧ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የታሸገ ውኃ ነው፡፡ የታሸገው ለአጠቃቀም ምቹ፣ ጥሩ ጣዕም ያለውና ጤናማ ሆኖ በመገኘቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው፡፡

ኢንጂነር ጌትነት በላይ የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃና ለስላሳ መጠጥ አምራቾች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር (ኢትዮጵያን ቦትልድ ዋተር ኤንድ ሶፍት ድሪንክ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪስ አሶሴሽን) ቦርድ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውኃ ማማ በመሆኗ ዓለም አቀፍ ገበያ እንገባለን ብለን እናስባለን፡፡ የብዙዎቹ አገሮች ውኃ ተፈጥሯዊ ባለመሆኑ የተነሳ የእኛን ውኃ ይፈልጉታል፤›› ብለዋል፡፡

ብዙዎቹ አምራቾች በኤሌክትሪክ መቋረጥ ሳቢያ 60 ከመቶ ያህል ምርታቸው እንደሚበላሽባቸው፣ በአምራች ተቋማት መካከል አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ውድድር እንዳለም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው፣ የታሸጉ ውኃዎች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አኳያ አበረታች ተግባር ቢያከናውኑም እንቅስቃሴው በቂ እንዳልሆነና ዛሬም በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በአገራችን የሚገኙ የልዩ ልዩ አገሮች ኤምባሲዎችና የውጭ ማኅበረሰቦች ለመጠጥ የሚውል ውኃ ከውጭ እያስገቡ ነው፡፡ ይህም በዘርፉ ያለንን አቅምና ተዓማኒነት በግልጽ የሚሳይ እንደሆነ አቶ እሸቴ ገልጸዋል፡፡  

የውኃ ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ በአደረጃጀት፣ በአሠራሮችና በቴክኖሎጂ ተደግፈው ጥራቱንና ደኅንነቱ የተጠበቀ ውኃ በዓለም ገበያ በማቅረብና ተወዳዳሪ በመሆን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ለዚህ አገልግሎት ታስበው በመንግሥት የተቋቋሙት መሠረተ ልማቶች (ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የብሔራዊ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት፣ የብሔራዊ ኤክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት) ኢንዱስትሪው በተገቢው ሁኔታ ተጠቅሞ በጥራትና በአቅርቦት ተወዳዳሪ እንዲሆን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡