Skip to main content
x
አቶ በረከት ስምኦን የሕግ ባለሙያ ለማቆም መቸገራቸውን ለፍርድ ቤት ተናገሩ
አቶ በረከት ስምኦን

አቶ በረከት ስምኦን የሕግ ባለሙያ ለማቆም መቸገራቸውን ለፍርድ ቤት ተናገሩ

ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቀደባቸው

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ወደ አማራ ክልል ተወስደው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ፣ በሕግ ባለሙያ ታግዘው ለመከራከር አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዓርብ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርበው እንዳስረዱት፣ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአካባቢው የሕግ ባለሙያ ለማቅረብ ተቸግረዋል፡፡ በመሆኑም የፍርድ ሒደቱ ሰብዓዊ መብታቸውን ሳይገፋ እንዲካሄድ እንዲደርግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እነሱን የመያዝም ሆነ የመክሰስ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደሌለው ለክልሉ ፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡

 ከጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ጋር በተያያዘ ፈጽመውታል ስለተባለው ከባድ የሙስና ወንጀል የሚያስረዱ ሰነዶችና የሰው ምስክሮች በተለያዩ ቦታ እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቶ በረከት የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ በመቃወም እንደተናገሩት፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል ተለይቶ እንዲቀርብላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ መርማሪው የጥረት ኮርፖሬት አክሲዮን ድርሻ ሲሸጥ ሕገወጥ ተግባር እንደፈጸሙ ቢገልጽም፣ የጥረት መመሥረቻና መተዳደርያ ደንብን ባለመገንዘብና ወንጀል ያልሆነን ጉዳይ ወንጀል እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

አቶ ታደሰ በበኩላቸው መንግሥት ተጠርጣሪዎችን ሳያጣራ እንደማያስር እየተናገረ፣ እነሱ ፈጽመዋል የተባለው ወንጀል ሳይጣራ መታሰራቸው ተገቢ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ወንጀል እንደፈጸሙ እየተገለጸ ያለው ከዳሸን ቢራ አክሲዮን ሽያጭ ጋር በተያያዘ መሆኑን ጠቁመው፣ የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገበ በመሆኑ ጉዳዩ መታየት ያለበት በክልል ፍርድ ቤት ሳይሆን፣ በፌዴራል ፍርድ ቤት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መጠየቅ ካለባቸው ወደ ፌዴራል ተወስደው መሆን ስላለበት፣ የተጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን የተጠርጣሪዎቹን መከራከሪያ ሐሳብ በመቃወም ክርክሩን አቅርቧል፡፡ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል በመንግሥታዊ ድርጅቶች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረስ ወንጀልና የሕዝባዊ ድርጅቶችን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ ጉዳት ማድረስ የሙስና ወንጀል መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለማየት የሚከለክላቸው የሕግ መሠረት እንደሌለ አስረድቷል፡፡

አቶ በረከትም ሆኑ አቶ ታደሰ ተጠርጥረው የተያዙበት ምክንያት እንደተገለጸላቸው አስታውሶ፣ ምርመራው ተጠናቆ ክስ ሲመሠረት በመደበኛ ፍርድ ቤት ስለሚታይ፣ ምርመራውን ለማጠናቀቅ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን መከራከሪያ ሐሳብ በማለፍ፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ ለየካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡