Skip to main content
x
‹‹ሼክ አል አሙዲ ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት አለኝታ ስለነበሩ እንዲፈቱ ጥረት አድርጌያለሁ››
ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ የተገኙት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዓርብ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጉብኝት ሲያደርጉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን አብረዋቸው ይታያሉ

‹‹ሼክ አል አሙዲ ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት አለኝታ ስለነበሩ እንዲፈቱ ጥረት አድርጌያለሁ››

ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ባደረገው የፀረ ሙስና ዘመቻ ከአንድ ዓመት በላይ ታስረው የቆዩት ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ፣ ከእስር እንዲፈቱ የዓለም ጤና ድርጀት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ሚና እንደነበራቸው ገለጹ፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ ከሳምንት በኋላ እዚህ መጥቼ ተገናኝተን ነበር፡፡ በወቅቱ የሼክ አል አሙዲን ጉዳይ በተመለከተ በጋራ ብንሠራ ጥሩ እንደሆነ ተነጋግረን ነበር፤›› ያሉት ቴድሮስ (ዶ/ር)፣ እሳቸው እንዲፈቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና የላቀ ቢሆንም፣ እሳቸውም የበኩላቸውን ማድረጋቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት አለኝታ የሆኑ ሰው ስለነበሩ አልረሳኋቸውም፡፡ እንዲፈቱ አቅሜ በፈቀደ ጥሬያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በሳዑዲ ዓረቢያ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወራት በላይ ታስረው በቆዩባቸው ጊዜያት በየጊዜው እንነጋገር ነበር፡፡ እየሄድኩም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር እነጋገር ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ያደረግኩት ጥረት ነው ለዚህ ያበቃቸው ለማለት እርግጠኛ አይደለሁም፤›› ሲሉ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

የሚድሮክ ኢትዮጵያ መሥራችና ሊቀመንበር ሼክ አል አሙዲ፣ በኢትዮጵያ 105 ኩባንያዎችን በመመሥረት ኢንቨስት ማድረግ ከጀመሩ 25 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረጉ ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎችም ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች እንዳላቸው ይነገራል፡፡

ባለፈው ዓመት አጠቃላይ ሀብታቸው 10.9 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር፣ ከመታሰራቸው በኋላ ግን ሀብታቸው ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሎ በፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር በ159ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ለሀብታቸው ማሽቆልቆል በፎርብስ የተሰጠው ምክንያት፣ የትኛው ሀብት የእሳቸው እንደሆነ ግልጽነት ባለመኖሩ ነው የሚል ነው፡፡ ከእስር እንዲፈቱ ከፍተኛ ገንዘብ ለሳዑዲ መንግሥት መክፈላቸውም ተሰምቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከወራት በፊት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ተጉዘው በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ አንድ ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ሲያስፈቱ፣ ከሙስና ጋር በተያያዘ በሳዑዲ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩት ሼክ አል አሙዲ በቅርቡ ከእስር ይለቀቃሉ ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ ‹‹የሼክ አል አሙዲ መታሰር በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አጀንዳ መሆን አለበት፣ ከገንዘብ ሰው ይበልጣል፣ እኛ ራሳችንን ስናከብር ሌላውም ያከብረናል፤›› ብለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ይፈታሉ ተብሎ ከተገመተው ጊዜ ዘግይቶም ቢሆን የተለቀቁት፣ ለዚህ ዕውን መሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ቴድሮስ (ዶ/ር) ደጋግመው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በጤና ጥበቃና በውጭ ጉዳይ በሚኒስትርነት፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት ቴድሮስ (ዶ/ር)፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሥራት ከጀመሩ ሁለት ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ዓርብ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጎብኝተዋል፡፡ ሆስፒታሉ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በጋራ ያስገነባውን የልብ ሕክምና ማዕከል፣ የእናቶችና ሕፃናት የሕክምና ክፍልን፣ እንዲሁም የቶክሲኮሎጂ ሕክምና ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴም ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡ የጤና መሠረተ ልማቱን በተመለከተም ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን፣ በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡