Skip to main content
x
የክቡር ሚኒስትሩ ልጆች ግቢው ውስጥ ሲጨቃጨቁ ክብር ሚኒስትሩ ወጡ

የክቡር ሚኒስትሩ ልጆች ግቢው ውስጥ ሲጨቃጨቁ ክብር ሚኒስትሩ ወጡ

[የክቡር ሚኒስትሩ ልጆች ግቢው ውስጥ ሲጨቃጨቁ ክብር ሚኒስትሩ ወጡ]

 • ምን ሆናችኋል ልጆች?
 • ምነው ዳዲ?
 • በጣም እየረበሻችሁኝ ነው ማረፍ አልችልም እንዴ?
 • ይቅርታ ዳዲ፡፡
 • ምንድነው የሚያጨቃጭቃችሁ?
 • የማን ይቁም የሚለው ላይ መስማማት አቅቶን ነው፡፡
 • ምንድነው የሚቆመው?
 • ሐውልት፡፡
 • የምን ሐውልት?
 • በቃ ለቤተሰባችን መታሰቢያ የሚሆን ሐውልት ማቆም ፈልገን ነው፡፡
 • የት?
 • እዚህ ግቢ ውስጥ፡፡
 • ለምንድነው ሐውልት ማቆም የፈለጋችሁት?
 • ያው ቤተሰባችን በጣም ስኬታማ ስለሆነ ለማስታወሻ ግቢ ውስጥ ሐውልት ቢቆም ብለን ነው፡፡
 • ይኼ እኮ የመንግሥት ቤት ነው፡፡
 • የመንግሥት ቢሆንም ይህ ቤተሰብ በአገር ደረጃ ራሱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለሆነ ሐውልቱ ቢቆም ችግር የለውም፡፡
 • ለመሆኑ አንተ የማን ሐውልት ይቁም ነው ያልከው?
 • እኔማ የአያታችን ሐውልት መቆም አለበት እያልኩ ነው፡፡
 • ለምን እሱን መረጥከው?
 • ዳዲ የዚህን ቤተሰብ ህዳሴ ያመጣው ማን ነው?
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • በዚያ ላይ የቤተሰቡ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያደረገው ማን ነው?
 • እሱ ነበር፡፡
 • ለቤተሰባችን ጤናማ የሕይወት ዘይቤን ያስተማረን እሱ እኮ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ሁሉም የቤተሰቡ አካል በየግቢው አረንጓዴ ቦታ እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡
 • እሱስ እውነትህን ነው፡፡
 • በዚያ ላይ ሁላችንም አመጋገባችን ሳይቀር አረንጓዴ እንዲሆን አድርጓል፡፡
 • ልክ ብለሃል፡፡
 • ስለዚህ የቤተሰባችን ወኪል ሆኖ ሐውልት ሊቆምለት የሚገባው እሱ ነው፡፡
 • አንቺስ ምንድነው ሐሳብሽ?
 • የአያታችን ሐውልት ሊቆም አይገባም ባይ ነኝ፡፡
 • ለምን?
 • በእርግጥ እኔ አያቴን እወደዋለሁ፣ ግን እሱ ከወንድሙ ጋር በመጣላቱ ምክንያት ነው እስካሁን ቤተሰቡ የተከፋፈለው፡፡
 • . . .
 • እንዲያውም አንተ ነህ እኮ አስታርቀሃቸው ሰላም መውረድ የቻለው፡፡
 • እሱስ ልክ ነሽ፡፡
 • ስለዚህ የእሱ ሐውልት እዚህ ሊቆም አይገባም፡፡
 • የማን ሐውልት ይቁም እያልሽ ነው ታዲያ?
 • የቅድመ አያታችን ነዋ ዳዲ፡፡
 • አንቺ የት ታውቂዋለሽ እሱን?
 • እንዴ ዳዲ ይኼ ቤተሰብ እንዲሰባሰብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው እሱ አይደል?
 • በምን አወቅሽ?
 • ዳዲ ትልቁን የቤተሰባችንን ማኅበር የመሠረተው እሱ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
 • ይኼን ማን ነገረሽ?
 • ሁሌ ማኅበራችን ላይ ሲወራ እሰማለሁ፡፡
 • እሱስ ልክ ነሽ፡፡
 • እንዲያውም አያታችን በቅድመ አያታችን ይቀና እንደነበር አውቃለሁ፡፡
 • ወይ የዛሬ ልጆች?
 • እውነቴን አይደል ዳዲ?
 • አሁን ምን እያላችሁ ነው?
 • እኔ የአያታችን ሐውልት ይቁም እያልኩ ነው፡፡
 • አንቺስ?
 • እኔማ የቅድመ አያታችን ሐውልት ነው መቆም ያለበት የምለው፡፡
 • ለማንኛውም እዚህ መቆም ያለበት ሐውልት የማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?
 • የማን ነው?
 • የእኔ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]

 • አንተ ሰውዬ ምን ሆነሃል?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ስልክ ብደውል ብደውል አታነሳም እኮ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ቢዚ ሆኜ ነዋ፡፡
 • ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?
 • ስብሰባው ነዋ፡፡
 • የምን ስብሰባ?
 • የመሪዎቹ ስብሰባ ነዋ፡፡
 • ጉረኛ አንተ ደግሞ ምን አገባህ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር ዋናው የዶላር ሥራ አሁን አይደል እንዴ?
 • እሱን ስታጧጡፍ ነዋ ሌላኛውን ቢዝነስ የዘነጋኸው?
 • የቱን ቢዝነስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስብሰባው ላይ እኮ አንድም የእኛን መኪና አላየሁም፡፡
 • የእኛ መኪኖችማ ሁሌም ሥራ ላይ ናቸው፡፡
 • አንድም አላየሁም ስልህ?
 • ማለቴ ከተማ ውስጥ እኮ የታክሲ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
 • ምን ነካህ እነዚያን ዘመናዊ መኪኖች ታክሲ እያሠራሃቸው ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የከተማችን የታክሲ አገልግሎት እኮ ዘመናዊ ሆኗል፡፡
 • እሺ እነዚያ ዘመናዊ ቫኖች ምን እየሠሩ ነው?
 • እነሱም ስኩል ባስ ሆነዋል፡፡
 • ተማሪ ማመላለሻ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት እነዚያን መኪኖች የተማሪዎች ማመላለሻ ታደርጋቸዋለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ተማሪዎች እኮ የወደፊቱ ተስፋ ናቸው፡፡
 • ዲስኩርህን እዚያው፡፡
 • ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • መኪኖቹን ለተሰብሳቢዎቹ ባለማከራየትህ እኮ ዶላር ነው ያስመለጥከኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር አልተደመሩም እንዴ?
 • የምን መደመር ነው?
 • አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው እኮ ለዜጋ ነው፡፡
 • በዶላር ቀልድ የለም ስልህ?
 • ካሉ እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ገብቶኛል፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • ማለቴ የስብሰባ ተሳታፊዎቹ መኪና እንዳይከራዩ ማድረግ አለብኝ፡፡
 • ታዲያ ከተማ ውስጥ በምን ይንቀሳቀሱ?
 • በታክሲ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ የታሰሩ ጓደኛቸውን ሊጠይቁ እስር ቤት ሄዱ]

 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም ነህ?
 • ምን ሰላም አለ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • መድኃኒት የለ፣ መጽሐፍ የለ፣ ሰው እንደ ልቡ መጥቶ አይጠይቀኝ፡፡
 • ይኸው እየመጣሁ እጠይቅሃለሁ አይደል እንዴ?
 • በፊት እየመጣ የሚሰግድልኝ ሁሉ አሁን የታለ?
 • የሚሰግደው ተገዶ እንጂ ወዶ መሰለህ?
 • በቃ በጣም መሮኛል፡፡
 • ምን ሆነህ?
 • እኔ እኮ ትልቅ ነገር ፈልጌ አይደለም፡፡
 • እኮ ምንድነው የፈለግከው?
 • ያው እስር ቤት ያለው ምግብ አልተመቸኝም፡፡
 • ምን ሆነብህ?
 • ደም ግፊቱ፣ ስኳሩም ስላለብኝ ጨው የሌለበት ምግብ መመገብ አልችልም፡፡
 • ታዲያ እንዲስተካከልልህ አትነግራቸውም?
 • ማን ይሰማኛል ብለው ነው? በዚያ ላይ እኔ የለመድኩት ዓይነት ምግብ ነው፡፡
 • ታዲያ እዚህ ሼፍ እንዲቀጠርልህ ፈልገህ ነው?
 • ለአገር ካበረከትኩት አንፃር እሱ ሲያንሰኝ ነው፡፡
 • ቀልደኛ ነህ እባክህ?
 • በዚያ ላይ መጽሐፍ ማንበብ እንደምወድ ያውቃሉ አይደል?
 • ታዲያ መጽሐፍ እየገባልህ አይደል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከዘመኑ ጋር መራመድ አለብን፡፡
 • እንዴት?
 • አሁን እኮ ብዙ ነገር የሚነበበው ኢንተርኔት ላይ ነው፡፡
 • . . .
 • ኦንላይን እኮ ነው ማንበብ የምፈልገው፡፡
 • ኦንላይን?
 • አዎን ምነው?
 • እውነትም ብሶብሃል፡፡
 • ምኑ?
 • ዕብደቱ፡፡
 • በዚያ ላይ እኔ ስፖርት መሥራት የለመድኩት ጂም ነው፡፡
 • እሺ ሌላስ?
 • በየሳምንቱ ስቲምና ሳውና መጠቀምም እወዳለሁ፡፡
 • በጣም ተቸግረሃልና?
 • ታዲያስ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ይሻላል ታዲያ?
 • እኔማ ከሌሎችም አገሮች ቢሆን ልምድ ብትወስዱ ባይ ነኝ፡፡
 • የምን ልምድ?
 • ማለቴ እስር ቤቴን ብትቀይሩልኝ፡፡
 • የት መታሰር አማረህ?
 • ሆቴል!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ከሥልጣን የወረዱ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሄሎ ማን ልበል?
 • ማን ልበል?
 • አዎን ማን ልበል?
 • እርስዎም ማን ልበል ማለት ጀመሩ?
 • ይቅርታ ከየት ነው የተደወለው?
 • ያኔ በቀን አሥሬ እንዳልደወሉልኝ አሁን ማን ልበል ይሉኛል ክቡር ሚኒስትር?
 • እስካሁን አላወቅኩህም፡፡
 • ለማንኛውም የቀድሞ ወዳጅዎ ነኝ፡፡
 • ውይ ቁጥርህ እኮ ተቀይሮብኝ ነው፡፡
 • እርስዎም ረሱኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ኧረ ሁሌ ልደውል አስባለሁ፡፡
 • ቢያስቡኝማ ይደውሉ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሁሌ ነው የማስብህ ስልህ?
 • ይኸው ድምፄን ራሱ መቼ ለዩት?
 • ከሥልጣን ስትወርድ የአንተም ድምፅ ተቀይሯል መሰለኝ፡፡
 • እንደዚህ የእርስዎም መቀለጃ ሆንኩ፡፡
 • ኧረ እየቀለድኩብህ አይደለም፡፡
 • ትዝብት ነው ትርፉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኧረ ሁሌ ከሚስቴ ጋር ስለእናንተ ነው የምናስበው፡፡
 • ቢያስቡማ ኖሮ ይደውሉልኝ ነበር፡፡
 • ያው እናንተ ጋ መደወል ችግር ነው ብዬ ነው፡፡
 • ይኸው እኔ እየደወልኩ አይደል እንዴ?
 • የሚገርምህ አሁን አንተ መሆንህን ሳውቅ መፍራት ጀመርኩ፡፡
 • ለማንኛውም በፊት እንደዚያ ጠብ እርግፍ እንዳላሉልኝ በአንዴ ይዝጉኝ?
 • ለመሆኑ ሌሎቹስ እንዴት ናቸው?
 • ኧረ ሌሎቹም ተቀይሞዎታል፡፡
 • ምን አጠፋሁ?
 • መቼ ዞር ብለው ዓይተውን ያውቃሉ?
 • ይቅርታ በሉልኝ፡፡
 • ይቅርታ ኪስ አይገባም ሲባል አልሰሙም፡፡
 • ምን ልቀጣ ታዲያ?
 • እዚህ ያረፍነው ሆቴል መሆኑን ያውቃሉ አይደል?
 • አዎን ሰምቻለሁ፡፡
 • የሆቴል ወጪያችን ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡
 • ምን ይደረጋል ታዲያ?
 • ስለዚህ ሰሞኑን እንልክልዎታለን፡፡
 • ምኑን?
 • ቢሉን!