Skip to main content
x
የቀድሞው ሚኒስትር ወደ ማረሚያ ቤት ይደውላሉ

የቀድሞው ሚኒስትር ወደ ማረሚያ ቤት ይደውላሉ

[ለአንድ የቀድሞ ሚኒስትር አንድ ዳያስፖራ ስልክ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ኧረ በዚህ ስም አትጥራኝ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ከሚኒስትርነት ካወረዱኝ ቆዩ እኮ፡፡
 • የቀድሞው ክቡር ሚኒስትር ልበል?
 • ተው እሱ ማዕረግ ምራቄን ያስውጠኛል፡፡
 • ምንም ነገር ቢውጡ መልሰው እንደሆነ አያገኙት፡፡
 • ይኸው አንተም ንቀኸኛል፡፡
 • ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይቆጨዋል ሲባል አልሰሙም?
 • ወይኔ ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ተረቱም ተቀይሯል ነው የምትለኝ?
 • ምን ያልተቀየረ ነገር አለ?
 • በሥራም ቢሆን ግን መቼ እኔ እታማለሁ?
 • ምነው እየተዋወቅን ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ማለት ነው?
 • እርስዎ መቼ በሥራ ይታወቃሉ?
 • በምንድነው የምታወቀው ታዲያ?
 • እርስዎ ከሥራ ይልቅ የሚታወቁት በሌሎች ነገሮች ነው፡፡
 • እኮ በምን?
 • በሴራ፣ በአሻጥርና በክፋት ነው፡፡
 • እ…
 • ይባስ ሲል በሙስና፣ በሌብነትና በሕገወጥነት ነው፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • የእርስዎ ሌጋሲዎች እነዚህ ናቸው፡፡
 • ወይ ጊዜ እኔም እንደዚህ የምዘረጠጥበት ጊዜ ይምጣ?
 • ሕዝቡን እንደዚያ ሲዘረጥጡና ሲያዋርዱ ነግ በእኔ መቼ ይሉ ነበር?
 • ምንም አይደል ይኼም ያልፋል፡፡
 • እስኪያልፍ ግን ያለፋል ይላል ተረቱ፡፡
 • እ…
 • ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ አያውቁም ነበር?
 • እኔ እኮ የዘራሁት ልማትና ዴሞክራሲ ነበር፡፡
 • የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ አሉ፡፡
 • እንዴት?
 • ልማትና ዴሞክራሲ ነው የዘራሁት ሲሉ ትንሽ አያፍሩም?
 • ምን ያሳፍረኛል?
 • ይኸው ሕዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲበላላ ያደረጋችሁት እናንተ አይደላችሁም እንዴ?
 • እኛማ ሕዝቡን ቀጥ ለጥ አድርገን አንቀጥቅጠን ነበር የገዛነው፡፡
 • ችግሩ እኮ እሱ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ለሕዝቡ ተንቀጥቅጣችሁ ማገልገል ሲኖርባችሁ፣ እያንቀጠቀጣችሁ ገዝታችሁ ይኸው አሁን ሕዝቡ በተራው እያንቀጠቀጣችሁ ነው፡፡
 • እሱ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡
 • አሁንም በጊዜ ብትደመሩ ይሻላችኋል፡፡
 • ተደመርን እኮ?
 • እንዴት ሆኖ?
 • አሁን አዋጪው መንገድ መደመር መሆኑ ገብቶናል፡፡
 • ይኼንን አላምንም፡፡
 • ጊዜው የፍቅርና የዕርቅ ነው ሲባል አልሰማህም?
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ስለዚህ እኛም ፍቅርና ዕርቅ ይሻለናል ብለናል፡፡
 • ይኼን የሚያወሩት እርስዎ ነዎት?
 • ይኸው ከመንግሥት ተምረን እኛም አቋቁመናል፡፡
 • ምንድነው ያቋቋማችሁት?
 • ክልላዊ የዕርቅ ኮሚሽን፡፡
 • ከመንግሥት ጋር ልትታረቁ?
 • ምን በወጣን፡፡
 • ማንን ነው የምትታረቁት ታዲያ?
 • የቀድሞ ታጋዮችን!

[የቀድሞው ሚኒስትር ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ሰሞኑን እንቅልፍ እምቢ ብሎኛል፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ ሰውዬ ለምን እንደዚህ ትጠራኛለህ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ከሚኒስትርነት ከወረድኩ ቆየሁ አላልኩህም እንዴ?
 • እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ለእኔ ሁሌም ክቡር ሚኒስትሬ ነዎት፡፡
 • ምነው ሁሉም እንዳንተ ቢቀበለኝ?
 • ለእኔ እኮ ከሚኒስትርም በላይ ነዎት፡፡
 • አንተ ደግሞ ዝም ብለህ ልቤን ታሞቀዋለህ፡፡
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን አደረግኩልህ ብለህ ነው?
 • ይኸው እርስዎ አይደል እንዴ ከአፈር ያነሱኝ፡፡
 • ምን አድርጌ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ አይደሉ እንዴ ከአንድ አይሉ ሁለት ዲግሪዎች ያሰጡኝ፡፡
 • ለአንተ እሱ ያንስብሃል፡፡
 • ከእሱም በላይ ያን ሁሉ ሀብት እንዳፈራ ያስቻሉኝ እኮ እርስዎ ነዎት፡፡
 • ለእኔና ለሥርዓቱ ታማኝ ስለነበርክ ነዋ፡፡
 • ምን ያደርጋል? ያ ሁሉ ሀብት መና ቀረ እንጂ፡፡
 • ለምን መና ይቀራል?
 • ክቡር ሚኒስትር ሦስት ቤቶች እኮ አዲስ አበባ ነው የሠራሁት፡፡
 • የእኔስ አምስት ሕንፃዎች ያሉት እዚያ አይደል እንዴ?
 • እሱን እኮ ነው የምልዎት፡፡
 • እንዲሁማ ተበልተን አንቀርም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን ጥናት ስሠራ ነበር፡፡
 • የምን ጥናት?
 • እዚህ የመሸግነው ምን ያህል ሕንፃ እንደተበላን፡፡
 • ውጤቱ እንዴት ነው?
 • በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • በነፍስ ወከፍ በአብዛኛው ከአምስት እስከ አሥር ሕንፃ ነው የተበላነው፡፡
 • አልቀናል በለኛ?
 • የሆነ መፍትሔ ማበጀት አለብን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ማድረግ እንችላለን?
 • እኔማ አንድ ሐሳብ መጥቶልኝ ነበር፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • ለምን አናቋቁምም?
 • ምንድነው የምናቋቁመው?
 • ኮሚቴ ነዋ፡፡
 • የምን ኮሚቴ?
 • ሕንፃ አስመላሽ ኮሚቴ!

[የቀድሞው ሚኒስትር ወደ ማረሚያ ቤት ይደውላሉ]

 • ሄሎ ማን ልበል?
 • የቀድሞ ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • ማንን ፈለጉ?
 • አንተን ማን ልበል?
 • አያውቁኝም እኔ አዲስ ነኝ፡፡
 • ወዳጆቻችን የት ገቡ?
 • ሚዲያ አይከታተሉም እንዴ?
 • ምን ሚዲያ አለ አሁን?
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • ምን ሚዲያ አለ ሲሉ ነዋ፡፡
 • እውነቴን እኮ ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ይኸው ነፃነት ተብሎ ማንም እየተነሳ አይደል እንዴ የሚፈነጭብን፡፡
 • ዴሞክራሲ ማለት ይኼ ነው፡፡
 • እየረገጡ መግዛት ነው የሚያስፈልገው፡፡
 • እሱ በእናንተ ጊዜ ቀረ፡፡
 • አሁን ወዳጆቼን አገናኘኝ?
 • ሚዲያ አይከታተሉም ወይ ያልኩዎት እኮ ለዚህ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • አብዛኞቹ እስር ቤት ገብተዋል፡፡
 • ሁሉም ታስረዋል?
 • ቀሪዎቹ ደግሞ ከእናንተ ጋር መሽገዋል፡፡
 • ማን ነው የሚረዳን ታዲያ?
 • ምን ፈለጉ?
 • ይኸው መንግሥት ስማችንን እያጠፋው ነው፡፡
 • ምን ብሎ?
 • ራሳቸውን በራሳቸው አስሯል ብሎ ነዋ፡፡
 • ታዲያ እውነት አይደል እንዴ?
 • እኛ እኮ እዚህ ተቸግረን ነው ያለነው፡፡
 • ለምን?
 • ሆቴሉ የሚሰጠን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰብን ነው፡፡
 • ምን ሆነ?
 • ይኸው እንደበፊቱ የፈለግነውን ምግብ አዘን መብላት አልቻልንም፡፡
 • እንዴ ለምን?
 • የእስካሁኑን ሒሳብ አልከፈልንማ፡፡
 • ያሳዝናል፡፡
 • አንሶላችን እንኳን ከታጠበ ቆይቷል፡፡
 • ለምን ለሆቴሉ አይናገሩም ታዲያ?
 • ሒሳብ ክፈሉ እያለን ነዋ፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • እኔማ እናንተ እንድትረዱን አስቤ ነበር፡፡
 • በምን እንርዳዎት?
 • ስማችንን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ጥያቄያችንንም መልሱ፡፡
 • የትኛውን ጥያቄ?
 • የሆቴል ወጪያችንን ክፈሉልን፡፡
 • ከየት አምጥተን?
 • ለምን ከበጀቱ ተቀናሽ አድርጋችሁ አትከፍሉልንም?
 • ከየትኛው በጀት?
 • ከታራሚዎች!

[ለቀድሞ ሚኒስትር አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ደወለላቸው]

 • እንደዚህ ሆናችሁ ማየቴ ደስ ብሎኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰውዬ ከሚኒስትርነት ከወረድኩ ቆይቻለሁ እኮ፡፡
 • ብቻ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
 • ምኑ ነው ደስ ያሰኘህ?
 • እናንተ እንደዚህ የመንግሥት ተቃዋሚ ሆናችሁ ማየቴ፡፡
 • እኛ አሁንም መንግሥት ነን፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • የልባችሁን ጥንካሬ ግን ሁሌም አደንቀዋለሁ፡፡
 • እንዴት?
 • አብቅቶላችሁም አለን ስትሉ ይገርመኛል፡፡
 • እንዳይመስልህ እንዲያውም አሁን ተጠናክረናል፡፡
 • አልሞት ባይ ተጋዳይ አለ፡፡፡
 • በቅርቡ በአዲስ የትግል ሥልት ብቅ እንላለን፡፡
 • የሚገርመኝ ለምን አይበቃችሁም?
 • ምኑ ነው የሚበቃን?
 • ፖለቲካው ነዋ፡፡
 • ለምን ይበቃናል?
 • አረጃችኋ፡፡
 • በፖለቲካ የምትበስለው እኮ ስታረጅ ነው፡፡
 • ለመሆኑ ልትገዙት የምታስቡት የአገሪቱ ሕዝብ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት መሆኑን አታውቁም?
 • ለዚያ እኮ ነው አገሪቱን ሽማግሌዎች መምራት ያለባቸው፡፡
 • ምክሬን ከሰሙ ግን ቢበቃችሁ ይሻላችኋል፡፡
 • እንዲያውም በቅርቡ በአዲስ መልክ ሥራ እንጀምራለን፡፡
 • ልክ እንደ ምግብ ቤት?
 • መቀለዱ ነው?
 • ለነገሩ ብዙ ጊዜያችሁን ሆቴል ስታጠፉ ከእነሱ ስትራቴጂ መማር ጀመራችሁ?
 • ነገርኩህ በቃ፡፡
 • ምን ልታደርጉ ነው?
 • ቀድሞ ከተጣላናቸው ጋር ሳይቀር ዕርቅ አውርደናል፡፡
 • እሱ ጥሩ ነው፡፡
 • ስለዚህ አዲስ ፓርቲ በቅርቡ ጠብቅ፡፡
 • ምን የሚሉት?
 • ሽ.ነ.ግ.
 • ምን ማለት ነው?
 • ሽማግሌ ነፃ አውጪ ግንባር!