Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ልጆቻቸው በመኝታ ቤት ሲጨቃጨቁ ከእንቅልፋቸው ነቁ

ክቡር ሚኒስትሩ ልጆቻቸው በመኝታ ቤት ሲጨቃጨቁ ከእንቅልፋቸው ነቁ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከጸሐፊያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምን ሆነሻል?
 • ምን ሆንኩ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንባሽ እየፈሰሰ እኮ ነው፡፡
 • አልቻልኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ተፈጠረ?
 • ጉድ ሆኜልዎታለሁ፡፡
 • እኮ ምን ሆንሽ?
 • ተዘረፍኩ፡፡
 • ተዘረፍኩ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ነው የዘረፈሽ?
 • ሌቦች ናቸዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ያስለቅስሻል ታዲያ?
 • ክቡር ሚኒስትር እሱን እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
 • ንገሪኝ አይዞሽ?
 • ሙሉ ደመወዜን ነው እኮ የወሰዱብኝ፡፡
 • በቃ ተረጋጊ፡፡
 • መንግሥት ግን አለ?
 • ምን እያልሽ ነው?
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር እስቲ መልሱልኝ?
 • በሚገባ እንጂ፡፡
 • አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • አገሩን ሁሉ እኮ ሌባ ብቻ ነው የሞላው፡፡
 • አልገባኝም?
 • ክቡር ሚኒስትር በከፍተኛ ሥጋት እኮ ነው እየኖርን ያለው፡፡
 • የምን ሥጋት ነው?
 • በቃ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት እኮ አጋጣሚ እየሆነ ነው፡፡
 • አንቺን ሌባ ሲሰርቅሽ ሕይወት ሁሉ ይጨልምብሻል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ሠርቶ አደር እንጂ እንደ ሌላው አይደለሁም፡፡
 • ሌላው ምንድነው?
 • ሌላውማ ሠርቆ አደር ነዋ፡፡
 • ቀልደኛ ነሽ መቼም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እየቀለድኩ ሳይሆን እጅግ ተማርሬ ነው የምነግርዎት፡፡
 • ይኼን ያህል መማረር አያስፈልግም ስልሽ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከተማው ውስጥ እኮ እንደ ሰደድ እየተፋፋመ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • ሌብነቱ፡፡
 • ይኼን ያህል?
 • ያልተነካ ግልግል ያውቃል አሉ፡፡
 • እንዴት?
 • በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ስርቆትና ዝርፊያ ነው ያለው ስልዎት፡፡
 • ለነገሩ ይኼንን ችግር ሌሎችም ሰዎች ነግረውኛል፡፡
 • ባለፈው ባለቤቴን ማጅራቱን መተውት ይኼ የአልጋ ቁራኛ ሆኗል፡፡
 • በጣም ያሳዝናል፡፡
 • ታዲያ አሁን ቤተሰቤን በምን ልቀልብ ነው ወሩን ሙሉ?
 • ችግር የለውም አንድ መላ እንፈጥራለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ነገም ይኼ ዕጣ እንደማይደርስብኝ ማረጋገጫ የለም፡፡
 • እስቲ እኔ ከሚመለከታቸው ጋር እነጋገርበታለሁ፡፡
 • በከተማዋ ውስጥ ያለው የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር ወጣቱን ለዘረፋ እያጋለጠው ነው፡፡
 • አሁን እኮ ወጣቶች እየተደራጁ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡
 • እሱን እንኳን ተውት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ወጣቶቹ ቢደራጁም ሥራ ካልተሰጣቸው ምን ያደርጋሉ?
 • ሥራ ይፈጥራሉዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንዲያውም ወጣቶቹ የሚደራጁት ለሥራ ሳይሆን ለሌላ ነገር ነው የሚመስለው፡፡
 • ለምንድነው የሚደራጁት?
 • ለዝርፊያ!  

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • እንቅስቃሴ እንዴት ነው?
 • ኧረ በጣም አሳሳቢ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው ያሳሰበህ?
 • ኢኮኖሚው እየተናጋ እኮ ነው፡፡
 • ምን ሆኖ?
 • እሱንማ እርስዎን ልጠይቅዎት እንጂ?
 • ኢኮኖሚው ምንም አልሆነም፡፡
 • የሁላችንም ምኞት እሱ ነበር፡፡
 • ይኼ ምኞት አይደለም እውነታ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼው ሁሉም ነገር እኮ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡
 • ስማ ይኼ ያልተደመሩ ሰዎች ወሬ ነው፡፡
 • የኪራይ ሰብሳቢዎች ማለትዎ ነው?
 • ኪራይ ሰብሳቢዎች ባልተደመሩ ተቀይሯል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ዲክሽነሪ ቀይሯል ማለት ነው?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • ስለዚህ ልማታዊ በምንድነው የተተካው?
 • እሱማ የተደመረ ነው የሚባለው፡፡፡
 • በፊት መንግሥት የጥፋት ኃይሎች ይል ነበር፣ እሱስ አቻ ትርጉም ተገኝቶለታ?
 • በሚገባ፡፡
 • ምን ተባለ?
 • አሁን ለውጡን የሚያደናቅፉ ነው የሚባሉት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን አንድ ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ያው እንደ ደላላ ሥርዓት በተቀየረ ቁጥር ውጤታማ ለመሆን የገዥውን ቋንቋ ማወቅ ግድ ይላል፡፡
 • ለዚያ አይደል እንዲህ እያስተማርኩህ ያለሁት?
 • እኔማ ለምን ሰፋ አናደርገውም ብዬ ነው፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • ክቡር ሚኒስትር በሁሉም ዘርፍ ከመንግሥት ጋር የማይሠራ የለም፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ስለዚህ ባለሀብቱም የአሁኑን መንግሥት ፍልስፍና ማወቅ ይፈልጋል፡፡
 • የመደመር ፍልስፍናን ነው መንግሥት የሚከተለው፡፡
 • አዩ አሁን ባለሀብቱ በፊት የመንግሥት ደጋፊ ከሆነ ልማታዊ ባለሀብት ነበር የሚባለው፡፡
 • አሁን ደግሞ የተደመረ ባለሀብት ነዋ የሚባለው፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢው ባለሀብትስ ምንድነው የሚባለው?
 • ያልተደመረ ባለሀብት፡፡
 • ስለዚህ ባለፈውም ከበፊቱ ክቡር ሚኒስትር ጋር ሆነን ተመሳሳይ መጽሐፍ አሳትመን ነበር፡፡
 • ምን ዓይነት መጽሐፍ?
 • የመንግሥትን ፍልስፍና ለሁሉም ዘርፍ በግልጽ ቁልጭ አድርጎ የሚሳይ መጽሐፍ አሳትመን ነበር፡፡
 • ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡
 • በወቅቱ ልማታዊነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ብለን ነበር ያሳተምነው፡፡
 • የሕዝቡ አቀባበል እንዴት ነበር?
 • ክቡር ሚኒስትር ከሚያስቡት በላይ ነበር የተጠቀምነው፡፡
 • ስለዚህ ተመሳሳይ መጽሐፍ ማሳተም አዋጭ ነው እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የበፊቱ መጽሐፍ ቅጽ ሁለት ብለን እናሳትመዋለን፡፡
 • የሚገርም የቢዝነስ ሐሳብ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሉም ባለሀብት ከእጁ የማይለየው መጽሐፍ ነው የምናሳትመው፡፡
 • የመጽሐፉን ርዕስ ግን ምን ይባል?
 • የተደመረና ያልተደመረ ከምንለው ገዥ ርዕስ ብንመርጥ ጥሩ ነው፡፡
 • እንዲያውም አጭር ርዕስ መጣልኝ፡፡
 • ምን?
 • ድምር!  

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ስልክ ደወለላቸው]

 • አገሪቱ ወዴት እያመራች ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ወደ ልማት ነዋ፡፡
 • ልማትማ ድሮ ቀረ፡፡
 • አንተ ያልተደመርክ ተቃዋሚ ነህ ማለት ነው?
 • ለማን ብዬ ነው የምደመረው?
 • አሁን አይደል እንዴ ለተቃዋሚዎች ቀን የወጣላችሁ?
 • ለእኔ ግን ቀኑ የጨለመብኝ አሁን ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ክቡር ሚኒስትር የሚሠራውን ነገር አያዩም እንዴ?
 • ምን ተሠራ?
 • እኛ ለስንት ዓመታት በሰላም ስንታገል ከርመን ይኼው ስንቱ ነፍጥ ያነሳ እንደ ጀግና እየተቆጠረ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አሁን እኮ ከውጭ የገቡት ብቻ ናቸው እንደ ተቃዋሚ እየተቆጠሩ ያሉት፡፡
 • እናንተማ በፊትም እኮ ቢሆን ልማታዊ ተቃዋሚዎች ነበራችሁ፡፡
 • ታዲያ አገሪቱ ውስጥ ለውጡን አላዩትም፡፡
 • የምን ለውጥ?
 • ይኼው እኛን እንደ ተቃዋሚ መቁጠር ስታቆሙ ሁሉም ነገር በአፍጢሙ መደፋት ጀመረ፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • እኛ መንግሥትን ስንቃወም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ11 በመቶ እያደገ ነበር፡፡
 • እ . . .
 • ይኼው እኛን እንደ ተቃዋሚ መቁጠር ስታቆሙ ኢኮኖሚው ሳይቀር ማሽቆልቆል ጀመረ፡፡
 • አንተ ግን ህሊና አለህ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምታወራውን ነገር ታውቀዋለህ?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም አንተም ተቃዋሚ ተብለህ መቆጠርህ ያሳዝናል፡፡
 • እኔ እኮ ልማታዊ ተቃዋሚ ነኝ አልኩዎት፡፡
 • አሁን ምንድነው የምትፈልገው?
 • መንግሥት እያገለለን ነው፡፡
 • ምን አድርጎ?
 • በየስብሰባው የሚጠራው ከውጭ የመጡትን ተቃዋሚዎች ብቻ ነው፡፡
 • እናንተ እኮ ተቃዋሚዎች አልነበራችሁም፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነን?
 • ሰላዮች፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሥርዓቱ ተቀይሯል ብለው ነው የሚሰድቡን?
 • እኔ እውነቱን ነው የነገርኩህ፡፡
 • በጣም ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በመጀመርያ ተቃዋሚ ለመባል የራሳችሁ የፖለቲካ አጀንዳ ይኑራችሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የደወልኩልዎት እኮ አብረን እንድንሠራ ጥሪ ለማቅረብ ነው፡፡
 • ለእናንተ የመንግሥት ምላሽ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምንድነው?
 • ጥሪ አይቀበልም!

[ክቡር ሚኒስትሩ ልጆቻቸው በመኝታ ቤት ሲጨቃጨቁ ከእንቅልፋቸው ነቁ]

 • እዚህ ቤት መተኛት አይቻልም?
 • ይቅርታ ዳዲ፡፡
 • በምንድነው የምትጨቃጨቁት?
 • በሳሎን ቤት፡፡
 • በሳሎን ቤት?
 • አዎን ዳዲ፡፡
 • በሳሎን ቤት ምን ያጣላችኋል?
 • ሳሎን ቤቱ ላይ እሷ የይገባኛል ጥያቄ አንስታ ነው፡፡
 • የምን የይገባኛል ጥያቄ ነው?
 • በፊት በፊት የማድርበት እኔ ስለነበርኩ ሳሎኑ የእኔ ነው አለችኝ፡፡
 • እ . . .
 • ምን እሱ ብቻ የሳሎን ቤቶቹን አትክልቶቹ የምንከባከባቸውና የተከልኳቸው እኔ ስለሆንኩ ሳሎኑ የእኔ ነው አለችኝ፡፡
 • አንተስ ምን አልካት?
 • እኔማ እንዲያውም ካልሽ ሳሎን ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ መጻሕፍት የእኔ ስለሆኑ ሳሎኑ የእኔ ነው አልኳት፡፡
 • እ . .
 • ዳዲ ፕሌይ ስቴሽን እየተጫወትኩ አብዛኛውን ጊዜ የማጠፋው እኮ ሳሎን ቤት ነው፡፡
 • እኔ የምለው ሁለታችሁም የራሳችሁ መኝታ ቤት አላችሁ አይደል እንዴ?
 • አዎን ዳዲ፡፡
 • ታዲያ በሳሎን ቤት ምን አጣላችሁ?
 • እሷ ሳሎኑ የእኔ ነው ውጣልኝ ስትለኝ ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም ሳሎኑ የሁለታችሁም አይደለም፡፡
 • ታዲያ የማን ነው?
 • የሁላችንም!