Skip to main content
x
ንዋይ ያንበረከከው የፊልም ኢንዱስትሪ

ንዋይ ያንበረከከው የፊልም ኢንዱስትሪ

እስከ አሥራ ዘጠነኛው ክፍል ዘመን ድረስ ኢትዮጵያ በተለያዩ ስመጥር የአካባቢ ነገሥታት የምትተዳደር አገር ነበረች፡፡ በዘመኑ ገናና ከነበሩ ነገሥታት መካከል የከፋው ጋኪ ሴሮቾ፣ የጅማው ንጉሥ አባጅፋር፣ የወላይታው ንጉሥ ካዎ ጦና በነበራቸው ጠንካራ አገዛዝ ታዋቂዎች ናቸው፡፡ ማዕከላዊ አገዛዝ ሥርዓትን እምብዛም በማታውቀው የዚያን ዘመኗ ኢትዮጵያ እንደ ካዎ ጦና ያሉ የአካባቢ ነገሥታትን ለማዕከላዊ መንግሥት እንዲገብሩ ማድረግ ትልቅ የቤት ሥራ ነበር፡፡

የአገሪቱ ንጉሠ ነገሥት በመሆን እነዚህን ገዥዎች የማስገበር ራዕይ የነበራቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከፊሉን በዲፕሎማሲ አግባብተው፣ አሻፈረኝ ያለውን ዳግም በጦር አሳምነው ሲያስገብሩ ከወላይታው ንጉሥ ካዎ ጦና በኩል ግን ብርቱ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ካዎ ጦና ለማዕከላዊ መንግሥት እንዲገብር አፄ ምኒልክ ሰባት ጊዜ ጦራቸውን ወደ ወላይታ መላክ ነበረባቸው፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠንካራ ተቃውሞ ወደገጠማቸው ወላይታ ንጉሠ ነገሥቱ ለስድስተኛ ጊዜ ሠራዊታቸውን የላኩት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ አስታጥቀው ነበር፡፡

ለስድስተኛ ጊዜ የዘመቱት የንጉሠ ነገሥቱ የጦር ሠራዊት ቁጥር ከቀድሞ መላቁና የታጠቋቸው የጦር መሣሪያዎችም ዘመናዊ መሆንን የተመለከቱ የካዎ ጦና ሠራዊት የጦር ሥልታቸውን ቀየሩ፡፡ ከየአካባቢው በተሰበሰቡ የንብ ቀፎዎች ውስጥ ንቦችን የሚያሳብድ ተክል አስቀመጡ፡፡ ምድር ቀውጢ ሆነች፡፡ ያገኙትን አሳደው ከሚነድፉት ንቦች ወላይታዎች ራሳቸውን በሸማ ሸፍነው አመለጡ፡፡

እንዲህ ያሉ በአገር ውስጥ የተከናወኑ የጦር ውሎዎችና ከውጭ አገር ወራሪን ለመከላከል የተካሄዱ የጦር ውሎዎችን በፊልም ማዘጋጀት ቢቻል ታሪኩ ከጌም ኦፍ ትሮን ያልተናነሰ ተመልካች ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ነጋሪት ተጎስሞ ክተት ሲታወጅ፣ አገሬው መሣሪያውን ሲወለውል፣ ምንሽሩን ሲያፀዳ፣ ጋሻና ጦሩን ሲያሰናዳ፣ አርበኞች ግርማው የሚያስፈራ የጦር ልብሳቸውን የሚያዘጋጁ፣ ምድር ቁና ስትሆን ጋሻና ጦር የያዙ እናቶች እምቢ ለአገሬ እያሉ በቀረርቶና በሽለላ ጦረኛውን ሲያጅቡ ሲያነሳሱ፣ ስንቅ ለመቋጠር ሽር ጉድ ሲሉ የሚያሳይ በነጋሪትና በፋኖ ፋኖ ሙዚቃ የታጀበ ኢትዮጵያዊ ፊልም ማየት መዝናናት ብቻ ሳይሆን ትውልድን ማነቃቃትና በማንነቱ እንዲኮራ የማድረግ ተልዕኮም ጭምር ነው፡፡ በእነዚህ የጦር ውሎዎች የሚሳተፉ አርበኞችና መሪዎች ታሪክም በራሱ ሌላ መሳጭ ታሪክ ያለው ፊልም ሊወጣው የሚችል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከጦር ሜዳ ታሪኮችም ባሻገር በርካታ ወደ ፊልም ሊቀየሩ የሚችሉ ታሪኮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ ኢትዮጵያዊ ፊልሞችን ለመመልከት ተመልካቹ የታደለ አይመስልም፡፡ የሚሠሩት ፊልሞችም እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችን ያላገናዘቡ ናቸው፡፡

የፊልም ባለሙያው በድሉ ድሪባ እንዲህ ያሉ ኢትዮጵያዊ ፊልሞችን ሠርቶ ለእይታ ማብቃት አሁን ካለው የኢንዱስትሪው አቅምና ዝግጅት በላይ ነው ይላል፡፡ በድሉ ‹‹ያልጅ››፣ ዩ ቶፒያ፣ አይራቅ፣ በልደቴ ቀን፣ የእናት መንገድና ሰኔ 30 የተባሉ ፊልሞችን በደራሲነት፣ በዳይሬክተርነትና በፕሮዲውሰርነት ሠርቷል፡፡ ሁለቱን ፊልሞች ፕሮዲውሰር ሆኖ፣ አራቱን ዳይሬክት አድርጓል የስድስቱንም ስክሪፕት መጻፉንም ይናገራል፡፡ ከሳምንታት በፊት የተመረቀ አንድ ፊልምም በረዳት አዘጋጅነት መሥራቱን ሰምተናል፡፡

እነኚህን ሥራዎች ሲሠራ በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት እንቅፋት የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ታዝቧል፡፡ ወጥ የሆነ ታሪክ ያላቸውን ብቁ ፊልሞች ለማዘጋጀት የዕውቀትም የገንዘብም ችግር አለ ይላል፡፡ ያለው የዕውቀት ችግር የሚጀምረው ስለ ታሪኩ በቂ ጥናት ከማድረግ ነው፡፡ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ለመግባት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም፡፡ አንድ ሰው እስክሪፕቶና ወረቀት አንድ ላይ አገናኝቶ ደራሲ ነኝ ካለ የመሥራት መብት አለው፡፡ ዳይሬክተር ነኝ ካለም መሥራት ይችላል፤›› የሚለው በድሉ የኢንዱስትሪው ዋነኛ ችግር በሥርዓት የሚመራ አለመሆኑ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሙያው በተሰጥኦ የሚሠራ ቢሆንም ተሰጥኦው በራሱ በትምህርትና በሥልጠና መገራትና መሟሸት አለበት ይላል፡፡

ጥሩ የመጽሐፍ ደራሲ ወይም ገጣሚ የፊልም ስክሪፕት መጻፍ ይችላል ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ‹‹በአሁኑ ሰዓት 90 በመቶ የሚሆኑት ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ሰዎችን የፊልም ባለሙያ ናቸው ለማለት አልደፍርም፤›› ሲልም ይናገራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንድ የፊልም ስክሪፕት ከ20,000 እስከ 50,000 ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የፊልም ስክሪፕቶች ከ10,000 ብር በታች በሆነ ገንዘብ የሚሸጡም አሉ ይላሉ፡፡

በመደበኛው አሠራር የፊልም እስክሪፕት ወጥ ታሪኩ መጀመሪያ ይጻፋል፡፡ ከዚያም ወደ ፊልም እስክሪፕት፣ በመጨረሻም ወደ ሹቲንግ እስክሪፕት ይቀየራል የሚለው የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ ነው፡፡ ጽሑፎቹን የሚያሰናዱት ሦስቱ አካላት ተናበው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከእስክሪፕቱ ጋር የተያያዙ ነገሮች ሲያልቁ ዋጋ ወደ ማውጣት ይገባል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የተሠራ ያለው ከዚህ በተለየ መንገድ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ መነቃቃት ያሳየው ባለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ የመጀመሪያው አምስት ዓመት ዋጋ የተከፈለባቸው፣ የባለሙያዎች ተሰጥኦ የወጣበት፣ ገንዘብ በመጠኑም ቢሆን የተገኘበት ነው፡፡ ሁለተኛው አምስት ዓመት ግን ሙያውን በፍላጎት ከመሥራት ይልቅ ገንዘብ ወደ መሰብሰብ የተገባበት ነው፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ ሙያው ሙሉ ሉሙሉ ንግድ የሆነበት ነው፡፡ በዓመት መቶ ገደማ የሚሆኑ ፊልሞች ይሠራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከሙያ አንፃር ተመዝነው ጥሩ የሚባሉት ከአራት የማይበልጡ ናቸው የሚለው በድሉ ነው፡፡

በየጊዜው የሚለቀቁ ፊልሞች በብዛት የታሪክ ወጥነት የጎደላቸው ከባህር ማዶ የተቀዱ ናቸው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ ታሪኩን በትክክል መቅዳት ላይም ችግር መኖሩ ነው፡፡ ‹‹በጣም ብዙ ፊልሞችን የሚናገሩት ታሪክ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰው የሚያውቀውን ነገር ደጋግሞ በመንገር የማሰልቸት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ፊልሞቻችን የሚያተኩሩት ተመሳሳይ ነገር ላይ ነው፡፡ አንድ ልጅ ከአንዲት ልጅ ጋር የሚገናኝበትን አጋጣሚ ይፈጥራሉ፡፡ ከዚያ እንዲጣሉ ያደርጓቸዋል፡፡ መጨረሻ ላይ መታረቂያ መንገድ ፈልገው ማስታረቅ ላይ ነው፤›› የሚለው የፊልም ባለሙያው በኃይሉ ዋሴ ኢትዮጵያ በፊልም ቢነገሩ የማንንም ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ታሪኮችና  ክስተቶች የተሞላች አገር ብትሆንም በፊልሞች የሚንፀባረቀው ግን ሌላ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ባለሙያው መለስ ብሎ የአገሩን ታሪክና ማኅበራዊ እሴቶች ማጥናት ይኖርበታል፡፡ ቀጥሎም የኢትዮጵያን እሴትና ታሪክ የሚያንፀባርቅ አካል በተቋም ደረጃ ማዋቀር ግድ ነው፡፡ አንደ ጠንካራ ተቋም ማቋቋም ከተቻለ ብቁ የሆኑ ወጥ ፊልሞችን ተቋሙ በሚያወጣው መስፈርት እየተመዘኑ እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚቻል ያምናል፡፡

‹‹እኛ አገር ፊልም የሚሠራው ከኪስ በሚወጣ ገንዘብ ነው፡፡ ባለን አቅም ተጠንቅቀን ልንሠራ እንችል ይሆናል ነገር ግን ባለን ገንዘብ የተዋጣለት ፊልም መሥራት አንችልም፤›› የሚለው በኃይሉ የፊልም ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ የሚያደርግ አካል ባለመኖሩ የፊልሞች ጥራት ባለው የገንዘብ አቅም የሚወሰን እንደሆነ ይገልጻል፡፡

አብዛኞቹ ፊልሞች እየተሠሩ ያሉትም በሰዎች ይሁንታና ትብብር እንደሆነ የሚናገረው በድሉ፣ ደግሞ የተዋናይ አልባሳትን አንደኛው ቡቲክ ስፖንሰር እንዲያደርግ ሌላውንም እንዲሁ አንዱ አካል ትብብር እየተጠየቀ የሚሠሩ ናቸው ይላል፡፡ ይኼንንም አንድ ካፊቴሪያ ላይ የሚቀረፅ ምሥል ለመውሰድ የሚኖረውን ፈተና በምሳሌ በማንሳት እንዲህ ያስረዳል፡፡ የሁለት ደቂቃ ምሥል ለመውሰድ አንድ ቀን ሊፈጅ ይችላል፡፡ እንዲቀርፁበት የፈቀደው ሰው ገቢው ቀኑን ሙሉ እንዲቋረጥ አይፈልግምና እንዲከፍሉት ይጠብቃል፡፡ ከክፍያው ባሻገር ደግሞ በሆቴሉ ወይም በካፊቴሪያው የሚዝናኑ ሰዎች ምሥሉ ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ከዋና ተዋናዮቹ በተጨማሪ ኮርሶችን (አጃቢዎችን) ማዘጋጀት ግድ ነው፡፡ በአንድ ሆቴል ወይም መዝናኛ ቦታ ላይ የሚወሰድ አንድን ምሥል በቪዲዮ ለማስቀረትም ከዋና ተዋናዮች በተጨማሪ ሌሎች በትንሹ 500 ኮርሶች ሊያስፈልጉ ይችላል፡፡ ይኼንንም ለማድረግ ለእያንዳንዳቸው ከ500 እስከ 1,000 ብር አበል መክፈል ግድ ነው፡፡

ነገር ግን በግለቦች ኪስ የተወሰነው ኢንዱስትሪው ይኼንን ያህል ገንዘብ ማውጣት ስለሚቸግረው ሌላ አቋራጭ ይፈልጋል፡፡ አቋራጩም ፊልሙን ጭር ባሉ ቦታዎች መቅረፅ ነው፡፡ የታሪኩን መቼት ከመፍጠር አኳያ ፈታኝ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በመላ በዘዴ መግፋት በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ የተለመደ ነው፡፡ ታሪኩን የሚወክል አልባስ፣ ሜካፕ፣ ቦታ፣ ሌሎችም ድባቡን ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማምጣት በኪስ ገንዘብ መወሰን፣ በሰዎች በጎ ፈቃድ መተማመን ከባድ ነው፡፡ በዚያ ላይ ብዙዎች ለሙያው ፍቅር ስላላቸው አልያም የቻሉ ስለሚመስላቸው ብቻ የሚገቡበትና በልምድ የሚሠሩበት ከመሆኑ አንፃር እጀ ሰባራ የሚያደርጉ ስህተቶች እንደዋዛ ይፈጠራሉ፡፡ ያሉትን ስህተቶች ነቅሶ ለማውጣትና እንዲስተካከሉ ለማድረግ ዕውቀቱም፣ ተነሳሽነቱም ከሁሉ ነገር በላይ ደግሞ ገንዘቡ ያስፈልጋል፡፡

‹‹አክተር ሆኜ ልብስ ግዛ ስባል ወጪ ነው፡፡ ተሰጥኦዬ ግን ወጪ የማልጠየቅበት በተፈጥሮ የተሰጠኝ ነገር ነው፡፡ እሱን አዳብረን መሥራት ላይ እንኳ ደካሞች ነን፤›› በማለት በድሉ ያለው ችግር ከገንዘብም ባለፈ ከተዋናዮች ብቃት ጋር የተያያዘም እንደሆነም ይገልጻል፡፡

ብቃቱ ኖሯቸው ከሚተውኑ በጣት ከሚቆጠሩ ባለሙያዎች ባሻገር ለመታወቅና ባለዝና ለመሆን ሲሉ ብቻ የትወናውን ዓለም በአጋጣሚ የሚቀላቀሉ ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹አክተር መሆን እንፈልጋለን ብለው የሚያስቸግሩን አሉ፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቃቸው በቃ መታወቅ እንፈልጋለን የሚሉን መተወን ተሰጥኦና ብቃት የሚጠይቅ ነገር መሆኑን የማያውቁ አሉ፤›› ያለው በድሉ ነው፡፡ ገንዘብ ስላላቸው ብቻ እንዲተውኑ የሚደረጉም አሉ፡፡ ስለዚህም መፍትሔው ተሰጥኦ ያላቸውን አንድ ሁለት ሰዎች ከሌሎች ጋር ደባልቆ ማሠራት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ‹‹የፊልሙ ኢንዱስትሪ በአጭሩ በባለገንዘቡ የተወሰነ ነው፡፡ አሁን እኮ ዳይሬክተር ያለው ሳይሆን ፕሮዲውሰሩ ያለውን መሥራት ተጀምሯል፤›› ሲልም ያክላል፡፡

ገንዘብ ስላላቸው ብቻ መድረኩን የሚያገኙ፣ ጀማሪዎችና አንድ ሁለት ታዋቂና ተወዳጅ ተዋናዮች ቀላቅለው የሚሠሩ ፊልሞች ለተዋናዮች የሚከፍሉት ክፍያ የተለያየ ነው፡፡ መድረኩን ማግኘት የሚፈልጉ ጀማሪዎች በነፃ ይሠራሉ፡፡ ሻል ያሉት ደግሞ ከ5,000 እስከ 10,000 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ በየፊልሙ የሚታዩ በተመልካቹ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ደግሞ ዳጎስ ያለ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ አንደኛ ደረጃ የሚባሉትና በየፊልሞቹ እንደ ቅመመ ጣል የሚደረጉ ተዋናዮች ከ50,000 ብር ጀምሮ እስከ 150,000 ብር ድረስ ይከፈላቸዋል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ተከፋይ የሚባሉት ተመልካቹ የወደዳቸው ናቸው፡፡ አቅሙ ያላቸውና ሙያው ገብቷቸው የሚሠሩት ያንን ያህል ተከፋይ እንዳልሆኑ በድሉ ይናገራል፡፡ እነዚህ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኙ ተዋናዮች ካልተገኙ ደፍረው ወደ ሥራ የማይገቡ ፕሮውዲውሰሮች ያጋጥማሉ፡፡ በዳይሬክተሩ ታምኖበት ካስት የተደረገ ማንኛውም ጀማሪም ይሁን ታዋቂ ተዋናይ የሚከፈለው ገንዘብ በፊልሙ እንደተሰጠው ቦታ ይወሰናል፡፡ የኢትዮጵያ ፊልም ካርፖሬሽን በነበረበት ወቀት የሚሠራው በዚህ መስፈርት መሠረት እንደነበር የሚናገረው ብርሃኑ በአሁኑ ወቅት ግን አከፋፈሉ ወጥ ካለመሆኑ ባሻገር እንከፍላለን ብለው የሚፈራረሙትና የሚከፍሉት አይገናኝም ይላል፡፡ ፕሮዲውሰሮች የሚያወጡት ገንዘብ ከሥራው በበለጠ እንደሚያሳስባቸውም የታዘበውን ይናገራል፡፡

ነባራዊው ሁኔታ ይኼንን ስለማይፈቅድ ‹‹ሰው ማየት የሚፈልገውን አክተር መርጠን ጠንከር ያለ ገንዘብ እንከፍላለን ምክንያቱም ከኪሱ እስከ 500 ሺሕ ብር አውጥቶ ፊልም የሠራ ፕሮዲውሰር ገንዘቡን አየር ላይ በትኖ አይቀመጥም፡፡ ስለዚህ ለሚታወቅ ሰው ከፍሎ ያሠራል፤›› የሚለው በኃይሉ ገንዘብ የተረፈው ካልሆነ በስተቀር በተዋናዮች ብቃት ብቻ ተማምኖ እንደማይሠራ ያስረዳል፡፡ ከዚያ ባለፈም ፊልሙ ያስገባውን ገንዘብ ተከታትሎ ከሲኒማ ቤቶች መውሰድ ሌላ ጣጣ ነው፡፡ ያላቸውን አሟጠው የሠሩ ፕሮዲውሰሮች ገንዘባቸው እስኪመለስ ዓመትና ከዚያ በላይ ሊጠብቁ ይችላሉ፡፡ ቀጣዩን ፊልም ለመሥራት መጀመርያ ላይ ያወጡት ገንዘብ እስኪመለስ መጠበቅም ግድ ይሆናል፡፡

እንዲህ ያሉ ድርብርብ ችግሮች ባሉበት የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ በነገሥታት መካከል የተከናወኑ የጦር ውሎዎች፣ የአርበኞች ጀብዱን እስክሪፕት አድርጎ ወደ ፊልም መቀየር ይቅርና መንገድ ላይ የሚቀረፁ ቀላል ተውኔቶችን እንኳ መሥራት አሳር ነው፡፡ ተገቢው ጥናት ላይ ተመሥርተው የተጻፉ እስክሪፕቶችን ከማድነቅ ባለፈ ወደ ፊልም መቀየርም ቆራጥነትን ይጠይቃል፡፡ በግለሰብ ኪስ ያልተወሰነ በጀትም ሊኖር የግድ ነው፡፡ ስለዚህም አንዳንድ ወጥ ታሪክ ይዘው የሚወጡ እስክሪፕቶችን እንደሚጠይቁት በጀት እያዩ ገሸሽ ማድረጉ አጭሩ አቋራጭ ሆኗል፡፡

‹‹እንኳን የሁለት ሰዓት ፊልም አይደለም የአምስት ደቂቃ የሙዚቃ ክሊፕ መቼቱን ጠብቆ መሥራት በጣም ከባድ ነው፡፡ የቴዲ አፍሮን ጥቁር ሰው ክሊፕ ለመሥራት ከ400 ሺሕ ብር በላይ ወጥቷል፤›› የሚለው በኃይሉ መሠል ታሪኮችን ወደ ፊልም ለመቀየር የሚጠይቀው ገንዘብ በፕሮውዲውሰሮች አቅም የማይታሰብ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዳገትና ቁልቁለት በበዛበት በዚህ የሙያ መስክ ያላቸውን አውጥተው ከመሥራት ያልቦዘኑ አንዳንድ ባለሙያዎች ብቅ እልም ሲሉ ግን ይታያል፡፡

ከተመረቀ ሳምንታትን ያስቆጠረው ከተለመዱ የኢትዮጵያ ፊልሞች ወጣ ያለ ሐሳብ ይዞ የቀረበው ‹‹ቁራኛዬ›› ፊልም የብዙዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ መቶ ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሶ በዘመኑ የነበረውን የፍትሕ ሥርዓት የሚያሳየውን ፊልሙን ለመሥራት ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን፣ እስክሪፕቱም ለ11 ጊዜያት ያህል መከለሱን፣ ፕሮዳክሹንም አራት ዓመታት መፍጀቱን ስክሪፕቱን የጻፉትና ፊልሙንም ዳይሬክት ያደረጉት ሞገስ ታፈሰ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ 14 ዋና ተዋናዮች፣ 400 ኮርሶች ተሳትፈውበታል፡፡ በዘመኑ የነበረውን ሁኔታ የሚወክል ነገር ለማቅረብም ለ400 ሰዎች በዚያ ዘመን የሚለበሱ አልባሳት አሰፍተዋል፡፡ 14 ተዋናዮችን ለመምረጥ ተዋናዮችን ጨምሮ 580 ሰዎች ተወዳድረዋል፡፡ ‹‹የፈለግነው ታዋቂ ሰዎችን ሳይሆን ፊልሙ የፈለጓቸውን ነው፤›› የሚሉት ዶክተር ሞገስ አንኮበር፣ ደብረብርሃን፣ እንጦጦ አካባቢ የተቀረፀውን ይኼንን ፊልም ሲሠሩ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለፉ ይናገራሉ፡፡

ፊልሙ ከመቶ ዓመታት በፊት የነበረውን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያነሳ እንደመሆኑ ‹‹የድሮ አይፈለግም፤›› እያሉ ያጣጥሉባቸው እንደነበር፣ በዘርፉም አዳዲስ ሰዎችን ይዘው በመግባታቸው ያላመኑባቸው ብዙ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡