Skip to main content
x
‹‹በጃፓን ያሉትን ዕድሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲጠቀሙባቸው ለማስቻል በሚረዱ ሥራዎች ውስጥ እሳተፋለሁ›› ዶ/ር ናጋቶ ናትሱሚ፣ በጃፓን የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ

‹‹በጃፓን ያሉትን ዕድሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲጠቀሙባቸው ለማስቻል በሚረዱ ሥራዎች ውስጥ እሳተፋለሁ›› ዶ/ር ናጋቶ ናትሱሚ፣ በጃፓን የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ

ዶ/ር ናጋቶ ናትሱሚ በሕክምናው መስክ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸውና በከንፈር ብሎም በላንቃ መሰጠንቅ ሕክምና መስክ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ጃፓናዊ ምሁር ናቸው፡፡ የጃፓን የላንቃ መሰንጠቅ ፋውንዴሽንን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ዶ/ር ናትሱሚ፣ በበርካታ አገሮች ውስጥም በሙያቸውና ከሙያቸው ውጪ ባሉ መስኮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በሙያቸው ብቻ ከበርካታ የጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች አልፈው፣ በቬትናም፣ በማይናማር፣ በሞንጎሊያ፣ በላኦስ፣ በካናዳና በኢትዮጵያ በተመላላሽ ፕሮፌሰርነትና በክብር ተወካይነት ጭምር እያገለገለጉ የሚገኙት ዶክተሩ፣ ላለፉት አሥር ዓመታትም በኢትዮጵያ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ሕፃናት የሕክምና ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ የአዲስ አበባና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎችን ከጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር፣ ተማሪዎችና የሕክምና ባለሙያዎች የልውውጥ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማገዛቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የሚመሩት ፋውንዴሽን በሚገኝባት በጃፓኗ የናጎያ ከተማ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ በመሆን ኢትዮጵያን በጃፓን በመወከል፣ ከሕክምናውም ባሻገር በንግድና በባህል መስኮችም በሁለቱ አገሮች መካከል ትብብሮች እንዲጠናከሩ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከአሥር ዓመታት በፊት ሲመጡ በደረሳቸው ግብዣ መሠረት ስለላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ መንስዔና በሽታ፣ እንዲሁም ስለሕክምናው ዘዴዎች ሙያዊ ገለጻ ለመስጠት ቢሆንም፣ በዚያ አጋጣሚ የተጀመረው እንቅስቃሴ አሁን የኢትዮጵያ የክብር ወኪል እስከመሆን ያበቃቸው ደረጃ ላይ አድርሷቸዋል፡፡ ዶ/ር ናትሱሚ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ወቅት ብርሃኑ ፈቃደ ስለከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግሮች፣ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስላላቸው ፍላጎት፣ በተለይም የጃፓን አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ስላሳየው ፍላጎትና ስለሌሎችም ጉዳዮች ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከአሥር ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ በከንፈርና በላንቃ መሰንጠቅ ሳቢያ ለሚሰቃዩ ሕፃናት የሕክምና ድጋፍ በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ እስካሁን ምን ያህል የቀዶ ጥገና ሕክምና አከናውነዋል? ምን ያህሉስ የድኅረ ቀዶ ጥገና ክብካቤ አግኝተዋል?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ይህንን ከመግለጼ በፊት በመጀመሪያ ስለጃፓንና ኢትዮጵያ ግንኙነት ጥቂት ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሁለቱ አገሮች የቆየ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ግንኙነታቸው የሚጀምረውም እ.ኤ.አ. ከ1675 ጀምሮ ነው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩትና ስማቸውን የዘነጋኋቸው መሪ ለጃፓን ንጉሥ ሁለት የሜዳ አህዮችን በስጦታ አበርክተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ እንስሳት በጃፓን ስላልነበሩን፣ ንጉሡ በስጦታው እጅግ በመደሰታቸው ጭምር ከኢትዮጵያ ጋር ኦፊሴላዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደጀመሩ ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት ጊዜ ድረስ ሁለቱ አገሮች አዎንታዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡ የ96 ዓመታት የዕድሜ ባለፀጋዋ እናቴ አሁንም ጤነኛ ነች፡፡ እሷ ሁልጊዜም እንደምትለው ኢትዮጵያና ጃፓን ሁልጊዜም ወዳጃዊ መልካም ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ሁለቱም አገሮች በግርማውያን ንጉሠ ነገሥታት ተመርተዋል፡፡ ሁለቱም ከ2,700 ዓመታት በላይ የዘለቀ ታሪክ ያላቸው ጥንታውያን አገሮች ናቸው፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በኢትዮጵያና በጃፓን ንጉሣውያን ቤሰተቦች መካከል የጋብቻ ዝምድና ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ልዑካኑን ወደ ጃፓን በመላክ ስለጋብቻው ሒደትና ሥነ ሥርዓቱ እንዴት መካሄድ እንደሚኖርበት ምክክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ የጋብቻ ትስስር እስከ ጦርነቱ መቀስቀስ ድረስ በዚህም በዚያም ወገን ዝግጅት ሲደረግበት ነበር፡፡ ይሁንና የዓለም ጦርነት ዳግም ሲጀመር፣ ሁለቱም አገሮች የየራሳቸውን መንገድ ተከተሉ [ጃፓን ትሪፕል አክሲስ እየተባለ ይጠራ ወደነበረው ወደ ጀርመንና ጣሊያን ጎራ ስታቀና፣ ኢትዮጵያም ትሪፕል አሊያንስ ይባሉ ለነበሩት ለእንግሊዝና ፈረንሳይ ወገን አደላች]፡፡

      ይሁንና ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ጃፓንን በመገብኘት ዕርዳታ ለግሰው ነበር፡፡ አንድ ሌላው መወሳት ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1962 በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማይረሳ ልዩ ትዝታ ጥሎ ያለፈው አትሌት አበበ ቢቂላ ነው፡፡ አበበ ዛሬም ድረስ በጃፓን ዝነኛ ነው፡፡ በማራቶን ሩጫ ድል አድርጎ የወርቅ ሜዳይ አስገኝቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ በጃፓንና በኢትዮጵያ መካከል ለተመሠረተው ታሪካዊ ግንኙነት መንገድ የጠረጉ መሠረታዊ ክንውኖች ናቸው፡፡ እኔ ስለምሠራው ጉዳይ ስንነጋገር፣ በሙያዬ ሐኪም ነኝ፡፡ በአብዛኛው ስፔሻላይዝ ያደረግሁት በድድ መሰንጠቅ ሕክምና ነው፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ስለከንፈርና ድድ መሰንጠቅ፣ እንዲሁም ስለሕክምናው ሒደት ሙያዊ ገለጻ እንድሰጥ ከኢትዮጵያ ግብዣ ደርሶኝ ነበር የመጣሁት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በየዓመቱ ከሕክምና ቡድኖች ጋር በመሆን በዚህ በሽታ ለተቸገሩ ሕፃናት ሕክምናውን ስናከናውን ቆይተናል፡፡ የጃፓን የድድ መሰንጠቅ ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም እመራለሁ፡፡ ተቋሙ በሕክምና ብቻም ሳይሆን፣ የሕክምናውን ዘዴዎች በማስተማርና ቴክኒክ ሥልጠናዎችን በመሰጠት ጭምር ይሳተፋል፡፡ በዚህ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ጃፓን እየሄዱ የበለጠ የሕክምናውን ሳይንስ እንዲረዱትና ሥልጠናም እንዲያገኙ ማኅበሩ እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሕክምናውን ለረጅም ጊዜ በተመላላሽ ከመስጠትዎ አኳያ ስለበሽታውና መከላከል ስለሚቻልበት ዘዴ ምን ሊነግሩን ይችላሉ?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- በአማርኛ የተተረጎመ መጽሐፍ አሳትሜያለሁ፡፡ ፍላጎቴ ለሕክምናው ዘርፍ ባለሙያዎችም ለማኅበረሰቡም ስለከንፈርና ድድ መሰንጠቅ በሽታ ምንነትና እንዴት መከላከል እንደሚቻል በሰፊው ማስገንዘብ ነው፡፡ መጽሐፉን ኢንተርነት ላይ በመጫን በርካቶች እንዲያገኙት የማድረግ ሐሳብ አለኝ፡፡ መጽሐፉን በእንግሊዝኛ ብጽፈውም ወደ አማርኛ በመተርጎም የተባበሩኝ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ናቸው፡፡ በመጽሐፉ የተካተቱ ሥዕሎችን በሙሉ ያዘጋጇቸው ባለቤቴና ልጄ ናቸው፡፡ ልጄ እንደእኔው በሕክምናው ዘርፍ የተሠማራችና ተማሪዬም ነች፡፡ መጽሐፉ ለማስተማሪያነት እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከመጽሐፉ ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ፖስተሮችንም በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅተናል፡፡ ይህም ስለበሽታው ተገቢውን ግንዛቤ ለመፍጠርና በበሽታው ጉዳት የደረሰባቸውን ሕፃናት በቤት ውስጥ እንዴት መንከባከብ እንደሚቻል ጭምር ለማስተማር ስለፈለግን ነው፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ስለከንፈርና ድድ መሰንጠቅ ሰፊ የግንዛቤ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ከ90 በመቶ በላይ በሕይወት የተወለዱ ሕፃናት በበሽታው ምክንያት በአግባቡ የእናት ጡት ወተት ለመጠጣትም ሆነ ለመተፈንስ ይቸገራሉ፡፡ በመሆኑም ብዙ ሳይቆዩ የመሞት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ያለው የበሽታው ሥርጭት ከሌሎች እርስዎ ከሚሠሩባቸው የእስያ አገሮች አኳያ ሲታይ ምን ያህል አስከፊ ነው?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ አገሮች በበሽታው የሚጎዱት በግንዛቤ ችግር፣ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ ለሕክምና የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት ስላለባቸው በበሽታው የሚጠቁ ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለበሽታው ጠባይ ምን ሊነግሩን ይችላሉ? ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በሽታው የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል ሊባል ይችላል?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ከአሥር ዓመታት በፊት በርካታ ሰዎች የሞባይል ስልክ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ግን ስልክ ብቻም ሳይሆን፣ ኮምፒዩተርና ሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ መገልገያ ዘዴዎች አሏቸው፡፡ ይህ ለእኛ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በቀላሉ ስለበሽታው መንስዔዎች፣ ስለጉዳቱና እንዴት ሊታከም እንደሚችል በቀላሉ ለማስተማር ዕድሉን ይሰጠናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የበሽታውን ሥርጭት በተመለከተ አንድ አኃዝ እንደሚጠቁመው፣ ከሚወለዱ 672 ሕፃናት አንዱ በከንፈር ወይም በላንቃ መሰንጠቅ በሽታ ተጠቂ ነው፡፡ ይህ ለአገሪቱ ብሎም እንደ እርስዎ ላለው የሕክምና ባለሙያ ጫናውና ፈታኝነቱ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- በብዛት ግምትን መሠረት ባደረጉ መረጃዎች ላይ ጥገኛ እየሆንን ያለነው፡፡ ምን ያህል ሕፃናት ይወለዳሉ? ምን ያህሉስ በበሽታው ይጠቃሉ? የሚሉትን የሚያሳዩ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎች ሊኖሩን ይገባል፡፡ የክትትል ሥርዓትም በተገቢው መንገድ በመዘርጋት ምን ያህል የበሽታው ክስተት እንደታየ አመላካች መረጃዎችን በአግባቡ መሰብሰብ ይገባል፡፡ ከ20 ወይም ከ30 ዓመታት በፊት ስናይ፣ በሽታው የሚከሰትባቸው አጋጣሚዎች ላይ የተለያዩ መረጃዎች ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት በከፍተኛ መጠን ይጨምርና በሌላ ጊዜ ደግሞ ጋብ ይል ነበር፡፡ በየዓመቱ ከፍ ዝቅ ይል ነበር፡፡ ይሁንና ከአሥር ዓመታት ወዲህ ግን እንድምናስበው የበሽታው ክስተት መጠን በጣም ከፍተኛ የመሆኑ ዝንባሌ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባሰባሰብነው መረጃ መሠረት፣ ስለበሽታው እኛ ከዚህ ቀደም እናስብ እንደነበረው ሳይሆን ጥቂት ሕፃናትን ብቻ ነው እያጠቃ የሚገኘው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንደ የንግግር ሕክምናን ጨምሮ ያለው የድኅረ ቀዶ ጥገና ሕክምናና ሌላውም ተካቶበት፣ አንድ በከንፈር ወይም በላንቃ መሰንጠቅ የተጠቃ ሕፃን ለማከም ወጪው ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ወጪው እንደሚቀርበው የሕክምና ሒደት፣ እንደሚሰጠው የሕክምና ክብካቤና እንደሚቀርበው የመድኃኒት ጥራትና ዓይነት ይወሰናል፡፡ እንበልና ርካሽ በሚባሉ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያዎች ለሚታከም ታማሚ ወጪው ምናልባት ከ200 እስከ 300 ዶላር ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና እኛ ከጃፓን ከምናስመጣቸው ጥራት ካላቸው የሕክምና ቁሳቁሶችና የሕክምና አሰጣጥ ሒደቶች ብሎም ከመድኃኒት ዓይነቶች አኳያ ሲታይ፣ ወጪው ምናልባትም ከ1,000 እስከ 1,500 ዶላር ሊደርስ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ የበሽታው ተጎጂ ሕፃናት በሕይወት ሊቀዩ የሚችሉበት ዕድል አላቸው?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ከ60 ዓመታትና ከዚያም በፊት ከበሽታው ጋር የሚወለዱ ሕፃናት ጉዳይ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ከተወለዱ በኋላ በበሽታው መጠቃታቸው ሲታወቅ፣ ዕጣ ፈንታቸው ሞት ነው የሚሆነው፡፡ አዋላጆቹ ከድድና ከከንፈር መሰንጠቅ በሽታ ጋር በተወለዱት ሕፃናት አፍና አፍንጫ ላይ እርጥብ ፎጣ በማኖር እንዲያሸልቡ ያደርጓቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ከባህላዊ ጉዳዮችም አንፃር ከንፈራቸው ወይም ላንቃቸው ተሰንጥቆ የተወለዱ ሕፃናት ከሕዝቡ እምነትና ባህል ውጪ ተደርገው ስለሚታዩ በሕይወት የመኖራቸው ጉዳይ ፈታኝ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት ግን በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አሁንም ፈታኝ ነው፡፡ በተለይም በኢኮኖሚ ደረጃቸው ዝቅ ያሉ አገሮች ውስጥ፣ በገጠራማ አካባቢ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች አካባቢ ከዚህ በሽታ ጋር የሚወለዱ ሕፃናት ዕጣ ፈንታ እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ተስፋ የማደርገው ወደፊት ከበሽታው ጋር የሚወለዱ ሕፃናት በቀላሉ በሕይወት መኖር የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እንደሚያገኙ ነው፡፡ ሁሉም እኮ መሠረታዊ የመኖር ሰብዓዊ መብት አላቸው፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ስለበሽታውና ሕፃናት ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ተገቢው ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ትክክለኛው መረጃ እንዲደርሳቸው መደረግ መቻል አለበት፡፡ ኢትዮጵያን መጎብኘት በጀመርኩበት ወቅት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ነበር ግንኙነት የማደርገው፡፡ በበሽታው ላይ የሚሠሩና የሚመራመሩ ሐኪሞችን በማግኘታችን በርካታ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት አስችሎናል፡፡ በርካታ የሕክምናና የክብካቤ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡ በማማከርና በድኅረ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሥራዎችም ላይ ብዙ አበርክተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጪዎቹ አምስት ወይም አሥር ዓመታት ውስጥ በሽታውን ለማስወገድ የሚያስችሉ ዕድሎች ወይም ተስፋዎች አሉ?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ይህ እንኳን በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ሊሆን የሚችል ነገር አይመስለኝም፡፡ በሽታው በቶሎ ይጠፋል የሚለው የማይሆን ነገር ቢሆንም፣ በበሽታው የተጎዱ ሕፃናት በሕይወት እንዳይኖሩ የሚያደርግ ፈተናም ተደቅኗል፡፡ በርካቶች እናቶች በማህፀናቸው ያለው ሕፃን የበሽታው ተጎጂ እንደሆነ ሲያውቁ ለማስወረድ እየሞከሩ ነው፡፡ ቅድም ከበሽታው ጋር የተወለዱ ሕፃናት በተለያየ ባህላዊ አመለካከቶች ሳቢያ በሕይወት የመቆየታቸው ጉዳይ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ ዓይተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ እየታገዙ እናቶች ከመውለዳቸው በፊት ሆዳቸው ውስጥ ስላለው ልጃቸው የጤና ሁኔታ አስቀድመው ያውቃሉ፡፡ በመሆኑም የከንፈር መሰንጠቅ ወይም የላንቃ መሰንጠቅ እንዳለበት ሲያውቁ የማስወረድ አባዜ እየታየ ነው፡፡ እናቶች ሊያጤኑት የሚገባቸው ጉዳይ ግን፣ ጤናማ ሆኖ የተወለደው ልጃቸውም ቢሆን በአደጋና ባልታሰበ ድንገተኛ በሽታ ምክንያት ጤናው ሊጎዳ እንደሚችል፣ የአካል ጉዳትና ሌላም የከፋ ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችል ነው፡፡ እየተለመደ የመጣው መጥፎ ሁኔታ ግን እናቶች በማኅፀናቸው ያለው ልጅ የሆነ የጤና እክል ያለበት እንደሆነ ማስወረድ ነው፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ አስገራሚ የሳይንስ ውጤቶችን የምናይበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በሕክምናውም ሆነ በሌላውም መስክ ተስፋ የሚጣልበት የ‹‹ጂን ኤዲቲንግ›› የሰዎችን ዘረ መል የማስተካከል ሕክምና ነው፡፡ የሕፃናት ዘረመል በማህፀን ሳሉ መስተካከል የሚችልበት ዕድል እንዳለ እየሰማን ነው፡፡ ይህ በከንፈርና በላንቃ መሰንጠቅ ለሚጎዱ ሕፃናት ሕክምና ላይ ተስፋ የሚሰጥ አዲስ ግኝት ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- በርካታ የምርምር ጽሑፎችን በጂን ኤዲቲንግ ላይ አካሂጃለሁ፡፡ በመጪዎቹ 20 ዓመታት ውስጥ የጂን ኤዲቲንግ ምናልባት ለካንሰር ታማሚዎች የሕክምና አማራጭ ሆኖ ሊያገልግል ይችላል፡፡ ሒደቱ ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ቢሆንም ለከንፈርና ለላንቃ መሰንጠቅ የሕክምና ሒደቶች አጋዥነቱ ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህንን የሕክምና ዘዴ ለእነዚህ ታማሚዎች ማዋል በጣም ከባድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ምናልባት የበሽታውን የመከሰት መጠን ልንቀንሰው እንችል ይሆናል፡፡ ከዚህ ይልቅ በአሁኑ ወቅት በቅድመ ወሊድና ድኅረ ወሊድ ወቅት የሚሰጡ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች ጤናማ ሕፃናት እንዲወለዱ እያገዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ፎሊክ አሲድን የመሳሰሉ ቅድመ ወሊድ እንክብሎች ለእናቶችም ሆነ ለሕፃናት ጤናማነት አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የከንፈርም ሆነ የላንቃ መሰንጠቅ በሽታን ማስወገድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የመከሰቻ መጠኑን መቀነስ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለሌላው የእርስዎ እንቅስቃሴ እናውራ፡፡ በጃፓን የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ እንደመሆንዎ በዚህ ውክልና ምንድን ነው የሚያከናውኑት ተግባር?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- በአገሮች መካከል ትብብርና የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር በሚያግዙ ሥራዎች ውስጥ ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ላለፉት 15 ዓመታትም ይህንኑ ሳከናውን ቆይቻለሁ፡፡ የክብር ቆንስላነት ማዕረግ ከተሰጠኝ በኋላም በአገሬና በኢትዮጵያ መካከል የጋራ ጥቅም በሚያስገኙ መስኮች ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ የንግድ ተቋማትንም በማስተባበር የምሳተፍባቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቶኪዮ የቀጥታ በረራ መጀመሩ በብዙ መልኩ እኛን የሚያግዝ ዕድል ፈጥሮልናል፡፡ በየዓመቱ ከአምስት ሚሊዮን ዘንግ ያላነሰ አበባ ከኢትዮጵያ ወደ ጃፓን ይላካል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይህ መጠን ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ዘንግ ያድጋል ብለን እናስባለን፡፡ እንዲህ ያለውን የንግድ ግንኙነትና ትብብር ወደ ሌሎቹም መስኮች ማስፋፋት እንፈልጋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለመገንዘብ እንደቻልኩት በጃፓኑ ሚትሱቢሺ አውሮፕላን አምራች ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የሥራ ግንኙነት እንዲመሠረት እርስዎ መሀል ሆነው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አብራርተው ቢነግሩን?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- አውሮፕላን አምራቹ የሚትሱቢሺ ኮርፖሬሽን ፕሬዚዳንት ወዳጄ ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴውን ማስፋፋት ይፈልጋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዕቅድ በሚሳካበት ወቅት፣ በአፍሪካ የጥገናና የመለዋወጫ አቅርቦት የሚያከናውንበት ቦታ ያስፈልገዋል፡፡ በእስያ የራሱን አውሮፕላኖች የሚያንቀሳቅስበት አየር መንገድ ያለው ሲሆን፣ ይህም እስከ 3,000 ኪሎ ሜትር ባለው ክልል ውስጥ መብረር የሚችሉና እስከ 90 መንገደኞችን ማጓጓዝ የሚችሉ አውሮፕላኖችን በማምረትና በአየር መንገዱ አማካይነት በማሰማራት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ነገሮች እንደሚፈለገው መሄድ ከቻሉ፣ የሚትሱቢሺ አውሮፕላኖች የጥገናና የመለዋወጫ ማዕከል ኢትዮጵያ እንድትሆን ይፈለጋል፡፡ አዲስ አበባን ዋና መገኛው በማድረግ አፍሪካን የጥገናና የመለዋወጫ ማዕከል የማድረግ ሐሳብ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረገ ወይም የተጀመረ የስምምነት ወይም የድርድር ሒደት አለ?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- ባለፈው [ከሦስት ዓመታት በፊት በናይሮቢ የተካሄደ] በቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ኮንፈረስ (ቲካድ) ስብሰባ ወቅት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የሚትሱቢሺ አውሮፕላን አምራች ኮርፖሬሽን ፕሬዚዳንት በጉዳዩ ላይ እንዲመክሩበት ለማድረግ ችዬ ነበር፡፡ ወደፊት ሊሳካ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ምናልባትም እ.ኤ.አ. ከ2022 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ አንድ ውጤት ማየት የምንችል ይመስለኛል፡፡ ገና ጅምር ላይ ያለ ሒደት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከንግድና ከመሰል ግንኙነቶች ባሻገር በባህልና በትምህርት ግንኙነትና ልውውጥ መስክ ምን ሊባል ይችላል?

ዶ/ር ናትሱሚ፡-  በአሁኑ ወቅት 1,000 ኢትዮጵያውያን በጃፓን ይኖራሉ፡፡ በርካቶች ወደ ጃፓን እንዲመጡ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ በጃፓን በርካታ የሥራ ዕድሎችም አሉ፡፡ የሕዝባችን ቁጥር 124 ሚሊዮን ነው፡፡ ይሁንና የውልደት ምጣኔው በአሳሳቢ ደረጃ በየጊዜው እያሽቆለቆለ በመሆኑ፣ በርካታ የሰው ኃይል ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ክህሎቱ ያላቸው ዜጎች በጃፓን መልካም አጋጣሚ እንዳለ ማሰብ አለባቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ጃፓን ለተጨማሪ የትምህርት ዕድል የሚያቀኑ ተማሪዎች እግረ መንገዳቸውን የአጭር ጊዜ ሥራዎችን ያገኛሉ፡፡ ከተሞክሯቸውም ቋንቋና ክህሎት ስለሚያካብቱ ከጃፓን ኩባንያዎች ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ይህንን ዕድል የሚያሰፋ እንቅስቃሴ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ዕቅዴም በኢትዮጵያና በጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የልውውጥ ፕሮግራሞች እንዲስፋፉ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም በጃፓን የሥራ ዕድሎችን እንዲያገኙ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ከመንግሥት ባሻገር በርካታ የግል ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት የነፃ ትምህርት ዕድል በመስጠት የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው፣ በጃፓን ያሉትን ዕድሎች ኢትዮጵያውያን እንዲጠቀሙባቸው ለማስቻል በሚረዱ ሥራዎች ውስጥ እሳተፋለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅን በተመለከተ መጪው ጊዜ ምን ይዟል? በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ በመጪዎቹ ሦስትና አምስት ዓመታት ውስጥ ሊኖር የሚችለው ለውጥስ ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ናትሱሚ፡- በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያና ጃፓን አንዱ ለሌላው በጣም ጠቃሚ አገሮች ናቸው፡፡ ሁለቱም በሚገኙባቸው አኅጉራት ውስጥ ወሳኝ ፖለቲካዊ ሥፍራ አላቸው፡፡ እንደማስበው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመሪነት ቦታውን ይዛለች፡፡ ጃፓንም በእስያ ተመሳሳይ ሚና አላት፡፡ በመሆኑም ካላቸው የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት አኳያ ወደፊትም ውጤታማና ይበልጥ እያደገ የሚሄድ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ አስባለሁ፡፡ በሙያዬ በሕክምናው መስክ በርካታ ለትብብር የሚያበቁ መስኮች አሉ፡፡ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሕክምና የልውውጥ ፕሮግራሞችን ዘርግተናል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲም ጋር ተመሳሳይ ግንኙነት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን፡፡ ሒደቱ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ በርካታ የጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር እህትማማች ግንኙነት እንዲመሠርቱ እፈልጋለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ፕሮፌሰር እንደ መሆኔ መጠን፣ በዩኒቨርሲቲውና በጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው ግንኙነትም የበለጠ እንዲስፋፋ የማድረግ ፍላጎት አለኝ፡፡