Skip to main content
x
እንኳን ክልላችን ኢትዮጵያም ትጠበናለች መባል አለበት!

እንኳን ክልላችን ኢትዮጵያም ትጠበናለች መባል አለበት!

ታላቁ የዓድዋ ድል 123ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተጠናቀቀ ማግሥት፣ እንደ ታላቅ አገር ሕዝብ አንዳንድ ጉዳዮችን ሰከን ብሎ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ከዛሬ 123 ዓመታት በፊት እግራቸውን ለጠጠር ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው ለእናት አገራቸው በክብር የተሰውትን ጀግኖች ገድል ስንዘክር፣ በእነዚህ ጀግኖች ተጋድሎ ምክንያት በዓለም ዙሪያ በቅኝ ገዥዎች ተደቁሱው ይገዙ የነበሩ ወገኖች እንዴት በኩራት አንገታቸውን ቀና እንዳደረጉ ማስታወስ የግድ ይላል፡፡ ዓድዋ ላይ ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ታላቅ ድንጋጤና ራስ ምታት የፈጠረ አንፀባራቂ ድል ሲመዘገብ፣ በመላው ዓለም የተፈጠረው መነቃቃትና እንቢ ባይነት የኢትዮጵያን ተምሳሌታዊነትና ፋና ወጊነት ሲዘክር ይኖራል፡፡ የአያቶቻችንና የቅድመ አያቶቻችን የእናት አገር ፍቅርና ወደር የሌለው መስዋዕትነት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሽጋገረ እዚህ ዘመን ላይ አድርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ስም በመላው ዓለም እየናኘ የጀግንነት ተምሳሌት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንና የቅኝ ግዛት ሰለባ የነበሩ በርካታ አገሮች መከረኞች ተስፋ እንደነበረች፣ በተለያዩ ድርሳናት ተከትቦ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ ናት፡፡ ይኼንን የመሰለ ድንቅ ታሪክ ያላት ታላቅ አገር ይዘን ለምን እናንሳለን? ለምን ራሳችንን በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በጎጥ እናጥራለን? የአፍሪካ መሪ መሆን ሲገባን ለምን እንጎተታለን? የዚህ ዘመን ትውልድ ራሱን መመርመር አለበት፡፡

በተለይ ወጣቶች ከጠባብ አካባቢ በላይ አገር፣ ከአገር በላይ አኅጉር፣ ከአኅጉር በላይ ደግሞ ሰፊዋ ዓለም እንዳለች መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዘመኑ የግሎባላይዜሽን እንደ መሆኑ መጠን፣ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ የዓለም ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጣም እየተቀራረበ ነው፡፡ በዚህች በጣም እየተጠጋጋች ባለች ዓለም ውስጥ እየኖሩ ክልል ወይም ጎጥ ውስጥ መወሸቅ፣ የዓይጥ ጉድጓድ ውስጥ ከመደበቅ አይተናነስም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ አንገትን ቀና አድርጎ የሚያስኬድ ታላቅ ተግባር የፈጸመች የጀግኖች አገር መሆኗ እየታወቀ፣ እንደ እንቁራሪት ከጉድጓዳቸው ውጪ ሌላ ዓለም የሌለ በማስመሰል ከሚያጭበረብሩ ሴረኛ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው ቅስቀሳ ራስን መጠበቅ ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን ወጣቶች ማንም እየተነሳ እንደ አህያ የሚጭናቸው፣ እንደ ፈረስ የሚጋልባቸው፣ ወይም እንደ ግመል የሚጎትታቸው ሳይሆኑ፣ እንደ ጀግኖቹ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው በህሊናቸው እየተመሩ አገራቸውን የሚጠብቁና የሚያሳድጉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ድንበር ድንጋይ አንድ ቦታ ተገትረው ምንም አያገኙምና፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር የመሆኗ ሚስጥር የጀግኖች፣ የአስተዋዮች፣ የቀናዎች፣ የታታሪዎችና የደጎች አገር ስለሆነች ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ የሚያኮሩ እሴቶች የሚጋሩ ኢትዮጵያዊያን የእንግዳ ተቀባይነታቸውን ያህል፣ አገራቸውን ለመውረር ወይም ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ሁሉ ሲያሳፍሩ ኖረዋል፡፡ በዓድዋ ጦርነት አይቀጡ ተቀጥቶ በኃፍረት የተባረረው ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ ዘመናዊ ሠራዊት፣ የጦር መሣሪያና የመርዝ ጋዝ ታጥቆ ቢመጣም፣ በዱር በገደሉ በተዋደቁ ጀግኖች አርበኞች ዳግም መደቆሱ ይታወሳል፡፡ ይህ የፋሽስት ኃይል የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር፣ በሃይማኖትና በተለያዩ መንገዶች ለመከፋፈል ቢሞክርም፣ ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን ግን በአንድነት በመቆም ድምጥማጡን አጥፍተውታል፡፡ ይኼንን የመሰለ ታላቅ ጀብድ የተፈጸመው ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን ለእናት አገራቸው የነበራቸው ፍቅር ቃላት ከሚገልጹት በላይ ስለነበር ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የአገሩን ታሪክ በሚገባ ቢመረምር፣ እንኳን ክልልና ጎጥ ውስጥ ሊወሸቅ ኢትዮጵያ ራሷ ትጠበው ነበር፡፡ ወጣቶች በራሳቸው ንፁህ አዕምሮ ታሪካቸውን መልሰው መላልሰው በማየት፣ አገር ከእነሱ ምን እንደምትጠብቅ መረዳት አለባቸው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ፈተናዎችን አልፋ እዚህ ደርሳለች፡፡ ለአገራቸው በደማቸው መስዋዕትነት የከፈሉ እጅግ በርካታ ጀግኖች ልጆች ቢኖሯትም፣ ለጠላት አሳልፈው የሰጧትም አሉ፡፡ እነዚህ በታሪክ ስማቸው የዘቀጠ ግለሰቦች ለልጅ ልጆቻቸው ማፈሪያ ሆነዋል፡፡ የዘመኑ ትውልድ መጠንቀቅ ያለበት ከእንዲህ ዓይነቱ የታሪክ ፍርጃ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ በሕክምና፣ በንግድ፣ በቤተ እምነቶችና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ወገኖች ትውልድን የማነፅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በክልልና በጎጥ ታጥሮ የአገሩን የታላቅነት ታሪክ እንዳያጠፋ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ አገር የማስተዳደር ኃላፊነት ላይ ያሉ ወገኖችና ተከታዮቻቸው፣ ወጣቱ ትውልድ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከቃል በላይ በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለምሥራቅ አፍሪካ፣ ከዚያም አልፋ ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆን እንደምትችል ራዕይ መሰነቅ አለባቸው፡፡ ከክልልና ከጎጥ አጥር ውጪ የማይታያችሁ ስመ ፖለቲከኞችም፣ ከተዘፈቃችሁበት አረንቋ ውስጥ ውጡ፡፡ ሰፊው ዓለም እያለላችሁ ጠባችሁ ጠባችሁ አትነሱ፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን የእናንተ ዓላማ በጣም ይጠባቸዋል፡፡

ለኢትዮጵያውያን የሚበጀው ማንነትን፣ ቋንቋን፣ እምነትን፣ ባህልን፣ ወዘተ እያከበሩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ነው፡፡ ይኼንን ማድረግ ሲቻል ሙሉ ሰው መሆን አያቅትም፡፡ ልዩነትን አክብሮ ስለጋራ ጉዳዮች መጨነቅና መጠበብ ሲቻል ትልቁ ምሥል አገር ትሆናለች፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ከዓለም ፀጋና በረከት የድርሻን ማንሳት ይቻላል፡፡ ራስን መንደር ውስጥ ወሽቆ የአገርን ታሪክ ማንቋሸሽና የጀግኖችን ስም ማጠልሸት ደካማነት ነው፡፡ ደካማ ደግሞ እንኳን ለመምራት ለመመራትም ብቁ አይሆንም፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች በጀግኖች መሪዎች እየተመሩ አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩት፣ ከበደልና ከግፍ በላይ አገር የምትባል የጋራ ቤታቸውን ማሰብ የቻሉ አስተዋዮች በመሆናቸው ነው፡፡ የተበዳይነት ትርክት ውስጥ ተቀርቅሮ የአባቶችንና የእናቶችን ተጋድሎ ማንኳሰስና ጎጥ ውስጥ መደበቅ፣ በዚህ በሠለጠነ ዘመን መሳቂያ ያደርጋል እንጂ አያስከብርም፡፡ የአሁኑ ዘመን ትውልድ ደግሞ እንኳን ክልል አገሩ እየጠበበችው መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ጀግኖችን በክብር እየዘከሩ የአገርን ታላቅነት ማስመለስ ይለመድ፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንና የዓለም ምንዱባን ተምሳሌት እንደነበረችው ሁሉ፣ ዛሬም በግንባር ቀደምትነት ስሟ በዴሞክራሲና በብልፅግና እንዲጠራ ትውልዱ ኃላፊነት አለበት፡፡ እንኳን ክልሉ ኢትዮጵያም እንደምትጠበው ትውልዱ በተግባር ያሳይ!