Skip to main content
x
ለአፋር ክልል 24 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሕክምና መሣሪያዎች ተሰጡ
ከተበረከቱት የሕክምና መሣሪያዎች መካከል አልትራሳውንድ ይገኝበታል

ለአፋር ክልል 24 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሕክምና መሣሪያዎች ተሰጡ

አምሪፍ ሔልዝ ኢን አፍሪካ የተባለ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ በአፋር ክልል ለማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞችና ለአዋላጅ ነርሶች አገልግሎት የሚውሉና 24 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሕክምና መሣሪያዎች ለአፋር ክልል ጤና ቢሮ ባለፈው ሳምንት በዕርዳታ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ምክትል ካንትሪ ዳይሬክተርና የፕሮግራሞች ኃላፊ የሺጥላ ኃይሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ ለሚገኙ 93 ጤና ኬላዎች፣ 23 ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም ለአሥር የወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤቶች የሚዳረሱት እነዚሁ የሕክምና መሣሪያዎች ሠራተኞቹና ነርሶቹ በጀርባቸው በሚያዝሏቸው ቦርሳቸው ውስጥ ከትተው በቀላሉ ሊያጓጉዙዋቸው የሚችሉ ናቸው፡፡

ከሕክምና መሣሪያዎቹም መካከል አልትራሳውንድ፣ የደም ግፊትና የልብ ትርታን የሚቆጣጠር ዲጂታል መለኪያዎች፣ የልብ መመርመርያ፣ ሕፃናት በሳንባ ምች መያዝ አለመያዛቸውን የሚለዩ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ መሣሪያዎቹም ከፊሊፕስ ኮሙዩኒቴ ላይፍ ሴንተር አውትሪች ኬት የመጡ መሆናቸውን ከሦስት ሳምንት በፊትም በጋምቤላ፣ በሶማሌ፣ በአፋርና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያለውን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በመካሄድ ላይ ላለው ፕሮጀክት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወይም 4.2 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የሕክምና መሣሪያዎችና ቁሳቁሶችን አምሪፍ መለገሱን ተናግረዋል፡፡  

ከዩኤስ ኤይድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተገዝተው ከተለገሱት ከእነዚሁ የሕክምና መሣሪያዎች መካከል ወደ ክልሎች ቢሄዱ ካላቸው የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አኳያ ሊጠቀሙባቸው የማይችሏቸውን በጣም ዘመናዊ የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎች ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅና ለጥቁር አንበሳ ቲቺንግ ሆስፒታል መስጠታቸውን ዶ/ር የሺጥላ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም መሣሪያዎች መካከል ለጥቁር አንበሳ ቲቺንግ ሆስፒታል የተሰጠው መሣሪያ ዋጋው አንድ ሚሊዮን ዶላር መሆኑንም ከምክትል ካንትሪ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

ከአሥራ ሰባት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመው አምሪፍ፣ አብዛኞቹ ፕሮግራሞቹ የሚገኙት በአፋር፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ነው፡፡ በተጨማሪም በመሀል ከተሞችና በአብዛኛው አቅም በሌላቸው ከተሞች ውስጥም እንደሚሠራ ገጸ ታሪኩ ያመለክታል፡፡