Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ይደውሉላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ይደውሉላቸዋል

[ለክቡር ሚኒስትሩ የእህታቸው ልጅ ስልክ ደወለላቸው]      

 • ሰላም ጋሼ፡፡
 • እንዴት ነህ ጎረምሳው?
 • አለሁ ጋሼ፡፡
 • እናትህ እንዴት ናት?
 • ትንሽ አሟታል ባክህ፡፡
 • ምን ሆነች ደግሞ?
 • ብዙ ነገር ነዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ምን ጋሼ የእኛን ኑሮ እያወቅከው?
 • እኮ ምን ሆናችሁ?
 • ጋሼ አራቱም ወንድሞቼ እኮ ሥራ የላቸውም፡፡
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ይኼን ቤተሰብ ከማስተዳደር እኮ አገር ማስተዳደር ይቀላል፡፡
 • ወዴት ወዴት?
 • ማለቴ ምን ያህል አስቸጋሪ ሕይወት እየመራች መሆኑን ልነግርህ ነው፡፡
 • ቢሆንም ከአገር ማስተዳደር ጋር ማነፃፀር አይገባም፡፡
 • እሱማ ምን ያህል ከባድ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
 • ምኑ ነው ከባድ?
 • አገር ማስተዳደሩ ነዋ፡፡
 • ማን ከበደን አለህ?
 • ባትሉም እንደ ከበዳችሁ ታስታውቃላችሁ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ጋሼ አገሪቱን እያየሃት አይደል እንዴ?
 • የለውጡ አደናቃፊ ነህ እንዴ?
 • ምነው ጋሼ?
 • ምነው?
 • ለለውጡ ስንትና ስንት መስዋዕትነት እንደከፈልን ረሳኸው?
 • ታዲያ ምን እያልክ ነው?
 • ያው ከለውጡ የጠበቅነውን አላገኘንም ብዬ ነው፡፡
 • ከለውጡ ምን ነበር የጠበቅከው?
 • ብዙ ነገር ጋሼ፡፡
 • እኮ ምን?
 • እኔን ጨምሮ ሁሉም ወንድሞቼ ሥልጣን የሚያገኙ መስሎኝ ነበር፡፡
 • ሌላስ?
 • በቃ ይኼ ዘግናኝ የድህነት ሕይወታችን በአንዴ የሚያበቃ መስሎኝ ነበር፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቶኝ በአንዴ ባለሀብት የምሆን መስሎኝ ነበር፡፡
 • ሲያምርህ ይቅር፡፡
 • አሁንማ ገባኝ፡፡
 • ምኑ ነው የገባህ?
 • የማስበው ሁሉ ህልም እንደሆነ፡፡
 • ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም ሲባል አልሰማህም?
 • ምን እያልክ ነው ጋሼ?
 • ለውጡ በአንድ ጊዜ አይመጣም፡፡
 • አሁን እንኳን አልታለልም ጋሼ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ለውጡ ለእኛ ጭራሽ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
 • መጀመሪያውንም ቢሆን እኮ ጠርጥሬያለሁ እኔ?
 • ምኑን ነው የጠረጠርከው?
 • ከለውጡ አደናቃፊዎች ጋር መወገንህን፡፡
 • ኧረ ለእርሱ እኔ ጊዜ የለኝም፡፡
 • ታዲያ ይኸው ለውጡ ለእኔ ጭራሽ አስቸጋሪ ሆኗል እያልክ አይደል እንዴ?
 • እኮ ሕይወታችን ከድጡ ወደ ማጡ ስለሆነብኝ ነዋ፡፡
 • ሁሉም ችግር በአገር የመጣ ስለሆነ መቻል አለብህ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን የደወልኩት አንድ ነገር ሰምቼ ነው፡፡
 • ምን ሰማህ?
 • የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሊወጣ ነው አሉ፡፡
 • አዎን ሰምቻለሁ፡፡
 • አንድ ባለሁለት ፈልጌ ነው፡፡
 • ባለሁለት ምን?
 • መኝታ ነዋ፡፡
 • ምን?
 • 20/80!

[የክቡር ሚኒስትሩ የታላቅ ወንድም ልጅ ስልክ ደወለችላቸው]

 • ሰላም ጋሼ፡፡
 • ከየት ተገኘሽ አንቺ ዱርዬ?
 • ምን መሄጃ አለኝ ብለህ ነው ጋሼ?
 • ለመሆኑ ምን እየሠራሽ ነው?
 • ምንም ጋሼ፡፡
 • ሥራ የለሽም?
 • ከየት መጥቶ ጋሼ?
 • ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀሻል አይደል እንዴ?
 • ብመረቅስ ታዲያ?
 • ሥራ እንዴት የለሽም ብዬ ነዋ?
 • እየቀለድክብኝ መሆን አለበት ጋሼ፡፡
 • የምን ቀልድ ነው?
 • አገሪቱ ውስጥ ሥራ ከማግኘት ሎተሪ ቆርጠህ የሚወጣልህ ዕድል የተሻለ ነው፡፡
 • አንቺም በለውጡ አታምኚም?
 • በለውጡማ በጣም አምናለሁ ጋሼ፡፡
 • ታዲያ ምን እያልሽ ነው?
 • በለውጡ ግን ሥራ የለም፡፡
 • ለምን አትፈጥሪም ታዲያ?
 • ምንድነው የምፈጥረው?
 • ሥራ ነዋ፡፡
 • እሱማ አያዋጣም ጋሼ፡፡
 • ለምንድነው የማያዋጣው?
 • ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል፡፡
 • ይኼ እንኳን ስንፍናሽን ለመሸፈን ይመስላል፡፡
 • እንዴት ጋሼ?
 • ሥራ መፍጠር ሲያቅትሽ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል ምናምን ትያለሽ፡፡
 • ሲጀመር ጋሼ ትምህርት ቤትስ ቢሆን መቼ ሥራ ፈጠራ አስተማሩን?
 • ምን?
 • በዚያ ላይ አሁን ወጣቱ ሥራ ከመፍጠር ግጭት መፍጠር ይቀለዋል፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ ዩኒቨርሲቲ ገብተን ተመርቀን እስክንወጣ ሜጀር ያደረግነው ግጭትን ነዋ፡፡
 • እውነትም ብልሹ የሆነ ትውልድ ነው፡፡
 • ከዚያም ባለፈ ሥራ ከመፍጠር ግጭት መፍጠር አሁን አዋጭ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ግጭት በመፍጠር በአንዴ ታዋቂ ትሆናለህ፣ ስለዚህ ራስህን ለመሸጥ ቀላል ነው፡፡
 • ምን?
 • በአጠቃላይ ሥራ በቀላሉ ማግኘት ከባድ ነው፡፡
 • ለምን በወረዳ አትደራጂም?
 • ተደራጅቼ ነበር ጋሼ፡፡
 • ሥራ አልሰጡሽም ታዲያ?
 • ጋሼ ሥራው ለእኔ የሚሆን አይደለም፡፡
 • አየሽ ሥራ ትንቂያለሽ ማለት ነው፡፡
 • ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት አንድ ነገር ሰምቼ ነው፡፡
 • ምን ሰማሽ?
 • የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሊወጣ ነው አሉ፡፡
 • እሺ፡፡
 • አንድ ባለሦስት ፈልጌ ነበር፡፡
 • ባለሦስት ምን?
 • መኝታ ነዋ፡፡
 • ምን?
 • 40/60!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ይደውሉላቸዋል]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ሥራ እንዴት ይዞታል?
 • መቆሚያ መቀመጫ የለኝም፡፡
 • ለውጡ አያስተኛም አይደል?
 • ተረቱ ራሱ ተቀየረ አይደል እንዴ?
 • የቱ ተረት?
 • ከመውለድህ በፊት ተኛ የሚለው ነዋ፡፡
 • ምን ተባለ?
 • ከለውጡ በፊት ተኛ ተባለ፡፡
 • እርሱስ እኔም እንቅልፍ የለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተማ በፊትስ መቼ ተኝተህ ታውቃለህ?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ በደህነኛውም ጊዜ በኪኒን ነው የምትተኛው ብዬ ነው፡፡
 • ቀልድ መቼም ያቁበታል?
 • በለውጡ ቀልድ የለም ወዳጄ፡፡
 • አንዳንድ ነገሮች ግን እያስፈሩኝ ነው፡፡
 • ምንድነው የሚያስፈራህ?
 • የዘረኝነት ጉዳይ፡፡
 • ምኑ ነው ያስፈራህ?
 • አገሪቱ እኮ በጣም እየተከፋፈለች ነው፡፡
 • ይኼ የፀረ ለውጡ ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዲያውም አገሪቱ ወደ አንድነት ጎዳና እያቀናች ነው፡፡
 • ቢሆንማ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
 • አይደለም እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በየቦታው የሚታየው ዘረኝነት ግን ያስፈራል፡፡
 • ዘረኝነት ለ27 ዓመታት የተዘራ የፖለቲካ ዘር ነው እኮ፡፡
 • እንዴት ማጥፋት ይቻላል ክቡር ሚኒስትር?
 • እ…
 • ማለቴ ሁሉም ቦታ ሕዝቡ በዘርና በጎሳ እየተደራጀ ነው፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ሳይቀሩ እኮ በዘርና በጎሣ ነው የሚታደሉት፡፡
 • ማን ነው እንደዚህ እያለ የሚያስወራው?
 • ክቡር ሚኒስትር የእኛ አገር ዘረኝነት እኮ ከሕዝቡም በላይ ሄዶ መሬቱም ዘረኛ ሆኗል፡፡
 • አልገባኝም?
 • ማለቴ የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት፣ የትግሬ መሬት ምናምን እያልን ከፋፍለነዋል፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • መሬቱ ራሱ የሚናገረው ቋንቋ አለው፡፡
 • ሰው እንዴት ነገረኛ ሆኗል ልበል?
 • ፌዴራሊዝሙ በቋንቋ ስለሆነ መሬቱም ቋንቋውን ለምዶታል፡፡
 • በፌዴራሊዝሙ ቀልድ የለም፡፡
 • ኧረ እኔ አልቀለድኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ፌዴራሊዝሙ ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም፡፡
 • ለማንኛውም ሕዝቡ በመንግሥት ሹመት ትችት እያቀረበ ነው፡፡
 • የምን ትችት?
 • ሹመት በብሔር ተዋጽኦ መሆን የለበትም እያለ ነው፡፡
 • ታዲያ በምን ተዋጽኦ ይሁን፡፡
 • በብቃት ተዋጽኦ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ይደውሉላቸዋል]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንኳን አደረሰዎት፡፡
 • ለሰማዕታት ቀን ነው?
 • አይደለም አይደለም፡፡
 • ሌላ ምን በዓል አለ?
 • ለዓብይ ፆሙ እንኳን አደረሰዎት፡፡
 • ምን?
 • ምነው?
 • ፆሙ ስሙ ካልተቀየረ አልቀበለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኧረ እንደዚህ መሆን አያስፈልግም፡፡
 • ለውጡን እንደማልቀበል ያውቃሉ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • ታዲያ ይኼ ከለውጡ ጋር ምን አገናኘው?
 • የፆሙን ስም አያውቁትም እንዴ?
 • በጣም ያሳዝናል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ፈጣሪ ራሱ ለውጡን እንዳልተቀበለው ገብቶኛል፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅዎታል ክቡር ሚኒስትር?
 • ተቃውሟችሁ ምን ድረስ እንደሚሄድ ሳስበው ያስቀኛል፡፡
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው መንግሥት ከእኛ ጋር በመጣላቱ ዝናብ እንኳን ዘንቦ አያውቅም፡፡
 • አሁንስ በጣም አሳቁኝ፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስቀው ክቡር ሚኒስትር?
 • ተቃውሟችሁ ራሱ እኮ መሠረት ሊኖረው ይገባል፡፡
 • ከዚህ በላይ መሠረት ምን ይፈልጋሉ?
 • ነገ ደግሞ ዝናብ ሲዘንብ ፀሐይ የማትወጣው መንግሥት ከእኛ ጋር ስለተጣላ ነው ትላላችሁ፡፡
 • መቼ ይቀራል?
 • ለማንኛውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ መሆኑ ያሳዝናል፡፡
 • ወደዱም ጠሉም ፆሙ ግን ስሙ ካልተቀየረ አልቀበለውም፡፡
 • የቱ ፆም?
 • ስሙን አልጠራውም ስልዎት፡፡
 • ዓብይ ፆም?
 • አዎ፡፡
 • ምን እንዲባል ነው የሚፈልጉት?
 • አቦይ ፆም!