Skip to main content
x
የጎዳና ተዳዳሪዎች የለውጥ መንገድ
የጎዳና ተዳዳሪዎች ማዕከል በገቡበት ወቅት ድምፃውያኑ ቤተልሔም ጌታሁን (ቤቲጂ) እና አስገኘው አሽኮ (አስጌ) ተገኝተዋልa

የጎዳና ተዳዳሪዎች የለውጥ መንገድ

በሄለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው

ዕድሜው በ20ዎቹ አካባቢ ይገመታል፡፡ ማዲያትና ጠባሳ የበዛበት ፊቱ በሱስ፣ በብርድና በፀሐይ ውርጅብኝ እንደተበላሸ ያስታውቃል፡፡ ዓይኖቹ ልክ ጀምበር ስትጠልቅ እንደምታሳየው ቀለም ደፍርሰዋል፡፡ ጠይም ፊቱ የኖረበትን ችግር ያስነብባል፡፡

ያደረገው ሰፋ ያለ ሱሪና ከላይ ያጠለቀው ቲሸርት ብዙም አላደፈም፡፡ ቁመቱ መካከለኛ ሆኖ ፀጉሩ ሞላ ያለው ወጣት፣ በንግግሩ ወቅት እጆቹን ማወራጨትና የአራዳ ቋንቋ መጠቀም ያበዛል፡፡ ስጦታው ተገኝ 14 ዓመታትን መስቀል አደባባይ እስጢፋኖስ አካባቢ በጎዳና ላይ እንዳሳለፈ፣ ከጓደኞቹ ጋር ባዘጋጁት ዳስ አንዳንዴም ድልድይ ሥር በመኖር ያሳልፉ እንደነበረ ያስታውሳል፡፡ የዕለት ጉርሳቸውን አስመልክቶም፣ ‹‹አንዳንድ ሥራዎችን ሠርቼ ከራሴ አልፌ ለሌሎች እተርፍ ነበር፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በት በት ብዬ አገኛለሁ፤›› ብሏል፡፡

“በት በት” ምን ማለት ነው? ብለን በጠየቅንበት ጊዜ ‹‹አትባንኑም እንዴ?›› ብሎ ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ ‹‹ሁሌም ማን ነኝ? ምናዊ ነኝ? ምንድን ነኝ? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በአንድ መሬት ተዘርተን፣ አንድ ዓይነት ሰው ሆነን፣ የምንም ዓይነት ተጠቃሚ ሳልሆን መቅረቴ ይከብዳል፤›› በማለት ስለ ሕይወቱ መራርነት የሚገልጸው ስጦታው፣ ቤተሰቦቹን እስካሁን እንደማያውቅና ባገኘው መጠለያ የመግባት ዕድል ተጠቃሚ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ በጎዳና ላይ ሲኖር ቢታመሙ የሚያስታምምና ከጎን የሚሆን እንደሌለ አሁን ያለበት ሁኔታ ግን ከምን ጊዜውም የተሻለ መሆኑንና ባገኘው ዕድል ተጠቅሞ ራሱን ለማሻሻል ቆርጦ መነሳቱን በፊንፊኔ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ያገኘነው ስጦታው ገልጿል፡፡

 ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የተጀመረው በጎዳና ላይ የሚኖሩትን የማንሳት ዕቅድ፣ ከስምንት የማቋቋሚያ ተቋማት የፊንፊኔ ጊዜያዊ ማቆያ ይገኝበታል፡፡ በተቋሙም ከስድስት እስከ 60 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 495 ወንዶች በጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ እንደተጠለሉ የተቋሙ አስተባባሪ ወ/ሪት ጽዮን አዲስ ተናግረዋል፡፡

 ማቆያው ውስጥ 19 የማኅበረሰብ ጥናትና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገኛሉ፡፡  ባለሙያዎቹም በእያንዳንዱ ክፍል  ሥልጠና እንደሚሰጡ አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው የሚሰጠው ጠዋት ሲሆን፣ ከሰዓት ፊልም በማየት፣ ኳስ በመጫወትና ሙዚቃዎችን በማዳመጥ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ በማቆያው ከሚገኙትና ከተለያዩ አካባቢ ከመጡት ጎዳና ተዳዳሪዎች 92ቱ ከሥልጠናው በኋላ ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ፍቃደኛ በመሆናቸው እነዚህን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከተለያዩ ክልል ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተጀምሯል፡፡

ከተቋሙ ከተገኘው መረጃ በዲግሪና በዲፕሎማ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተመረቁ 141 የጎዳና ተዳዳሪዎች በማዕከሉ መኖራቸውን አስተባባሪዋ ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥ ከሥነ ምግባር አኳያ በአጥር ሲዘሉ፣ የተለያዩ አደንዛዥ ዕፅ ይዘው ሲገኙና የእርስ በርስ ፀብ ሲኖር የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥና የማስጠንቀቂያ ፊርማ እንደሚፈርሙ አክለዋል፡፡

ጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና የማንሳት ሥራው ከተጀመረ ወዲህ በማዕከሉ የገቡት ኑሮ ምን እንደሚመስል ከቃኘንባቸው የማቋቋሚያ ማዕከል ሌላኛው ኦአይሲኢ ነበር፡፡ የማቋቋሚያው ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ወንድሙ ሽመልስ እንደተናገሩት፣ ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 60 ሚደርስ 177 የጎዳና ተዳዳሪዎች በተቋሙ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ተቋም ውስጥም በ10 የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች አማካይነት ሥልጠና እየተሰጠ ሲሆን፣ ፈቃደኛ በሆኑ ግለሰቦችና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡ ባለሙያዎች የሕይወት ተሞክሮ ሥልጠና እየተሰጠም ይገኛል፡፡ ከሥልጠናው በኋላ ቤተሰብ የማገናኘት ሥራ ይቀጥላል፡፡

ወላጅ ያላቸውን ከወላጆቻቸው ጋር የማገናኘትና ወላጅ የሌላቸውን ከሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ጋር በመሆን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የማድረግ፣ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የማሠማራት ሥራ ይቀጥላል፡፡

የጎዳና ተዳዳሪዎች ያለማንም ሃይ ባይ በጎዳና የመኖራቸውን ያህል የሥነ ምግባር ጉድለት ይታይባቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ለሱስ ተጋልጠዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ውስጣዊ ችግራቸውን ከመፍታት ጎን ለጎን ደግሞ የአልባሳት  ጉዳይ የሚነሳ ነው፡፡ በተቋሙ የአልባሳት ችግር እንዳለም ሰምተናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ እንደሚሉት፣ 3147 የጎዳና ተዳዳሪዎች ከጎዳና ተነስተዋል፡፡  ከነዚህም ውስጥ 17 አካል ጉዳተኞች ወደ አካል ጉዳተኛ ማዕከል ሲገቡ፣ 12 መሥራት የማይችሉ አረጋውያን ደግሞ መርጃ ማዕከል እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው 24 ሕፃናትም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ማዕከል እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

 በማዕከል ለገቡ ጎዳና ተዳዳሪዎች እየተደረጉ ካሉ ድጋፎች ዋነኛው፣ ጤንነትን የመጠበቅና የሥነ አዕምሮ ምርመራ እንዲከታተሉ ማድረግ ነው፡፡ በማዕከሉም ውስጥ ከሚገኙት አንዳንዶቹ በሱስ የጠመዱ በመሆናቸው ከሱስ ለመላቀቅ ጊዜ የሚጠይቁ እንደሆነ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ተናግረዋል፡፡ ከክልሎች ጋር በመወያየት ወደ ቤተሰቦቻቸው ለሚሄዱ ልጆች ክልሉ ኃላፊነት ወስዶ ከቤተሰብ ጋር እንደሚያገናኝና ቤተሰብ የሌላቸውን በሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ በከተማው በሚገኙ የሥራ መስኮች  እንዲሠማሩ የመለየት ሥራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

 የመጀመሪያ ትኩረት የተሰጠው ሴቶችንና ሕፃናትን የማንሳት ቢሆንም፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በአብዛኛው ወጣት ወንዶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ ሴቶችን፣ ነፍሰጡሮችን፣ የሚያጠቡ እናቶችና ሕፃናትን የተሻለ እንክብካቤ እንዲያገኙ ታስቦ ወደ አንድ ማዕከል  የማሰባሰብ ዕቅድ እንዳለም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ባለትዳሮች ‹‹ከባለቤታቸው አንለይም›› በማለታቸው እዚያው የወንዶች መኖሪያ ቤት እንዲኖሩ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሁኔታ በፈቃደኝነት 61 ሴቶችና በአጠቃላይ ከነልጆቻቸው 101 የሚሆኑ በአንድ ማዕከል ላይ እንዲሰባሰቡ መደረጉን  ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ማዕከል ከገቡት መሀል 318ቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ደግሞ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይና ከደቡብ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከክልሎቹ ጋር በመሆን የጋራ መድረክ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ የየክልሎቹ አመራሮችም ኃላፊነት ወስደው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ማኅበረሰቡ የኢኮኖሚ ችግር ቢኖርበትም ልጆች ከቀዬአቸው ሳይፈናቀሉ ባሉበት ሆነው የመደጋገፍ ባህል እንዲዳብር ለማድረግ የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫዎች እየተሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለጎዳና ተዳዳሪ ተብሎ በተዘጋጀው ማዕከል አቅም እያላቸው ተጠቃሚ ለመሆን ሲሉ ብቻ የገቡም አልታጡም፡፡ አቅምና የባንክ አካውንት እያላቸው፣ ቤታቸውን ትተው ወደ ማዕከል የገቡ ተገኝተዋል፡፡

የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማንሳቱን የከተማው አስተዳደር በራሱ በጀት የጀመረው ሲሆን፣ በተቋቋመው የቦርድ አመራር በኩል የተለያዩ ገንዘብ የማግኛ ምንጭ የማፈላለግ እንቅስቃሴ መጀመሩንና በማኅበረሰቡ በኩል በአጭር የጽሑፍ መልዕክት 6400 A በመላክ ከኅብረተሰቡም ገቢ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡