Skip to main content
x
የእናቶች ልዕልና በሲንቄ

የእናቶች ልዕልና በሲንቄ

እንደ ካባ ከላይ የደረቡት ሻካራ ቆዳ በጨሌዎች ያጌጠ ነው፡፡ ከትከሻው ጀምሮ እስከ ግርጌው ድረስ ጨሌዎች ተሰካክተውበታል፡፡ ሰማያዊ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ቀይ፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ ቡኒ ቀለም ያላቸው ጨሌዎቹ ለካባው ልዩ ግርማ ሆነዋል፡፡ በተንቀሳቀሱ ቁጥር ይወዛወዛል እንጂ ለተመልካች ከሻካራው ቆዳ ጋር ግጥም ተደርገው የተሠፉ ይመስላሉ፡፡ ከአንገታቸው ልጥፍ ብሎ ወደታች የሚንዥረገጉ ዘንጎች ያሉት በደቃቅ ጨሌዎች የተሠራም የአንገት ጌጥ በአንገታቸው አኑረዋል፡፡ በላዩም መነኮሳት አንገታቸው ላይ የሚያጠልቁትን ቢጫ መቁጠሪያ የሚመስል ሌላ ዶቃ ጣል አድርገዋል፡፡ ከሥሩም ቤት ያፈራውን በጨሌ በተሠሩ መጌጫዎች ደማምቀዋል፡፡ አናታቸው ላይ ከሥር ጥቁር ከላይ ደግሞ መቀነት የመሰለ ሻሽ ሸብ አድርገዋል፡፡ ዙሪያውንም በደቃቃ ጨሌዎች የተሠራ ቀጠን ያለና በግራና በቀኝ እንዲሁም ከበስተጀርባ የሚንጠለጠል ዘርፍ ያለው ጌጥ እንደዘውድ ደፍተዋል፡፡ በቀለማት ባሸበረቁ አልባሳትና መጌጫዎች የዘነጡት እናቶችና አያቶች ከሻሸመኔ ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኮፈሌ ሰኞ አመሻሹ ላይ አንዴ ክብ እየሠሩ፣ አንዴ ደግሞ በሠልፍ እየቆሙ የተለያዩ ኅብረ ዝማሬዎችን ተቀባብለው የሚከተለውን ዜማ አሰምተዋል፡፡

‹‹ሀዮ ኦፌሌ ቲያ ኦልፈቲ

ፋያ ናንጀቴ

ተደቃ ገላ ኦፎሎ

ቲያ ኦፎልቲ ፋያ ናንጀቴ

አና ዳብዲ ኦፎሌ

ቲያ ኦፎልቲ ፋያ ናንጀቴ

አብዲን ተረቢ ኦፎሌ

ቲያ ኦፎልቲ ፋያ ናንጀቴ››

እያሉ ግጭት እንዲበርድ ወይ ሌላ ጉዳይ ገጥሟቸው ፈጣሪን ተለማምነው ምላሽ ሲያገኙ የሚያዜሙትን የምሥጋና ዜማ አሰምተዋል፡፡ ይኼን ዜማ ፈጠን ካለጭብጨባ ጋር አንገታቸውን ደፋ ቀና እያደረጉ በሚጫወቱት ባህላዊ ጭፈራ ያጅቡታል፡፡ ዘፈኑም ጸሎታችን ሰምሯል ደስተኛ ሆነናል  የሚል መልዕክት የያዘ ነው፡፡

ኅብረ ዝማሬው ሲቀየር ውዝዋዜውም ሆነ አቋቋማቸው አብሮ ይቀየራል፡፡ ክብ ሠርተው ሲዘምሩ ሁለት ሰዎች መሀል ገብተው ምቱን ተከትለው ይጨፍራሉ፡፡ ትይዩ ሆነው በቆሙበት አንደኛዋ ወደ ግራ፣ ሌላኛዋ ደግሞ ወደ ቀኝ ዘምበል እያሉ ቦታ እየተቀያየሩ ይጨፍራሉ፡፡ ግጭትን ለማብረድና ሌሎችንም ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ሥልጣን የምትሰጣቸውን ቀጭን በትር ትከሻቸው ላይ አስደግፈው ሥልታዊ ምት ባለው መልኩ ይወዛወዛሉ፡፡ ወደ ግራና ቀኝ በተወዛወዙ መጠን ትከሻቸውን ወደ ጀርባቸው መታ ያደርጋሉ፡፡ ፀጉር የሚመስለው ረዥሙ ሻሻቸው፣ የተሽሞነሞኑበት ቀለማም ጨሌያቸው አብሯቸው ይጨፍራል፣ አንገታቸውን እያወዛወዙ የፋያ ኦፈሌን ዝማሬ ሲዘምሩ ቅጭል ቅጭል የሚል ድምፅ የሚያወጡት ጨሌያቸው ለጭፈራቸው ድምቀት ይሰጣሉ፡፡ ፈጠን ያለ ጭብጨባቸው ደግሞ ለባህሉ እንግዳ የሆነን እንኳ ያስጨፍራል፡፡

ይኼንን ባህላዊ ዜማ ሲያዜሙ የሚደክም፣ በጭፈራው የሚዝል የለም፡፡ በገብስ ገንፎ፣ በጩኮ፣ በአንጮቴ፣ በወተትና ቅቤ የጠነከረ አካላቸው ድካም አያውቅም፡፡ የሚያውቁትን ዝማሬ በሙሉ ይዘምራሉ፡፡ ሲያልቅባቸው መጀመርያ ያዜሙትን ደጋግመው ያዜማሉ፣ ይጨፍራሉ፡፡ ምክንያቱም ይኼንን የመሰለ ጭፈራና ዝማሬ የሚያሰሙትም ማኅበራዊ ችግራቸው ተቀርፎ የተሻለ ቀን በመምጣቱ በምሥጋና እና በደስታ ነው፡፡

በእነዚህ ጭፈራዎች የሚሳተፉት ያገቡ ሴቶች ናቸው፡፡ ነቀዝ ከማይበላው፣ ለምስጥ ከማይበገር ጠንካራ የዛፍ ዘር ቀጭኑ ተመርጦ ቀጥ ያለው ብትር የሚሰጣት አንዲት ሴት ስታገባ ነው፡፡ አንዲት ሴት ልጅ ስትዳር በስጦታ መልክ የሚሰጧት ይህቺ የሰላም ተምሳሌት የሆነችው ብትር ዕድሜ ልኳን አብራት ትኖራለች፡፡ ሀሮሬሳ ከሚባል የእንጨት ዘር የሚሠራው በትሩ ቀጥ ማለቱ በራሱ ያልተዛባ ፍትሕ የመስጠት፣ የእኩልነትና ያልተዛባ ነገር ተምሳሌት ነው፡፡ የሲንቄ ባህላዊ ሥርዓት በስፋት የተለመደው በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን፣ ቦረና፣ ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን ላይ ነው፡፡

በአካባቢው አለመግባባት ሲፈጠር እናቶች የድረሱልኝ ጥሪ እንደሚያሰሙት ሁሉ  ሀደ ሲንቄዎች ብትራቸውን ይዘው እልልታ እያሰሙ ይወጣሉ፡፡ እልልታውን የሰሙ ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ ሀደ ሲንቄዎችም ብትራቸውን ይዘው እልል እያሉ ይሰባሰባሉ፡፡ ‹‹እልልታው እጆቻችንና ልቦቻችንን አንድ ላይ አስተሳስረን የተፈጠረውን ግጭት እናብርድ ድምፅችን ይሰማ›› የሚል መልዕክት አለው፡፡ በጠበኞቹ መሀል ብትራቸውን ከወረወሩ ሲንቄውን ተሻግሮ ለዱላ መጋበዝ የማይታሰብ ነው፡፡ እንደዋዛ የምትወረወረው ቀጭኗ ብትር የሚንቀለቀልን እሳት የማብረድ ኃይል አላት፡፡ ብትሯን ተሻግሮ ለፀብ መጋበዝ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ባህላዊ እሴት መናቅ ነውና ፀቡ ከማኅበረሰቡ ጋር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም እናቶችን የሚያከብር፣ ከማኅበረሰቡ አብሮ መኖር የሚፈልግ የፈለገ ነገር ቢመጣ ብትሯን አይሻገርም፡፡ ፍትሕ ሊያገኝ ነውና ከቁጣውም ቀዝቀዝ ይላል፡፡

አባ ገዳዎች ደርሰው ችግሩ እስኪፈታም ሀደ ሲንቄዎች ብትራቸውን ወደ ጎን አስተሳስረው ይይዛሉ፡፡ የታሠረው በትራቸው የሚፈታው ሰላም ከወረደ በኋላ ነው፡፡ በኦሮሞ የግጭት አፈታት ሥርዓት ውስጥ የአባገዳዎችና የሀደ ሲንቄዎች ሚና ምን እንደሆነና ተፅዕኖውም እምን ድረስ እንደሆነ ከወር በፊት በኦዲፓና በኦነግ መካከል የነበረውን ግጭት ለማብረድ የነበራቸውን ሚና ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን የግጭት ቀጣና አድርጎ የነበረውን አለመግባባት እንዲረግብ ሀደ ሲንቄዎች ብትራቸውን አንስተዋል፣ አባገዳዎች ሸምግለዋል፡፡ የገዳ ሥርዓት አካል የሆነው ሲንቄ በሕግ የመገዛት፣ እናቶችን የማክበር፣ ባህልን የመጠበቅ፣ ማኅበራዊ እሴቶችን የማቆየት ምሳሌ ነው፡፡ ራስን ገዝቶ በምክንያታዊነት ለመዳኘት መፍቀድንም ያሳያል፡፡ የሲንቄ ሥርዓት በኦሮሞ ባህል ሴት ልጅ ልዩ ክብር እንዳላት ማሳያም እንደሆነ ይነገራል፡፡

በምዕራብ አርሲ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የባህል ባለሙያዋ ወ/ሮ ሳራ ዱቤ፣ በአካባቢው ባህል መሠረት ሴት ልጅ በተለይም እናት ልዩ ክብር ይሰጣታል ይላሉ፡፡ የእግዜር ሰላምታ ለመስጠትም ሆነ አንድ ንግግር ለመጀመር በቅድሚያ እናቶችን ይቅርታ መጠየቅ ግድ ነው፡፡ በነዋሪዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ግጭቱን ያስቆሙ ሀደ ሲንቄዎችን አባገዳዎች ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ነው በኮቱ ዱፌ ወግ ዕርቅ ወደ ማውረድ የሚገቡት፡፡

 ግጭቱ በሀደ ሲንቄዎች ከበረደ በኋላ አባገዳዎች በሽምግልናው ቦታ ላይ ተገኝተው በሁለት ረድፍ ቁጢጥ ብለው ይቀመጣሉ፡፡ ንግግር የሚጀምሩትም ‹‹ኢልቴ ዴና›› ወይም እንድንናገር ይፈቀድልን ብለው ሀደ ሲንቄዎችን ከጠየቁና ‹‹ሆበያ›› የሚል ፈቃድ ካገኙ በኋላ ነው፡፡ ሀደ ሲንቄዎች ሆበያ ብለው ፈቃዳቸውን ከሰጡ በኋላ የልምላሜና የሰላም ተምሳሌት የሆነውን ሳር ነጭተው ይበትናሉ፡፡ ይኼንን የሚያደርጉት ለዳኝነት የተቀመጡ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችም ናቸው፡፡ ሳር መበተን ጥሩ ተስፋን ለአባቶች፣ ጥሩ ተስፋን ለእናቶች እንመኛለን እንደማለት ነው፡፡ ይኼንን ካሉ በኋላ ነው ወደ ሽምግልና ገብተው ችግሩ ምንድነው ብለው ማሸማገል የሚጀምሩ፡፡

ከሁለቱም ወገን ያለውን ጉዳይ ‹‹ኮቱ ዱፌ›› እያሉ ካደመጡ በኋላ ነገሩን ይፈቱታል፡፡ ሰላም በመውረዱ ደስተኛ የሆነ ሰው በባህሉ መሠረት ጥሉ የተነሳበት ቦታ ላይ ኮርማ ያርዳል፡፡ እንዲህ የሚያደርገው ፈቃደኛ የሆነ ሰው ያለውን ክብር ለማሳየት ነው፡፡ ሀደ ሲንቄዎችም ኮርማ ያረደላቸውን ግለሰብ ይመርቁታል፡፡ ‹‹ሲንቄያቸውን ያሸክሙትና እመርቅሀለሁ እጅህን ዘርጋ፣ እመርቅሀለሁ ስማኝ፡፡ ፈጣሪ ከቤተሰብህ፣ ከሕዝብህ፣ ከአገርህ ጋር ያኑርህ እያሉ ይመርቁታል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሳራ ምርቃቱ ኮርማውን ላረደላቸው ብቻ ሳይሆን ለታረቁትና ላስታራቂዎቹም ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹ገደቢ ገላ ኦዱ ናኦዴፈዱ

ኤባሲ ኬና ወያ አስቆጴፈዱ›› እያሉ ምርቃቱን በዜማ ያደርሳሉ፡፡  በኮቱ ዱፌ ሽምግልና ዋሽቶ ማስታረቅ ሳይሆን እውነት ተፍረጥርጣ ጥፋተኛም ጥፋቱን የሚያምንበት ተጎጂውም የሚካስበት የፍትሕ ሥርዓት ስለሆነ ቅር መሰኘት የለም፡፡ ለዱላ የተጋበዙ በኮቱ ዱፌ ከተሸመገሉ በኋላ ተቃቅፈው ይቅር ለእግዚአብሔር ይባባላሉ፡፡ ሀደ ሲንቄዎችም ቀጫጭን ብትሮቻቸውን ወደ ጎን ደርድረው አንድ ላይ በመያዝ የምሥጋናና የምርቃት ዜማ ሲያዜሙ ሰላም ጨርሶ መውረዱን በሚያንፀባርቅ መልኩ ነው፡፡ የምርቃቱን ዜማ ካዜሙ በኋላም ክብ ሠርተው የምሥጋናውን ዜማ ሀዮ ኦፈልቴን ያዜማሉ፡፡ ፈጠን ያለ ጭብጨባቸውን ተከትሎ አንገታቸውን ይወዘውዛሉ፣ በጨሌና ዶቃ ያጌጠ ቆሪያቸውንም ወተት እንደሚናጥበት ቅል ሽቅብ ይገፉታል፣ ቁልቁል ይመልሱታል፡፡ የልጅ ልጅ ያደረሱ አያቶች በቅርብ ከተዳረች ልጃቸው እኩል ሳይደክሙ በሞራል ይጨፍራሉ፡፡ የሚያውቁትን ኅብረ ዝማሬ ሁሉ እየደጋገሙ ፈጣሪን ያመሰግናሉ በዙሪያቸው ያሉን ይመርቃሉ፡፡ 

‹‹ሕግ ከገዛው ይልቅ ባህል የገዛው ይበልጣል›› የሚሉት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ወይንሸት ኃይለ ማርያም፣ ባህል ሰላምን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ቦታ አለው ይላሉ፡፡ ስለዚህም መሥሪያ ቤቱ በባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝም ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚተገበሩ የባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ላይም ጥናት ማድረግ መጀመሩን ያስረዳሉ፡፡ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራበት በሚገኘው የሲንቄ ሥርዓትም ጎልቶ እንዲወጣ መሥሪያ ቤቱ ጥረት ማድረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በኦሮሞ ባህል የግጭት አፈታት ሥርዓት አካል የሆነችው የሲንቄ በትርም የሰላም ተምሳሌት ሆና ማኅበረሰቡን ትገዛለች፡፡

የሲንቄ በትር ግጭት ከማብረድም ባለፈ የእናቶችን መብት የማስከበር ኃይል አላት፡፡ እመጫትነቷን የሚያሳይ ከእንጨት የተሠራች ‹‹ቀነፋ›› የተባለችውን ጌጥ ግንባሯ ላይ ያደረገች ሴት የተለየ ክብር ይሰጣታል፡፡ ቀነፋ ግንባሯ ላይ ያጠለቀች እናት ወንዝ ወርዳ ውኃ ልቅዳ ብትል፣ ወፍጮ ቤት ብትሄድ ተራ መጠበቅ ሳይኖርባት ቅድሚያ ይሰጣታል፡፡ በአራስነቷ ወቅት ባሏ ሳት ብሎት እጁን ሊያነሳባት ቢሞክር ቀድማ የምታነሳው ሲንቄዋን ነው፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎችም እንዲደርሱላት እልል ብላ ድምፅዋን ታሰማለች፡፡ ‹‹ጡቷ ያጋተ አራስ ሴትን መምታት ትክክል አይደለም›› የሚል መልዕክት ያዘለ ኅብረ ዜማ እያዜሙ ይወቅሱታል የሚሉት ወ/ሮ ወይንሸት፣ ካሳ እንዲሰጥ እንደሚደረግም ያስረዳሉ፡፡

ሲንቄ እንደ ልማት ባሉ ማኅበራዊ ጉዳዮችም ትልቅ አስተዋፅኦ አላት፡፡ ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር የደረሰ ሰብሉን ከማሳው ለማንሳት የሰዎችን ዕርዳታ ቢሻ ችግሩን የሚያስረዳው ለሀደ ሲንቄዎች ነው፡፡ ሀደ ሲንቄዎች ብትራቸውን ይዘው በየቤቱ እየዞሩ ደቦ ይጠራሉ፡፡ ብትራቸውን ይዘው ያስተባበሩት ነዋሪውም በደቦ ማሳው ላይ ያለውን ሰብል በአንድ አፍታ አጭዶ ያነሳል፡፡ የሚወቃም ከሆነ ይወቃል፣ እብቁን ከእህሉ መለየትም ካስፈለገም አበጥሮና አናፍሶ ጎተራ ሊያጉር ይችላል፡፡ ይኼንን ለሴቶች ልዩ ክብር የሚያጎናጽፈውን ባህላዊ እሴት ለዓለም ለማስተዋወቅና የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡