Skip to main content
x
በፆታ እኩልነት አለመከበር ሳቢያ ዓለም የ160 ትሪሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ታስተናግዳለች
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከቬራ ሶንግዌና ከሌሎች የተመድ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የግሎባል ሔልዝ ሪፖርትን ይፋ አድርገዋል

በፆታ እኩልነት አለመከበር ሳቢያ ዓለም የ160 ትሪሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ታስተናግዳለች

በኢትዮጵያ ከ70 በመቶ በላይ ኩባንያዎች ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን ለመቅጠር ያደላሉ

በዓለም ላይ በተንሰራፋው የፆታ መድልኦ ሳቢያ ከ160 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ የዓለምን የፆታ እኩልነት ጥያቄዎች የቃኘው ሪፖርት ከጤና ዘርፍ አኳያ የሚታዩ ችግሮችን ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ግሎባል ሔልዝ 50/50›› የተሰኘውና በፆታ እኩልነት ላይ የተመሠረተው ዓለም አቀፍ ሪፖርት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ በተደረገበት ወቅት፣ የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) እንደጠቀሱት፣ የፆታ እኩልነት የመላው ዓለም ችግር ሆኖ በመንሰራፋቱ ሳቢያ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጫና እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ ዓለም የ160 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ለማስተናገድ ተገዳለች ብለዋል፡፡

አያይዘውም አገሮች ለፆታ እኩልነት በሚሰጡት ደካማ ትኩረት ሳቢያ ከኢኮኖሚ ባሻገር በጤና፣ በትህምርትና በሌሎችም መስኮች ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ሶንግዌ፣ በዓለም ላይ የሚታየውን የፆታ እኩልነት ክፍተቶች ለማስተካከል አሁን በሚታየው አካሄድ ዓለም ከተጓዘች፣ እኩልነትን ለማስፈን ከ217 ዓመታት በላይ እንደሚፈጅባት የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ይፋ ያደረጋቸውን ትንበያዎች ጠቃቅሰዋል፡፡ አፍሪካም 102 ዓመታት ሊፈጅባት ይችላል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው በአንድ ወቅት የተመድ የልማት ፕሮግራም ያጠናው እንደሆነ በመግለጽ የጠቀሱት አኃዝ፣ በኢትዮጵያ ከ77 በመቶ ያላነሱ ድርጅቶች ከወንዶች እኩል የብቃት ደረጃና የትምህርት ማስረጃ ያላቸውን ሴቶች ከመቅጠር ይልቅ ለወንዶች እንደሚያደሉ መረጋገጡን፣ ይህም በንግድና ኢኮኖሚው ዘርፍ የሚስተዋል የፆታ እኩልነት ችግሮች መገለጫ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የፆታ እኩልነት ችግሮች መንሰራፋታቸው በመንግሥታት በኩልም ስምምነት የተደረገባቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ካለማክበር ጭምር እንደሚመነጭ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፣ በርካታ የአፍሪካ አገሮችም የፈረሟቸውን ስምምነቶች ለማክበር እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል፡፡ ማፑቶ ፕሮቶኮል የተሰኘውና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታ ተኮር ሁሉም ዓይነት የማግለልና የመብት ረገጣዎችን ለመከላከል ስምምነት የተደረገበት ሕግ ቢወጣም፣ አብዛኞቹ አገሮች ስምምነቱን ወደ አገራቸው ሕግ በመቀየር ያላፀደቁ በርካታ የአፍሪካ አገሮች መኖራቸው የፆታ እኩልነትና የመብት ጥያቄዎችን ለማስከበር አዳጋች እንደሚያደርገው አስታውሰዋል፡፡

በተለያዩ የዓለም አገሮች ውስጥ በፆታ ጥቃትና ማግለል ላይ ዘመቻ የሚያደርጉ በርካታ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በርካቶችም በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች አማካይነት የሚካሄዱትን ጨምሮ በአፍሪካም ለየት ያሉ እንቅስቃሴዎችን መታዘብ ተችሏል፡፡ ለአብነትም በኡጋንዳ ሴቶች በባሎቻቸው በሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ ጫናና መድሎ ሳቢያ በወሲባዊ ግንኙነት ላይ ታክስ መጣላቸው ከተሰማ ሰነባብቷል፡፡ የኡጋንዳ እናቶች ባሎቻቸው ለግንኙነት በጠየቋቸው ጊዜ የስድስት ዶላር ታክስ በመጣል ራሳቸውንና ልጆቻቸውን ለመደጎም የሚችሉበትን አዲስ ሥልት ቀይሰዋል፡፡ ባሎች በቤት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በአግባቡ ካለመወጣቸውም ባሻገር፣ ለቤት ቀልብና አስቤዛ በአግባቡ ወጪ ስለማይደጉሙም ጭምር ታክሱ እንደተጣለባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡