Skip to main content
x
እንደወጣ የቀረው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302

እንደወጣ የቀረው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302

እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሠራኞች እንደ ወትሮ መደበኛ ሥራቸውን በማካሄድ ላይ ነበሩ፡፡ ገቢና ወጪ መንገደኞችን እንደተለመደው ሲያስተናግዱ ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ዱብ ዕዳ አያውቁም ነበር፡፡ ረፋዱ ላይ የደረሰው አስደንጋጭ ዜና ኤርፖርቱን በዋይታ ሞልቶታል፡፡

መዳረሻውን ወደ ናይሮቢ ያደረገው ቦይንግ 737-800 ማክስ አውሮፕላን 149 መንገደኞችን አሳፍሮ ከጠዋቱ 2፡38 ሰዓት ላይ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተነስቶ ለስድስት ደቂቃ ያህል እንደበረረ፣ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ያሬድ ጌታቸው (ካፒቴን) የቴክኒክ እክል እንደገጠማቸው ለአዲስ አበባ ኤርፖርት የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በማሳወቅ ተመልሶ ለማረፍ ፈቃድ ይጠይቃሉ፡፡ የበረራ ተቆጣጣሪዎቹ ለተላለፈው የአደጋ ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት፣ የአዲስ አበባ ኤርፖርት ማረፊያን ከትራፊክ ነፃ በማድረግ ለበረራ ቁጥር 302 የማረፊያ ፈቃድ ሰጡ፡፡

ዋና አብራሪው ያሬድና ረዳት አብራሪ አህመድ ኑር መሐመድ አውሮፕላናቸውን ወደ ቦሌ ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም፡፡ የአደጋ ጥሪውን ካስተላለፉና የማረፊያ ፈቃዱን ካገኙ በኋላ የበረራ ቁጥር 302 ወዲያው 2፡44 ሰዓት ላይ ከራዳር ተሰወረ፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በመሩት የፈልጎ ማዳን ዘመቻ የአውሮፕላኑ ስብርባሪ በቢሾፍቱና ሞጆ መካከል ኤጄሬ የተባለ አካባቢ ተገኝቷል፡፡ በአደጋው 149 ተሳፋሪዎችና ስምንት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት አልፏል፡፡

ከተሳፋሪዎቹ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የኬንያ ዜጎች ናቸው፡፡ በአደጋው 32 ኬንያውያን ሕይወታቸውን ያጡ በመሆኑ አደጋው በደረሰ ዕለት ምሽት የኬንያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ልዑኩ በማግሥቱ ከትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊ ሞገስ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል) እና ከሌሎች የአቪዬሽን ባለሙያዎች ጋር አደጋው የደረሰበትን ሥፍራ ጎብኝተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ በርካታ ኬንያውያን አስከሬን ለመውሰድ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ዜጎቻቸውን ያጡ በርካታ አገሮች አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዋና መሥሪያ ቤትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አጨናንቀው ሰንብተዋል፡፡

እሑድ ከቀትር በኋላ ስለአደጋው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ያሬድ ልምድ ያላቸው ፓይለት እንደሆኑ መስክረውላቸዋል፡፡ ዋና አብራሪው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከሐምሌ 2010 ጀምሮ እንዳገለገሉና መልካም የበረራ ታሪክ ያላቸው አብራሪ እንደነበሩም ጠቁመዋል፡፡

ከኢትዮጵያዊ አባትና ኬንያዊ እናት የተወለዱት ያሬድ (ካፒቴን) በአጠቃላይ የተጠራቀመ 8,231 የበረራ ሰዓት ልምድ ያላቸው ፓይለት ነበሩ፡፡ በካፒቴንነት 1,500 ሰዓት ያበረሩ ሲሆን፣ በቦይንግ 737 ካፒቴን የሆኑት እ.ኤ.አ. በኅዳር 2017 ነበር፡፡ አባታቸው ዶ/ር ጌታቸው ተሰማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሐኪም ሆነው እንዳገለገሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር መሐመድ ድሬዳዋ የተወለዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቆይታቸው ለ200 ያህል ሰዓት እንዳበረሩ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝ የበረራ ደኅንነት እንዳለው በርካታ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ባለሙያዎች እየመሰከሩለት ነው፡፡ አየር መንገዱ ከአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን አካዳሚ እንደገነባ፣ ግዙፍ የጥገና ማዕከል እንዳለውና አፍሪካ ውስጥ አስተማማኝ የበረራ አገልግሎት እንደሚሰጥ በባለሙያዎች ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. 1998 ጀምሮ ወደ አሜሪካ የሚበር በመሆኑ በአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን፣ በአውሮፓ የአቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ የሚደረግበትን ጥብቅ የደኅንነት ፍተሻ በጥሩ ውጤት እንደሚያልፍ፣ በዚህም ምክንያት ወደ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች ለበርካታ ዓመታት በረራውን ያለ ችግር ሲያካሂድ እንደኖረ ተገልጿል፡፡

ስለአደጋው መንስዔ የተጠየቁት አቶ ተወልደ የአደጋ ምርመራ ሳይከናወን ግምት መስጠት አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጠር 302 የገጠመውን አደጋ በመመልከት ቀደም ሲል በኢንዶኔዥያ በቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ላይ ከደረሰ አደጋ ጋር በማስተያየት፣ በማክስ አውሮፕላኖች የበረራ ደኅንነት ላይ ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር ከኢንዶኔዥያ ጃካርታ ከተነሳ 12 ደቂቃዎች በኋላ ጃቫ ባህር ላይ በመውደቁ የ189 መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት ጠፍቷል፡፡

የኢንዶኔዥያና የኢትዮጵያ አደጋዎች በአንድ ዓይነት አውሮፕላን መከሰታቸውና ሁለቱም አደጋዎች አውሮፕላኖቹ ከተነሱ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ያጋጠሙ በመሆኑ፣ በማክስ አውሮፕላን ላይ የቴክኒክ ችግር ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ተወልደ በአሁኑ ወቅት የአደጋው መንስዔ ይህ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡

አሻጥር ሊሆን ይችላል ወይ ተብለው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አየር መንገዱ ማንኛውንም ጥርጣሬ ውድቅ ማድረግ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ይህ ሊሆን ይችላል፣ ይህ ላይሆን ይችላል ማለት አንችልም፡፡ ይህን ጉዳይ ለምርመራው ሥራ እንተዋለን፡፡ ግምት ጥሩ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አደጋው የደረሰበት የምዝገባ ቁጥር ET-AVJ አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተረከበው እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 15 ቀን 2018 እንደነበር የገለጹት አቶ ተወልደ፣ የቴክኒክ ችግር ያልነበረበት 1,200 ሰዓት ብቻ የበረረ አዲስ አውሮፕላን እንደነበር አስረድተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 4 ቀን 2019 የቴክኒክ ፍተሻ በአውሮፕላኑ ላይ እንደተካሄደና ምንም ዓይነት ችግር እንዳልተገኘበት ተናግረዋል፡፡ አውሮፕላኑ አደጋው በደረሰ ዕለት ጠዋት ከጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪካ ያለምንም ችግር በርሮ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡

በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ የቴክኒክ ፍተሻ በአምራቹ ቦይንግ ኩባንያ እስኪካሄድ ድረስ፣ ለጥንቃቄ ሲባል ያሉትን አምስት 737 ማክስ አውሮፕላኖች አየር መንገዱ እንዲቆሙ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ የቻይና ሲቪል አቪዬሽን አስተዳደር በአገሪቱ ውስጥ ያሉ 100 ያህል ማክስ አውሮፕላኖች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አዟል፡፡ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ አየርላንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሲንጋፖር፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ሜክሲኮና ሞሮኮ ተመሳሳይ ዕርምጃ ወስደዋል፡፡ የህንድ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በማክስ አውሮፕላኖች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የጣለ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካው ኮምኤርና የካሪቢያኑ ካይማን ኤርዌይስ ማክስ አውሮፕላኖቻቸው እንዳይበሩ ወስነዋል፡፡ ማክሰኞ ማምሻውን የወጡ ዜናዎች እንደሚያመለክቱት የአውሮፓ ኅብረት አቪዬሽን ባለሥልጣን ቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ ወስኗል፡፡

የቦይንግ ኩባንያ አዲስ ምርት የሆነው B737-8 ማክስ አውሮፕላን ወደ ሥራ የገባው እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. ነበር፡፡ ማክስ ነዳጅ ቆጣቢ፣ ምቾት ያለውና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የአሜሪካ ጄኔራል ኤሌክትሪክና የፈረንሣይ ሳፋራን ኩባንያ በጋራ ያመረቱት ሊፕ የተሰኘ ሞተር የተገጠመለት ማክስ፣ የብዙ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችን ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር፡፡ ከ100 በላይ የሚሆኑ አየር መንገዶች 4,700 ማክስ አውሮፕላኖች እንዳዘዙ የቦይንግ ድረ ገጽ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 30 ማክስ አውሮፕላኖችን ያዘዘ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ማክስ አውሮፕላን በሰኔ 2010 ዓ.ም. መረከቡ ይታወሳል፡፡ የተመሰከረላቸው ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ከኢንዶኔዥያው አደጋ በኋላ በማክስ አውሮፕላን የበረራ ደኅንነት ላይ ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያው ተመሳሳይ አደጋ ሲደገም በአውሮፕላኑ የኤሮዳይናሚክስ ንድፍና የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ላይ የብቃት ችግር እንዳለ እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 302 አደጋ ከተከሰተ በኋላ፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአደጋ ምርመራ ቡድን አቋቁመዋል፡፡ አደጋ የደረሰበት ሥፍራ ተለይቶ በፌዴራል ፖሊስ፣ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስና በደኅንነት አካላት ጥብቅ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል፡፡

አምስት አባላት ያሉት የአደጋ ምርመራ ቡድን በዋና መርማሪነት እንዲመሩ የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አምድዬ ፈንታ ተሰይመዋል፡፡ ኮሚቴው ሥራውን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ጀምሯል፡፡ የአደጋ ምርመራ ሥራ የመጀመሪያ ዕርምጃ መረጃ ማሰባሰብ በመሆኑ፣ የአስከሬንና የተለያዩ የአውሮፕላኑን አካላት ፍለጋ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአደጋው ምርመራ ሥራ ቁልፍ ሚና ያለው የመረጃ ሳጥን (በተለምዶ ጥቁር ሳጥን) ተገኝቷል፡፡

የመረጃ ሳጥኑ ሁለት ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው በአውሮፕላኑ የበረራ ክፍል ውስጥ ማንኛውንም ድምፅ የሚቀዳ (Cockpit Voice Recorder) እና ሁለተኛው ክፍል የበረራ መረጃ የሚሰበስበው (Flight Data Recorder) ነው፡፡ መቅረፀ ድምፅ አብራሪዎቹ እርስ በርሳቸው የተነጋገሩትን፣ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር የተለዋወጡትን ንግግርና ሌሎች በበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥና አካባቢ የተፈጠሩ ድምፆች ይቀዳል፡፡ የበረራ መረጃ የሚሰበስበው መሣሪያ አውሮፕላኑ ይበርበት የነበረበትን ከፍታ፣ አቅጣጫ፣ ፍጥነትና የመሳሰሉትን መረጃዎች ቀርፆ ያስቀራል፡፡

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የተገኘው የመረጃ ሳጥን ጉዳት እንደደረሰበት የተገለጸ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአቪዬሽን ባለሙያ ጉዳዩ ተስፋ አስቆራጭ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጉዳቱ የደረሰበት የሳጥኑ የውጪ ክፍል በመሆኑ የሜሞሪ ቺፕሱ አልተጎዳም የሚል እምነት አለን፡፡ የሜሞሪ ቺፕሱ በባለሙያዎች እንዲወጣ ተደርጎ በሌላ መሣሪያ ውስጥ ተከትቶ ማንበብ ይቻላል፡፡ ለማንኛውም ይህ ሁሉ የሚታወቀው በምርመራ ሒደት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዓለም ላይ "CVR" እና "FDR" መረጃ ትንተና የሚታወቁት አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ቦይንግ ኩባንያ፣ የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የእንግሊዝ ኤኤአይቢ ባለሙያዎች ምርመራውን ለማገዝ ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ የእስራኤል የፎረንሲክ ባለሙያዎችም ሰኞ ዕለት እንደመጡ ታውቋል፡፡ የቦይንግ፣ የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድና የኤኤአይቢ ባለሙያዎች ማክሰኞ ቀትር ላይ አደጋው ወደ ደረሰበት ሥፍራ አቅንተዋል፡፡

የመረጃ ሳጥን ርክክብ ሰኞ ዕለት እንደተካሄደ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ አባላትና በደኅንነት ሠራተኞች ታጅቦ ወደ ኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት የመጣው የመረጃ ሳጥን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በተገኙበት የአደጋ መርማሪ ቡድኑ ተረክቧል፡፡

የመረጃ ሳጥኑ የት ሄዶ ይመርመር በሚለው ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች በመምከር ላይ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ‹‹ይህ የመንግሥትን የበላይ አካል ውሳኔ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡

ሦስት አባላት ያሉት የእንግሊዝ ኤኤአይቢ ቡድን ብላክ ቦክሱን ወስዶ የምርመራ ሥራውን ለማከናወን ፍላጎቱን የገለጸ ቢሆንም፣ አሜሪካውያን በዚህ የተደሰቱ አይመስሉም፡፡ የናሽናል አቪዬሽን ሴፍቲ ቦርድ ልዑክ የመረጃ ሳጥኑን ወስደው መመርመር ያለባቸው እነርሱ እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ከገበያ ሽሚያ በላይ ነው፤›› ብለዋል አንድ ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያ፡፡

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በአቪዬሽን መስክ እስከ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ምሥረታ 1945 ዓ.ም. የዘለቀ በመሆኑና ናሽናል አቪዬሽን ሴፍቲ ቦርድ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለው ጠንካራ ተቋም በመሆኑ፣ የመረጃ ሳጥኑ ወደ አሜሪካ ሳያቀና እንደማይቀር አንድ የዘርፉ ዓለም አቀፍ ባለሙያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የመረጃ ሳጥኑ በዚህ ሳምንት ወደ አሜሪካ እንደሚላክ የገለጹት ባለሙያው፣ ሳጥኑን በኃላፊነት ይዘው የሚሄዱት ኮሎኔል አምድዬ ፈንታ እንደሆኑና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዥም ልምድ ያለው ካፒቴን ተመርጦ አብሮ እንደሚጓዝ ታውቋል፡፡ የናሽናል አቪዬሽን ሴፍቲ ቦርድ ባለሙያዎችም የመረጃ ሳጥኑን አጅበው የሚጓዙ ቢሆንም፣ ሳጥኑ ከኮሎኔል አምድዬ እጅ እንደማይወጣ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ኦዲት ባደረገበት ወቅት ባቀረበው ምክረ ሐሳብ መሠረት፣ የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ ከባለሥልጣኑ ተነጥሎ እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ቢሮው በአሁኑ ወቅት በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ሥራውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የአደጋ ምርመራ ሥራው ሁለተኛ ክፍል የመረጃ ትንተና እንደሆነ የገለጹት ዓለም አቀፍ አማካሪ፣ ይህን ሥራ ለመጀመር የመረጃ ሳጥኑ ምርመራ ሥራ ተጠናቆ ውጤቱ መምጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሦስተኛው ክፍል ድምዳሜ መስጠት ሲሆን የመጨረሻና አራተኛው ክፍል ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የሚረዳ ምክረ ሐሳብ ማስቀመጥ ይሆናል፡፡

የአደጋ ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ለማውጣት ሦስት ወራት ሊፈጅ እንደሚችል የገለጹት አማካሪው፣ የመጨረሻው ሪፖርት ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ዋና ዓላማ መወቃቀስ ሳይሆን ለወደፊት ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደርስ መከላከል በመሆኑ፣ ሁሉም ወገን የምርመራውን ውጤት በትምህርታዊነቱ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡ ለጊዜው የአደጋውን ቁልፍ ሚስጥር የያዘውና በጥቁር ወፍራም ላስቲክ የተሸፈነው የመረጃ ሳጥን፣ በፌዴራል ፖሊስና በደኅንነት አባላት ጥብቅ ጥበቃ እየተደረገለት በአንድ ቢሮ ውስጥ ተቀምጧል፡፡