Skip to main content
x

ከዘጠና ሺሕ በላይ መምህራን የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ሊሰጥ ነው

በሔለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው

ትምህርት ሚኒስቴር ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ መምህራንና ርዕሰ መምህራን እንዲሁም ሱፐርቫይዘሮች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ሊሰጥ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

92,313 የሚደርሱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን እንደተመዘገቡ የመምህራንና የትምህርት ተቋማት አመራር የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ዳይሬክተር ወ/ሮ ካሳነሽ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሯ ምዘናው ሚያዝያ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚካሄድና በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የሚያስተምሩ መምህራንን እንደሚያጠቃልልም አስረድተዋል፡፡

የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ፕሮግራሙ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሲተገበር ቢቆይም  በየትምህርት ደረጃውና የሥራ ድርሻ ተለይቶ ምዘና ሲካሄድ ግን ይህ የመጀመርያ ነው፡፡ በቀጣይ ግን በየዓመቱ በቋሚነት እንደሚሠራበት፣ ምዘናው የሚካሄደውም በተመረጡ የክልል ትምህርት ቤቶችና በተመረጡ ሁለት የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ይሆናል፡፡

አሁን በሚካሄደው ምዘና የሚሳተፉት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ገልጸው ምዘናው በቀጣይ የግል ትምህርት ቤቶችን እንደሚያካትትና ሁሉንም ትምህርት ቤቶች እንደሚመለከትም የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ምዘናው በሁሉም አካባቢዎች ሲዳረስ ‹‹አንድም መምህር ያለ ሙያ ፈቃድ ማስተማር›› እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

በስድስት ዓመታት ውስጥ ከነበሩት የብቃት ማረጋገጫ ምዘናዎች በ2010 ዓ.ም. የነበረው ምዘና የተሻለ መሆኑንና በወቅቱ ከተመዘገቡት 90,000 ሺሕ መምህራን 56,000 መመዘናቸውና ከእነሱም መካከል ምዘናውን ያለፉት 23 ከመቶ ያህሉ እንደነበሩ ዳይሬክተሯ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ዓምና ከተመዘገቡት ተመዛኞች በምዘናው የተሳተፉት አነስተኛ መሆን በወቅቱ የጊዜ መራዘምን እንደምክንያት እንደተነሳ ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፣ ዘንድሮ ግን የጊዜ መራዘም ስለማይኖር አብዛኛዎቹ በምዘናው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት፣ በብቃት ምዘናው ያላለፉት በቀጣይ ምዘናዎች ለመመዘን የሚያስችል ዕቅድም ተይዟል፡፡ መንግሥት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ምዘናውን ለሚያልፉ መምህራን አጫጭር ሥልጠና ለመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በሙያ ፈቃድ ሥርዓት ውስጥ ሦስት የሙያ ፈቃድ ዓይነቶች አሉ፡፡ ከነዚህም አንደኛው የመጀመርያ ሙያ ፈቃድ ለጀማሪ መምህራንና በትምህርት ተቋማት አመራርነት ሠልጥነው ወደ ሙያው ለሚገቡ፣ እንዲሁም ለደረጃው የብቃት መመዘኛ ላሟሉ የሚሰጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ሙሉ የሙያ ፈቃድ ለአምስት ዓመት የሚያገለግሉ ሆኖ የመጀመርያ ሙያ ፈቃድ በማግኘት ሲሠሩ ቆይተው ላጠናቀቁ ይሰጣል፡፡ የሦስተኛው ደግሞ ቋሚ የሙያ ፈቃድ ሲሆን፣ ይህ ፈቃድ ሙሉ የሙያ ፈቃድ ከያዙ በኋላ ለደረጃው የሚመጥን አገልግሎት አጠናቀው የሙያ ፈቃድ ብቃት መመዘኛ ላሟሉ መምህራን፣ ለርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የሚሰጥና በየአምስት ዓመቱም የሚታደስ ቋሚ የሙያ ፈቃድ ነው፡፡