Skip to main content
x

ለአዕምሮ ሕሙማን ከለላ

የሰው ልጅ አንጎል ወደ 100 ቢሊዮን የሚጠጉ የነርቭ ሴሎች አሉት፡፡ እነኚህ 100 ቢሊዮን የነርቭ ሴሎች በትሪሊዮኖች ከሚቆጠሩ የነርቭ መገናኛ ሒደቶች ጋር ይያያዛሉ፡፡ አዕምሮ ሦስት ትልልቅ ክፍሎችን ሲይዝ አንደኛው እሳቤ፣ ሁለተኛው አስተውሎት ሦስተኛው ደግሞ ድርጊት ነው፡፡ በእነዚህ ላይ የሚፈጠር ዕክል ሰዎች የአዕምሮ ሕሙማን እንዲሆኑ የሚያደርግ ቢሆንም፣ ስለአዕምሮ ሕሙማን ያለው ግንዛቤ ግን አናሳ ነው፡፡

መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተካሄደው አራተኛው የኢትዮጵያ የአንጎል ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሐኪምና መምህሩ መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) ልጆች ድንገት የአዕምሮ በሽተኞችን ሲያዩ ድንጋይ መወራወር እንደሚጀምሩ፣ ሰው ሁሉ ልክ እንደ ውሻ እንደሚያያቸው፣ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ትክክል እንዳልሆነ፣ ከበድ ያለ የአዕምሮ ሕመም ካለበት የመታከም፣ የጥበቃና የእንክብካቤ መብቶች ሊኖሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአዕምሮ ሕሙማንን አስገድዶ ማከም ተገቢ ነው ወይ? ማስገደድ ይቻላል ወይ? ወይም አንድን ሰው ሰብዓዊ መብቱ ተጥሶ፣ እጁ ወደኋላ ታስሮ አማኑኤል አዕምሮ ሕክምና ሆስፒታል ወስዶ ማሳከም ይቻላል ወይ? ብለው ራሳቸው ለሰነዘሯቸው ጥያቄዎች በፈረንጆች ነውር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በምዕራብ አውሮፓ አገሮች አንድ ሰው በፈቃዱ ሐኪም ቤት መምጣት አለበት፡፡ ተገዶ ሐኪም ቤት የሚመጣው በኅብረተሰቡ ወይም በራሱ ላይ አደጋ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ሲገመት ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የመጣን የአዕምሮ ሕመምተኛ ሐኪሙ እስከ 72 ሰዓት ድረስ አስገድዶ ማቆየት የሚችል ሲሆን፣ ሕመምተኛው መድኃኒት አልወስድም ካለ መብቱ መሆኑንና ሐኪሙም ሊያስገድደው እንደማይችል ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለሠላሳ አምስት ዓመታት ያህል በአዕምሮ ሕክምና ዙሪያ ነው ያለሁት፤ የአዕምሮ ሕመምተኛ አንድም ቀን መትቶኝም ሆነ በክፉ ተናግሮኝና ሰድቦኝ አያውቅም፡፡ ይህም የሆነው በሽተኞችን ስለማከብር ነው፡፡ ስለዚህ ወጣት ሐኪሞች የአዕምሮ በሽተኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም በሽተኛ ፍቅር የመስጠትና የማክበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸሁ፤›› ብለዋል፡፡

የአዕምሮ በሽተኛን ሐኪሞች ካከበሩ እንደማንኛውም ሕመምተኛ እነሱም እንደሚያከብሯቸው፣ ተዓማኒነትን ወይም አመኔታን እንደሚፈጥሩ፣ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ሐኪሙ የሰጣቸውን መድኃኒት እንዲወስዱ የሚያደርጓቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሜድኮ ሌጋል ኮንሰልታንስና አሠልጣኝ አቶ ሱሌይማን ሽጉጤ፣ አዕምሮአቸውን የሚያማቸው ሰዎች በኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕሙማን ሕጋዊ መብቶች ምን ይመስላሉ? አዕምሮ ሕሙማንን አስገድዶ ወደ ሕክምና ተቋም ማምጣት ከሕግ አንጻር እንዴት ይታያል? በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደ አቶ ሱሌይማን፣ አዕምሮዋቸውን ለሚያማቸው ሰዎች ተጠያቂ መሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 48፣49፣50 በግልጽ ተደንግጎ ቢገኝም፣ በአጭሩ በመቀመጡ ግልጽ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡

ማንም ሰው በዕድሜ፣ በሕመም፣ ባልተለመደ የዕድገት መዘግየት ወይም ጥልቅ በሆነ የአዕምሮ መገንዘብ ወይም የማመዛዘን ችሎታ መቃወስ ሳቢያ በሚፈጽማቸው ድርጊቶች ውስጥ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን የአዕምሮ ሕመም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ውሳኔ እንደሚሰጥ ነው አቶ ሱሌይማን የተናገሩት፡፡

የሕግ የመጀመርያው ዓላማ ግለሰቡን ማስተማር ሲሆን ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ ተከሳሹን ከወንጀል ማስቆም ወይም የተከሳሹን መታሰር የሚያዩ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ወንጀል ከመፈጸም ይታቀባሉ ተብሎ የሚታሰብ ነው፡፡ እነዚህ የቅጣት ዓይነቶች አዕምሮውን በሚያመው ሰው ላይ ተግባራዊ ቢደረግ ውጤት አይኖረውም ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በወንጀል ክርክር ላይ የአዕምሮ ታማሚ ነው ከተባለ ወደ ፍሬ ነገሩ እንደማይገባ፣ ወደ ፍሬ ነገሩ የሚገባው መጀመርያ አዕምሮው ይሠራል? ወይስ አይሠራም? በሚሉት ላይ ክርክር ከተደረገና በባለሙያዎች ከተረጋገጠ በኋላ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የፍትሐ ብሔር ክስ ከሆነ ግን የአዕምሮ ታማሚውን የሚቆጣጠሩና የሚንከባከቡ ሰዎች ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ በሆስፒታሎች ውስጥም ሕክምና በሚሰጥበት ጊዜ የአዕምሮ ታማሚዎችንና የአዕምሮ ታማሚ ያልሆኑ ሰዎችን ለይቶ የማከም ግዴታን እንደሚያስቀምጥ አቶ ሱሌይማን ይገልጻሉ፡፡

የወርልድ ዋይድ ዲዜቢሊቲ አሶሴሽን ካንትሪ ዳይሬክተር ፓስተር ዘካርያስ ዓምደብርሃን (ዶ/ር) የአዕምሮ ጤና ሕክምና ከሃይማኖት አንፃር እንዴት ይታያል? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዘካርያስ ገለጻ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም የእምነት ተቋማትና ሁሉም ዓይነት እምነቶች የአዕምሮ ሕሙማንን የሚመለከቱበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡

እንደ ዶ/ር ዘካርያስ፣ አንድ ግን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር በሃይማኖት እምነት ውስጥ ያሉ አስተምህሮና ባህል መካከል ያለው አረዳድ ነው፡፡ የአዕምሮ ሕሙማን ከሃይማኖት አንጻር የሚታዩት በሦስት መንገድ ነው፡፡ የመጀመርያው አዕምሮው በትክክል መሥራት አለመቻል፣ ጥልቅ ቁዘማ ወይም ከባድ ድባቴ ነው፡፡ ሁለተኛው ሙሉ ለመሉ በሰይጣን ቁጥጥር ስር መሆን (ዲሞኒክ አታክ) ሲሆን ሦስተኛው የሁለቱንም ቅልቅል አንድ አድርጎ ማየት ነው፡፡ በመሆኑም የሃይማኖት መሪዎችና ሐኪሞች ተቀናጅተው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ጠቅላላ ሐኪም፣ የኢትዮጵያ የአንጎል ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት አስተባባሪ ኮሚቴ መሥራችና ዋና አዘጋጅ ምትኩ ጌቱ (ዶ/ር) የአንጎል ግንዛቤ ሳምንት በ2006 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ተነስቷል ብለዋል፡፡ የመጀመርያው ስለ አዕምሮ ሕመም ከፍተኛ የሆነ ግንዛቤ መፍጠር፣ በሥነ አዕምሮ ላይ የሚሠሩ ጥናቶች እንዲበዙ፣ የሳይካትሪስት ባለሙያዎች ቁጥር ከፍ እንዲል ለማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ ያሉዋት ሳይካትሪስቶች 80 ብቻ እንደሆኑና በዚህም አንድ ሳይካትሪስት ለስንት ሰዎች እንደሚያገለግል ማስላቱ ቀላል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ካሉት ሳይካትሪስቶች መካከልም አብዛኞቹ በአዲስ አበባና ከዚህ በዘለለ በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በጣም ገዝፎ የታየው የአዕምሮ ሕመም ስለሆነ ነው እንጂ ከአንጎል ጋር የተያያዙ ሌሎች እንደ ብሬን ቱመር፣ የነርቭ ሕመሞች ወዘተ እንዳሉ፣ በአዕምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ የአዕምሮ ሕመም የበለጠ ትኩረት ሊደረግበት የቻለው ትንሽ አስከፊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ምትኩ፣ እንቅስቃሴው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በአዕምሮ ጤና ላይ የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶች (ጌርጌሴኖን፣ ሜቄዶንያ፣ አማኑኤል፣ ገፈርሳ የአዕምሮ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከል) ተገናኝተው ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር ከመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 50 መምህራን የአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ሥልጠና መስጠቱን አስረድተዋል፡፡

መምህራኑ በየትምህርት ቤታቸው ክለብ እንዲያቋቁሙና ስለአዕምሮ ጤና ተማሪዎቻቸው በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ መጣር እንዳልባቸው የተነገራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡