Skip to main content
x
ለሴቶች ያልተመቹ መኖሪያዎች

ለሴቶች ያልተመቹ መኖሪያዎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ አስከፊ በተባለ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙትን ለመታደግ እ.ኤ.አ. በ1933 የተመሠረተው ዓለም አቀፉ ሪስኪዩ ኮሚቴ (አይአርሲ)፣ በጤና፣ በደኅንነት፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በአስቸጋሪ ግጭት ውስጥና በስደት የሚገኙ ሰዎችን ለመታደግ ይሠራል፡፡ በአሜሪካ 28 ቢሮዎችን በመክፈት በ40 አገሮች ውስጥ የሚሠራው አይአርሲ፣ በየዓመቱ ማርች 8 ታስቦ የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ለሴቶች አመቺ ያልሆኑ ሥፍራዎችንና ተያያዥ ጉዳዮችን አትቷል፡፡ ድርጅቱ ማርች 8ን አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ምሕረት ሞገስ እንደሚከተለው አቀናብራዋለች፡፡

ጥያቄ፡- በየዓመቱ ታስቦ የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8ን) አስመልክቶ ለሴቶች ምቹ መኖሪያ ያልሆኑ ሥፍራዎች እንዴት ይገለጻሉ?

መልስ፡- በዓለም በተለይም ባላደጉት አገሮች ሴቶች ከግርዛት ጀምሮ ለተለያዩ የአዕምሮአዊና አካላዊ ጥቃቶች እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ ይህ ለሴቶች ኑሮ ምቹ አይደለም አይአርሲ ደግሞ በተለይ አምስት ሥፍራዎችን በአሁኑ ጊዜ ለሴቶች አመቺ ያልሆኑ ሲል ይገልጻቸዋል፡፡

ጥያቄ፡- እነዚህ አምስት ሥፍራዎች እነማን ናቸው? ማሳያዎቹስ ምን ነበሩ?

መልስ፡- በአሁኑ ሰዓት ለኮረዳ ሴቶች መኖሪያነት ምቹ ያልሆኑ ሥፍራዎችን የአይአርሲ የጥቃት ባለሙያዎች ለይተዋል፡፡ ሥፍራዎቹን ለመለየት የተጠቀሟቸው ማሳያዎች ያለዕድሜ ጋብቻ፣ አፍላ እርግዝና፣ መሃይምነት፣ ጥቃትና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚሉትን ነበር፡፡ በዚህም ኒጀር፣ የመን፣ ባንግላዲሽ፣ ደቡብ ሱዳንና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ለሴቶች መኖሪያነት አደገኛ አገሮች ተብለዋል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ በተለይ በእነዚህ የሚስተዋሉትን የሴቶች ጥቃት ለመታደግና ሰብዓዊ ቀውሱን ለማርገብ ሁሉም አካላት እንዲተባበሩ ጥሪ ያቀርባል፡፡

ጥያቄ፡- በእነዚህ አገሮች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አስመልክቶ ቁጥሮች ምን ያሳያሉ?

መልስ፡- በእያንዳንዱ  አገር ያለው የሴቶች ጥቃት የየራሱ መገለጫ አለው፡፡ መገለልና የዕድሎች እኩል ተጠቃሚ አለመሆን፣ የሚጠቀሱ ፈተናዎች ናቸው፡፡ በኒጀር ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ከ18 ዓመት በፊት ያገባሉ፡፡ ደቡብ ሱዳን በዓለም ከሚገኙ አገሮች በሴቶች ላይ በሚፈጸም ጥቃት ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች፡፡ በደቡብ ሱዳን 65 በመቶ ያህሉ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው አካላዊ ወይም ፆታዊ (መደፈር) ጥቃት የደረሳባቸው ናቸው፡፡ በባንግላዲሽ የተጠለሉ የሮሃኒያ ስደተኞች በሥጋት ውስጥ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡ በኮክስ ባዛር አካባቢ በ28 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከሰፈሩ እናቶችና ኮረዳዎች 77 በመቶ ያህሉ በሥጋት ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፕብሊክም ሴቶች ተመሳሳይ ሥጋት አለባቸው፡፡

ጥያቄ፡- ምን ዓይነት ሥጋት?

መልስ፡- በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፕብሊክ ፆታን መሠረት ያደረገ ከፍተኛ ጥቃት ይፈጸማል፡፡ በተለይ ሴቶችን መድፈር የጦርነቱ አንድ አካል ነው፡፡ በሁሉም ግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ኃይሎች ሴት መድፈርን እንደ ጦር መሣሪያ እየተጠቀሙበት ነው፡፡

ጥያቄ፡- ይህ ምን ያሳያል?

መልስ፡- ሴቶች በከፍተኛ መጠን ለሥጋት እየተጋለጡ መሆናቸውን ያሳያል፡፡  ይህም አይአርሲና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከልም ሆነ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት ምን ያህል አዳጋች እንደሆነባቸው የሚያመላክት ነው፡፡ ኮረዳዎች ልዩ ፍላጎት ስላላቸው የተለየ ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለሴቶች አመቺ ባልሆኑ ሥፍራዎች የሚኖሩ ኮረዶች በጣም የተገለሉ ናቸው፡፡ ለእነሱ የሚደረግ ዕርዳታ ሕይወት አድን ነው፡፡ የሴቶች እኩልነት እስኪረጋገጥ ድረስ ወጣት ሴቶች ይሰቃያሉ፡፡ ይህ በአይአርሲ በኩል ተቀባይነት ስለሌለው በሁሉም ሥፍራ የሴቶች እኩልነት እስኪረጋገጥ የውትወታና እገዛ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ተገቢውን ድጋፍና ኢንቨስትመንት በማድረግ ወጣት ሴቶች እንዲጎለብቱ፣ የወደፊት መሪ እንዲሆኑና የራሳቸውን ሕይወት መምራት እንዲጀምሩ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ሴቶች የትምህርት፣ የጤናና የፆታዊ ጥቃት ከለላ አገልግሎቶት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ መልካም ድባብ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

ጥያቄ፡- አይአርሲ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ምን ይሠራል?

መልስ፡- ድርጅቱ ሰብዓዊ ዕርዳታ ከመስጠት ጎን ለጎን ቀውስ ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ኮረዶች የሚያስፈልጓቸውን የተለዩ ፍላጎቶች ለማሟላት ይሠራል ‹‹ገርል ራይዚንግ››፣ ከሲቲ እንዲሁም ከኤችፒ ጋር በመተባበርም በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በስደተኛ ሴት ላይ ያጠነጠነ ፊልም ለቋል፡፡ በሰብዓዊው ድጋፍ ዘርፍ የፆታ እኩልነት እንዳይረጋገጥ የሚያደርጉ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ችግር ባለበት ቦታ ለሚኖሩ ሴቶች ድጋፍ ለማድረግ በየቀኑ የሚኖሩበት ሁኔታ ይወስነዋል፡፡ አይአርሲ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆምና ለችግሮች ምላሽ ለመስጠት ፕሮግራም ነድፎ እየሠራ ነው፡፡ በሴቶች ጥበቃና ማብቃት ፕሮግራሙም በአፍሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ 25 አገሮች ይሠራል፡፡  ከ10 እስከ 19 ዕድሜ ክልል ያሉት ኮረዳዎች ጤናማ፣ የተማሩና የበቁ እንዲሆኑም ይሠራል፡፡

ጥያቄ፡- ሴቶችን በማብቃቱ በኩል ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

መልስ፡- ሁሉም የአይአርሲ ፕሮግራሞች የተቀረፁት ሰዎች በጤና፣ በደኅንነት፣ በትምህርት፣ በገቢና በሕይወታቸው ላይ ጫና በሚፈጥሩ ውሳኔዎች ረገድ አወንታዊ ዕድገት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በሴቶችና በሕፃናት በተለይም በኮረዳዎች እንዲሁም ሌሎች ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑት ምላሽ ለመስጠትም ይሠራል፡፡

ጥያቄ፡- መፈናቀል ለጥቃት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ በዓለም ከቀዩ መፈናቀል እንዴት ይታያል?

መልስ፡- ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን መፈናቀል አባብሰውታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 60 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላዩ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፡፡ በግጭት ወቅት ለሰብዓዊ መብት መከበርና ጥበቃ ማድረግ የሚሠሩ መንግሥታዊ ተቋማት ይንኮታኮታሉ፡፡ ስደተኞች ካሉበት ቦታ ይፈናቀላሉ፡፡ ሌሎች የተገለሉ ክፍሎች ይብሱኑ ለጥቃት ይጋለጣሉ፡፡ በርካታ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ነው፡፡ በመሆኑም ሕጋዊ ከለላ የላቸውም፡፡ ከጤናና ትምህርት አገልግሎቶችም ተቋዳሽ አይደሉም፡፡

ጥያቄ፡- በሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ምን ይመስላል?

መልስ፡- በጥቃት ምክንያት በየአምስት ደቂቃው አንድ ሕፃን ይሞታል፡፡ በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትም በዓለም ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ግማሽ ያህሉን ይይዛል፡፡ በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ሕፃናት ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከሁለት እስከ 14 ዓመት የሚደርሱና ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ታዳጊ ሕፃናት በአሳዳጊዎቻቸው በየጊዜው አካላዊ ቅጣት ይፈጸምባቸዋል፡፡ በተለይ በግጭት ውስጥ በሚገኙ 23 አገሮች ከአምስት ሕፃናት አንዱ ከባድ አካላዊ ቅጣት ይፈጸምበታል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከአንድ እስከ 10 ዓመት ከሚገኙ ሴቶች ከአራት አንዷ እንዲሁም ከአምስት ወንዶች አንዱ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ፆታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሁለንተናዊ ዕድገታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል፡፡ በአዕምሮ ጤናና በትምህርት ቅበላ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በተጨማሪ ልጆቹ ኃይለኛና ቁጡ እንዲሆኑም ያደርጋቸዋል፡፡

ጥያቄ፡- ግጭት ባለበት አካባቢ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ምን ይመስላል?

መልስ፡- ግጭት ባለበት አካባቢ ከሦስት ሴት አንዷ ፆታዊ ጥቃት ይፈጸምባታል፡፡ ከ20 ዓመት በታች የሚገኙና 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች ይደፈራሉ፡፡ በቅርቡ በአይአርሲ የተደረገ ጥናት በዴሞክራቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ 40 በመቶ እንዲሁም በኢትዮጵያ 30 በመቶ ያህል ሴቶች ባለፉት 12 ወራት አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞችም ለጥቃት የታገለጡ ናቸው፡፡ መሠረታዊ አገልግሎት የማግኘት ዕድላቸውም ጠባብ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ድርጅቱ ጥቃትን ለመቆጣጠር ምን ዓይነት መንገድ ይከተላል?

መልስ፡- አይአርሲ ጥቃትን ከመሠረቱ ለማጥፋት ከማኅበረሰቡ፣ ከተቋማትና መንግሥታት ጋር ይሠራል፡፡ በፕሮግራሞቻችንም በሴቶች ላይ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር እንሠራለን፡፡