Skip to main content
x
የሚዲያ ባለሙያዎችን ያወዛገበው የሚዲያ ውይይት
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ከተገኙ ተሰብሳቢዎች በከፊል

የሚዲያ ባለሙያዎችን ያወዛገበው የሚዲያ ውይይት

እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ፣ የተለያዩ የሚዲያው ጎምቱ ባለሙያዎችና ባለቤቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የኪነ ጥበብና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን አንድ ላይ አገናኝቶ ነበር፡፡ ይኼም ‹‹በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር የሚዲያዎች ሚና›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደ የውይይት መድረክ ነበር፡፡ በመድረኩ በአወያይነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ሲሰየሙ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ ሲሳይ አጌናና አቶ ንጉሡ ጥላሁን ደግሞ የመወያያ ጽሑፍ አቅራቢነት ሚናን ይዘው ተገኝተዋል፡፡

ይኼ አራተኛ ዙር ላይ የደረሰው ‹‹ስለኢትዮጵያ እንወያይ›› (Dialogue on Ethiopia) በሚል መሪ ቃል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የሚካሄደው ተከታታይ የውይይት መድረክ ቀጣይ ክፍል ሲሆን፣ በርካቶች በመድረኩ በሰጡት አስተያየት እንዳስታወቁትም በሥፍራው የታደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይገኛሉ ብለው በመጠበቅ ነበር፡፡ ሆኖም መድረኩ በአወያዩ ተከፍቶ፣ በመወያያ ሐሳቡ አቅራቢዎች ተከታይነት ቀጥሎ በ16 አስተያየትና ጥያቄ አቅራቢዎች በተሰነዘሩ ሐሳቦችና ከሐሳብ አቅራቢዎች በተሰጡ ምላሾች ተደምድሟል፡፡

ሦስቱ ጽሑፍ አቅራቢዎች እንዲዘጋጁባቸው ተነግረዋቸው የነበሩት የሐሳብ ርዕሶች ‹‹በሥርዓት ሽግግር ወቅት ሚዲያ ያለው ሚና›› ለአቶ ጃዋር፣ ‹‹የሚዲያ ሚና በአገር ግንባታ›› ለአቶ ሲሳይ፣ ‹‹የሚዲያው ወቅታዊ ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫ›› ለአቶ ንጉሡ ሲሆን፣ አቶ ሲሳይ በመድረኩ ቀርበው ለተጠቀሰው ርዕስ የተሰጣቸው ጊዜ አጭር ስለነበር እንዳልተዘጋጁበት ገልጸው አጠር ያለ የመክፈቻ የሚመስል ገለጻ አድርገዋል፡፡ በዚህም ወደሚመቻቸው ርዕስ በመውሰድም የመናገር ነፃነትን፣ የሚዲያው አጭር የነፃነት ትውስታና አሁን አለ ያሉትን ለውጥ እንዴት በኃላፊነት መጠቀም ይቻላል የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን አነሳስተዋል፡፡

በመጀመርያ የመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት አቶ ጃዋር ከሽግግሩ በፊት የነበረው ሥርዓት ተገድዶ የለውጥ ኃይሉ ወደ ፊት ከመውጣቱ በፊት፣ ሁለት ዓይነት ሚዲያ በአገሪቱ ነበር ሲሉ ሚዲያውን የተገዛ ወይም የተገራና ያፈነገጠ በማለት ከፍለውታል፡፡ የመጀመርያው የመንግሥትን ትርክት ብቻ የሚያቀርቡ ናቸው በማለት በዚህ ዘርፍ የሚወድቁ የግል ሚዲያዎች፣ የመንግሥትን እያቀረቡ ግፋ ቢል ለስለስ ያለ ትችት ያቀርቡ ነበር ሲሉ ለመተንተን ሞክረዋል፡፡ ሁለተኛው ጎራ ደግሞ በዋናነት የፓርቲ ሚዲያዎች መሆናቸውን በማውሳት፣ ‹‹ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ በመሆናቸው መንግሥትን የሚያብጠለጥሉና የሚተቹ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡

የመጀመርያዎቹ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃን የማግኘት ዕድል ያላቸው መሆኑ ጥንካሬያቸው ሲሆን፣ ድክመታቸው አሠራራቸው እውነት ያፍናል ሲሉ ተንትነዋል፡፡ በሁለተኛው ጎራ የሚመደቡት ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቁርኝት ስለነበራቸው ያልተዛባ ዘገባ ለማቅረብ አልተቻላቸውም ሲሉ ደምድመዋል፡፡

‹‹ከለውጡ በኋላ የፖለቲካውን ምኅዳር መስፋት ተከትሎ ይኼንን ዕድል ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከሲቪክ ማኅበረሰቡ በቀዳሚነት የተጠቀሙበት ሚዲያዎች ናቸው፤›› ያሉት አቶ ጃዋር፣ ለዚህ መገለጫ እንዲሆን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሚዲያዎችን፣ ታስረው የነበሩና የተፈቱ ጋዜጠኞችን፣ እንዲሁም የመንግሥት ሚዲያው የግል ይመስል ትችቶችን ማስተናገድ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ባለፈው ሥርዓት  ተዘርግቶ የነበረው አሠራርና የመጫወቻ ሕጉ ፈርሶ ሳለ ሌላ አለመተካቱ ለሚዲያው ሥራ ድንበር ሳይበጅ ክፍት አድርጎታል በማለት፣ ‹‹መንግሥትም አስፋፍቶታል ግን የት ቀዩ መስመር እንዳለ አላወቀም፤›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አሁንም ጭምር ከበፊቱ የበለጠ ሚዲያው ላይ በር የመዝጋት ችግር እንዳለና በሚዲያውም፣ በመንግሥትም፣ በሕዝብም ላይ ችግሮች አሉ ሲሉ ተችተዋል፡፡ ‹‹ይኼን የሰፋውን ምኅደር እንዴት መጠቀም አለብን የሚለውን ገና እየተለማመድን ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ችግሮቹን በማንሳት የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርቡም ሚዲያው ራሱን መግራት እንዳለበት፣ እርስ በርሱ መገማገምና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልገው፣ የሚዲያ ሕጉ በቶሎ ፀድቆ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሰፊ ውይይቶች መደረግ እንዳለባቸውና የመንግሥት ተቋማትን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ይሁንና ይኼ የአቶ ጃዋር የሚዲያ ችግር ትንተናና የመፍትሔ ሐሳብ ከተሳታፊዎች በርካታ ትችቶች አስከትሏል፡፡

የመጀመርያው ችግርን የተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡት የቁም ነገር መጽሔት ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ኃይሉ የጋዜጠኝነትና የአክቲቪስትነት መደበላለቅ የሚታይባቸው አንዱ እሳቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ ሰው እንዴት እንደሚረዳቸው ጠይቀዋል፡፡ በማከልም፣ ‹‹እስካሁን የነበረው መንገድ ይታወቃል፡፡ ኢሳትም ኦኤምኤንም ሲያቀርቡ የነበረው፡፡ አሁን ግን ለውጥ መጥቷል ካልን ትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥራ የሚሠራባቸው ሚዲያዎች የመሆን ዕድላቸው ምን ያህል ነው?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ሌላው ጠያቄ የነበሩት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር አባል አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣  አቶ ጃዋር መሐመድ ያፈነገጡ ሚዲያዎች አሉ ያሉት በማንሳት፣ ‹‹በፖለቲካ ፓርቲዎች ከተያዙ በተጨማሪ በግለሰቦች በፈላጭ ቆራጭነት የተያዘ ሚዲያ መኖሩን ለምን ዘለልከው?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሬዲዮ እንደመጡ የገለጹትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኖራሉ ብለው ጠብቀው መሳተፋቸውን የተናሩት አቶ ቃለ አብ ሞላ፣ ‹‹ጃዋር ስታቀርብ እኔን የሳበኝንና ካንተ ሰብዕና ጋር የሚጣረስ የጠቀስከውን ነገር ጠቅሼ እጠይቃለሁ፡፡ ሚዲያዎች ራስን ማረቅ፣ ራስን መግዛት አለባቸው ብለኸናል፣ ቀይ መስመር እያልክ ሌሎች የጠቀስካቸው አሉ፡፡ በእርግጥም ከትናንት ወዲያ አዲስ አበባን እንደ አንድ ኩንታል ጤፍ ብንቆጥራት፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ውስጥ አንዲት ፍሬ ጤፍ የሚያህል የኮንዶሚኒየም ሕንፃ ሥር ሆነህ ኮንዶሚኒየም ወይም ሞት ብለህ የምትናገር ሰው፣ ሚዲያ በጀርባህ የምትመራ ሰው ራስህን ሳታርቅና ሳትገዛ... በአወያይነት መምጣትህ እስከማይገባኝ ድረስ . . . ከትናንት ወዲያ ይኼንን ዓይነት ንግግር የሚያደርግ ሰው በምን ሁኔታ ነው ስለራስ መግዛት የሚናገረው? ከራስህ አትጀምርም ወይ?›› በማለት ጥያቄውን ሰንዝሯል፡፡

ለተነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ጃዋር በስፋት የሚታየው ችግር ምንጩ ለውጡ ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ የአክቲቪዝምና የሚዲያ ባለሙያነት የተቀላቀለ መሆኑ በደንብ መታየት ያለበትና ሰፊ ውይይት የሚጠይቅ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ለጠያቂው ግን በቂ ምላሽ ሳይሰጡ ወደ ሌላ ጉዳይ ገብተዋል፡፡

‹‹ሚዲያው ታፍኖ ስለነበር ሚዲያዎችን ያቋቋሙት የመብት ተሟጋቾች ናቸው፡፡ ለመብት የማይሟገት ጋዜጠኝነትን ብቻ መቀጠል የፈለጉት በመንግሥት ሚዲያ ውስጥ ወይም ዳግም በግል ሚዲያ ውስጥ አፋቸውን ዘግተው የቆዩ ናቸው፡፡ ሌሎቹ እስር ቤት ገቡ፡፡ ከእስር ቤት ሲወጡ ወይ በማኅበራዊ ሚዲያ ወይ በተለመደው ሚዲያ በውጭ አገር በተለያየ መልኩ ሲሠሩ ቆዩ፡፡ ስለዚህ አብዛኛው በአፈንጋጭ ሚዲያ የነበሩት ጋዜጠኞች ሙሉ በሙሉ የጋዜጠኝነት ባለሙያዎች ናቸው ለማለት አይቻልም፣ በመሆኑም አይሳካላቸውም፤›› ብለው ይኼንን ማስተካከል በአንድ ሌሊት የሚመጣ አይደለም ብለዋል፡፡

‹‹ሙሉ ለሙሉ እንለያያለን ማለት ራስን መዋሸት ነው፣ በተለይ በዚህ በሽግግር ወቅት ውስጥ ጋዜጠኛው ወገንተኛ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ ሚዲያዎች የአንድን ብሔርና የፖለቲካ ፍላጎት አያራምዱም ማለት ራስን መዋሸት ነው፡፡ ይቀጥላል፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊዎች በተለይ አቶ ጃዋር ላይ ያቀረቡት ትችት፣ ግለሰቡ በስብሰባው የተገኙት የትኛው ኃላፊነታቸውን ወክለው እንደሆነ በመጠየቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም አቶ ጃዋር አንዴ የአክቲቪስት፣ ሲላቸው የጋዜጠኛ፣ እንዲሁም ሲያሻቸው የፖለቲከኛ ኮፍያ በማጥለቅ ስለሚንቀሳቀሱ ነበር፡፡ እሳቸውም ለጊዜው ሦስቱንም ኮፍያዎች በማጥለቅ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡ አቶ ጃዋር የሚመሩት የሚዲያ ተቋም ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የጋዜጠኝነት የሥነ ምግባር መመርያ ወጥቶላቸው በዚያ መሠረት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸው፣ እሳቸው ያንን የሥነ ምግባር መመርያ እንደማይገዛቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹እርስዎስ ለምን በዛ አይገዙም?›› ተብለው ተጠይቀው፣ ወደፊት የሚዲያ ተቋማቸው የማኔጅመንት ኃላፊዎች የሚገዙበት መመርያ ሊያወጡ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ አሁን ግን በሦስቱም ኮፍያዎች መንቀሳቀስ እንደሚመርጡ ገልጸዋል፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ የራሱ የሆነ የሥነ ምግባር መመርያ ያለውና በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት ሊሠራ የሚገባ ሙያ ሲሆን፣ የአቶ ጃዋር ምላሽ ግን በርካቶችን አስገርሟል፡፡ ምክንያቱም የአክቲቪስትና የፖለቲከኛ ሥራ ከጋዜጠኝነት በተቃራኒው የአንድን ወገን ሐሳብ ወይም እምነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ ነው፡፡

የሚዲያ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚሉ ጉዳዮች ላይ የመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ መምጣት በመደበኛ ሚዲያው ተጠቃሚነት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ በመግለጽ ጎን ለጎንም ዕድሎችን ይዞ መጥቷል ብለው፣ ለአብነትም መረጃን በቀላሉና በአነስተኛ ወጪ መሰብሰብና ማሰራጨት ማስቻሉን አውስተዋል፡፡

ነገር ግን ከመንግሥት ወገን ሁሉንም የመቆጣጠር ፍላጎት መኖሩ፣ በጥቃቅን ነገሮች ሁሉ አተካሮ ውስጥ መግባት፣ ሬጉሌሽን የሚለውን ሐሳብ ወደ መቆጣጠር (ማሰናከል) መቀየር፣ በአዋጅ፣ ደንብና መመርያ ሳንሱር የሚመስል አሠራር መዘርጋት፣ ጋዜጠኝነትን እንደ ሥጋት መመልከት፣ ሚዲያዎች በጋዜጠኝነት መርህ እንዲሠሩ አለማብቃትና የመረጃ ተደራሽነት አናሳ መሆን የወቅቱ ፈተናዎች ናቸው በማለት ተችተዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ሁለቱ ሐሳብ አቅራቢዎች ከውጭ የመጡ መሆናቸውና አንዱ ደግሞ የመንግሥት ተሿሚ መሆናቸው፣ የአገር ውስጥ የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች አለመወከል በርካቶችን ግራ ያጋባ ሲሆን፣ የተሰብሳቢዎቹ ስብጥርም እንዲሁ ጥያቄ ያጫረ ነበር፡፡

የዛሚ ራዲዮ መሥራችና ጋዜጠኛ ወ/ሮ ሚሚ ስብሐቱና፣ ‹‹የእኛ የሙያ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በተለጠጠው ምኅዳራችን በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ለወደፊት ይኼ ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ሙያችን ደግሞ የራሱ የሆኑ መመርያዎች፣ መሥፈርቶች ያሉት ነውና እዚህ ግን ሁልጊዜ ሚዲያ ሲጠራ ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር ይጠራል፡፡ አንደኛ ሁለታችን በጣም የተለያየን ነን፡፡ የተለያየን እንስሳት ነን፡፡ ስለዚህ የእኛ ኢንዱስትሪ በጣም ብዙ ችግር አለበት፡፡ እነዚህ ችግሮች ስለተበተቡትም ነው ውጤታማ ሊሆንም የማይችለው፡፡ ስለዚህ የኢንዱስትሪው አባላት፣ በቀጥታ ሙያው የሚመለከታቸው ሰዎች ቁጭ ብለው፣ ተወያይተው እነዚህ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መድረክ ነው መሆን የሚገባው፡፡ አሁን ይኼ አጠራሩ በቀጥታ በእኛ ዘርፍ የሌሉ ሰዎች ጋር ነው አንድ ላይ የተጠራነው፤›› በማለት ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ላይ፣ የመገናኛ ብዙኃንን ወክለው የተገኙ ጋዜጠኞችና የሚዲያ መሪዎች ቅሬታዎቻቸውን ሲያሰሙ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚዲያ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ የተነገረው ባለመከበሩ፣ በአወያይነት የተመረጡት ግለሰቦች በምን መመዘኛ እንደቀረቡ፣ የሚዲያ ባለሙያዎች በገዛ ጉዳያቸው ላይ ድምፃቸውን ማሰማት አለመቻላቸውና የውይይቱ መሪ ይኼንን ተገንዝበው ለሚዲያ ሰዎች በተሻለ ዕድል አለመስጠታቸው የብዙዎች ቅሬታ ነበር፡፡ በተለይ ጋዜጠኝነትና የፖለቲካ አክቲቪስትነትን በተለያዩ ባርኔጣዎች ማፈራረቅ እንደሚቻል በልበ ሙሉነት በአቶ ጃዋር የተሰጠው አስተያየት ብዙዎችን አስገርሞ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያንና ሥነ ምግባርን በተቻለ መጠን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጣጣሩ ሚዲያዎችን እንደ ሥርዓቱ አፈቀላጤነት ወይም አንገታቸውን በፍርኃት እንደደፉ ተደርጎ የተሰጠው ማብራሪያም፣ የሙግት ሐሳብ ሳይቀርብበት በመድረክ መሪው ድክመት መታለፉ እንዳስቆጣቸው ከውይይቱ በኋላ መነጋገሪያ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ ምግባርን እንዴት ተላብሶ ኃላፊነትን በገለልተኝነት መወጣት ይቻላል ከማለት ይልቅ፣ ገለልተኝነት ሊኖር አይችልም ብሎ መደምደም ትክክለኛ አለመሆኑን ሐሳባቸውን የመግለጽ ዕድል ያጡ ጋዜጠኞች ከውይይቱ በኋላ ሲቆጩ ተስተውለዋል፡፡ አወያዩ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት መሪ ሆነው ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ላይ በጋዜጠኝነት እየሠሩ ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡት ሐሳብ ካለ ብለው መጠየቅ ሲገባቸው፣ መድረኩን እንደ ዋዛ ማባከናቸው ለብዙዎች አልተዋጠላቸውም፡፡