Skip to main content
x

የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ሒሳብ ለመክፈል መቸገራቸውን ደንበኞች ይናገራሉ

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች የፍጆታ ሒሳብ ለመክፈል በየአካባቢው በሚገኙ የክፍያ ጣቢያዎች ከፍተኛ መጉላላት እየገጠማቸው መሆኑንና የተጠቀሙባበትን ለመክፈል መቸገራቸውን ገለጹ፡፡ ለዓመታት የቆየው ይህ ችግር እስካሁን ዕልባት አላገኘም፡፡

በርካታ ደንበኞች ክፍያ ለመፈጸም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የክፍያ ጣቢያዎች ተሠልፈው ማየት የሰርክ ተግባር እየሆነ በመጣበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዕከላት ውስጥ በርካታ ደንበኞች ለሰዓታት ተሠልፈው ክፍያ ለመፈጸም ከሚጠባቁባቸው ማዕከላት አንዱ፣ ከዛንቺስ አካባቢ የሚገኘው የክፍያ ጣቢያ ዋናው ማዕከል በመሆን በመላው አዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞች ከየአቅጣጫው በመሄድ የሚስናገዱበት እስከመሆን ደርሷል፡፡

ምንም እንኳ በአዲስ አበባ ደረጃ 41 ያህል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በአራቱም የአገልግሎት ዲስትሪክቶች አማካይነት ክፍያ እንደሚቀበሉ ቢታወቅም፣ አብዛኞቹ ግን ‹‹ሲስተም የለም›› እና ‹‹ኔትወርክ የለም›› በሚሉ ምክንያቶች የታወቁ ናቸው ያሉት ሪፖርተር ማክሰኞ፣ በካዛንቺሱ የክፍያ መቀበያ ማዕከል ያነጋገራቸው ደንበኞች ናቸው፡፡ በወቅቱ ረዥም ሠልፍ የታየበት ክፍያ ማዕከሉ፣ በተለይም በቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ደንበኞች ዘንድ ግቢው ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ታይቷል፡፡ የድኅረና የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ደንበኞች የሚስናገዱባቸው ሁለት የተለያዩ የክፍያ መቀበያ ክፍሎች ቢኖሩም፣ በአገልግሎት አሰጣጣቸው እጅግ የተንቀረፈፉና ደበንኛው እንደአመጣጡ የማይስተናገድባቸው ሆነው ታይተዋል፡፡

አቅመ ደካሞች፣ እናቶችና ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ሕፃናት ያዘሉ እናቶች፣ በርካታ ሴቶችና ወጣት ወንዶች ረዣዥም ሠልፎች ሠርተው በአገልግሎት መስጫ ግቢው ተኮልኩለዋል፡፡ በተለይ በቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚዎች በኩል ለታየው ረዥም ሠልፍ አንዱ ምክንያት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ኮምፒዩተሮችና ከሰርቨር ጋር ለማገናኘት ይደረግ የነበረው ችግር ብሎም የካርድ ንባብ የሚፈጸምባቸው ኮምፒውተሮች (ሦስት ናቸው) ለማስተካከል በወሰደው ጊዜ ምክንያት ደንበኞች እንዳመጣጣቸው ክፍያ መፈጸም ቸግሯቸው ለረዥም ሠልፍ ተዳርገዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች እየታዩም በወቅቱ ምላሽ መስጠት አለመቻሉ፣ ደንበኞች እጅግ እንዲማረሩ አድርጓል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ከጣፎ፣ ከየካ አባዶ፣ ከጀሞ፣ ከሳሪስና ከሌሎች የከተማው ዳርቻዎችና መሀል አካባቢዎች ወደ ካዛንቺሱ የክፍያ ማዕከል በማቅናት ተራቸውን የሚጠባበቁ ነበሩ፡፡

እንዲህ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገልግሎት ክፍያዎችን በባንክ፣ በሞባይልና በኢንተርኔት፣ እንዲሁም በየኪዮስኩ በኩል አደርጋለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ይህ ዕቅድ ምናልባት ወደ ተግባር የሚለወጠው ከነሐሴ ወር ጀምሮ እንደሆነ የአገልግሎቱ ኃላፊዎች በቅርቡ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይሁንና እንዲህ ያለውን የደንበኞች እንግልት እስከዚያው ድረስ ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዕርምጃዎች አለመታየቸው ግን ምሬትና ቅሬታን እያስከተለ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴን ስለጉዳዩ በስልክ ለማነጋገር ተሞክሮ ባይሳካም፣ በከተማው የሚታየውን ችግር ግን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎችም የሚያውቁት ነው፡፡ እንዲያውም በአንዳንዶቹ አገልግሎት መስጫዎች ጣቢያዎች፣ ‹‹ፕሪንተር ተበላሽቷል››፣ ‹‹ኮምፒዩተር አይሠራም›› በሚሉ ተራ ምክንያቶች ሳቢያ አገልግሎት እንደማይሰጡ ኃላፊዎቹ በመስክ ጭምር ባደረጉት ማጣራት መገንዘባቸውን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ ይህ ይባል እንጂ አብዛኛው ደንበኛ የተጠቀመበትን ለመክፈል ደጅ መጥናቱ ቅሬታ አሳድሯል፡፡

መሥሪያ ቤቱ በአንድ በኩል ቆጣሪ እየነካኩና መስመር እየሰረቁ ለበርካታ ዓመታት ያለ ክፍያ ሲጠቀሙ የነበሩ ሕገወጦችን ለመከላከል እየሠራሁ ነው ቢልም፣ በአንፃሩ በቅድመና በድኅረ ቆጣሪ ክፍያ ለመፈጸም ረዣዥም ሠልፍ ለመያዝ የሚገደዱ ደንበኞቹ የሚሰጠው ምላሽ አላስፈላጊ ድርጊት የሚፈጽሙትን የሚያበረታታ መስሎ እንደሚታያቸው ደንበኞቹ ይናገራሉ፡፡ ይህም ሆኖ በቅርቡ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባካሄደው የ2011 ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ወቅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 15,523 አዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማስቻሉን አስታውቆ ነበር፡፡ በስብሰባው ወቅት ዓብይ መነጋገሪያ ከነበሩት ውስጥ የኢነርጂ ሽያጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ የኃይል መቆራረጥ መቀነስ፣ የግብዓት አቅርቦትና የቆጣሪ ምርመራ ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደነበረም ከተቋሙ ለመረዳት ተችሏል፡፡

      የቅድመ ቆጣሪ ደንበኞች በተለይ የአገልግሎት ሒሳባቸውን ቀድመው በካርድ የሚከፍሉ በመሆናቸው፣ የሞሉት የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ባለቀ ጊዜ ለማስሞላት የሚያዩት እንግልት ሊቀርፍ አልቻለም፡፡ ዋና ችግራቸውም ክፍያ የሚፈጽሙበት የተመቻቸ ሥርዓት በአቅራቢያቸው እንደ ልብ ባለማግኘታቸው እንደሆነ ብዙዎቹ ይናገራሉ፡፡

ደንበኞቹ ይህንን ቢሉም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ግን ተደራሽነቱን እያስፋፋ ይልቁንም 540 ሺሕ አዲስ ደንበኞች በቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ከ370 ሺሕ በላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡ የቅድመ ቆጣሪ ደንበኞችን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የኢንተርኔት ኔትወርክ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ፣ ያልተቋረጠና ጥራቱን የጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት የሚችልበትን መንገድ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆነም ይፋ አድርጓል፡፡

እስካሁን ከሦስት ሚሊዮን በላይ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎችን የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በርካታ ማሻሻያዎችን፤ በተለይም ያረጁ ኃይል ተሸካሚና ማሠራጫ መስመሮችን በአዲስ እየቀረ እንደሚገኝ በመግለጽ በበርካታ አካባቢዎች ኃይል ሲያቋርጥ ቆይቷል፡፡ 

በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ውስጥ ተቋሙ ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ማስታወቁንና ከታኅሳስ ወር ጀምሮም አዲሱን የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ መዘገባችን አይነዘጋም፡፡ ይህንን ተከትሎም በተለይ የቅድመ ቆጣሪ ተጠቃሚዎች በንባብ ወቅት ከፍተኛ ሒሳብ መጠየቃቸውን በመግለጽ አቤቱታቸውን እያሰሙ እንደሚገኙም መዘገቡ ይታወሳል፡፡