Skip to main content
x
ኅብረት ባንክ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተያዙ አክሲዮኖችን በከፍተኛ ዋጋ አገበያየ
ኅብረት ባንክ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን የአክሲዮን ድርሻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመሸጥ ተቀዛቅዞ የቆየውን መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል

ኅብረት ባንክ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተያዙ አክሲዮኖችን በከፍተኛ ዋጋ አገበያየ

በተለያዩ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የአክሲዮን ባለድርሻ በመሆን የቆዩ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያዊያን ይዞታ ሥር የነበሩ አክሲዮኖች እንዲመለሱላቸው ቢወሰንም፣ አሁንም ግን ድርሻዎቻቸው ለጨረታ እየቀረቡ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

 ኅብረት ባንክ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጨረታ የ100 ብር ዋጋ ያለውን አንድ አክሲዮን እስከ 1,027 ብር መሸጡ ተገልጿል፡፡ በየጊዜው በሚደረግ ማጣራት የውጭ ዜግነት ባላቸው ኢትዮጵያዊያን የተያዘ የአክሲዮን ድርሻ በሽያጭ ለኢትዮጵያዊያን እንዲተላለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት፣ ኅብረት ባንክ ለጨረታ ያቀረበው 1,600 አክሲዮኖችን ነበር፡፡

በዚህ መሠረት ባንኩ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጨረታ ላይ ተጫራቾች የ100 ብር ዋጋ ላለው አንድ አክሲዮን እስከ 1,027 ብር ዋጋ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ከባንኩ በተገኘው መረጃ መሠረት በ1,027 ብር ዋጋ የተሸጡት አክሲዮኖች 15 መሆናቸው ታውቋል፡፡ ለጨረታ ከቀረቡት አክሲዮኖች ውስጥ (የአገልግሎት ፕሪሚየም ዋጋን ጨምሮ) የተሰጣቸው ዝቅተኛ ዋጋ 200 ብር ነው፡፡ ይህም ዝቅተኛ ዋጋው 100 ብር የሆነውን አንድ አክሲዮን የአገልግሎት ዋጋውን አክሎ ባንኩ በእጥፍ ለመሸጥ እንዳቀረበው የሚያመላክት ነው፡፡ ለጨረታ የቀረቡትና እያንዳንዳቸው የ100 ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች በአማካይ የተሸጡበት ዋጋ 214 ብር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ሕግ የደነገገ ሲሆን፣ ባንኮችም የውጭ ዜግነት ባላቸው ኢትዮጵያዊያን የተያዙ አክሲዮኖችን በማጣራት አክሲዮኖቻቸውን እንዲያስተላልፉ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ገዥው ባንክ መመርያውን ካስተላለፈ ጀምሮ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ይህንኑ ሲያከናውኑ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

በመመርያው መሠረት የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የነበሯቸውን የአክሲዮን ድርሻዎች መሸጥ የሚፈቀድላቸው ወይም መረከብ የሚችሉት ዋጋ አክሲዮን የገዙበትን መጠን ብቻ እንደሆነም የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ውሳኔም በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስነሳት ትልቅ ተቃውሞ እንዳስተናገደና ወደ ፍርድ ቤት እስከመሄድ የደረሰ ውዝግብ ማስከተሉ ይታወቃል፡፡

የፋይናንስ ተቋማቱ አክሲዮኖቹን ለጨረታ ካቀረቡ በኋላ ከዋናው የአክሲዮን ዋጋ በላይ በሽያጭ የተገኘውን ተጨማሪ ትርፍ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርጉም መመርያው ያስገድዳቸዋል፡፡ በመመርያው መሠረት ኅብረት ባንክ በ1,027 ብር ከሸጠው አንድ የአክሲዮን ዋጋ ውስጥ 100 ብሩን አስቀርቶ ቀሪውን ለመንግሥት ገቢ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ መመርያው ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁሉም የግል ባንኮች በውጭ ዜጎች ኢትዮጵያዊያን ባለድርሻነት ተይዘው የነበሩ አክሲዮኖችን በመሸጥ ከ800 ሚሊዮን ብር ግብይት እንደፈጸሙ ይታወቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት ባንኮች የውጭ ዜግነት ባላቸው ኢትዮጵያዊያን የተያዙ አክሲዮኖችን ባገኙ ቁጥር መመርያውን ተፈጻሚ እያደረጉ ቢሆንም፣ እየተሸጡ የሚገኙት የትውልድ ኢትዮጵያዊያን አክሲዮኖች ቁጥር ግን በየጊዜው ቅናሽ እየታየባቸው ስለመሆኑ በባንኮች ውስጥ አሉ ተብለው የሚገመቱና በትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተያዙ አክሲዮኖች ብዛት ከአምስት በመቶ እንደማይበልጡ ይገመት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ መጠን በእጅጉ እንደሚቀንስ ይጠበቃል፡፡

አነጋጋሪ የሆነው ይህ መመርያ መተግበር የለበትም የሚል ተቃውሞ የቀረበበት ቢሆንም፣ እንዲህ ባለው መንገድ የሚሸጡ የባንክ አክሲዮኖች ጨረታ ሲወጡ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በተለይ ትልልቅ የሚባሉት ባንኮች ላይ በሚወጣ የአክሲዮኖች ጨረታ ላይ የጨረታ ተሳታፊዎች ከፍተኛ ዋጋ መስጠታቸው  በባንኮች ላይ አክሲዮን ለመግዛት ያለውን ፍላጎት ያሳየ ነው ተብሏል፡፡

የውጭ ዜጎች እስካሁን ባለው ሕግ በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ባለድርሻ መሆን እንደማይችሉና ሆነው ከተገኙም ከባለአክሲዮኖቻቸው እንዲለቁ እየተደረገ ቢሆንም፣ ዳያስፖራው በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆንበት ሕግ እየተረቀቀ ነው፡፡

ከሦስት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንዳመለከቱት ዳያስፖራውን በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚያሳትፍ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑንና ረቂቁን በማፅደቅ ወደ ሥራ የሚገባ ስለመሆኑ ያስታወቁ ቢሆንም፣ በአንፃሩ ግን ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዜግነታቸውን የለወጡ ኢትዮጵያዊያን ይዘው የቆዩት የአክሲዮን ድርሻቸው ለጨረታ እያቀረቡና እየተሸጡ ነው፡፡