Skip to main content
x
ለጌዴኦ ተፈናቃዮች ዕርዳታ እንዳይደርስ ያደረጉ በሕግ ይጠየቁ!

ለጌዴኦ ተፈናቃዮች ዕርዳታ እንዳይደርስ ያደረጉ በሕግ ይጠየቁ!

በኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከደረሱ ዋነኛ ቀውሶች መካከል አንደኛው፣ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ከ800 ሺሕ በላይ የጌዴኦ ተወላጆች መፈናቀላቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር በሐምሌ መጨረሻ 2010 ዓ.ም. በሥፍራው ተገኝቶ በሠራው ሰፊ ዘገባ፣ በጉጂና በጌዴኦ ተወላጆች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀዬአቸው በግፍ መፈናቀላቸውን ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ አጥቢ እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ሕፃናት፣ አቅመ ደካሞችና አዛውንቶች የመፈናቀሉ ሰለባ በመሆን፣ ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ መጋለጣቸው በዘገባው በሰፊው ተተንትኗል፡፡ ከግጭቱ ሕይወታቸው የተረፈ የአንድ አባወራ ቤተሰቦች በአማካይ አሥር እንደሚሆኑ፣ ከደቡብ ክልል የጌዴኦ ዞን የወጡ መረጃዎች ያመላክቱ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ዕርዳታ ተከልክለው በረሃብ እየተቀጡ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ በሕግ የማይጠየቁ በመብዛታቸው ነው አገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀውስ ውስጥ እየገባች ያለችው፡፡

 በወቅቱ ለተፈናቃዮቹ ዕርዳታ ለማቅረብ የተለያዩ አካላት ርብርብ እያደረጉ እንደነበር በዓይን ቢታይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ መረጃዎች ግን አስደንጋጭ ናቸው፡፡ ተፈናቃዮቹ ዕርዳታ እንዳያገኙ በመከልከላቸው ምክንያት ቀውስ እየተፈጠረ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የፌዴራልም ሆነ የሚመለከታቸው የክልል ብሔራዊ መንግሥታት ዳተኛ በመሆናቸው፣ የጌዴኦ ተፈናቃዮች ቀውስ ለአገር እንዳይተርፍ ያስፈራል፡፡ ሰብዓዊ ዕርዳታ የተነፈጉት ወገኖች ጉዳይ እጅግ በጣም አሳሳቢ መሆኑን በመገንዘብ፣ አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ ካልተቻለ፣ አገሪቱ የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ስለምትገባ ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙትም በአስቸኳይ ለሕግ ይቅረቡ፡፡

የጌዴኦ ተፈናቃዮች ለዚህ ሁሉ መከራ የተዳረጉት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚጮሁ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስለሌሉዋቸው እንደሆነ በተግባር ታይቷል፡፡ አሁንም በተወሰኑ ሰብዓዊነት በሚሰማቸው ወገኖች አማካይነት የእንድረስላቸው ጥሪ ቢሰማም፣ እጅግ በጣም በሚያሳፍር ሁኔታ የመንግሥት አንደበት ተሸብቧል፡፡ ብርጭቆ ተሰበረ ብለው አገር የሚያሸብሩ አክቲቪስት ተብዬዎች የመንግሥትን ውሳኔ በሚያስቀለብሱበት አገር ውስጥ፣ የጌዴኦ ተፈናቃይ ወገኖችን እሪታ አለመስማት ይዘገንናል፡፡ የጌዴኦ እናቶች፣ አባቶችና ጨቅላ ሕፃናት በረሃብ እየተገረፉ ነው፡፡ ይህ ሰው ሠራሽ ችግር ተባብሶ አገርን የበለጠ ከቀውስ ውስጥ ከመዳረጉ በፊት፣ ጆሮ ዳባ ያለው መንግሥትም ሆነ በየደረጃው ያሉ ሹማምንት ዓይናቸውን ይግለጡ፡፡ በተረፈ ለወገኑ ያለችውን የማይሰስተው ደጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተቻለ አቅሙ እንዲረዳ እንቅፋት የምትሆኑ እጃችሁን ሰብስቡ፡፡ በገዛ ወገን ቀልድ የለም መባል አለበት፡፡   

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከጌዴኦ ተፈናቃዮች ውስጥ ጎቲቲ በምትባል መንደር ውስጥ ብቻ 30 ሺሕ ያህል ወገኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳያገኙ ተከልክለው እየተራቡ ናቸው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያዊያን ጆሮ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ከመፈናቀላቸውም በላይ የሚበሉት ተከልክለዋል ሲባል ያሳፍራል፡፡ ይኼንን እያደረጉ ያሉ አካላት በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል እየሠሩ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ወገኖች በተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር ግንባር ቀደሙ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እነዚህ ተፈናቃዮች በነበሩበት ሥፍራ ቤተሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በግጭቶች ከመነጠቃቸውም በላይ፣ መኖሪያዎቻቸውና ማሳዎቻቸው ወድመውባቸዋል፡፡ ለእነዚህ ወገኖች የዕለት ዕርዳታ ከመስጠት ባሻገር፣ ለዘለቄታው በማቋቋም ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው መመለስ የመንግሥት ግዴታም ኃላፊነትም ነው፡፡ አሁን ባለው አሳዛኝና አስደንጋጭ ሁኔታ በፍጹም መቀጠል አይቻልም፡፡

እየተነጋገርንበት ያለው ጉዳይ በቀጥታ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎችን ይመለከታል ቢባል እንኳ፣ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት የግድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ግጭት በተነሳባቸው ሥፍራዎች ተገኝተው እንዳደረጉት ሁሉ፣ ለጌዴኦ ተፈናቃዮችም በፍጥነት መድረስ አለባቸው፡፡ በጌዴኦ ተፈናቃዮች ጉዳይ በጣም የዘገዩ ቢሆንም፣ አሁንም ትንሽም ቢሆን ጊዜ አለና ከእሳቸው የሚጠበቀውን ማድረግ አለባቸው፡፡ የጌዴኦ ተፈናቃዮችም የእሳቸውን ጣልቃ ገብነት ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል በግላቸው ተነሳስተው ዕርዳታ በማሰባሰብ ለወገኖቻቸው ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ያሉ በጎ አድራጊዎች፣ ክፋት በተጠናወታቸው ኃይሎች ሰብዓዊ አገልግሎታቸው እንዳይደናቀፍ መንግሥት ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ተፈናቃዮቹ ዕርዳታ እንዳይደርሳቸው እያደረጉ ያሉ ኃይሎችም በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነትና መልካም ሥነ ምግባር በተቃራኒ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙ በግልጽ ሊወገዙ ይገባል፡፡ ተፈናቃዮቹ ያለ ኃጢያታቸው የግፍ ሰለባ መሆናቸው ምንጊዜም ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሐዘን ላይ ናት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙ ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ከ8.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እየተለመነላቸው ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ 157 ሰዎች አልቀዋል፡፡ የሟቾች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በሐዘን ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህን ድርብርብ ሐዘኖች በተሸከመች አገር ውስጥ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ የግፍ ሰለባ ወገኖች የሚበሉት አጥተው ሲራቡና ሲታረዙ እንደ መርግ ይከብዳል፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመው ችግሮቻቸውን መፍታት ሲገባቸው፣ የኢትዮጵያዊያንን የተከበሩ የጋራ እሴቶች የሚንዱ እኩዮች ግን ክፋት ይፈጽማሉ፡፡ ሰብዓዊነትን እየተጋፉ ጭካኔ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንኳን እርስ በርሳቸው ለባዕድ ሳይቀር አዛኝና ሩህሩህ እንደሆኑ በግልጽ የታወቀ ነው፡፡ ሕዝብን እርስ በርሱ ለማጋጨትና አገርን ቀውስ ውስጥ ለመክተት የሚተጉትን በኅብረት ማስቆም የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወሳኝ ወቅት ለወገኖቻቸው በአንድነት በመቆም አጋርነታቸውን ማሳየት፣ የውዴታ ግዴታ መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ በዚህ ስሜት ለጌዴኦ ተፈናቃዮች እንድረስላቸው ሲባልም፣ ዕርዳታ ያስከለከሉ አካላትም በሕግ ይጠየቁ መባል አለበት!