Skip to main content
x
ሞዛምቢክ ዚምባቡዌንና ማላዊን የመታው ‹‹ሳይክሎን ኢዳይ››
በሞዛምቢክ ቤይራ በተባለ ሥፍራ ከባድ ዝናብና አውሎ ንፋስ ካስከተለው ጎርፍ ነዋሪዎች ራሳቸውን ለማዳን ጣሪያ ላይ መውጣት ግድ ሆኖባቸዋል

ሞዛምቢክ ዚምባቡዌንና ማላዊን የመታው ‹‹ሳይክሎን ኢዳይ››

ያለፈው ሳምንት በሞዛምቢክ፣ ዚምባቡዌና ማላዊ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን የፈተነው ከባድ በአውሎ ንፋስና ዝናብ በተያዘው ሳምንት ለዘብ ቢልም፣ በአውሎ ንፋሱ የተጎዱ ሥፍራዎችን ለመድረስ የሚደረገው ጥረት ግን ፈተና ውስጥ ነው፡፡ ከባድ ጎርፍ ያስከተለው ሳይክሎን ኢዳይ የተባለው አውሎ ንፋስ መንገዶችን፣ ድልድዮችንና ቤቶችን አውድሟል፡፡ ከ200 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታታ ድርጅት እንደሚለውም፣ 1.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በሰዓት 124 ማይልስ ወይም 200 ኪሎ ሜትር ያህል በሚነፍሰው ከባድ አውሎ ንፋስና ባስከተለው ዝናብ ሳቢያ ተጎድተዋል፡፡

ጎርፉ የሞዛምቢኳን ቤይራ ያጥለቀለቀና ቤቶችንና ተሽከርካሪዎችን የዋጠ ሲሆን፣ የስልክና የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ተቋርጧል፡፡ ንፋሱ ወደ ምሥራቃዊ ዚምባቡዌ ያቀና ቢሆንም፣ የሞዛምቢኩን ያህል የከፋ አልነበረም፡፡ ሆኖም ናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ እንደ ሞዛምቢኩ የከፋ አደጋ ባይደርስም መሠረተ ልማቶችንና ቤቶችን አፈራርሷል፡፡ በምሥራቅ ዚምባቡዌ ከፍተኛ ሥፍራ የሚኖሩ ነዋሪዎችንም ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ አድርጓል፡፡

Betty ሞዛምቢክ ዚምባቡዌንና ማላዊን የመታው ‹‹ሳይክሎን ኢዳይ››
የአውሎ ንፋሱ ጫና በሚታይባት ደቡብ አፍሪካም ወንዞች በጎርፍ ሙላት ተጥለቅልቀዋል

 

ሳይክሎን ኢዳይ ከመከሰቱ አስቀድሞ በሞዛምቢክና ማላዊ በነበረው አውሎ ንፋስ 122 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል፡፡ የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ፊሊፕ ኒይሱ ሰኞ በሰጡት መግለጫ 84 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸው፣ ይህ ከባድ አውሎ ንፋስ ባስከተለው ውድመት በአጠቃላይ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡

የዚምባቡዌ ፓርላማ አባል ጆሽዋ ሳኮ በበኩላቸው፣ ባለሥልጣናት ስለሟቾች ቁጥርም ሆነ ስለደረሰው ውድመት በቂ መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የሞት መጠን አሁን ከሚነገረው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተንብየዋል፡፡

ትላልቅ መኪኖችንና ቤቶችን ጭምር ጠራርጎ ለመውሰድ አቅም ያለው ጎርፍ፣ በዚምባቡዌ ሩሲቱ በሚገኘው ኒያሆንዴ ወንዝ አቅራቢያም ተከስቷል፡፡

የጎርፉ ጫና ከዚምባቡዌ ድንበር 200 ማይልስ ርቆ በሚገኘው የአገሪቱ ዋና ከተማ ሃራሬ ድረስ መኖሩ የተዘገበ ሲሆን፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማናንጋጋዋም በተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ የነበራቸውን ጉብኝት አቋርጠው አደጋው በደረሰባቸው ሥፍራዎች የአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ አውጀዋል፡፡

የዚምባቡዌ ቀይ መስቀል ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ካሪኮጋ ኩትድዛውስ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ያለው አደጋ እጅግ የከፋ ነው ብለዋል፡፡

ዚምባቡዌ ባጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ላይ ይህ ችግር መከሰቱ፣ በልተው የሚያድሩትን ፆም አሳድሯል፡፡ ባለመጠለያዎቹን አውላላ ሜዳ ላይ አውጥቷል፡፡ የቀይ መስቀል ባለሥልጣናቱም፣ ከስፍራው ለተፈናቀሉት መጠለያ፣ ምግብ እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው አፋጣኝ ሕክምና ያስፈጋል ብለዋል፡፡

በዚምባቡዌ የሚገኙ የሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በጎርፉ ከሞቱት ይገኙበታል፡፡

አውሎ ንፋሱ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በጊዜያዊነት በከፍተኛ ሥፍራ፣ በትምህርት ቤቶችና በአብያተ ክርስቲያናት ተጠልለዋል፡፡ በምሥራቃዊ ዚምባቡዌ በምትገኘውና በአውሎ ንፋስ በአብዛኛው በምትመታው ቺማኒማኒ፣ አንድ ሆቴል ከ300 በላይ ሰዎችን ለማስጠለል ተገዷል፡፡

Betty ሞዛምቢክ ዚምባቡዌንና ማላዊን የመታው ‹‹ሳይክሎን ኢዳይ››
ሞዛምቢክ፣ ማላዊንና ዚምባቡዌን የመታው አውሎ ንፋስና የተከሰተው ከባድ ዝናብ የተለያዩ አካባቢዎችን በጉም እንዲሸፈኑ አድርጓል

በጎርፉ የተመቱትን ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት ድልድዮች በመፈራረሳቸውና ጎርፉም ባለማክተሙ የተነሳ ተደናቅፏል፡፡ እሑድ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. አውሎ ንፋሱና ዝናቡ ጋብ በማለቱ የዚምባቡዌ አየር ኃይል የተጎዱትን ከየሥፍራው ለማውጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን የአገሪቱ መገናኛ ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡

ሦስቱ አገሮች በከፋ ሁኔታ በአውሎ ነፋሱ ቢመቱም ደቡብ አፍሪካም የጫናው ሰለባ ሆናለች፡፡ ሳውዝ አፍሪካን ኒውስ እንደሚለው፣ የሞዛምቢክ፣ ዚምባቡዌንና ማላዊን አንዳንድ ክፍሎች የመታው አውሎ ንፋስና ከባድ ዝናብ ደቡብ አፍሪካ ላይም ጫና አሳድሯል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስቴር ሊንድዊ ሲሱሉ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለማላዊ፣ ዚምባቡዌና ሞዛምቢክ ተፈናቃዮች ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አውሎ ንፋሱ በሞዛምቢክ የኤሌክትሪክ ማቋረጡም የደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ክፍሎች በተዘዋዋሪ የኤሌክትሪክ አቀርቦት እንዳያገኙ አድርጓል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ በዚምባቡዌ የተከሰተውን ቀውስ ለማረጋጋትም ወታደሮቻቸውን ልከዋል፡፡

ድርቅ ፈተና በሆነባቸው አካባቢዎች ጎርፉ ተጨምሮ የደረሱ ሰብሎችን መጠራረጉም ለአገሮቹ ተጨማሪ ሥጋት ሆኗል፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ የመሬት መንሸራተትና የቤቶች መደርመስ አደጋ በገጠማት ዚምባቡዌ፣ የገበሬዎች እርሻዎች ወድመዋል፡፡

አውሎ ንፋሱ በፀናባት የቤይራ ከተማ 90 በመቶ ያህሉ የወደመ ሲሆን፣ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎችም አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ በሦስቱም አገሮችም በመቶዎች የሚቆጠሩ የገቡበት አልታወቀም፡፡