Skip to main content
x
በክር እና በመርፌ የተሠሩ ሥዕሎችን በዐውደ ርዕይ የማሳየት እክል

በክር እና በመርፌ የተሠሩ ሥዕሎችን በዐውደ ርዕይ የማሳየት እክል

ወይዘሮ ሳባ ፀሐዬ የሠዓሊ ንጉሤ ታፈሰ ባለቤት ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወደ 18 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ወ/ሮ ሳባ፣ ባለቤታቸው በሕይወት በነበሩበት ዘመን የሠሯቸውን ልዩ ልዩ ሥዕሎች በኤግዚቢሽን መልክ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሥዕሎቻቸው ከክር የተሠሩ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ልዩ ልዩ ዓይነት ቅርፃ ቅርፅ ናቸው፡፡ የባለቤታቸውን የሥዕልና የቅርፃ ቅርፅ ሥራዎችን በመጠበቅና በመንከባከብና በሥዕሎቹ ዙሪያ ወ/ሮ ሳባ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የባለቤትዎን የትምህርት ደረጃና የሥዕል ሥራ እንዴት እንደጀመሩ ቢያራሩልን?

ወ/ሮ ሳባ፡- ባለቤቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ አድምኒስትሬሽን አጥንቶ ለመመረቅ ሦስት ወራት ሲቀረው የአዕምሮ ሕመም አደረበት፡፡ በዚህም የተነሳ ቤት መዋል ጀመረ፡፡ ከሕመሙ ትንሽ ሻል ሲለው ሀርድ ቦርድ፣ ክርና መርፌ እንዲገዛለት ጠየቀ፡፡ የጠየቀው ሁሉ ተፈጸመለት፡፡ ከዛም ሀርድ ቦርዱ ላይ በክርና መርፌ 25 ልዩ ልዩ ዓይነት የሥዕል ሥራዎች ሠራ፡፡ ይህንንም ለማከናወን አምስት ዓመት ፈጀበት፡፡ ከሠራቸውም ሥዕሎች መካከል አምስቱ የክር ሥራዎች ኢትዮጵያን እንዳለ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከሥዕሎቹም መካከል የአርሲ፣ የትግራይ፣ የሀመር ሴቶች አለባበስን፣ እንዲሁም ዋሊያ፣ አጋዘን፣ ዓባይ ወንዝ፣ ላሊበላ የመሳሰሉትና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የትኛው የሥዕል ትምህርት ቤት ገብተው ነው በሥዕል ሥራ የሠለጠኑት?

ወ/ሮ ሳባ፡- የትኛውም የሥዕል ትምህርት ቤት አልገባም፡፡ በተፈጥሮ የታደለው ነው፡፡ ከወላጆቹም ሲወርድ ሲዋረድ ወይም ተያይዞ የመጣ አይደለም፡፡ የአዕምሮ ሕመም ሲገጥመው ትምህርቱን አቋርጦ ቤት ዋለ፡፡ ትንሽ ሻል ሲለው ድንገት ብድግ ብሎ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ጥያቄ አቀረበ፡፡ ጥያቄው ወዲያው ተመለሰለት፡፡ ከዛም በቀጥታ ወደ ሥዕል ሥራው ገባ፡፡ በዚህም የተነሳ ለሥዕል የሚያሳየው ፍቅር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ሥራውን በስፋት ተያያዘው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትዎን በሕይወት ዘመናቸው ከሠዓሊያን ጋር ግንኙነት ነበራቸው? ከነሱ ልምድና ተሞክሮ የቀሰሙት ነገር ይኖር ይሆን?

ወ/ሮ ሳባ፡- ከማንኞቹም ሠዓሊያን ጋር ተገናኝቶ አያውቅም፡፡ ከነሱም ተሞክሮና ልምድ የቀሰመው ነገር የለም፡፡ በአጠቃላይ ከሠዓሊያን ጋር መገናኘት አይፈልግም፡፡ ለዚህም ይሰጥ የነበረው ምክንያት ከሌሎች ሰዓልያን ጋር ከተገናኘሁ ውስጤ ያለው የሥዕል ችሎታ ይበላሽብኛል የሚል ነው፡፡ ሞት ቢቀድመውም፣ ምኞቱና ዓላማ ወጣቶችን ሰብስቦ በሥዕል በተለይም በክር በተደገፈ የሥዕል ሥራ ማሠልጠን ነበር፡፡ ይህንንም ሊያደርግ ያነሳሳው ሙያው እኔ ዘንድ ብቻ ተቀብሮ መኖር የለበትም፣ ለትውልድ ማስተላለፍ አለብኝ ከሚል አመለካከቱ በመነሳት ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ በኤግዚቢሽን ለሕዝብ የማቅረብ ምኞትም ነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤግዚቢሽን የማዘጋጀት ዓላማውን ከምን አደረሱት?  

ወ/ሮ ሳባ፡- በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በ1977 ዓ.ም. ኤግዚቢሽን አቀረበ፡፡ ይህንንም ኤግዚቢሽን ላይ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች እንዲሁም እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተመለከቱት ሲሆን፣ ሥዕሉን በተመለከተ የአድናቆት ፊርማቸውን አኑረውለታል፡፡ ከዚህም ሌላ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የዓደዋን ፊልም በ1989 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በኤግዚብሽን በቀረበበት ጊዜ የባለቤቴንም የሥዕል ሥራዎች አካትተዋል፡፡ ከዛም ወዲህ ግን የሚያነሳሳለትንና የሚያነቃቃለትን ያጣ የሥዕል ሥራ ሆኖ ቀረ፡፡

ሪፖርተር፡- የባለቤትዎ የአዕምሮ ችግር ምን ሆነመፍትሔ አግኝቶ ነበር?

ወ/ሮ ሳባ፡- የተጠቀሱትን የክር ሥዕሎች በመሥራት ላይ እያለ ከበሽታው ቀስ በቀስ እየዳነ መጣ፡፡ የሥዕሎቹን ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ተፈወሰ፡፡

ሪፖርተር፡- በአዕምሮ መታወክ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሥዕል ሥራ ሲገቡ በዚህ ቀጠሉበት ወይስ ሌላ ሥራ ያዙ?

ወ/ሮ ሳባ፡- የሥዕል ሥራውን ሳያቋርጥ ባህር ትራንስፖርት ተቀጥሮ ገባ፡፡ በሥራውም ላይ እያለ የምህንድስና ሙያ ተማረ፡፡ ይህ ዓይነቱም ሙያ የሥዕል ሥራውን በይበልጥ እንዲያዳብረው ከማድረጉም በላይ ሎጎ መሥራቱንም ተያያዘው፡፡ ኤርትራ ስትገነጠል ባህር ትራንስፖርትም ተዘጋ፡፡ በዚህም የተነሳ ቤት ውስጥ የሥዕሉን ሥራ አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ በተጨማሪም የመስተዋት ፍሬም መሥራት ጀመረ፡፡ ከውጭ አገር ከሚመጡት በስተቀር ባለቤቴ የሠራውን ዓይነት የመስተዋት ፍሬም እስከሁን ድረስ በአገር ውስጥ ተሠርቶ አላየሁም፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትዎ የሥዕል ሥራቸውን ቤት ውስጥ ባከናወኑ ቁጥር የእርሶ ድርሻ ምን ነበር?

ወ/ሮ ሳባ፡- ከጎኑ ቆሜ አማክረዋለሁ፡፡ ልዩ ልዩ የመገልገያ መሣሪያዎችን አዘጋጅለታለሁ፡፡ ቤት ዋልኩ ብሎ ተስፋ እንዳይቆርጥና እንዳይበሳጭ እንከባከበዋለሁ፡፡ የያዘው የሥዕል ሥራ በጣም ተፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን እየነገርኩት እንዲገፋበት የተለያዩ ኤግዚብሽኖች በማዘጋጀት ወደ ሕዝብ እንዲገባ የተቻለኝን ሁሉ በማድረግ አበረታታው ነበር፡፡ መተዳደሪያችን ባለቤቴ በሚሠራቸው ሥዕሎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እኔ ደግሞ አልባሳትና ዕቃዎች በመሸጥ ለኑሮአችን እንተጋገዝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከባለቤትዎ ስንት ልጅ አፍርተዋል?

ወ/ሮ ሳባ፡- ካረፈ 18 ዓመት ከስድስት ወር ሆኖታል፡፡ አንድ ልጅ አፍርተናል፡፡ ባለቤቴ ያረፈው የልጃችን ዕድሜ አራት ወር ከ15 ቀን ሲሆን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ልጁ የ19 ዓመት ወጣት ሆኗል፡፡ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ተፈታኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የባለቤትዎ የሥዕል ሥራዎች በአሁኑ ጊዜ የት ነው ያሉት? ኤግዚቢሽን አዘጋጅተው ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ሳባ፡- የሥዕል ሥራዎቹ በአሁኑ ጊዜ ያሉት በአንድ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ሥራዎቹን በኤግዚቢሽን ለማቅረብ ስፖንሰር እያፈላለኩ ነው፡፡ ብዙዎቹ መልሳቸው በጀት የለንም የሚል ነው፡፡ በተረፈ የባለቤቱ ሁሉም የሥዕል ሥራዎች በቅርቡ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ለሕዝብ ታይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ቴሌቪዥኑን ከተመለከቱት የኅብረተሰብ ክፍሎች ምን ዓይነት ግብረ መልስ አገኙ?

ወ/ሮ ሳባ፡- ሥዕሉን በጣም አድንቀዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የክር ሥራ መኖሩን አናውቅም፡፡ መቼና የት ነው በኤግዚብሽን የሚቀርበው እያሉ የጠየቁን ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ስፖንሰሮች በጀት የለንም ያሉትን ምክንያት እርስዎ እንዴት ያዩታል?

ወ/ሮ ሳባ፡- የጠየኳቸው ስፖንሰሮች ሁሉ የሰጡት መልስ እውነት ነው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ እኔ የማየው የሥዕሎቹን ባለቤት አያውቁትም፣ ሥራዎቹም ተደብቀው ቀርተዋል፣ አደባባይ አልወጡም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ስፖንሰሮች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ይገፋፋቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ ለሚታወቁ ሠዓሊያን ስፖንሰር ሲደረግላቸው በየጊዜው እናያለን፡፡ ሄንከን ዋሊያ ቢራ ስፖንሰር ጠይቂያቸው ነበር፡፡ እነሱም ፕሮፖዛልሽን አቅርቢ ብለውኛል፡፡ በተስፋ እየተጠባበኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በአሁኑ ጊዜ በእጅዎ ያሉት የሥዕል ሥራዎች ስንት ናቸው? ወደፊትስ ምን ሊያደርጓቸው አስበዋል?

ወ/ሮ ሳባ፡- በክርና በመርፌ ከተሠሩት 25 ሥዕሎች መካከል ሁለቱ ሲሰረቁ 23 ቀርተዋል፡፡ የቅርፃ ቅርፅና የመስታወት ፍሬምን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 50 ይጠጋሉ፡፡ በኤግዚቢሽን ላይ አቀርብና ቡዙዎቹን ለሽያጭ፣ የቀሩትን ጥቂት ሥራዎች ደግሞ ለመታሰቢያነት በሙዚየም እንዲቀመጡ አደርጋለሁ የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ከሽያጩ በሚገኘው ገቢ ልጁ ትምህርቱን ዳር እንዲያደርስ እናደርግበታለን፡፡

ሪፖርተር፡-የባለቤትዎን የሥዕል ሥራዎችን በተመለከተ የሚፈልጉትን እገዛና ትብብር እንዲያገኙ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጥያቄ አቅርበዋል?

ወ/ሮ ሳባ፡- እስካሁን አላሳውኩም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን እገዛና ትብብር እንዲደረግልኝ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አልልም፡፡