Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ከውጭ ከመጣ ተመራማሪ ጋር ስብሰባ ላይ ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አላወኩህም ማን ልበል?
 • በውጭ አገር የምኖር ተመራማሪ ነኝ፡፡
 • ምን ላይ ነው የምትመራመረው?
 • የፖለቲካ ተመራማሪ ነኝ፡፡
 • እ . . .
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላይ ነሃ፡፡
 • ኧረ በፍጹም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነህ?
 • እኔ በውጭ አገር ያለ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነኝ፡፡
 • ምን ልታደርግ መጣህ ታዲያ?
 • የመንግሥትን ጥሪ ተቀብዬ ነዋ፡፡
 • የምን ጥሪ?
 • ኢትዮጵያውያን አገራችሁ ገብታችሁ አገልግሉ ብላችሁ አልነበር እንዴ?
 • እሱስ ብለናል፡፡
 • ስለዚህ እኔም የአቅሜን ላበረክት ነበር የመጣሁት፡፡
 • አገሪቱን እንዴት አገኘሃት ታዲያ?
 • እሱን እንኳን ይተውት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • አሁን ልመለስ ነው፡፡
 • እንዴ ለምን?
 • አገሪቱ እኮ አስፈሪ ሁኔታ ላይ ናት፡፡
 • ምን ሆነች?
 • መቼም ይኼ ይጠፋዎታል ብዬ አላስብም፡፡
 • ምኑ ነው የሚጠፋኝ?
 • አገሪቱ ምን ያህል አስፈሪ ሁኔታ ላይ እንዳለች ነዋ፡፡
 • ለውጥ ላይ እኮ ሁሌም መንገራገጭ ያለ ነው፡፡
 • የምን ለውጥ?
 • አሃ አንተ ከለውጡ አደናቃፊዎች ጋር ነው የተሠለፍከው ማለት ነው?
 • የሚገርመው አሁንም የመፈረጅ ፖለቲካ እንደቀጠለ ነው፡፡
 • ታዲያ ለውጥ የለም እያልክ ነው?
 • ለውጥማ አለ፡፡
 • ታዲያ የምን ለውጥ የምትለኝ ለምንድነው?
 • የጠበቅነው ለውጥ ስለሌለ ነዋ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የዘር ፖለቲካ እኮ ከድሮው ብሶበታል፡፡
 • ምን እናድርግ ታዲያ?
 • ይኸው ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ በዘራቸው ምክንያት ብቻ እየተፈናቀሉ ነው፡፡
 • ያው ይኼ እኮ የለውጡ አካል ነው፡፡
 • በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶች በየጊዜው እየጨመሩ ነው፡፡
 • የለውጡ አደናቃፊዎች ሴራ ነዋ፡፡
 • አሁን ጣት መቀሰር ያቁሙ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሁሉንም ነገር ታዲያ መንግሥት ላይ ለምን ይደፈደፋል?
 • አገር የማስተዳደር ሥራ እኮ የመንግሥት መስሎኝ?
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ስለዚህ ሥርዓተ አልበኝነት በአገሪቱ ሲሰፍን ከመንግሥት ውጪ ማን ይጠየቃል?
 • ቢሆንም ሕዝቡ ካልተባበረን ብቻችን እንዴት እንችላለን?
 • ለማንኛውም እኔ ልመለስ ነው፡፡
 • አንተም እኮ ኃላፊነት አለብህ፡፡
 • እኔ ኃላፊነቴን የምወጣው እናንተም ኃላፊነታችሁን መወጣት ስትችሉ ነው፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን እናድርግ?
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ሥራውን እየሠራ አይደለም፡፡
 • ምን?
 • እንዲያውም አሁን መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ያውቃሉ?
 • ምንድነው የሚሠራው?
 • ጠብ ሲል ስደፍን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ባለሀብት ስልክ ይደውላሉ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ወዳጄ፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው?
 • ይኸው ተወጥረናል፡፡
 • እኛን አላልታችሁ ነዋ እናንተ የተወጠራችሁት፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሌም እነግርዎት ነበር እኮ፡፡
 • ምንድነው የምትነግረኝ?
 • ፖለቲካው ያለ ኢኮኖሚው ዋጋ የለውም፡፡
 • ታዲያ ኢኮኖሚው ምን ሆነ?
 • ክቡር ሚኒስትር ኢኮኖሚው የት አለ?
 • አልገባኝም?
 • አሁን እኮ በአውቶ ፓይለት ነው እየሄድን ያለነው፡፡
 • እ . . .
 • እንዳንከሰከስ መፍራት ነው፡፡
 • ኧረ ተው አታሟርት፡፡
 • ለመሆኑ ምን እያሰባችሁ ነው?
 • ስለምኑ?
 • ስለኢኮኖሚው ነዋ፡፡
 • የለውጡ ጠላቶች የኢኮኖሚውን ዋልታ መያዛቸውን አትርሳው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን ጣት መጠቋቆም የትም አያደርሰንም፡፡
 • ስማ ለውጥ የሚያደናቅፉ አይጠፉምና መረጋጋት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ስለምን ለውጥ ነው የሚያወሩት?
 • የለውጡ አደናቃፊዎች ጠልፈውህ ይሆናል ብዬ በፊትም ጠርጥሬ ነበር፡፡
 • ኧረ እኔ ማንም አይጠልፈኝም፡፡
 • ለምንድነው በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ ያልመጣኸው?
 • የፕሮግራሙን ዓላማ እንዳልጣረስ ብዬ ነዋ፡፡
 • ለምን ትጣረሳለህ?
 • የጠራችሁን እኮ ገንዘብ እንድናዋጣ ነው፡፡
 • ታዲያ ለምን መጥተህ አላዋጣህም?
 • ከየት ክቡር ሚኒስትር?
 • እ. . .
 • ሰው እኮ ሥራ ስለቀዘቀበት ከሠራተኞቹ ጉሮሮ ላይ እየነጠቀ ነው የሚያዋጣው፡፡
 • እየተዋወቅን አንተናነቅ አለ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የእኛ አገር ነጋዴ ደግሞ እስከ ዛሬ ያተረፈውን እንኳን ተጠቅሞበት በትኖት ይጨርሰዋል እንዴ?
 • የሌላውን ባላውቅም እኔ ለፍቼ ነው የማገኘው፡፡
 • ስማ ሕዝቡን እያማረራችሁ ያካበታችሁትን ሀብት አሁን ሕዝቡ ሲጠይቃችሁ ፊታችሁን ታዞራላችሁ፡፡
 • እኔ የምለው ምን ነግደን እንስጣችሁ?
 • የእስከ ዛሬውን አውጡት፡፡
 • ከዚያ ባዷችንን እንቅር?
 • አንተ የሚነገርህ አይገባህም እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር እናንተም ሥራችሁን ሥሩ እንጂ፡፡
 • ምን እናድርግ?
 • ኢኮኖሚውን አንቀሳቅሱት፣ ፓራላይዝድ ሊሆን ነው፡፡
 • መንግሥት እኮ አዲስ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ሊያስተዋውቅ ነው፡፡
 • እሱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ሕዝቡ አውቆታል፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የመዋጮ ኢኮኖሚ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር መኪና ውስጥ እያወሩ ነው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ፊትዎ ጠቋቁሯል፡፡
 • እንዴት አይጠቋቁር?
 • አዲስ ነገር አለ እንዴ?
 • ሁሉ ነገር ያስጨንቃል፡፡
 • ይገባኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንዱን ስትለው አንዱ ይከተላል፡፡
 • አገር መምራት ከባድ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያለ ዕድሜዬ በሽታ አሸከመኝ እኮ፡፡
 • ምንድነው የሚደረገው?
 • እኛም ግራ ገብቶናል፡፡
 • ብዙ ሰው እኮ ተስፋ ቆርጧል፡፡
 • ለምን?
 • በለውጡ በጣም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡
 • አሁንስ?
 • አሁንማ ለውጡ ተጠልፏል እየተባለ ነው፡፡
 • ማን ነው ግን የጠለፈው?
 • የሕዝቡም ጥያቄ እሱ ነው፡፡
 • ወይ ያለብን ጣጣ፡፡
 • አገሪቱ ተስፋ አላት ግን ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛማ ተስፋ አለን እያልን ነው፡፡
 • በየቀኑ የሚሰማው ወሬ እኮ ዘግናኝ ነው፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር ረሃብ የድሮ ታሪካችን ነው ብለን ሳንጨርስ ይኸው በርካቶች ተርበዋል፡፡
 • እስኪ ተው፡፡
 • መፈናቀሉ አሁንም አለ፡፡
 • ምን ይደረግ ብለህ ነው?
 • ከሁሉም አስፈሪው ደግሞ የኢኮኖሚው ጉዳይ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ሁሉም ነገር ተቀዛቅዟል፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡
 • ታዲያ እንዴት ይፈታ?
 • ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ ሲጨንቀኝ መኪና መንዳት ያረጋጋኛል፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው?
 • በቃ እኔ ልንዳ፡፡
 • ኧረ አይሆንም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • ፕሮቶኮል የሚባል ነገር አለ፡፡
 • ይኸው አለቃችን ሁሌ መሪዎችን የሚያሽከረክሩት እሳቸው አይደሉ እንዴ?
 • ትክክል አይደለም ክቡር ሚኒስትር ፕሮቶኮል መጠበቅ አለበት፡፡
 • እኔ እንዳየሁት ግን መሪዎቹ በጣም ነው ደስ የሚላቸው፡፡
 • ስለፕሮቶኮል መቼም ለእርስዎ አልነግርዎትም፡፡
 • ማካበድ አያስፈልግም እባክህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኸው አለቃችሁ መኪና እያሽከረከሩ ፕሮቶኮል ስለማይጠብቁ፣ ሌላ አገር ሲሄዱ ለእሳቸውም ፕሮቶኮል አይጠበቅላቸውም፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው በቅርቡ ሰሞኑን ማን እንደተቀበላቸው አላዩም፡፡
 • ማን ተቀበላቸው?
 • የትራንስፖርት ሚኒስትር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እግዚአብሔር ይይላችሁ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው እሳት ላይ አስቀምጣችሁን ሄዳችሁ፡፡
 • እኛም እኮ ነግረናችሁ ነበር፡፡
 • ምኑን?
 • አገር መምራት እንዲህ ቀላል እንዳልሆነ፡፡
 • እናንተ ያጠፋችሁትን እያረምን እኮ ነው የተቸገርነው፡፡
 • እንዴት ነው ማረም ታዲያ?
 • የጊዜ ጉዳይ እንጂ መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡
 • አለቃችሁን ግን ይኼ ሁሉ የቤት ሥራ ትተው ውጭ መሽከርከራቸው ምንድነው?
 • የእናንተን ስህተት ለማረም ነዋ፡፡
 • ቢሆንም ሁሉ ነገር ከውስጥ መጀመር ይሻላል፡፡
 • እንዴት?
 • ተለውጠናል እያላችሁ አይደል እንዴ?
 • ግጥም አድርገን ነዋ የተለወጥነው፡፡
 • ስለዚህ ወደ ውጭ ከማየት ወደ ውስጥ መመልከቱ ይበጃል፡፡
 • አሁን እናንተም ለምክር በቃችሁ?
 • ለማንኛውም ሰሞኑን አለቃችሁ የውጭ ጉዞ ስላበዙ ሥልጠናቸው ተቀየረ ወይ ለማለት ነው?
 • ወደ ምንድነው የሚቀየረው?
 • ሳናውቅ ሾማችኋቸው እንዴ?
 • ምን አድርገን?
 • በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ . . .
 • እ. . .
 • የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር!