Skip to main content
x
‹‹የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣው መልካም ዕድል ነው›› አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

‹‹የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣው መልካም ዕድል ነው›› አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት የተጀመረውን እንቅስቃሴ በመደገፍ 49 አገሮች ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ የአፍሪካን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ለማጠናከርና የጠነከረ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲረዳ ታስቦ አገሮቹ የፈረሙት፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ለመመሥረት ፈቃደኝነታቸውን ካሳዩ አገሮች ሃያ ሁለት የሚሆኑት፣ በየአገራቸው ባሉ ከፍተኛ ሕግ አውጪ አካላት ካፀደቁ የአፍሪካ ነፃ ገበያ እንደሚመሠረት ይጠበቃል፡፡ ገበያው እንዲፈጠር ይሁንታ ከሰጡት 49 አገሮች ውስጥ እስካሁን 21 አገሮች በየአገሮቻቸው ሕግ አውጪ አካል ገበያው እንዲፈጠር አፅድቀዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ስምምነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. አፅድቃ የሕግ አካል አድርጋዋለች፡፡ ይህ የንግድ ቀጣና ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል በሚለው ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል ስትሆን በነፃ ገበያ የሚደረገውን ውድድር እንዴት ትቋቋማለች የሚለው ጥያቄ በዋናነት ይነሳል፡፡ ከዚህ ስምምነት ጋር በተያያዘ ጥቅል አንድምታውንና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል በሚለው ጉዳይ ላይ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለመፍጠር እንደ መነሻ የተወሰደው ምንድነው? ግቡስ? 

አቶ እንዳልካቸው፡- የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት የሚያስችለው ሐሳብ ጎልቶ የወጣው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት በሚቀየርበት ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ አጀንዳ 2063 የሚባል በሚቀጥሉት 50 ዓመታት አፍሪካ የምትጓዝበትን ፍኖተ ካርታ ዲዛይን በማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በኋላ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ተሰባስበው ነው የተወያዩበት፡፡ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. በ2012 በዚያን ጊዜ አፍሪካውያን ገበያችንን ለምን አናቀላቅልም በሚል ተነስቶ የተጀመረ ነው፡፡ አፍሪካውያን አንድ ነፃ የንግድ ቀጣና እንፍጠር በሚል ይስማማሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በ2015 ድርድር ይጀምራሉ፡፡ ከድርድሩ በኋላ በማርች 2018 በኪጋሊ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ለመጣል የሚያስችል ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ ይህ ትልቅ ስምምነት ነበር፡፡ የዚህ ቀጣና መፈጠር የአፍሪካን 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ገበያ በአንድ ላይ ብናመጣው፣ ለአፍሪካ የዕድገት መልካም ዕድል ይፍጥርላታል በሚል ነው፡፡ አፍሪካ የሌሎች ሸቀጥ ማራገፊያ ከምትሆን የራሷን ገበያ ፈጥራ መጠቀም እንደምትችል ታምኖ የተገባበት ነው፡፡ የራሷን ገበያ ለመፍጠር ደግሞ እርስ በርሳችን ስንነግድ ጭምር ነው በማለት፣ ወደዚህ እንዲገባ ለማድረግ የተቀረፀም ጭምር ነው፡፡ እርስ በርሳችን ስንሠራና እኛ ያመረትነውን ስንጠቀም ነው እንደ አውሮፓ ማደግ የምንችለው በሚልም ነው፣ የአፍሪካ መሪዎች የተስማሙትና ገበያውን ለመፍጠር ወደሚያስችል ሒደት የገቡት፡፡

ሪፖርተር፡- የኪጋሊው ስምምነት ሲፈረም እርስዎም በቦታው ነበሩና እስቲ የስምምነቱ ይዘትና እየተከናወነ የነበረውን ሥራ ቢገልጹልኝ? እንዴትስ ነው ተግባራዊ የሚሆነው? 

አቶ እንዳልካቸው፡- ኪጋሊ ላይ በነበረው ስብሰባ 44 የአፍሪካ አገሮች ገበያውን ለመፍጠር ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡ ሦስት ሰነዶች ነበሩ፡፡ ሁሉንም ባይሆን ሁሉም አንድ ሰነድ ፈረሙ ማለት ነው፡፡ እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገሮች ይህንን ሰነድ ሳይፈርሙ ቀሩ፡፡ ያልፈረሙበት ምክንያት በደንብ መወያየት አለብን በሚል ነው፡፡ እንዲያውም ጥሩ ያልሆነ ስም ነው የሰጡት፡፡ ገበያችንን ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ውስጥ ማስገባት ነው የሚል ነው፡፡ ጠንከር ብለው ነበር፡፡ ለማንኛውም አሁን አፍሪካ ውስጥ 55 አገሮች አሉ፡፡ 44ቱ ኪጋሊ ላይ መፈረማቸው በአፍሪካ ታሪክ ያልታየ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እየተንጠባጠቡ 44 የነበሩት አገሮች ወደ 49 ደረሱ፡፡ በኪጋሊው ስምምነት መሠረት ወደ አገሮቻቸው ተተመልሰው በከፍተኛ ሕግ አውጪ አካል (ኢትዮጵያ እንዳደረገችው ማለት ነው) አገሮች አፀደቁት፡፡ ሃያ ሁለት አገሮች በከፍተኛ ሕግ አውጪ አካል ሲያፀድቁት ወደ ሥራ ይገባል የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ስለነበር ወደዚያ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ አንደኛው ይኼ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 21ኛ ሆና አፀደቀች፡፡ በከፍተኛ የሕግ አካል የሚያፀድቁ አገሮች 22 ካልሞሉ ወደ ሥራ አይገባም፡፡ ሼልፍ ላይ ይቀመጥና ድርድሮቹ ይቀጥላሉ፡፡ ለምሳሌ መቀመጫው የት ይሆን የሚለውና ወደ ትግበራ ሊያስገቡ የሚችሉ አንዳንድ ውሳኔዎች መተላለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ ግን ወደ ሥራ ለመግባት አገሮቹ ይገበያዩባቸዋል የተባሉ አምስት ዘርፎች የተለዩ በመሆኑ፣ እነዚህን የተለዩትን የቢዝነስ ዘርፎች ለማስጀመር መሟላት ያለበት ነገር እንዲሟላ ይደረጋል፡፡ አሁን ያለው ሒደት ይህ ነው፡፡ ቀጣይ ሥራዎች አሉት፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ስምምነት የራስዋ የሕግ አካል አድርጋ አፅድቃለች፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ስምምነት መሠረት ወደ ሥራ የሚገቡባቸው የቢዝነስ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው? 

አቶ እንዳልካቸው፡- ለምሳሌ የባንክ ዘርፍ አለ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ስምምነቱን ባፀደቀችበት ሕግ ውስጥ ይህ ተጠቅሷል፡፡ ትራንስፖርት፣ ቴሌኮምና ሆቴል ዘርፍ እዚህ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ የእነዚህን አፈጻጸሞች ደግሞ የተለየ የሚያደርገው ነገር አለ፡፡ ይህም በቀጥታ ተግባራዊ የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን እየሠራህ ባለህበት ታሪፍ መሠረት ነው ተግባራዊ የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሚደረግ ድርድር ባውንደሪ ሬት የሚባል ነገር አለ፡፡ አሁን እያስከፈልክ ያለውን ታሪፍ እስከዚህ ድረስ መውሰድ ትችላለህ ተብሎ ከፍተኛ ጣሪያውን ነው የምታስቀምጠው፡፡ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ስትደራደር ግን አሁን ባለው ታሪፍ ነው፡፡ አፈጻጸሙ እንዴት ይሄዳል? እንዴትና የት አገር ይፋ ይደረጋል? የሚሉት ነገሮች ሁሉ አካቶ በዝርዝር ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት ውስጥ መግባቷ የሚያስገኝላት ጠቀሜታ እንዴት ታይቷል? በዚህ ስምምነት ውስጥ መግባት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክፍተቶች የሉም?

አቶ እንዳልካቸው፡- ትልቁ ነገር እሱ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የሚባለው የገበያ ጉዳይ ነው፡፡ ገበያን የሚያቀላጥፍ ነው፡፡ ለምርቶችህና ለአገልግሎቶችህ ገበያ ማመቻቸት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ፋብሪካ ከፍተህ ስትሠራ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ገበያ ታሳቢ አድርገህ ትሠራለህ፡፡ በዚህ ነፃ ገበያ ስምምነት መሠረት ግን 110 ሚሊዮን የነበረውን የገበያ ዕድል ወደ 1.2 ቢሊዮን ከፍ ያደርግልሃል፡፡ ስለዚህ ገበያን ማስፋት በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ ያሉ አገሮች በመካከላቸው ያሉትን የገበያ መሰናክሎች መነቃቀልና ማስወገድ ማለት ነው፡፡ ከየትኛው የአፍሪካ አገር ወደ የትኛውም የአፍሪካ አገር የሚሄዱ ምርቶች በቀላሉ የሚንቀሳቀሱበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ ዋናው ዓላማ ገበያውን ማመቻቸት ነው፡፡ ወደኋላ ስንመጣ ግን አፍሪካ ምንድነው የሚያስፈልጋት? የአፍሪካን ዋና ጉዳይ ስታይ አፍሪካ የኢንዲስትራላይዜሽን ትልቅ ጥያቄ አለባት፡፡ ሥራ አጦችን ሥራ የማስያዝ የቤት ሥራ አለባት፡፡ ነገሩን ስታየው ደግሞ ጥሬ ዕቃ እየላከች ያለችው አፍሪካ፣ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ዕቃ በዝቅተኛ ዋጋ ለሌላ የምትሸጥ ነች፡፡ አሁን ለኢንዱስትሪላይዜሽን የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ምንድናቸው? አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ስንሄድ የኢንዱስትሪ ጂዲፒ እየቀነሰ መሆኑን እናያለን፡፡ ከአንዳንዶቹ ደግሞ ኢንዱስትራላይዜሽን ላይ የተጠናከረ ሥራ የሚሠሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጠቅላላ የሸቀጥ ማራገፊያ ሆነዋል፡፡ እጃቸው ላይ ያለውን ጥረት ብዙ ሳያጠናክሩ ነዳጅና ጥሬ ዕቃ እየሸጡ የሸቀጥ ማራገፊያ መሆናቸውን ታያለህ፡፡

      ስለዚህ የአፍሪካ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ግብዓት ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ አንደኛው ገበያ ነው፡፡ አንተ ገበያ ገንብተህ አምርተህ ለመሸጥ ስትነሳ ገበያ ትልቅ ማነቃቂያ ነው፡፡ አሁን የንግድ ቀጣናውን ስታየው እኛ ያመረትነውን ለአፍሪካ ገበያ ማቅረብ ካልቻልን፣ ይህንን የተከፋፈተና የተመቻቸ ገበያ ለሌሎች ከፍተኛ አምራቾች ማራገፊያ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ከቻይና በሚመጣ አንድ ምርት ላይ ኢትዮጵያ 30 ወይም 35 በመቶ ታሪፍ ብታስከፍል፣ ኬንያ ደግሞ 20 በመቶ ብታስከፍል የኬንያና የኢትዮጵያ ድንበሮች ተከፍተው ነፃ የንግድ ቀጣና ሲፈጠር የቻይናው ምርት 35 በመቶ ከፍሎ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባት፣ 20 በመቶ ታሪፍ በመክፈል ኬንያ ገብቶ ወደ ኢትዮጵያ በነፃ የመግባት ዕድል አለው፡፡ ይኼ ‹‹ሩትስ ኦፍ ኦሪጅን›› በሚባለው ድርድር ውስጥ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት የሚታይ ነው፡፡ ያ ነገር የት ነው የተመረተው? በእርግጥ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ያለው ምርት የኬንያ ምርት ነው ወይ? በእርግጥስ የአፍሪካ ምርት ነው ወይ? የሚለውን በተጠናከረ ሲስተም የማጣራት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የሚጠበቅ ሥራ የኢትዮጵያን ጉዳይ በተለይ ስታይ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓመት ከ17 እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር ኢምፖርት ታደርጋለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ከአፍሪካ አገሮች ኢምፖርት የምታደርገው 4.1 በመቶ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ አፍሪካ ብዙ ኢምፖርት የምታደርገው ነገር የለም፡፡ ከወጪ ንግድ አንፃርም ሲታይ ደግሞ የኢትዮጵያ ዓመታዊ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ አካባቢ የሚሆነው ወደ አፍሪካ አገሮች ከምትልከው የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርታችን ከፍተኛ፣ ኢምፖርታችን ደግሞ ዝቅተኛ በመሆኑ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል በመሆናችን ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ እንዳልካቸው፡- ገበያው ያስፈልገናል፡፡ የምናስገባውም ብዙ ስላልሆነ ይህን ሚዛን አስጠብቀን እንድንሄድ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የዚህ ቀጣና አባል በመሆናችን ተጠቃሚ ሊያደርገን የሚችለው ገበያውን ያሰፋልናል፡፡ እንደገናም ከአፍሪካ የምናስገባውም ብዙ ስላልሆነ ተጠቃሚ የምንሆንበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡ በሌላ በኩል ስታየው ደግሞ በእኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተከናወነ ያለ ሥራ አለ፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ፓርኮች ታሳቢ የሚደረግ ነገር አለ፡፡ በእርግጥ እያሰብነው ብዙ አልተሳካልንም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ጂዲፒው ከስድስት በመቶ አልዘለለም፡፡ ይኼ ማለት በጣም በፍጥነት ለሚያድግ ኢኮኖሚ ቢያንስ ከኢንዱስትሪው 20 በመቶ ማምጣት ካልቻልክ የምትፈልገው ደረጃ ላይ ላትደርስ ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም የገቢ ንግድ ሕግን ማመጣጠን አያስችልህም፡፡ ይህም አሁን አገሪቱ ውስጥ የምናየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ በጥቅሉ ግን በኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንጉን ለማሳደግ አሁን እየወሰድናቸው ያሉ ዕርምጃዎች በአንፃራዊነት ሲታዩ ተቃሚ ያደርጉናል፡፡ ውድድራችን አሁን ከጎረቤት አገሮች ጋር ስለሆነ እንጂ በማኑፋክቸሪንግ ጡንቻቸው ከፈረጠመ የእስያ አገሮች ጋር ቢሆን ኖሮ ውኃ ላይቋጥር ይችላል፡፡ እኛ ዝቅተኛ ሆኖ ነው ማደግ ያለበት እንላለን፡፡ በአፍሪካ አገሮች ደረጃ ስናይ ደግሞ አበረታች ነው ብለህ የምትወስደው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህም ቢሆን ግን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ በቂ ተወዳዳሪ ትሆናለች ብሎ ማሰቡ አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ ለምሳሌ የአንዳንድ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሲታይ ከኢትዮጵያ የተሻለ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝቷ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የተጠጋ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያን እጥፍ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲህ ያለው መረጃ ሲታይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሲተገበር እንዴት ብቁ ተወዳዳሪ መሆን ይቻላል? እንዴት ተጠቃሚ መሆን ይቻላል? በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ስምምነት የሚያሳጣው ነገር አለ ይባላል፡፡

አቶ እንዳልካቸው፡- አዎ ልክ ነው፡፡ አሁን ልንከፍታቸው ያሰብናቸው አገልግሎቶች ናቸው፡፡ እንደ ትራንስፖርትና የፋይናንስ ዘርፎችን ነው ለመክፈት የሚታሰበው፡፡ ከዚህ አንፃር አንተ የጠቀስካቸው አገሮች በእነዚህ ዘርፎች ፈርጠም ያሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኬንያ በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ነው ያላት፡፡ በመጠን በልጠናታል፡፡ የኬንያ ግን ጠንካራ ነው፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ነጥብ ይኼ ነፃ የንግድ ስምምነት ጽንሰ ሐሳብ መንግሥታትን የሚያሳጣቸው ገንዘብ ነው፡፡ ምክንያቱም ታሪፍ ነው የሚያነሱት፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው እርስ በርሱ ሲዳቀልና እርስ በርሱ መሥራት ሲጀምር የፈጠራ ውድድር ስላለ፣ በዚያ ውድድር የሚገኘው ነፃ ገበያ ሲፈጠር ሊያጡ ከሚችሉት በላይ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ እንዳልካቸው፡- የእኛ የፋይናንስ ተቋማት የሚቀሩባቸው አገልግሎቶች ጥራትና ዓይነቶቹ አሉ፡፡ አፍሪካ በቀል ባንኮች ገብተው ከእነዚህ ጋር ሲወዳደሩ ኢኮኖሚው የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት ያቀርባል፡፡ ይኼ የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት ደግሞ ኢኮኖሚ ውስጥ የሀብት ፈጠራን በተጠናከረ መንገድ ያሳድጋል ብሎ አንክታድ በጥናት ያስቀመጠውን ነገር በምሳሌ ማቅረብ ይችላል፡፡ በአንክታድ ጥናት ይህንን ነፃ የንግድ ቀጣና በመተግበራቸው በዓመት በአማካይ አራት ቢሊዮን ዶላር ያጣሉ፡፡ ነገር ግን በሌላ መንገድ 16 ቢሊዮን ዶላር ያስገኝላቸዋል፡፡ ይኼ ጉዳይ አሁን ካነሳኸው ጥያቄ ጋር ይሄዳል፡፡ የወዲያውኑ ውጤቱ ጠንካራ ኩባንያዎች መጥተው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ኩባንያዎች ሊፈትኑዋቸውና አንዳንዶቹም ተፈጥሯዊ ሞት ይሞታሉ፡፡ ነገር ግን አገልግሎት ወደ ኢኮኖሚው በመምጣቱ እየተባዛና ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ጥቅም ያመጣል ነው፡፡ ብቃቱ ይጨምራል፡፡ ውድድር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ያ ሲሆን ደግሞ እነዚህ ፈራሚ አገሮች ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ያገኛሉ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የአሁኑን ብቻ አትዩ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ያ ነገር በመምጣቱ እናንተ ጋ የሚከስሙ ነገሮች ቢኖሩም፣ ኢኮኖሚው ግን የተሻለ ይሆናል ነው የሚባለው፡፡ የእኛም እዚያ ሄደው የሚከፍቱት ይኖራል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ይኼን ገበያ ሰዎች አጋንነው በተለያየ መንገድ ችግሮችን ሁሉ የሚፈታ አድርገው የሚገልጹ ሰዎች አሉ፡፡ ወይም ደግሞ አሁን ያለው ችግር ላይ ሌላ ራስ ምታት የሚጨምርና የአፍሪካ ኩባንያዎች መጥተው የእኛን ኩባንያዎች በአንድ ምሽት ውጠው የሚያስቀምጧቸው ያደርጓቸዋል፡፡ ሁለቱም ግን ፅንፍ የረገጠ አመለካከት ነው፡፡ ይኼ የገበያ ማመቻቸት ነው፡፡ ትልቅ ገበያ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ መጥቶ ሲያከፋፍል የነበረ አንድ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ወደ ስድስት ሚሊዮን ገበያ ሊኖረው ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የነበረውን ገበያ ወደ ክልሎችም ወስዶ ከሠራ ትልቅ ገበያ ተፈጠረለት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት ከዚህ የዘለለ ነገር የለውም፡፡ ገበያ ነው የሚፈጥረው፡፡ በማምረት አቅም ራሳችንን ካላጠናከርን ምንም ጥቅም የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያ መፈረሟ ሊያስገኝም ሆነ ሊያሳጣ የሚችለው ነገር እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ በተባለው መሠረት በነፃ ግብይቱ ብቂ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በንግዱ ኅብረተሰብ በኩል ያለው ዝግጁነት ምን ያህል ነው? እንዲህ ላለው ውድድርስ እንዲዘጋጅ ምን እየተደረገ ነው? ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የኮሜሳ አባል በመሆን ለመተግበር የተሞከረው ነገር አልሰመረም፡፡ በኮሜሳ ውስጥ ተሳታፊ ሆኖ ለመሆን ዋናው ችግር የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ከሙሉ አፍሪካ አገሮች ጋር መወዳደርን የሚጠይቅ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በምን ሁኔታ ተወዳድረው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠራት ያለበት ነገር የለም? የእናንተስ ሚና ምንድነው?

አቶ እንዳልካቸው፡- መረጃ መስጠት የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እየሞካከርን ያለነው ነገር አለ፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ በእኛ አገር ዓውድ ሰፋ ያለ ጥናት አስጠንተን በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ግቡም የእኛን የቢዝነስ ኅብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የንግድ ኅብረተሰቡ መንቃቃት ያለበትና በቢዝነሱ ዙሪያ ማሰብ እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የኬንያ ኩባንያዎች በራሳቸው ወጪ ወጥተው እያዩ ነው፡፡ በምን ዓይነት መንገድ መጠቀም እንዳልባቸው ቀደም ብለው መረጃ ለመያዝ እየሠሩ ነው፡፡ አንዳንድ የኬንያ ኩባንያዎችም የኢትዮጵያን ገበያ ታሳቢ አድርገው ለመሥራት በራሳቸው መንገድ ጥናት እያደረጉ መሆን እያየን ነው፡፡ የእኛም የቢዝነስ ኅብረተሰብ እንዲህ ወዳለው ነገር መግባት እንዳለበት  ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የበለጠ እየሠራ ያለው መንግሥት ነው፡፡ ነገር ግን የንግዱ ኅብረተሰብ ደግሞ ዛሬ ከሚሠራው የዕለት ተዕለት ቢዝነሱ ተነስቶ ጎረቤት አገሮች ሄጄ ምርትና አገልግሎቴን ለማቅረብ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ ብሎ ማሰብ ያለበት ከዛሬ ጀምሮ ነው፡፡ መረጃ በማቅረብና በተያያዘ ጉዳይ በእኛ በኩል እየሞካከርን ያለው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ እኛ የምንሠራው ሥራ አንዱ ይህ ነው፡፡ ሌላው እንግዲህ የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ አቅም እንግዲህ በተለያየ መንገድ የሚፈጠር ነው፡፡ የፋይናንስ አቅም አለ፡፡ የአስተዳደራዊ ወይም የአመራር ብቃት አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሒደት የሚመጡ ቢሆንም፣ የእኛ የንግድ ኅብረተሰብ ለዓለም አቀፍ ገበያዎችና ኢንዱስትሪዎች ቅርብ የሚሆንበትን ነገር በተለያየ መንገድ እንዲያገኝ ጥረት ያደርጋል፡፡ ያለውን ብቃት ለማሳደግ በተለያዩ መንገዶች በሥልጠናና በመሳሰሉት እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ የመደራደር አቅሙን ለማሳደግ የምንሞካክራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ነገሩ ሰፊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአፍሪካ ውጪ የሆኑ ኩባንያዎች በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ስላሉ፣ እነዚህ ኩባንያዎች በዚህ ስምምነት ውስጥ ታቅፈው የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ? አጎዋን ብንወስድ የውጭ ኩባንያዎች እጅ ካለበት እንደ አፍሪካ ምርት አይታይም በማለት የሚያስቀምጠው ገደብ አለ፡፡ በአፍሪካ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውስጥ እንዲህ ያለው ጉዳይ እንዴት ይታያል?   

አቶ እንዳልካቸው፡- ምርቶች በሚመረቱበት ሥፍራና አገር ላይ ተግባራዊ የሚደረጉባቸው የስሪት አገር ሕጎች አሉ፡፡ እነዚህ ሕጎች በተለያየ ደረጃ በማንም ይመረቱ፣ ኢትዮጵያዊም ይሁን የውጭ ዜጋ ያምርታቸው፣ ነገር ግን ‹‹በኢትዮጵያ የተመረተ›› ታግ ለማግኘት ‹‹ሲግኒፊካንት ኦፍ ትራንስሚሽን›› የሚባል አለ፡፡ ጥሬ ዕቃው ምን ያህል እሴት ተጨምሮበት ተመርቷል ተብሎ ይመዘናል፡፡ በዚህ ምዘና ኢትዮጵያ ውስጥ ተመረተ ለመባል ቢያንስ 30 እና 35 በመቶ የእሴት ጭማሪ ያካተተ መሆን አለበት፡፡ መሥፈርቶችን የሚያሟሉ ማናቸውም አገልግሎቶችና ምርቶች ናቸው በዚህ ነፃ የንግድ ቀጣና በነፃ የሚስተናገዱት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በዚህ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ቀድመው ይተገበራሉ ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያና ዜጋ የተዘጋ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ኢትዮጵያ የተቀበለችውና የሕግ አካል ማድረጓን ያወጀችበት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ደግሞ የፋይናንስ ተቋማትም እንዲሠሩ የሚፈቅድ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ሕጓን ከዚያ አንፃር ማስተካከል አለባት ሊባል ይችላል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አስገብተው ይሠራሉና እነዚህ ኩባንያዎች በእጅ አዙር ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል አይፈጥርም? እንዲህ ያሉትስ እንዴት ይስተናገዳሉ? 

አቶ እንዳልካቸው፡- ያነሳኸው ነገር ትክክል ነው፡፡ ‹‹ሩትስ ኦፍ ኦሪጅን›› ብዬ መጀመሪያ ላይ ያነሳሁልህ ነው፡፡ ድርድሩ ዝርዝር ጉዳዮች ይፈልጋል የሚባልበት አንዱ ምክንያት ይኼ ነው፡፡ ምክንያቱም የውጭ ባንኮች ዝርዝር ነገሮች ከሚፈልጉት ውስጥ ደግሞ አንደኛው አሁን አንተ ያነሳኸው ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ባንኮች ለምሳሌ በኬንያ ያሉት እንደ በርክሌይና የመሳሰሉት የኬንያ ባንኮች አይደሉም፡፡ የውጭ ባንኮች ናቸው፡፡ ‹‹ሩትስ ኦፍ ኦሪጅኑን›› እንዴት ነው የሚተነትናቸው? እንዴት ነው መሥፈርቶች አውጥቶ የሚለያቸው? የሚለው ነገር ሁሉ ትልቅ ቴክኒካዊ ሥራዎችን የሚጠይቅ ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ለእነዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች የማስወገጃ ሳይት ማዘጋጀት ይሆናል፡፡  ከቀደመው ጊዜ በተሻለ ለትልልቆቹ ኩባንያዎችና አምራቾች የተሻሻለና የተመቻቸ ነገር ነው የምትፈጥርላቸው፡፡ ድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ወደ ኬንያ ለመሻገር የሚፈልግ የቻይና ምርት ቢኖር፣ የኢትዮጵያና የኬንያን ድንበር ለማለፍ ጥያቄዎች ይኖሩበታል፡፡ አሁን ግን መሀል ላይ ያለውን ድንበር ስታጠፋለት የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ገበያ ነው የምትከፍትለት፡፡ ይኼ ጉዳይ የስሪት አገር ሕግ የሚባለው ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡ አንተ ያነሳሃቸው ባንኮች አፍሪካ በቀል መሆናቸውን ግልጽና በተብራራ ክራይቴሪያ አውጥተህ የማጣራት ሥራ ይጠበቃል ማለት ነው እንጂ፣ አፍሪካ በቀል ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም በዚህ ከነፃ ገበያው ስምምነት ፈራሚ አገሮች ውስጥ ያልበቀሉት ኩባንያዎች በዚህ ስምምነት ውስጥ የሚካተቱ አይሆኑም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጥያቄ ደግሞ ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት ለመተግበር ወስናለችና በመቀጠል ልትፈጽመው ይገባታል ተብሎ የሚጠበቀው ዓብይ ጉዳይ፣ አንዳንድ ሕግጋቶቿን መለወጥ እንደሚኖርባት ነው፡፡ ስለዚህ ስምምነቱን ለማስፈጸም የግድ የተለያዩ ሕጎቿን ትቀይራለች ማለት ነው፡፡ ? 

አቶ እንዳልካቸው፡- በትክክል፡፡ አዎ፡፡ መቀየር ያለባት ሕጎች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አሁን ነፃ የንግድ ቀጣናውን ለመቀላቀል የሚያስችላትን ይሁንታ ሰጥታለችና ከዚህ በኋላ ወደ ትግበራው ይገባል ማለት ነው፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ ወደፊትም መነሳቱ ስለማይቀር፣ በእርስዎ ዕይታ የዚህ ስምምነት አካል መሆኗን እንዴት ይገልጹታል? 

አቶ እንዳልካቸው፡- የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣው መልካም ዕድል ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህንን ገበያ በአግባቡ ከተጠቀምንበት የተጀመረው ኢንዲስትራላይዜሽን እንደ አገርም ሆነ እንደ ክፍለ ቀጣናው ስታየው በጣም ሊያግዝ የሚችል ነገር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አፍሪካ የምታመርተውን ምርት አትጠቀምበትም፡፡ የምትጠቀምበትን ምርት ደግሞ አታመርተውም፡፡ ይህ ልዩነት አለ፡፡ ይህንን ዝንፈት መስመር ለማስያዝና የእርስ በርስ ግብይታችንን ለማሳደግ ይጠቅማል፡፡ አሁን የአፍሪካን የእርስ በርስ ንግድ ስታይ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ አፍሪካውያን ከአፍሪካውያን ጋር የሚያደርጉት የእርስ በርስ ንግድ ከአሥር እስከ 12 በመቶ ቢሆን ነው፡፡ አውሮፓ ስትሄድ ግን ከ60 በመቶ በላይ ነው፡፡ ግን የአፍሪካ የእርስ በርስ ንግድ እ.ኤ.አ. በ2022 ወደ 52 በመቶ ለማሳደግ ይህ ስምምነት ግብ አድርጎ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ እርስ በርሳችን መነጋገድ ከቻልን እናድጋለን፡፡ እርስ በርሳችን ለመነጋገድ ገበያውን መከፋፈት ብቻ ሳይሆን የምናመርተውንም ምርት የማሳደግ ኃላፊነት ይኖርብናል፡፡ አፍሪካ ውስጥ የምንጠቀምበትን ምርት ለማምረት ግን ገበያ ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮች ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን አባል መንግሥታት ትኩረት አድርገው ከሠሩበት ስምምነቱ በጣም የሚጠቅም ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡