Skip to main content
x
በቬንዙዌላ ጉዳይ የሚወዛገቡት ሩሲያና አሜሪካ
‹‹የሽግግር መንግሥት መሪ ነኝ›› የሚሉት ሚስተር ጋይዶ የሕዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ይነገራል

በቬንዙዌላ ጉዳይ የሚወዛገቡት ሩሲያና አሜሪካ

ከወር በፊት በቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮና ‹‹የሽግግር መንግሥት መሥርቻለሁ›› ባሉት ተቀናቃኛቸው ሁዋን ጋይዶ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሩሲያና አሜሪካ ጎራ ለይተው እንዲወዛገቡ ሌላ በር ከፍቷል፡፡

በሶሪያ፣ በኢራን፣ በሰሜን ኮሪያም ሆነ በሌሎች አገሮች ጉዳይ ሁሌም ፅንፍ በመያዝና ሲላቸውም የውክልና ጦርነት በማድረግ ለብዙዎች ሞትና ለሚከሰቱ ቀውሶች እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሱት አሜሪካና ሩሲያ፣ ዛሬ ላይ ደግሞ በቬንዙዌላ ጉዳይ እኔ አውቅልህ እየተባባሉ ይገኛሉ፡፡

አሜሪካ ራሳቸውን ‹‹ጊዜያዊ የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ነኝ›› ብለው ካወጁት ጋይዶ ጎን ስትሠለፍ፣ ሩሲያ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ ተመርጠው አገሪቷን ከሚመሩት ፕሬዚዳንት ማዱሮ ጎን ቆማለች፡፡

‹‹የቬንዙዌላ ሕጋዊ መሪ ነኝ›› የሚሉትን ፕሬዚዳንት ማዱሮ፣ ከሩሲያ በተጨማሪ ቻይና ቱርክ፣ ኩባ እና ኢራን ቢደግፏቸውም የቃላት ምልልስና የአስጠንቅቄአለሁ ዛቻ ውስጥ የገቡት አሜሪካና ሩሲያ ናቸው፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮብ ጋር በቬንዙዌላ ጉዳይ መነጋገራቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሮበርት ፖላዲኖ፣ ሩሲያ በቬንዙዌላ ላይ የምታሳየውን ‹‹ገንቢ ያልሆነ ባሕሪ›› እንድታቆም ማስጠንቀቃቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

​​በቬንዙዌላ ጉዳይ የሚወዛገቡት ሩሲያና አሜሪካ
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ ፕሬዚዳንት ማዱሮ እና ተቀናቃኛቸው ጋይዶ ውዝግብ መግባታቸውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተው ነበር

 

‹‹ሩሲያ በቬንዙዌላ ያለውን ውጥረት የምታባብስ ከሆነ አሜሪካ ዝም ብላ አትቀመጥም›› ማለታቸውም ተነግሯል፡፡ ሩሲያ፣ የቬንዙዌላን መከላከያ ኃይል በተደጋጋሚ መደገፏንም አስመልክቶ ‹‹ሕጋዊ ላልሆነው የኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት ትረዳለች›› በማለት አብጠልጥለዋል፡፡ አብዛኞቹ ቬንዙዌላውያን ‹‹የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ነኝ›› ያሉትን ጋይዶ ይደግፋሉ ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ ከአሜሪካ ለተሰነዘረባት ማስጠንቀቂያ ምላሽ ባትሰጥም፣ የቬንዙዌላን መከላከያ ኃይል የሚያማክሩ ሩሲያውያንን ወደ ቬንዙዌላ ልካለች፡፡

በካራካስ በሚገኘው በሲሞን ቦሊቫር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወታደራዊ አማካሪዎችን የያዘ የሩሲያ አውሮፕላን ማረፉን ተከትሎ፣ ሩሲያ ላይ ለተነሳው ጥያቄም፣ ጉዳዩ ምንም የሚያስገርም ነገር እንደሌለውና ሩሲያና ቬንዙዌላም ወታደራዊ ትብብርን ጨምሮ በርካታ በመተግበር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ ስምምነት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

ለአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ያልሰጠችው ሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከወራት በፊት ‹‹የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ነኝ›› ላሉት ጋይዶ፣ ‹‹ከአሜሪካ በዕርዳታ ሰበብ በሚጫኑ መርከቦች ቬንዙዌላን ለሌላ አገር ጣልቃ ገብነት አትጋብዛት›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

ሚኒስትሩ ላቭሮቭ አሜሪካ የቬንዙዌላን መንግሥት ተቀናቃኝ ጋይዶ መደገፏ ቬንዙዌላን ለውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ያጋልጣልም ብለዋል፡፡ አሜሪካ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ሚስተር ጋይዶን ለመርዳትና በቬንዙዌላ ወታደራዊ ዕቅዷን ልታራምድ ነው ሲሉም የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአሜሪካ ዕርዳታ አያስፈልገንም›› ሲሉም አሜሪካን አውግዘዋል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም የቬንዙዌላን ሰብዓዊ ቀውስ በመጠቀም በአገሪቱ ወታደራዊ ዓላማቸውን ለማሳካት እየሠሩ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡

በቬንዙዌላ ጉዳይ የሚወዛገቡት ሩሲያና አሜሪካ
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቬንዙዌላ አቻቸው ኒኮላስ ማዱሮ ጋር ከወራት በፊት ተወያይተዋል

 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭም፣ ቀጥታም ሆነ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም የሚደረግ ጣልቃ ገብነት፣ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ነኝ የሚሉትን ጋይዶ ወደ ሥልጣን ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

100 ወታደሮችና ወታደራዊ ባለሥልጣናትን የያዙ ሁለት አውሮፕላኖች ባለፈው ቅዳሜ ቬንዙዌላ መግባታቸው ከአሜሪካ በኩል ተቃውሞ እንደገጠመው ያሰፈረው ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ሩሲያ ለቬንዙዌላ የምታደርገው ወታደራዊ እገዛ አሜሪካ የቬንዙዌላን ፕሬዚዳንት ማዱሮ ከሥልጣን ለማውረድ የምታርገውን ጥረት ያደናቅፋል ብሏል፡፡

አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ራሳቸውን ለሾሙት ጋይዶ ዕውቅና የሰጡ ቢሆንም፣ በአገሪቱ በስምንት ቀናት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ያሳለፉት ከወር በፊት ነበር፡፡ ሆኖም በቬንዙዌላ ምርጫ አልተካሄደም፡፡

በሰላማዊ መንገድ ለመደራደር ሐሳብ የቀረበ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንት ማዱሮ፣ ‹‹ጋይዶ በአሜሪካ የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግሥት ለመፈጸም ተጠምዷል፡፡ በአገሪቱ ገንቢ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት ዕድል አልሰጠም፤›› ብለዋል፡፡

በቬንዙዌላ በምርጫ አገሪቷን የሚመሩት ፕሬዚዳንት ማዱሮ እና ተቀናቃኛቸው ሚስተር ጋይዶ ሲፋጠጡ፣ ከውጭ ደግሞ አሜሪካና ሩሲያ ጎራ ለይተዋል፡፡

በቬንዙዌላ ጉዳይ የሚወዛገቡት ሩሲያና አሜሪካ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በቬንዙዌላ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል