Skip to main content
x
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • ምን እያደረጋችሁ ነው?
 • ምን አደረግን?
 • አገሪቱን አያዩዋትም እንዴ?
 • ምን ሆነች?
 • ከጫፍ እስከ ጫፍ እኮ እየተፍለቀለቀች ነው፡፡
 • ቡና እኮ ከኢትዮጵያ ተገኘ የምንለው ዝም ብለን አይደለም፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አየህ ቡና ተፈልቶ ከተንተከተከ በኋላ ሲሰክን ነው የሚቀዳው፡፡
 • ምን እያሉ ነው?
 • ስለዚህ አሁን አገሪቱ ልክ እንደ ቡና እየተንተከተከች ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ቡናው እኮ እሳት ከበዛበት ገንፍሎ ያልቃል፡፡
 • እንግዲህ እሳቱን መመጠን ነው ዋናው ጨዋታ፡፡
 • እሳቱን የምታነዱት ራሳችሁ ናችሁ ማለት ነው?
 • እንደ እሱ አልወጣኝም፡፡
 • ለነገሩ ባይሉም ግልጽ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • መንግሥት ሁሌም ጭር ሲል አይወድማ፡፡
 • ስማ መንግሥት እሳት ያነዳል እያልክ ነው?
 • ባያነድም ሌሎች ሲያነዱ አብሮ ይሞቃል፡፡
 • የምን አሽሙር ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኸው አንዱ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ያወራውን አልሰሙም?
 • ስለምን ያወራውን?
 • ስለሥራ ቋንቋ ነዋ፡፡
 • ምን አለ?
 • የብሔራችሁን ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች ውጪ አታግቡ ያለውን ነዋ፡፡
 • እ…
 • እንደ እኛ ተመፃዳቂ ኅብረተሰብ መቼም አላየሁም፡፡
 • እንዴት?
 • ሥራ ሳይኖረን በሥራ ቋንቋ እንጣላለን፡፡
 • እዚህስ ላይ ትክክል ነህ፡፡
 • ለማንኛውም ሕዝቡ ሿሿ ተሠርተናል እያለ ነው፡፡
 • ምንድነው ሿሿ?
 • የታክሲ ላይ የዘረፋ ስልት ናት፡፡
 • ሰውዬ ፈር አትልቀቅ እንጂ፡፡
 • ምን አደረግኩ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሌቦች እያልክ እየተሳደብክ እኮ ነው፡፡
 • ሕዝቡ የሚላችሁን ነው የነገርኳችሁ፡፡
 • እኮ ምን አደረግን?
 • ሰሞኑን እንኳን ያደረጋችሁትን ረሳችሁት?
 • ምን አደረግን?
 • በኮንዶሚኒየሙ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እንድትታወቅ እያደረጋችኋት ነው፡፡
 • በመደመር ፍልስፍናችን ማለትህ ነው?
 • ኧረ የለም፡፡
 • ታዲያ በምንድነው?
 • መንግሥት ሆኖ መንግሥትን በመቃወም፡፡
 • እ…
 • ራሳችሁ ቤት ሰጥታችሁ ራሳችሁን ትቃወማላችሁ?
 • እ…
 • ለማንኛውም እናንተን ለማስመዝገብ ደፋ ቀና እያልኩ ነው፡፡
 • የት? ምርጫ ቦርድ?
 • እዚያማ ተመዝግባችኋል፡፡
 • ታዲያ ምን ላይ ነው የምታስመዘግበን?
 • የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • አንተ ልጅ ምን እያደረግ ነው?
 • ኢንተርኔት ላይ የሆነ ጽሑፍ እያነበብኩ ነው፡፡
 • ከትምህርትህ ጋር ይገናኛል?
 • አይገናኝም ዳዲ፡፡
 • ለመሆኑ ዛሬ ትምህርት የለም እንዴ?
 • ኧረ አለ ዳዲ፡፡
 • ታዲያ ከትምህርት ቤት ቀርተህ ነው ኢንተርኔት የምትጠቀመው?
 • ምን ያደርግልኛል ዳዲ?
 • ምኑ?
 • ትምህርቱ፡፡
 • ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው አሉ፡፡
 • ምነው ዳዲ?
 • ትምህርትን ነው ምን ያደርግልኛል የምትለው?
 • አዎን ዳዲ ምነው?
 • ካልተማርክማ የፈለግከውን መሆን አትችልም፡፡
 • የማላውቅ መሰለህ እንዴ ዳዲ?
 • ምኑን ነው የማታውቀው?
 • ኢትዮጵያ ውስጥ መማር አያዋጣም ብለዋል፡፡
 • ምን?
 • ተምረው ኮብል አይደል እንዴ የሚፈልጡት?
 • ወይ የዛሬ ልጆች?
 • ተምሬ ድንጋይ ፈላጭ ልሁን?
 • የተማረ ሰው ድንጋይ አይፈልጥም፡፡
 • እሱማ ትንሽ ከተማርክ የሰው ጭንቅላት ትፈልጣለህ አሉ፡፡
 • ምን?
 • እንዴ ይኸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሌ አይደል እንዴ የሚደባደቡት?
 • ስማ ልጄ መማር በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡
 • ዳዲ እኔ እኮ ሁሉን ነገር በሚገባ አውቃለሁ፡፡
 • ምንድነው የምታውቀው?
 • መቼ ዕለት አለቃችሁ በቲቪ ሲያወሩ ሰምቻቸዋለሁ፡፡
 • ምን አሉ?
 • ኢንጂነሩም፣ ዶክተሩም፣ ሁሉም ሥራውን ትቶ እየሠራው ያለ ነገር አለ፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ ሁሉም ተምሮ አሁን የሚሠራው ሌላ ነገር ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ስለዚህ እኔም በሌላ ነገር ጊዜዬን ከማቃጥል ከአሁኑ ብጀምር አይሻልም?
 • የምታወራው ምንም አልገባኝም?
 • በዚያ ላይ ደግሞ አዋጭ ነው አሉ፡፡
 • እ…
 • ዕውቀት ኖረህም አልኖረህም መሥራት ትችላለህ፡፡
 • ያለ ዕውቀት ምንም መሥራት አትችልም፡፡
 • ዳዲ እኔም በጥቂት ዕውቀት ጥሩ ገቢ የሚገኝበት መሆኑን ስለተረዳሁ ትምህርት በመማር ጊዜዬን አላጠፋም፡፡
 • ተሳስተሃል ልጄ፡፡
 • አልተሳሳትኩም ዳዲ፣ ምን መሆን እንደምፈልግ በደንብ አውቃለሁ፡፡
 • ምንድነው መሆን የምትፈልገው
 • አክቲቪስት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ወዳጃቸው ስልክ ደወለላቸው]

 • ምን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • እኔ ለእናንተ እንደዚህ ነኝ?
 • ምን ሆነህ ነው?
 • ለውጡን እዚህ ያደረስኩት እኔ አይደለሁ እንዴ?
 • እሱማ ምን ጥርጥር አለው፡፡
 • እውነት ብንነጋገር ያለ እኔ እዚህ ትደርሱ ነበር?
 • አይታሰብም ስልህ፡፡
 • ታዲያ ለምንድነው የሚገባኝን ቦታ የማትሰጡኝ?
 • ከዚህ በላይ ምን እናድርግ ጌታዬ?
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ደስተኛ አይደለሁም፡፡
 • ምን ጎደለብህ?
 • ይኸው ትንሽ ከፊታችን ዞር በል እያሉኝ ነው፡፡
 • አገር እንዲረጋጋ እኮ ነው፡፡
 • እኔ እኮ በሐሳቡ ተስማምቼ ነበር፡፡
 • ምን ጎደለህ ታዲያ?
 • ኤርፖርት ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
 • የምን ችግር?
 • አትወጣም እያሉኝ ነው፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • ኤርፖርት ያሉ ኃላፊዎች፡፡
 • ለምን?
 • የያዝኩት ዶላር ይወረሳል እያሉ ነው፡፡
 • የምን ዶላር ነው?
 • የሥራ ማስኬጃ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የኤርፖርት የጥበቃ ኃላፊዎች ጋ ደወሉ]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንድ ወዳጄ ስልክ ደውሎልኝ ነበር፡፡
 • ምን ልርዳዎት ታዲያ?
 • አትወጣም ብላችሁታል መሰለኝ፡፡
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን ከለከላችሁት?
 • ሕገወጥ ገንዘብ ይዟል፡፡
 • ሕገወጥ ገንዘብ አይደለም፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • መንግሥት የፈቀደለት ገንዘብ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ለግለሰብ ይኼን ያህል ዶላር እንደማይፈቅድ አውቃለሁ፡፡
 • እሱ ግለሰብ አይደለም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • መንግሥት ነው፡፡
 • አሁን ምን ልርዳዎት?
 • ከአገር እንዲወጣ ፍቀዱለት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በስልክ እኮ ትዕዛዝ መስጠት ድሮ ቀረ፡፡
 • የእኛው ሰው ነው ስልህ፡፡
 • ለማንኛውም አንድ ነገር ልተባበርዎት እችላለሁ፡፡
 • ምን?
 • እሱን ልለቀው እችላለሁ፡፡
 • ዶላሩስ?
 • ይታሰራል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • የድጋፍ ቲሸርታችን ሳያረጅ እንዲህ ጉድ ትሠሩናለችሁ?
 • ምን አደረግን?
 • ክቡር ሚኒስትር ለውጡን እኮ ከልብ ነበር የደገፍነው፡፡
 • አሁንም ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉበት፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • ምነው?
 • ገና ወንበራችሁ ሳይፀና ሴራችሁ እኮ ተጋለጠ፡፡
 • የምን ሴራ?
 • ሁሉም ነገር የእኛ ነው እየተባለ እኮ ነው፡፡
 • እ…
 • ለውጡን ሳትጨርሱት ከተማዋ የእኛ ናት ማለታችሁ ግን ያስተዛዝባል፡፡
 • ምን መሰለህ?
 • ሌላው ደግሞ ከተማዋ የአፍሪካ መዲና ናት ይላል፡፡
 • እ…
 • ሌላው ደግሞ የሁሉም ናት ይላል፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • አንዱ ደግሞ ሌሎቹም ከተሞች የእናንተ ናቸው ይለናል፡፡
 • እውነት ነው እኮ፡፡
 • ለማንኛውም የከተማዋን ነዋሪ ግራ አጋብታችሁታል፡፡
 • ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡
 • በነገራችን ላይ ከተማዋ ራሷ በውዝግቡ ግር ስላላት ሰሞኑን ሁላችሁንም ትጋብዛችኋለች፡፡
 • ምንድነው የምትጋብዘን?
 • ሙዚቃ፡፡
 • የማንን?
 • የአስቴርን፡፡
 • ምን የሚለውን?
 • የማን ነሽ ይሉኛል. . .
 • እ…
 • . . . የማን ልበላቸው!