Skip to main content
x
አለመደማመጥ አገርን ለኪሳራ ይዳርጋል!

አለመደማመጥ አገርን ለኪሳራ ይዳርጋል!

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታ፣ በታሪክ ሊታወሱ የሚችሉ በርካታ አገራዊ ጉዳዮች ተከናውነውበታል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ብዙዎቹ አገርን ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ የሚያሸጋግሩና በአዎንታዊነት ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ አገርን ለአደጋ የሚዳርጉ አስፈሪ ክስተቶችም ተስተውለዋል፡፡ በሰከነ መንገድ መደማመጥና ልዩነቶችን እያከበሩ ተባብሮ መሥራት ቢቻል አንፀባራቂ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ክንውኖች ይኖሩ ነበር፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት በርካታ ተስፋ የተጣለባቸው ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የንግግር ነፃነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥራ ላይ እየዋለ ነው፡፡ አፋኝና ጨቋኝ የሆኑ የሚዲያ፣ የፀረ ሽብርና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕጎችን ለማሻሻል ምሥጉን የሆኑ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ወሳኝ የሆኑ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ በመሆናቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ለመንቀሳቀስ እየቻሉ ነው፡፡ ብዛት ያላቸው ሚዲያዎች ሥራ እየጀመሩ ነው፡፡ ሌሎች ተስፋ ሰጪ በርካታ ጅምሮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ተስፋ እየለመለመ ቢሆንም፣ ነውረኛና አፀያፊ ድርጊቶች በተለያዩ ሥፍራዎች ተከስተው የንፁኃን ሕይወት በከንቱ ተቀጥፏል፡፡ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፡፡ ኢኮኖሚው ከሚሽከመው በላይ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ የሥራ አጡ ቁጥር መላ ካልተፈለገለት ከባድ ፈተና ነው፡፡ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ተደማምረው ሚሊዮኖች አሁንም የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስፈልጋት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም መደማመጥ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ለዓመታት ተሰንቅሮ በረባ ባልረባው ምክንያት ችግር የሚፈጠረው፣ መነጋገርና መደማመጥ ባለመለመዱ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ከየጎራው እየተነሳ የራሱን ብሶት ወይም ጀብዱ ብቻ ማቀንቀን ከመጠን በላይ በመለመዱ፣ በፖለቲካው ሠፈር ውስጥ መደማመጥ ብርቅ ሆኗል፡፡ ባለመደማመጥ ምክንያት ሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች አየሩን ሞልተውታል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን ከሚለያዩ ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች እያሉ፣ ባለመደማመጥ ምክንያት ሐሰተኛ ወሬዎች ክፍፍል እየፈጠሩ ነው፡፡ ልዩነትን አክብሮ ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች በአንድነት መቆም እየተቻለ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና የመሳሰሉትን ከለላ በማድረግ መናቆር የዘወትር ትዕይንት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአራቱም ማዕዘናት ቢሠራጭም በሥነ ልቦና ተቀራራቢ መሆኑ እየታወቀ፣ ‹ያኛው ወንዝ የማን ነው? ይኼ መንደር የማን ነው?› ወዘተ እየተባለ ይታመሳል፡፡ በሥርዓቱ ተቀምጠው መነጋገር የማይችሉ ስሜታውያን በሚፈጥሩት ግጭት፣ የንፁኃን ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ በሰከነ መንገድ መነጋገር በማይችሉ ስሜታውያን ምክንያት፣ ዘመናትን የተሸጋገሩ ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴቶች ይናዳሉ፡፡ አስተዋዩ ሕዝብ ያለችውን ተካፍሎ ተዛዝኖ ነው የሚኖረው፡፡ በጥባጭ በዛ እንጂ፡፡

እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ እናንሳ፡፡ በቅርቡ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በወደቀበት ሥፍራ አካባቢ የሚኖሩ ቅን ኢትዮጵያውያን፣ ሰው ማለት ምን እንደሆነ አስተምረውናል፡፡ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ማን እንደሆኑ የማያውቋቸውን የ35 አገሮች ዜጎችን እንደ ቤተሰቦቻቸው ቆጥረው እንባቸውን እያዘሩ፣ እውነተኛውን የኢትዮጵያውያን የዘመናት ወግ አሳይተውናል፡፡ የእነዚህ ወገኖቻችን ሐዘን ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎዋቸው ያላቸውን በማሰባሰብ ለአደጋው ሰለባዎች ዝክር አድርገዋል፡፡ ይኼንን የመሰለ ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽሙ ለታይታ አልነበረም፡፡ ከዚህ ቀደም የጋሞ አባቶች ወጣቶቻቸው አደጋ እንዳይፈጽሙ ያደረጉት ተጋድሎ አይዘነጋም፡፡ እነሱ እርጥብ ሳር ይዘው ወጣቶችን በማብረዳቸው የተቀለበሰው አደጋ ይታወቃል፡፡ ይህንን የመሰለ ድንቅና አስተዋይ ሕዝብ ይዞ ስንትና ስንት ገድል መፈጸም ሲቻል፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት የሚባሉት ደግሞ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ወኔ አጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሚበቃት በላይ ጦርነቶች የተካሄዱባት አገር መሆኗን፣ የታሪክ ድርሳናትን በማገላበጥ መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ የድህነትና የኋላቀርነት መፈንጫ የሆነችው ሰላሟ እየተናጋ መረጋጋት በመጥፋቱ ነበር፡፡ ከዚያ ዓይነቱ አስከፊ አዙሪት ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ቦታ አለመስጠት መዘዙ የከፋ ነው፡፡

ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ የመንግሥት ዋነኛ ችግር አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽ አለመሆኑ ነው፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም መንግሥት መንቀሳቀስ የሚጀምረው፣ ችግሩ የተለየ ገጽታ ከያዘ በኋላ ነው፡፡ የመሰንበቻውን ጉዳይ ብናነሳ እንኳ በአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ ያ ሁሉ ትርምስ ሲነሳ መንግሥት ተኝቶ ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ ነዋሪዎች ችግር ህልቆ መሳፍርት የሌለው መሆኑ እየታወቀ፣ እዚህ ግባ በማይባል ጥያቄ ምክንያት የደረሰው ኪሳራ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃቸውን አጣጥፈው አክቲቪስቶች ቅራኔውን በማጦዝ ሙቀቱ ኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት ሲሰራጭ፣ በግብታዊነት ግጭት ተቀስቅሶ ንፁኃን ሰለባ ቢሆኑ ኃላፊነቱን ማን ነበር የሚወስደው? የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ተካሂዶብኛል ያሉትን ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለማስተካከል የዘገየ ማብራሪያ የሰጡት ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ ብዙዎች ንግግራቸውን ከሰሙ በኋላ በመቆጨት የጠየቁት ለምን ዘገዩ በማለት ነው፡፡ መንግሥት ከሥር ከሥር እየተከታተለ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ባህል ባለመገንባቱ፣ ብዙዎች ቀድሞ በደረሳቸው መረጃ ላይ ተመሥርተው የሚሰማቸውን ቢናገሩ ምን ይደንቃል? የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን ለአክቲቪስቶች አሳልፈው ሰጥተው ቢብጠለጠሉ በማን ነው ማዘን ያለባቸው? ካለፈው ስህተት በመማር ለፈጣን ምላሽ ራስን ማዘጋጀት አደጋ ይቀንሳል፡፡ የመነጋገርና የመደማመጥ ባህሉን ለማሳደግ ደግሞ በሙሉ ኃይል መሥራት የግድ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው በአንድነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ነው፡፡ ልዩነትን እያከበሩ፣ ጥላቻና ቂም በቀልን እያስወገዱ፣ የበዳይና የተበዳይነት ትርክትን ለታሪክ ዶሴ እየተውና የዘመኑን ሥልጣኔ በጋራ እየተቋደሱ አብረው መሥራት ከቻሉ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ትሆናለች፡፡ አገርን ወደ ዴሞክራሲ ጎራ መቀላቀል ሲገባ በጉልበት እንፈታተሽ ማለት ውጤቱ ሞት፣ ስቃይ፣ እስራትና ስደት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ መቆም የሚችለው መነጋገርና መደማመጥ ባህል በሆነበት አገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማሳካት ሲቻል የሐሳብ ብዝኃነት ይንሰራፋል፡፡ ዴሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ስለሆነ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ዕድል መሰጠት አለበት፡፡ ከእኔ በላይ ላሳር ማለት የኋላቀርነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ ሰው የመሆን ባህሪ የሚያሳጣ አውሬነት ነው፡፡ የማናምንበት ሐሳብ ቢሆን እንኳን እየመረረንም ማዳመጥ አለብን፡፡ ተናጋሪዎችን በተናጠልና በጅምላ እየፈረጁ ማስደንበር ለዘመኑ አይመጥንም፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች ከነውጠኛ ባህሪያት በመላቀቅ፣ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ባህል ግንባታ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ ሐሰተኛና የጥላቻ ንግግሮች ናቸው የመደማመጥ ባህል እንዳይሰፍን እያደረጉ ያሉት፡፡ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት በጋራ መሥራት እየተቻለ በጎጥ ፖለቲካ ታጥሮ መነጋገርና መደማመጥን ማጥፋት ለማንም አይበጅም፡፡ አለመደማመጥ አገርን ለኪሳራ ይዳርጋል!