Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው

ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው

[ክቡር ሚኒስትር ወደ ሥራ ከመሄዳቸው በፊት ከባለቤታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • በጠዋት ምን ተገኝቶ ነው በደስታ የተሞላሽው?
 • ጓደኛዬ አዲስ የቢዝነስ ፕሮፖዛል ሠርታልኝ ነው፡፡
 • የምን ፕሮፖዛል?
 • የአስመጪነት ቢዝነስ ፕሮፖዛል፡፡
 • ነጋዴ ልትሆኚ?
 • የተከበሩ ሚኒስትር እኔ ምን ያንሰኛል?
 • በተማርሽበት ብትሠሪ ይሻልሻል፡፡
 • የማይደረገውን?
 • እንዴት?
 • ብር ከአካፋ በሚዛቅበት ጊዜ ሞኝ አይደለሁም፡፡
 • ካዋጣሽ ቀጥይ፡፡
 • እንደሱ ብሎ ነገር የለም፡፡
 • ምን ማለት ይሆን?
 • አንተም ታግዘኛለህ፡፡
 • እንዴት ነው የማግዝሽ?
 • ሥልጣንህ ለመቼ ሊጠቅመኝ ነው ታዲያ?
 • ለመሆኑ ምንድነው የምታስመጪው?
 • ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኙ ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶችን፡፡
 • ካፒታሉን ከየት ለማግኘት አቅደሻል?
 • ዕድሜ ለአንተ የባንክ ብድር ታመቻችልኛለህ፡፡
 • እኔ?
 • አዎ አንተ፡፡
 • እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር መስማት አልፈልግም፡፡
 • ከብድር በተጨማሪ ሌላም ነገር እፈልጋሁ፡፡
 • ሌላው ደግሞ ምንድነው?
 • የውጭ ምንዛሪ በቅድሚያ በአስቸኳይ እንዲፈቀድልኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • አንቺ ሴትዮ ገና አንድ ዓመታችን እኮ ነው፣ ያምሻል?
 • የሚያምህስ አንተ፡፡
 • እኔን ምንድነው የሚያመኝ?
 • ሰው ሁሉ እየተተኮሰ አንተ ከመጋቢት እስከ መጋቢት እያልክ ታወራለህ፡፡
 • እኔ አገሬን በቅንነት ነው ማገልገል የምፈልገው፡፡
 • በዚህ በፍየል ዘመን በግ አትሁን፡፡
 • ምንድነው የምትይው?
 • መጀመርያ ለራስ ከዚያ ለአገር ይሞከራል፡፡
 • ኧረ ይኼ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ይቅርብሽ፡፡
 • ከራስ በፊት ምንም የሚቀድም የለም፡፡
 • ለእኔ ግን አገሬ ትቀድማለች፡፡
 • አገሬ አገሬ ብትል ማንም አይሰማህም፡፡
 • ለምን?
 • አልሰማህም እንዴ?
 • ምኑን?
 • ኢትዮጵያዬ በማለታቸው ተሰደብኩ ብለው ሲበሳጩ፡፡
 • በአገሩ ምክንያት የተሰደበ ሰው አላውቅም፡፡
 • ሰውየው በንዴት እየተንገበገቡ ሲናገሩ አልሰማህም?
 • የቱ ሰውዬ?
 • ለኢትዮጵያዊነት ቀብድ የሰጠኝ ማን ነው ያሉት ናቸዋ፡፡
 • እሳቸው ሲናገሩ እንኳ ዕንባዬ ነበር የመጣው፡፡
 • እዚህ አገር እኮ መተማመን ጠፍቷል፡፡
 • የጊዜ ጉዳይ ነው ይስተካከላል፡፡
 • እንዳይመስልህ፡፡
 • አንቺ ግን ምን ነክቶሻል?
 • በማንም መበለጥ አልፈልግም፡፡
 • ምናለበት ቢቀርብሽ?
 • ያሰብኩትን ከማሳካት ወደኋላ አልልም፡፡
 • አጉል ድፍረት ጣጣ ያመጣል፡፡
 • ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም ተብሏል፡፡

[ክቡር ሚኒስትር ቢሮ እንደደረሱ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • ለበላይ አካል የሚቀርበው ዓመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት አለቀ?
 • ክቡር ሚኒስትር ትንሽ ይቀራል፡፡
 • ምንድነው የሚቀረው?
 • የአንድ ዓመት አፈጻጸማችን ዝቅ ያለ ስለሆነ እያስተካከልኩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑን ነው የምታስተካክለው?
 • ቁጥሮቹን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቁጥሮቹ ምን ሆኑ?
 • ያሳጡናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የሥራ አፈጻጸማችን በመቶኛ ስንት ነው?
 • 77 በመቶ ብቻ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የፋይናንስ ክዋኔያችንስ?
 • 80 በመቶ ብቻ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ ስንት ለማድረግ አሰብክ?
 • ከ95 በመቶ በላይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን እንዋሻለን ግን?
 • ክቡር ሚኒስትር የመንግሥት ሪፖርት የሚታወቀው እኮ በውሸት ነው፡፡
 • ካልዋሸን የሠራን አይመስልህም በቃ?
 • ባህል ስለሆነ አይሥጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ ግን በዚህ አልስማማም፡፡
 • የአንድ ዓመት ተሿሚ ስለሆኑ የምልዎትን ቢሰሙ ይሻላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አቅራቢውም ተቀባዩም ሞቅ ሞቅ ሲል ነው የሚወዱት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ገና በአንድ ዓመታችን ውሸትን ይዘን እንነሳ?
 • የበዓለ ሲመቱ አንደኛ ዓመት ሞቅ ደመቅ የሚለው ቁጥሮችም ከፍ ሲሉ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኧረ ሰው ይታዘበናል አንተ ሰውዬ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሰው በነገር ጦዞ ቁጥር ላይ ሳይሆን ያለው ሌላ ነገር ላይ ነው፡፡
 • ምን ላይ?
 • አዲስ አበባ፣ ኮዬ ፈጬ፣ ጌዴኦ፣ . . . የሚባሉ አጀንዳዎች ናላውን አዙረውታል፡፡
 • አንተ ደግሞ ቁጥር እየቀሸብክ ሌላ ራስ ምታት ትፈጥራለህ፡፡
 • የዛሬ ዓመት እርስዎ እኔን በእጥፍ ያልበለጡኝ እንደሆነ ከምላሴ ፀጉር ይነቀል፡፡
 • እኔ እንዳንተ አይደለሁም፡፡
 • ሌሎችም እንዲህ እያሉ ነው ሰተት ብለው የገቡበት፡፡
 • እኔ እኮ የሥልጣን ጉጉት የለብኝም፡፡
 • የበፊቶቹም እንዲህ ይሉ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ ሌላ ያ ሌላ፡፡
 • ሁሉም ያው ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነው ያው የሚሆነው?
 • የማንም ፖለቲከኛ ግቡ ሥልጣን እንደሆነ ያጡታል እንዴ?
 • ሥልጣን ለእኔ ተራ ነገር ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለእኔ ደግሞ ሌላ ነው፡፡
 • ማለት?
 • እርስዎ ሥልጣን ተራ ነው ሲሉ እኔ ደግሞ . . .
 • አንተ ደግሞ ምን?
 • ሥልጣን ተራ አይደለም እላለሁ፡፡
 • ምንድነው ታዲያ?
 • የሁሉም ነገር ምንጭ ነው፡፡
 • ለአንተ ሊሆን ይችላል፡፡
 • ሲባል አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ተባለ?
 • ሥልጣንና የነብር ጅራት ከተያዘ ለመልቀቅ ይቸግራል፡፡  

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ዲፕሎማት ጋር እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ደህና ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እግር ጣለህ?
 • የመጣሁበትን ጉዳይ ሳያውቁት አይቀርም፡፡
 • ምን ይሆን?
 • ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ ለታየው ለውጥ ደስታዬን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
 • ጥሩ፡፡
 • አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም ተስፋ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡
 • ጥሩ፡፡
 • በሌላ በኩል ለለውጡ የማይመጥኑ ድርጊቶች ይታያሉ፡፡
 • ለምሳሌ?
 • የበቀደሙ ጋዜጣዊ መግለጫ ክልከላ አንዱ ነው፡፡
 • የቱ ጋዜጣዊ መግለጫ?
 • የባልደራስ ምክር ቤት መግለጫ፡፡
 • እሱ እኮ ፖሊስ የፀጥታ ሥጋት አለ ስላለ ነው ያልተካሄደው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ፖሊስ የፀጥታ ሥጋትን ማስወገድ እንጂ መግለጫ ማስቆም የለበትም፡፡
 • ሥጋቱ ተጨባጭ ሲሆንስ?
 • የከተማ አስተዳደሩ ይወስናል እንጂ ፖሊስ ለምን ይወስናል?
 • ከፖሊስ በላይ የፀጥታ ሥጋትን ማን ሊናገር ይችላል?
 • በበኩሌ እንዲህ ዓይነቱ ነገር አይጥመኝም፡፡
 • ለምን?
 • የፀጥታ አካላት ገለልተኛ መሆን አለባቸው እንጂ፣ አስፈጻሚውን መተካት አይጠበቅባቸውም፡፡
 • እኛ ሥጋቱ አሳስቦን እንጂ ክፋት አላሰብንም፡፡
 • ሌላው ወገን ግን ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም ስብሰባው ወደፊት መካሄድ ይችላል ተብሏል፡፡
 • ዘላቂና አስተማማኝ ዴሞክራሲ የሚገነባው ግልጽነት ሲኖር ስለሆነ ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው፡፡
 • እኛ እኮ ለራሳችን ስንል ነው እንጂ ለታይታ አንሠራም፡፡
 • እኛም ቢሆን ደስ ይለናል ግን . . .
 • ግን ምን?
 • አንዳንዴ የተደበላለቁ ነገሮች ይታያሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምሳሌ?
 • በአንድ በኩል ለለውጡ ተስፋ የሚሰጡ ሥራዎች ሲታዩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚያስቀለብሱም ይታያሉ፡፡
 • በሽግግር ወቅት የሚያጋጥም ነው፡፡
 • ቢሆንም ከሕዝብ ጋር ጀርባና ሆድ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ፡፡
 • ወዳጄ እኛ እኮ ለሕዝባችን እናስባለን፡፡
 • ቢሮክራሲያችሁ ቀርፋፋ ስለሆነ ብዙ ነገር ከተበላሸ በኋላ ነው ድምፃችሁ እንኳን የሚሰማው፡፡
 • እንዲህ እንኳን አንታማም፡፡
 • ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የለውጡ ቡድን ከዘገየ በኋላ አይደል እንዴ እየተናገሩ የነበረው?
 • የአዲስ አበባ ጉዳይ በእርግጥ ችግር ፈጥሮብን ነበር፡፡
 • መንግሥት ሲንቀራፈፍ አቋሙ ባለመታወቁ ብዙዎች ማኩረፋቸውን እናውቃለን፡፡
 • እናንተማ ከዚህም በላይ ባታውቁ ነው የሚገርመኝ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ማታ ምን በልተን እንደተኛን እንኳ ታውቃላችሁ፡፡
 • እ . . . ?
 • በየትኛው ጎናችን ተኝተን እንዳደርን ጭምር ነው የምታውቁት፡፡
 • ይቀልዳሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቀልድ ብችል ኖሮ ኮሜዲያን ነበር የምሆነው፡፡
 • ኧረ ሌላም መሆን ይችላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን?
 • አስማተኛ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው]

 • እነዚህ ሁሉ መኪኖች መንገድ ዳር ለምንድነው የቆሙት?
 • ባለቤቶቻቸው መጠጥ እየጠጡ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ጠጥተው ይነዳሉ ማለት ነው?
 • አጠጣጥስ ልክ አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ትራፊክ ፖሊሶች የሉም እንዴ?
 • ቢኖሩስ ክቡር ሚኒስትር?
 • አይቆጣጠሩም እንዴ?
 • ለሁሉም ነገር መላ አለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን መላ?
 • ሰጥቶ መቀበል የሚሉት መላ ነው፡፡
 • አንተ በምን አወቅክ?
 • ከአሥር ዓመት በላይ ሾፌር ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሥር ዓመት ሙሉ መኪና ትነዳለህ?
 • ምን ላድርግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለማደግ ጥረት አታደርግም?
 • እዚህ አገር ለማደግ አቋራጩ ነጋዴ መሆን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በቃ?
 • ይልቅ እርስዎም ባለቤትዎን ንግድ ውስጥ በቶሎ ይክተቱ፡፡
 • እኔማ አላደርገውም፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር ነገ የምናየውን?
 • ምንድነው የሚታየው?
 • አለ አይደል . . .
 • አለ ምን?
 • ባለቤትዎ ንግዱን ማቀላጠፍ ሲጀምሩና ብር በአካፋ ሲዝቁ ያኔ ይገባዎታል፡፡
 • አሁን አይገባህም እያልከኝ ነው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • በምሳሌ ላስረዳዎት፡፡
 • በላ ንገረኝ፡፡
 • የአገራችን ፖለቲካ ለምን ንጭንጭ እንደሚበዛበት ያውቃሉ?
 • አንተ ንገረኛ?
 • የገንዘብ ድርቅ ስላለበት ነው፡፡
 • እ?
 • ሁሉም የሚጮኸው ሥልጣን ይዞ ገንዘብ ለመቀራመት ነው፡፡
 • ወይ ጉድ?
 • በእግሩ አገር የሚያካልል ፖለቲከኛ ከመብዛቱ የተነሳ ፓርቲዎች ከመቶ በላይ ናቸው፡፡
 • ህም . . .
 • ይኼ ሁሉ ወፈ ሰማይ ፓርቲ ውስጡ ቢፈተሽ ደግሞ ባዶ ነው፡፡
 • እና?
 • እናማ በባዶ እጅ ሥልጣን ይደብራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔም ልነግድ?
 • ከተገኘ ከእነ ባለቤትዎ በሰፊው ይግቡበት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለአገር አይጠቅምም፡፡
 • የበፊቱም ሚኒስትር እንዲህ ይሉ ነበር፡፡
 • ከዚያስ?
 • ከዚያማ ምኑ ይነገራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተም እንዲህ ነው የምታስበው?
 • ባገኝ አልጠላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ የሌብነት ሱስ የለብኝም፡፡
 • የአገር ሱስ ደግሞ የትም አያደርስም፡፡
 • ለምን?
 • ትርፉ ብስጭት ነው፡፡
 • የፈለገው ይሁን ለጥቅም ብዬ አገሬን አልሰርቅም፡፡
 • የሚያምንዎት የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ ከህሊናዬ በላይ ምስክር አልሻም፡፡
 • የዘንድሮ ሰው ለህሊና ደንታ የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቢሆንም እኔ ህሊናዬን ብያለሁ አንተስ?
 • ግራ ገብቶኛል!