Skip to main content
x
ቁመት የፈተናቸው
የድንኮች እጅና እግር ዕድገት በጣም ውስን ነው

ቁመት የፈተናቸው

መንገድ ላይ ስትንቀሳቀስ የሚያዩዋት እንደ እንግዳ ፍጥረት ትክ ብለው ነው፡፡ ዓይኗ የተለየ ኃይል እንዳለው ሁሉ እንዳታያቸው የሚጠነቀቁም አሉ፡፡ እንደ ትንግርት ከሚመለከቷት አዋቂዎች በተቃራኒው ሕፃናት ደግሞ ይወዷታል፡፡ በተረት ላይ የሚያውቋትን ገፀ ባህሪ በአካል ያገኙ እስኪመስላቸው ሲያገኟት ይፍነከነካሉ፡፡

ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ሰርቪስ ውስጥ እንዳሉ ተጠማዘው ያዩዋታል፡፡ ለእነሱ ሁሌም አዲስ ነች፡፡ መንገድ ላይ ባዩዋት ቁጥር ‹‹ወይኔ ጉዴ›› ብለው ያዩትን ማመን እስኪያቅታቸው የሚደነቁባት አጭር ፍጥረት፡፡ የአዋቂዎቹን ትዝብትና ሽሙጥ ያዘለ አተያይ አትወደውም፡፡ ከበስተጀርባው ምንም ዓይነት ክፋት የሌለበትን የሕፃናቱን የፍቅር አተያይ ግን ትወደዋለች፡፡ ቁመቷ እንደ ሰባት ዓመት ልጅ አንድ ሜትር ከ20 ሳንቲ ነው፡፡ ፈርጣማ ሰውነቷና አለባበሷ እንደ አዋቂ ቢሆንም፣ ቁመቷ ከልጆች እኩል የሚያደርጋትን ቤተልሔምን (ስሟ ተቀይሯል) ሲመለከቱ ሕፃናት ይቦርቃሉ፡፡ ‹‹ጉትት አድርጌ እጃቸውን እስማለሁ፤›› ትላለች፡፡ አክላም እንደ ቡዳ የሚያዩኝ ትልልቅ ሰዎችም አሉ፤›› ትላለች፡፡

የ35 ዓመቷ ቤተልሔም ትውልድና ዕድገቷ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ለወላጆቿ ሁለተኛና የመጨረሻ ልጅ ነች፡፡ ‹‹ሸበላ›› ከምትላቸው ቤተሰቦቿ መሀል ድንክ ሆኖ መፈጠሯ እንድትመራመር አድርጓታል፡፡ የተለየዩ መጣጥፎችን አንብባ ድንክነት በዘር የመተላለፍ ዕድል እንዳለው አውቃለች፡፡ ወደ ኋላ ተመልሳ የዘር ግንዳቸውን አጣርታ ግን አንድም ድንክ አላገኘችም፡፡ ‹‹ልጅ ሆኜ እንደኔ ዓይነት ሰው መኖሩን አላውቅም ነበር፤›› የምትለው ቤተልሔም፣ አንድ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ አስደናቂ ነገር እንዳጋጠማት ታስታውሳለች፡፡

ከሰዎች መሀል አንዲት ልጅ ተመለከተች፡፡ ልጅቱ እንደ እሷ ድንክ ነበረች፡፡ የተመለከተቸውን ማመን እስኪያቅታት ክው አለች፡፡ በዓለም ላይ እንደሷ ያለች ሁለተኛዋ ድንክ ተገኘችና፤ ምናልባትም ሌሎች ይኖራሉ ብላ አሰበች፡፡ ይህ ለቤተልሔም አዲስ ታሪክ ነው፡፡ የሸበላዎች በሆነች ዓለም ውስጥ እንደሷ ያለች ስታልፍ ስታገድም እንደ ጉድ የምትታይ መሰሏን ማግኘት አስባውም የማታውቀው ነገር ነበር፡፡ ልትተዋወቃት ቸኮለች፡፡ መንገድ ላይ ያየቻት ድንክ ግን ደንግጣ ነበረና እሺም እምቢም ሳትል ዝም አለች፡፡ የቤተልሔም ጓደኛ ተስፋ አልቆረጠችም፣ በግድ አስተዋወቀቻቸው፡፡

እየተገናኙም የሚሰማቸውን የሚገጥማቸውን ሁሉ እንደ ጓደኛ ያወራሉ፡፡ ‹‹እሷም ሌላ ድንክ ያለ እንደማይመስላት ነገረችኝ ተሳሳቅን፤›› ትላለች፡፡ በአጋጣሚ መንገድ ላይ ካገኘቻት ልጅ ጋር እስካሁን ድረስ የልብ ጓደኛሞች ናቸው፡፡

 ቤተልሔም አንድ ጓደኛ ካገኘች በኋላ ሌሎች ድንኮችን ማሰባሰብ ጀመረች፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ እስከ 50 የሚደርሱ ሌሎች ድንኮችን አሰባሰበች፡፡ ‹‹በጣም ነው የምወዳቸው መንገድ ላይ ስንሄድ ሁሉ አቅፌያቸው ነው የምንቀሳቀሰው፤›› ስትል ከድንክ ጓደኞቿ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደምትወድ ትገልጻለች፡፡ የሰው ዓይን በቡድን ሲሆኑ እንደሚብስ ‹‹ከየት ተገናኙ ብለው ቆም ብለው እንደ ጉድ ያዩናል፡፡ በእርግጥ ሁሉንም እንቅስቃሴያችንን ሰው በግርምት ነው የሚያጤነው፡፡ ሰው መሆናችንን የሚጠራጠሩ አሉ፡፡ እንደ ቁስ ሊነኩን የሚፈልጉም ብዙ ናቸው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ቀና ብሎ ለመሄድ እስኪቸገሩ የሁሉም ዓይን እነሱ ላይ መሆኑ ከቤት መውጣትን እንዲፈሩ ያደርጋቸዋል፡፡ መዝናኛ ቦታዎች ለመሄድ ብዙ እንደሚቸገሩ ትናገራለች፡፡ በተለይም ሰው በሚበዛባቸው የሳምንቱ ቀናት ቅዳሜና እሑድ ካፊቴሪያ ተገናኝቶ ሻይ ቡና ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ ሰው በሚበዛበት አሳቻ ሰዓት ላይ ሽው ብለው ገብተው ሹልክ ብለው ይወጣሉ፡፡ ምክንያቱም እንደ ቤተልሔም ያሉ ድንኮችን ሲገቡ ሞቅ ያለ ጨዋታቸውን አቁመው እንደ ትንግርት ትክ ብለው የሚያዩዋቸው ብዙ ናቸው፡፡ የእምነት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ድንኮች ሲገቡ ፀሎታቸውን ወደ ጎን ብለው በግርምት የሚመለከቷቸው ብዙ እንዳሉ ‹‹ቤተ ክርሲያን ውስጥ ፀሎት እያደረጉ ሁሉ አተኩረው ይመለከቱናል፡፡ የፈጣሪ ቤት ስንሄድ ቤታቸው እንደሄድን የሚሰማቸውም አሉ፤›› ትላለች፡፡

ከቁም ነገር የሚቆጥራቸው ባለመኖሩ ከብዙ ማኅበራዊ ክዋኔዎች ይለያሉ፡፡ ለነገሮች ያላቸውን አመለካከት፣ ብቃት፣ ሙያና ሌሎችም ድንኩ ቁመታቸው ገዝፎ ይሸፍነዋል፡፡ ተቀጥሮ መሥራት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ፈተና ቢሆንም ለድንኮች ግን የማይታለፍ መሰናክል ነው፡፡ ተወዳድሮ ለመቀጠር ማስረጃቸውን ሲያቀርቡ ቁመታቸው በቁም ነገር እንዳይቆጠሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ‹‹በጭንቅላት እንደሚሠራ አያውቁም፡፡ ቀድመው ዓይናቸውን የሚተክሉት ቁመትሽ ላይ ነው፡፡ ጩጬ ናችሁም ይሉናል፡፡ አንዳንድ ዕድለኞች ሥራ አግኝተው ሲቀጠሩ እናያለን፡፡ ይኼንንም በመንግሥት ተቋማት እንጂ በግል የማይታሰብ ነው፤›› ስትል ታስረዳለች፡፡

ትዳር ይዞ ወልዶ መክበድ ትፈልጋለች፡፡ ለቤተልሔም የምትፈልገው ትዳር የሚሳካላት ግን አይመስላትም፡፡ ብታገባ ደስ የሚላት ከልጅነት ጀምሮ የምታውቀውን ሸበላ ጓደኛዋን ነው፡፡ ከልጁ ጋር በጓደኝነት ዓመታት አብረው ቆይተዋል፡፡ እንደሚወዳት ባትጠራጠርም ትዳር እንደሚያስብ ግን እርግጠኛ አይደለችም፡፡ የእሷ ቤተሰቦችም ወደውላታል፡፡ ተጋብተው ቢኖሩም ደስታቸው ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የእሱ ቤተሰቦች የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ልጃቸው ከድንክ ጋር መወዳጀቱን ቢሰሙ ሊፈጠር የሚችለው አይታወቅምና ነገሮችን በጥንቀቄ ነው መያዝ የመረጡት፡፡ አብረው እንዳይታዩ ይጠነቀቃሉ፣ ወሬ እንዳይሰማም ነገሮች በምስጢር ነው የሚያዙት፡፡ ‹‹ከዘመዶቹ ላጣላው አልፈልግም፡፡ ከእኔ አንድ ነገር አጥቶ እንዲኖር አልፈልግም፤›› ስትል ተጋብተው እንዲኖሩ ፍላጓቷ ቢሆንም፣ ደስተኛ ላይሆን ይችላል ብላ ስለምታስብ እንደምትጠነቀቅ ትገልጻለች፡፡

በዚህ መካከል ግን በአጋጣሚ እርግዝና ተከስቶ ልጅ ወልዳለች፡፡ ማርገዟን ስትነግረው ‹‹ባይሆን ጥሩ ነበር›› ብሏታል፡፡ ነገር ግን እኔ ልጅ ስለምፈልግ ወለድኩኝ የምትለው ቤተልሔም፣ የሰባት ዓመት ወንድ ልጅ እንዳላት ትገልጻለች፡፡ የልጄ አባት ሕፃኑን በቫይቨር፣ በዋትሳፕ እየደወለ ያገኘዋል እስካሁን ግን በአካል አልተገናኙም ትላለች፡፡

‹‹የልጄ ቁመት እስካሁን ደህና ነው፡፡ ነገር ግን አይታወቅም ሄደት ብሎ ሊቀር ይችላል፤›› ብላለች፡፡ በሕይወቴ ደስተኛ ነኝ የምትለው ቤተልሔም ሁለተኛ ልጅ ብትወልድ ምኞቷ ነው፡፡ 31 ቁጥር ጫማ ታደርጋለች፡፡ ሌሎች እንደ ቁምጣ የሚለብሱት ሱሪ አድርጋ ትለብሳለች የልጇ ጓደኞች ቤተልሔምን ትክ ብለው ያዩዋትና ዞር ብለው ያወራሉ፡፡ መልሰው እናትህ ‹‹ዶጮ ናት›› ይሉታል፡፡ የቁመቷ ነገር ሁሉም እንደ ትንግርት እንዲመለከቷት ቢያደርግም፣ ቤተልሔም በሕይወቷ ደስተኛ ነች፡፡ ከእሷ አልፎ ሌሎች ነገ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ትጥራለች፡፡ ያሉበት ድረስ ፈልጋ ታገኛቸዋለች፡፡ ተገናኝቶ ማውራታቸው ቤት ተዘግቶባቸው ለሚቀመጡ እንደ አያልቅበት ላሉ ትልቅ ተስፋ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ቤተልሔም የምታዝንለት የ25 ዓመቱ አያልቅበት ታደሰ፣ ድንክ መሆኑ የቁመት ጉዳይ ብቻ አልሆነም፡፡ አያልቅበት ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ አቃቂ በሰቃ አካባቢ ነው መገለል የጀመረው ገና ሕፃን ሳለ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ነገር በዘሬ የለም ያሉ አባቱ አያልቅበትን ማየት አልፈለጉም፡፡ ልጄ ብለው መቀበል አልቻሉም፡፡ እናትየው አያልቅበትና ስድስት ልጆቻቸውን ይዘው ለዓመታት ከኖሩበት የቀበሌ ቤት በባላቸው ተፈናቀሉ፡፡

ልጆቹን የማስተዳደር ኃላፊነት ሰው ቤት በሚሠሩት እናት ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡ ቁመቱ አንድ ሜትር ከአሥር ሳንቲ የማይሞላው አያልቅበት ደግሞ በተለየ እንክብካቤ ያስፈልገው ነበር፡፡ ሲያልፍ ሲያገድም እንደ ተዓምር የሚመለከቱትን ሲያልፍም በሚሰድቡት ልጆች ብዙ ያስቸግሩታል፡፡

በአካባቢው የሚገኝ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ለማስገባት የተደረገው ሙከራ ሞራል በሚሰብር ምላሽ ተጨናግፏል፡፡ በወቅቱ የነበሩ መምህራን አያልቅበት ጠረጴዛ ላይ መድረስ ስለማይችል መማር እንደሌለበት ወሰኑ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩም ልጆች ካዩት ይደነግጣሉ በሚል አያልቅበት በትምህርት ቤቱ ገብቶ መማር እንደማይችል ውሳኔ አሳለፉ፡፡ እናትየው ግን ተስፋ አልቆረጡምና በተገኘው አጋጣሚ ትምህርት ቤት ገብቶ እንዲማር ዕድሉን ይሞክሩ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ዕድል ቀንቶት አንድ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የሚማሩበት የትምህርት ፕሮግራምን ተቀላቀለ፡፡

ጓደኞች መስማት፣ መናገር፣ ማየት የተሳናቸው ነበሩ፡፡ ቁመቱ ከማጠሩ በስተቀር ሌላ ችግር አልነበረበትምና አስተማሪው በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ እንዲማር ዕድሉን አመቻቸችለት፡፡ 25 ዓመት በኖረበት ሰፈሩ እንደ አዲስ የሚያዩት ብዙ ናቸው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት የሚያደርሱትም እናቱ በቀሚሳቸው ደብቀውት ነው፡፡ በእረፍት ሰዓት እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች ወጥቶ እንዲጫወት አይፈቀድለትም፡፡ እሱም ድፍረቱ አልነበረውም፡፡ እናቱ ዴስኩ ላይ እንዳስቀመጡት ይውላል፣ ወደ ቤት የሚመልሱትም እሳቸው ናቸው፡፡

‹‹ልጄ አጭር ነው እንጂ ጉዳት የለበትም፤›› የሚሉት እናቱ፣ መንገድ ላይ ብዙ ነገሮች ስለሚያጋጥሙት ብቻውን መንቀሳቀስ እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ አያልቅበት ጓደኛም የለውም፡፡ የሚያውቁት ጓደኛው መሆን ቀርቶ ለስሜቱ እንኳ አይጠነቀቁም፡፡ ‹‹የፍቅር ጓደኛማ የማይታሰብ ነው፤›› የሚሉት እናቱ፣ ያዩት ሁሉ እንደሚስቁበት፣ እሱን እንደ ትንግርት ሲመለከቱ እንቅፋት መቷቸው የሚወድቁ  ሁሉ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ አያልቅበትም እንዲሁ ከእኩዮቹ ለመጎዳኘት ድፍረቱም እንደሌለው ይናገራል፡፡

ማኅበረሰቡ እንደ እሱ ላሉ ድንኮች ያለው አመለካከት በራሱ  እንዳይተማመን አድርጎታል፡፡ የሚደርስበት ጫና ትምህርቱን እንዲጠላና ከስምንተኛ ክፍል እንዲያቋርጥ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ስለራሱ እንኳ መናገር ይከብደዋል፡፡ ስለሱ የተሻለ መናገር የሚችሉት የ68 ዓመቷ እናቱ ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ብቻቸውን ብዙ ለፍተዋል፡፡ አያልቅበትን ለቁም ነገር ማብቃት ደግሞ መከራ ሆኖባቸዋል፡፡ ትምህርቱን አቁሞ ቤት በመቀመጡም አዝነዋል፡፡

ቤት ሲውል ምግብ ያዘጋጃል፣ ቡና ያፈላላቸዋል፣ ያፀዳልም፡፡ ራሱን ችሎ ለመኖር ትልቅ ምኞት ቢኖረውም ምንም ነገር ሠርቶ ለማደር አቅም ግን ያለው አይመስለውም፡፡ በአቅሜ የምሠራውን ሥራ ባገኝ ደስ ይለኛል ነው የሚለው፡፡ አቅሙ አይታየውም፡፡ ቤት ቀጥ አድርጎ መያዙ ብዙም ዋጋ ያለው አይመስለውም፡፡ ልጄ አይደለም ብለው ከቤት አውጥተው ለጣሉት አባቱ ብቁም አልሆነም፡፡

ቢያውቃቸው ደስ ይለው ነበር፡፡ ነገር ግን ገና የአምስት ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር የሞቱት ‹‹አይቼው ቢሆን ደስ ይለኛል፤›› ይላል፡፡

‹‹ብዙ ሰዎች ያልተማርን ቤት የቀረን ይመስላቸዋል፤›› የምትለው የ29 ዓመቷ ሠርካለም አየለ፣ ድንክ መሆናቸው ከብዙ ነገር ሊገድባቸው እንደሚችል የሚያስቡ እንዳሉ ትናገራለች፡፡ ሠርካለም ሆቴል ማኔጅመንትና የምግብ ዝግጅት ተምራለች፡፡ በአገር አቀፍ የፓራ ኦሊምፒክ ስፖርት ዘርፍ ዲስክስና አሎሎ ትወረውራለች፡፡ ቡና እያፈላችም ትሸጣለች፡፡ የራሷ መኖሪያ ቤትም አላት፡፡ ለድንኮች ባልተመቸ ዓለም ውስጥ ከብዙዎች የተሻለ መኖር ችላለች፡፡ የደረሰችበት ለመድረስ ብዙ መሰናክሎችን ብታልፍም ፈተናው ከባድ እንደሆነ አትዘነጋም፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊ ሆኜ መፈጠሬን የምጠላበት አንዱ አጋጣሚ ድንክ ሆኜ መፈጠሬ ነው፤›› ትላለች፡፡ ለድንኮች ባልተሠራ ዓለም ውስጥ በምንም ዓይነት አጋጣሚ ድንክ ልጅ መውለድ እንደማትፈልግ ትናገራለች፡፡ ድንክ የምትወልድበትን ዕድል ለማጥበብ ይመስላል ረዥም ወንድ ማግባትም የምትፈልገው፡፡ ነገር ግን ‹‹ከእኛ ጋር ደፍረው ትዳር ለመያዝ ብዙዎች ይፈራሉ፤›› ትላለች፡፡

‹‹እንደ ትልቅ ሰው ማሰብ የምንችል አይመስላቸውም፡፡ ሐሳባችንንም በጥርጣሬ ነው የሚያዩት፣ አይቀበሉንም፡፡ ሁሌ እንደ አዲስ ነው የሚያዩን፤›› የሚለው ገነነ አማረ፣ ወደዚህ ምድር ድንክ ማምጣት ኩነኔ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡ ለዚህም ነው እሱም ሆነ ሌሎች መሠሎቹ ሸበላ አግብተው ረዘም ያለ ልጅ ለመውለድ የሚፈልጉት፡፡ ድንክ ሆኖ በመፈጠሩ ብዙ ነገሮች እንደደረሱበት የሚያስታውሰው ገነነ፣ ከቤተሰቦቹ ተገልሎ ነበር ያደገው፡፡ ‹‹ያደግኩት አያቴ ጋር ነው፡፡ በምን ምክንያት አያቴ እንደወሰደችን አላውቅም፡፡ ከእናቴ ጋር ብዙ አልተዋወቅም ነበር፡፡ ለበዓል ትመጣለች ከእኔ ጋር ግን ብዙም አናወራም፡፡ ወንድሞቼንም አላውቃቸውም ነበር፡፡ እንደ ሌላ ሰው ነው የሚያስቡኝ፤›› ሲል ሁኔታዎችን ያስታውሳል፡፡

ተወልዶ ያደገው አርሲ አካባቢ በሚገኝ ገጠራማ ቦታ ነው፡፡ ከመላው ቤተሰቡ ብሎም በአካባቢው ድንኩ ገነነ ብቻ ነበር፡፡ እልፍ ሲል የሚያማትቡ ብዙ ናቸው፡፡ ነገሮች ተደማምረው በራሱ እንዲሸማቀቅ ሆኗል፡፡ ልጅ ሳለ እንግዳ ቤታቸው ሲመጣ ከጓዳ ወጥቶ ለማናገር ይሳቀቅ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሲወጣና ሲገባ እንደ ትንግርት የሚያየውን ማኅበረሰብ አልፎ ትምህርቱን እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ለመማር የሚያደርገው ጥረት የወላጅ ድጋፍ ስላልታከለበት በትምህርቱ ሊገፋ አልቻለም፡፡

ከወንድሞቹና ወላጆቹ ጋር የተቀራረበው በቅርቡ ነው፡፡ ‹‹ብዙ አነብ ስለነበር ራሴን ብቁ ማድረግ ችያለሁ፤›› ይላል፡፡ ከቤተሰቡ ከመቀላቀል በዘለለ አደባባይ ወጥቶ ፊልም እስከ መሥራት ደርሷል፡፡ ገነነ ስኬታማ ከሚባሉ ድንኮች አንዱ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ማኅበረሰቡ ለድንኮች የተመቸ እንዳልሆነ ይሰማዋል፡፡

ገነነ ገንዘብ ቢኖረውም የሚፈልገውን ዓይነት ልብስ መልበስ አይችልም፡፡ የጫማ ቁጥሩ 33 ሲሆን፣ 33 ቁጥር ያለው የአዋቂዎች ጫማ ለማግኘት ይቸገራል፡፡ ሱሪም ቢሆን በልኩ አያገኝም፡፡ ፋሽን ቦይ፣ ኪድስ የሚል ዓርማ ያላቸው የሕፃናት ጃኬትና ከኔቴራዎችን ይለብሳል፡፡ ድንኮችን እንደ እንግዳ ፍጥረት መመልከት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ መንገድ ላይ የሚያዩዋቸው እንደ ቁስ ሊነኳቸው፣ ሲያልፉም ሊስቁባቸው ይችላሉ፡፡ ወንድምና እህቶቻቸውም ሊያፍሩባቸውና ዝምድናቸውን ሊክዱ ይችላሉ፡፡