Skip to main content
x

የኦነግ ጦር አዲስ አበባ ካለው አመራር ጋር ያለውን ግንኙነት ማቋረጡን አስታወቀ

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ሲንቀሳቀስ የቆየው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጦር፣ አዲስ አበባ ካሉ የኦነግ አመራሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማቆሙንና ከፓርቲው መነጠሉን አስታወቀ፡፡

ጦሩ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ‹‹ይህ አዋጅ ከወጣበት ቀን መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ጊዜ አንስቶ፣ አዲስ አበባ ካሉ አመራሮች ጋር የማዘዝና የመታዘዝ ግንኙነት እንደሌለን እንገልጻለን፤›› ሲሉ አስታውቋል፡፡

‹‹ከጦሩ ጋር ያለን ግንኙነት ተቋርጧል፡፡ በዚህ ሁኔታ የእኛ ጦር ነው ብለን ለመምራት እንቸገራለን፤›› ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኦነግ አመራር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በመግለጫው እንደተገለጸው ግንኙነታችን ተቋርጧል፤›› ሲሉ የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቶሌራ አዳባ በተመሳሳይ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

በአስመራ ከመንግሥት ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም. ኤርትራ የሚገኘው የኦነግ አመራሮች 1,500 ያህል የጦር አባላት ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

ነገር ግን መንግሥትና ኦነግ ደረሱበት በተባለው የስምምነት ጭብጥ ላይ በተለይ በኦነግና በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) አመራሮች መካከል ልዩነትን ፈጥሮ ለወራት ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል፡፡

በዚህም ምክንያት ኦነግ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰውን ጦሩን ትጥቅ ማስፈታት ባለመቻሉ፣ ከመንግሥት ጋር የከረረ ልዩነት መፈጠሩ ይታወሳል፡፡

የከረረው ልዩነት ምክንያት በምዕራብ ኦሮሚያ ግጭቶች ተከስተው ጉዳት ደርሷል፡፡ ነገር ግን በጥር 2011 ዓ.ም. የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች በመካከላቸው የነበረውን ውጥረት ለማርገብ 71 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሩን ለመፍታት እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአባ ገዳዎች ኅብረትና በሽማግሌዎች አማካይነት በፓርቲዎቹ መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድና የኦነግ ጦር ትጥቅ እንዲፈታ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ነበር፡፡ ኦነግ ጫካ ያለውን ሠራዊቱን ጉዳይ ለአባ ገዳዎች ኃላፊነቱን መስጠቱን አስታውቆ ነበር፡፡ ከአባ ገዳዎች፣ ከምሁራንና ከሁለቱ ፓርቲዎች የተወከሉበት ኮሚቴ ኃላፊነቱን ወስዶ ለወራት ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን፣ በኮሚቴው ውስጥ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ኃላፊ አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ ተሳትፈውበት ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የኦነግ ከ800 በላይ የሚሆኑ የጦር አባላት ትጥቅ  መፍታታቸውን፣ የኦነግ አንድ አመራር ለሪፖርተር ገልዋል፡፡

ከ800 በላይ የሚሆኑት የኦነግ ጦር አባላት ትጥቅ ከፈቱ በኋላ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን አለማድረጉን ወታደሮቹንም በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ወታደራዊ ካምፕ መግባታቸው አግባብ እንዳልነበረ የኦነግ አመራሮች ሲናገሩ ነበር፡፡

የኦነግ ጦር ከመንግሥት ጋር የነበረውን ስምምነት በማክበር ጦርነት ቢያቆምም፣ በመንግሥት በኩል ተመሳሳይ ዕርምጃዎች አለመወሰዳቸውን ጦሩ በመግለጫው ገልጿል፡፡

በዚህም ምክንያት ቀሪው የኦነግ ጦር አባላትና አመራሮች ትጥቃቸውን ለመፍታት አለመፈለጋቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

‹‹አሁን ሁሉም እየታጠቀ ባለበት ወቅትና ይኼም እስካልቆመ ድረስ ትጥቃችንን አንፈታም፤›› ይላል መግለጫው፡፡

የኦነግ ጦር አዲስ አበባ ካለው አመራር ጋር ያለውን ግንኙነት በይፋ ማቋረጡን ተከትሎ፣ የራሱን አመራሮች መምረጡን ከምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሰባት ዕዞች በመላው ኦሮሚያ እንዳሉት የሚናገረው የኦነግ ጦር፣ ከሁሉም ዕዞች የተወጣጣ ጦሩን የሚመራ የላዕላይ አመራር ኮሚቴ መምረጡ ይነገራል፡፡

‹‹ሁለተኛ ተመልሰን ከመንግሥት ጋር የምንስማማው ያለ ምንም ጫና ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ዋስትና ሲኖር፣ እንዲሁም ጦራችንን በራሱ ማረፊያ አርፎ በኦነግ ከተመራ ብቻ ነው፤›› ሲል ጦሩ በመግለጫው ገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ ያለው ኦነግና አመራሩ በምርጫ ቦርድ እንደ አገራዊ ፓርቲ ለመመዝገብ እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን፣ ፊርማዎችን ለማሰባሰብ በቀጣይ ሕዝባዊ ጉባዔ እንደሚጠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡