Skip to main content
x
‹‹አብዛኞቹ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ችግራቸው ብዙ ነው››

‹‹አብዛኞቹ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ችግራቸው ብዙ ነው››

አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ ከተሾሙ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ወቅት የተቋሙን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ተቋሙ ስለሚገኝበት ደረጃ ሰፊ ግምገማ ማካሄዱን ይናገራሉ፡፡ ከመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት በግንባር በተካሄደው ውይይት ወቅትም፣ ተቋሙ ስለሚገኝበት ደረጃና ስለወሰዳቸው የለውጥ ዕርምጃዎች አብራርተዋል፡፡ የተቋሙ ሀብትና ንብረቶች ምን ያህል እንደሆኑ አይታወቅም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአሁኑ ወቅት የተቋሙን የሒሳብ ሥርዓት ከመቀየር ባሻገር ያሉት ሀብቶችና ንብረቶች ምን ያህል እንደሆኑ ማስጠናት እንደተጀመረም ገልጸዋል፡፡ የኃይል ማመንጨት፣ ማሠራጨትና ሰብስቴሽኖችን መትከል ላይ ተጠምዶ የቆየው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንም እንኳ ገቢ አመንጪ ድርጅት ቢሆንም፣ እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ እንደ ልማት ድርጅት እንዳልነበሩ አብራርተዋል፡፡ በአብዛኛው በብድር በሚያገኘው ገንዘብ ፕሮጀክቶችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውቀው፣ በአሁኑ ወቅት ግን የሚያመነጨው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ሪፖርት አቀራረብና አዘገጃጀት ሥርዓትን በመከተል የራሱን ገቢ በተገቢው መንገድ የሚያመነጭ የንግድ ተቋምነት ቁመና እንዲላበስ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል ሥራቸው ተቀዛቅዞ ወይም ተቋርጦ የነበሩ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችንና በግንባታ ላይ የነበሩ ፕሮጀክቶችን ወደ ግንባታ ሥራቸው እንዲገቡ፣ ኃይል ማመንጨት ያቆሙትም ወደ ኃይል ምርት እንዲገቡ መደረጉን ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ወቅት አብራርተዋል፡፡ በጠቅላላው አምስት ዋና ዋና የሚባሉ የለውጥ ሥራዎች በተቋሙ መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተለይ በገንዘብ ረገድ ተቋሙ ‹‹እንደ ኮርፖሬት ተቋም የሚሠራ፣ ሀብት የሌለው፣ የሚጠቀምባቸውን ማሽኖችን መጠገን የማይችል›› በማለት የገለጹት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ሥርዓቱን በመቀየር ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመከተል ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጓዳኝ በውስጣዊ አሠራሮቹ የወጪ ቆጣቢና የወጪ ቅነሳ ሥራዎችም ላይ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል፡፡ ከገንዘብ አያያዙና አሠራሩ አኳያ ሲታይ ‹‹መወገድ የነበረበት›› ተቋም ነው በማለት የገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ይህ ነው የሚባል ሀብትና ገንዘብ ሳይኖረው በብድር ሲሠራ መቆየቱ ለህልውና አስከፊ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በየወሩ እስከ 200 ሚሊዮን ብር ለደመወዝ በችሮታ እየተሰጠው ሲንቀሳቀስ የነበረ ተቋም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብርሃም (ዶ/ር)፣ ከአሁን በኋላ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎቹ ግን የሚሸጠውን የኃይል መጠን በስማርት ቆጣሪ እየለካ፣ ወይም በ40/60 የሽያጭ ዋጋ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርብበት አሠራር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሕዝቡ ላይ ጫና ሳይደረግ ነገር ግን ለአምራች ፋብሪካዎችና ለሌሎችም የሚቀርበው ኃይል ላይ መክፈል በሚችሉበት አቅም ልክ የታሪፍ ማስተካከያ እንደሚደረግ፣ መንግሥት ድርጅቱ ያለበትን የውጭ ብድር ዕዳዎች በመክፈል በኩል ጫናውን እንዲጋራው፣ የአገር ውስጥ አበዳሪዎችም የብድር ክፍያ ማራዘሚያ እንዲያደርጉለት ስምምነት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን በተገነቡት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና ማሰራጫ መስመሮች ላይ የጥገናና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በማካሄድ የኃይል አቅርቦቱን የማሻሻል ሥራ ይከናወናል ያሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ የለውጥ ሥራዎች ባይከናወኑ ኖሮ ‹‹ከጥቅምት ወር ጀምሮ ኃይል ማመንጨት ይቆም ነበር›› በማለት ተቋሙ ደርሶበት የነበረውን አሳሳቢ ሁኔታ አመላክተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለተቋሙ ሠራተኞች በማብራራት ከተቋሙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም ሪፖርተርን ጨምሮ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅራቸዋል፡፡ 

ጥያቄ፡- የመልካሰዲ ፕሮጀክት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለና እንቅስቃሴው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቢገለጽ?

ዶ/ር አብርሃም፡- የመልካሰዲ ፕሮጀክት ከመነሻውም የጥናት ችግር ነበረበት፡፡ በድጋሚ እንዲታይ ጥያቄ ስለተነሳበት፣ ሥራው እንዲቆም ተደርጎ በአማካሪ በኩል እንዲታይ እየተደረገ ነው፡፡ መሠራት የነበረበት ሳይሠራ በመቅረቱ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡

ጥያቄ፡- በተንዳሆና በሌሎችም አካባቢዎች የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች የኮንትራት ስምምነት ቢብራራ?

ዶ/ር አብርሃም፡- መንግሥት ለጂኦተርማል ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ትልቅ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተጀመሩትን እንደ አሉቶ ላንጋኖ ያሉትንና ሌሎችንም በማንቀሳቀስ የኃይል አቅርቦቱን ከልዩ ልዩ ምንጮች ለማሟላት እየሠራ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት በጂኦተርማል ኃይል ልማት መስክ ውል ታስሮ ሥራ ተጀምሯል፡፡ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት በኩል በግል አልሚዎች የሚለሙ በርካታ ፕሮጀክቶችም እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

ጥያቄ፡- የግልገል ጊቤ ሁለት ፕሮጀክት ከአሥር ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ኃይል የለም፣ ውኃም የለም፡፡ በዓመት ከ1.23 ሚሊዮን ብር በላይ ለናፍጣ እየወጣ ነው፡፡ የነዳጅ ኃይል ማመንጫ እየተባለ መጠራት ሁሉ ጀምሯል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም በችግር ውስጥ ኃይል ማመንጨቱ ከፍ ብሏል፡፡ የሠራተኛው የሥራ ላይ ደኅንነት ማስጠበቂያ ቁሳቁስ ችግር እንዳለ እስከ ላይ ባለው አመራር አካል ይታወቃል፡፡ ምንም የተደረገ ነገር ስለሌለ ይህ ጉዳይ እንዴት እየታየ ነው?

ዶ/ር አብርሃም፡- የጊቤ ሁለት ችግር የሰፋ ሆነ እንጂ አብዛኞቹ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ችግራቸው ብዙ ነው፡፡ አብዛኞቹ ራሳቸውን የረሱ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ ማሽነሪ ተክለው የወጡ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ተገቢ ካምፕ የሌለው፣ መንገድ በአግባቡ ያልተሠራለት፣ የውኃ አቅርቦት የሌለው፣ ኃይል እያመነጨ ለራሱ ግን ኃይል የማያገኝ ማመንጫ ነው ሲገነባ የቆየው፡፡ ችግሩ የሚጀምረው ቀድሞ ማሰብ ካለመቻል ነው፡፡ ኃይል ማመንጫ እንዲህ ያሉ አቅርቦቶች ያስፈልጉታል ተብሎ ገና ከጅምሩ አይታሰብም፡፡ ፕሮጀክቱን የሚሠራው ሌላ ሰው፣ ኃይል የሚያመነጨውና ኦፕሬሽኑን የሚሠራው ሌላ ሰው እየሆነ፣ ፕሮጀክቱ ይሠራ ያልነበረና የማያውቀው ሰው በኦፕሬሽን ሥራው ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ችግሮች እየተበራከቱ ቆይተዋል፡፡ ይህ እየተስተካከለ ነው፡፡ በኃይል ማመንጫዎች፣ በማሠራጫዎችና በሰብስቴሽን ሥራዎች ላይ መፍትሔ እየተሰጠ ችግሮችም እየተስተካከሉ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የኃይል ማስተላለፊያ ማማያዎች (ታወርስ) እየተሰረቁ እየተወሰዱ ነው፡፡ ይህንን ለማስቆም የተሠራው ሥራ ምንድነው? ኃይል ማመንጫዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ከዚያው ማመንጫ ጣቢያ ኃይል የሚያገኝ እየመሰለው ከግንዛቤ ችግር የተነሳ፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ለእኛ ምን አደረጉልን በማለት ኃይል ካልተሰጠን እያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ጣና በለስ አካባቢና አመርቲ ነሺ አካባቢ ያለው ችግር ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ምክንያት ችግር ገጥሟል፡፡ በሥራ አካባቢ የሠራተኛው ደኅንነት እንዲረጋገጥ ቢደረግ?

ዶ/ር አብርሃም፡- የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለራሳቸውም ሆነ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ኃይል መስጠት እንዲችሉ ከመጀመርያውም ታስቦበት ስላልተሠራ እንጂ ችግሩ የኅብረተሰቡ  አይደለም፡፡ ሕዝቡ ትክክለኛ ጥያቄ ነው ያነሳው፡፡ ኃይል ማግኘት አለበት፡፡ የኃይል ማመንጫዎች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ተጠቃሚ መሆን መቻል አለበት፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አካባቢ ለሚኖረው ማኅበረሰብ ኃይል እንዲቀርብለት ይደረጋል፡፡ መጀመርያውኑ ታቅዶበት የሚደረግ ነው፡፡ ሕዝቡ ጥያቄ በማንሳቱ ትክክል ነው፡፡  

ጥያቄ፡- በጣና በለስ ኃይል አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በመሠረተ ልማት ጥያቄ የተነሳ፣ የመጠጥ ውኃ ከሚገኝበት አካባቢ መጠቀም ስለተከለከለ ሠራተኛውም ተቋሙም ተቸግረዋል፡፡ ይህ ችግር ይፈታ፡፡ ከዚህ ባሻገር የእሳት ማጥፊያ ታንከር በማመንጫው ዋሻ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ ከፍተኛ ስርገት ወይም ሊኬጅ ስላለው ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ይስተካከል፡፡  

ዶ/ር አብርሃም፡- የውኃ አቅርቦት ችግሩ የመነጋገርና የመወያየት ችግር እንጂ፣ ሕዝቡ ለልጆቹ ውኃ አይከለክልም፡፡ እኛ ሥራችንን ማሳየትና ማስረዳት አለብን፡፡ ሕዝቡ ከምንሠራው ሥራ ተጠቃሚ እንደሆነ ማሳየት አለብን፡፡ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር እንፈታዋለን፡፡

ጥያቄ፡- በመለዋወጫ ዕጦት የተነሳ የአሼጎዳ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ከ50 በመቶ በታች አቅሙ እየሠራ ነው፡፡ አብዛኞቹ አየር መቅዘፊያ ተርባዮኖቹ አይሠሩም፡፡ ማሽኖቹን በአግባቡ ለማሠራት የሚረዳው ሮተን ግሪስ የተባለው ቅባትም የለም፡፡ ይህ ችግር በቶሎ ይፈታ፡፡

ዶ/ር አብርሃም፡- ለአምስት ዓመታት የመለዋወጫ ግዥ ሳይፈጸም ቆይቷል፡፡ በለስም፣ ጊቤም፣ ሌሎቹም መለዋወጫ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡ የማመንጫ ጣቢያዎቹ አንዴ ከተሠሩ በኋላ ዞር ብሎ የማየት ችግር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የመለዋወጫ ቀጥተኛ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችለንን ስምምነት ግድቦችን በመገንባት ከተሳተፉትና ኃይል ማመንጫዎቹን ከተከሉ መለዋወጫ አቅራቢዎች ጋር ስምምነት በማድረግ፣ በቀጥታ መለዋወጫዎቹን ማግኘት የምንችልበት ዕድል ይኖራል፡፡

ጥያቄ፡- በሥራው ጠባይ በየአካባቢው በፕሮጀክት ቦታ ለብዙ ጊዜ ሠራተኞች ስለሚቆዩ በቋሚ የመኖሪያ አካባቢ መታወቂያ ለማግኘት እየተቸገሩ ነው፡፡ ቤት ማግኘት የሚቻልበትና መደራጀት የሚቻልበት ዕድል ይመቻች፡፡

ዶ/ር አብርሃም፡- በኦፕሬሽን ሥራ ሥምሪት አካባቢ የስኬልና የግሬድ ወይም የደረጃ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ የኦፕሬሽን ሥራ ዘርፍ ከሌሎች የሥራ ዘርፎች እኩል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የደኅንነት ማስጠበቂያ ቁሳቁሶች ግዥ ሒደትና ሥርዓቱ ላይም ማሰተካከያ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በፊት በመስረከም ጥያቄ ቀርቦ ግዥው ከተፈጸመ በኋላ፣ ለሠራተኛው የሚደርሰው ግን ሰኔ ላይ ስለነበር ይህንን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ በሥርዓቱና በወቅቱ እንዲደርስ፣ ቢቻል ቀድሞ እንዲደርስ ለማድረግ ለግዥና ለፋይናንስ ክፍል አቅጣጫ ተሰጥቶበታል፡፡ በፀደቀ በጀት መሀል ስለገባን እንጂ በመጪው ዓመት ለአብዛኛው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት ነው፡፡ የቤት አቅርቦት ላይ እየሠራንበት ስለሆነ አሁን የምላችሁ ነገር የለም፡፡ የመታወቂያ ጥያቄ ግን የነዋሪነት ብቻም ሳይሆን፣ የመሥሪያ ቤቱ መታወቂያ እንደ መደበኛው መታወቂያ እንዲያገለግል ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ 

ጥያቄ፡- የገናሌ ዳዋ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በካሣ ጥያቄ ሳቢያ ለሦስት ዓመታት መጓተቱን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካሣው ተከፍሎ ግድቡም ውኃ ስለመያዙ ገልጸዋል፡፡ የተከፈለው ካሣ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር አብርሃም፡- የገናሌ ዳዋ ፕሮጀክት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገርና የተጠየቀውን ካሣም ተቋሙ እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ የገናሌ ዳዋ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የካሣ ክፍያ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ለሦስት ለዓመታት ግድቡ ውኃ ሳይዝ ቆይቷል፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የጋራ ምክክሮች በማድረግ ተቋሙ 2.9 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ እንዲከፍል፣ ነዋሪው ደግሞ የምንጣሮ ሥራዎችን እንዲያከናውን በመስማማት ግድቡ ውኃ እንዲይዝ እየተደረገ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የኮይሻ ግድብ በፋይናንስ እጦት ሳቢያ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶ/ር አብርሃም፡- አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በብድር ገንዘብ ሲገነቡ የቆዩ ናቸው፡፡ የኮይሻ ግድብም በአጭር ጊዜ ብድር ወይም በኮሜርሺያል ብድር እንዲገነባ ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም፣ የዚህ ዓይነቱ ብድር አሁን በመቅረቱ የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው በመምጣት መገንባት የሚችሉ አልሚዎች እንዲገነቡት ታቅዷል፡፡ በዚህ አግባብ መገንባት የሚፈልጉ ኩባንያዎች የሚመጡ ከሆነ እነሱን እናያለን፡፡

ጥያቄ፡- ተቋሙ የኃይል ማመንጫዎችን ከመገንባት ወጥቷል ብለዋል፡፡ ይህ ከመቼ ጀምሮ ነው ተግባራዊ የሚደረገው?

ዶ/ር አብርሃም፡- የኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን በራሳችን ማካሄድ አቁመናል፡፡ የነበሩትንም ሆኑ አዳዲሶቹን የሚገነቡት የግል ኩባንያዎች እንዲሆኑ በመወሰን፣ እኛ በኦፕሬሽን ሥራው ላይ እንድናተኩር ተደርጓል፡፡ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት የወጪ መጠኑን እየቀነሰና ገቢውን እያሳደገ በመምጣቱ ምክንያት፣ የፕሮጀክቶችን ወጪ በራሱ እየሸፈነ የመጣበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ የባህር ዳር - ወልዲያ - ኮምቦልቻ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ፣ የአዳማ ሁለት የማከፋፈያ ኔትወርክና የተጨማሪ ትራንስፎርመሮች ግዥ በራሱ የፋይናንስ ወጪ ለመሸፈን ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- ከመጋቢት እስከ መጋቢት ከሚለው የአንድ ዓመት የመንግሥት ቆይታ ጋር በማገናኘት፣ ይህንን ስብሰባ ማካሄድና ሪፖርት ማቅረብ ከሕግ አኳያ ጥያቄ አያስነሳም?

ዶ/ር አብርሃም፡- ምንም የሕግ ጥያቄ አያስነሳም፡፡ ከመጋቢት እስከ መጋቢት ተባለ እንጂ በሚያመቸን ወር መርጠን የለውጡን ውጤቶች ማሰብና መወያየት ምንም ዓይነት የሕግ ጥያቄ አያስነሳም፡፡ ውይይቱ የተጠራው እስካሁን ስለተሠሩ ሥራዎችና ስለተገኙ ውጤቶች ለመወያየት እንጂ፣ መደበኛ ሪፖርት ለማቅረብ አይደለም፡፡ መደበኛ ሪፖርትም አልቀረበም፡፡ በየሩብ ዓመት ወይም በግማሽ ዓመት ደረጃ የቀረበ ሪፖርትም የለም፡፡ የተደረገው ነገር ሠራተኛውም ተቋሙም በአንድ ዓመት የለውጥ ሒደት ውስጥ ተቋሙ ያሳየውን ለውጥና የሥራ እንቅስቃሴ እንዲያወቀው ነው የተደረገው፡፡ ከመጋቢት እስከ መጋቢት በሚል የተካሄደው ውይይት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየመጣ ያለው ለውጥ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑ የተገለጸበት ነው፡፡ ለውጡ የተቋሙ አመራሮች ሙያዊ ብቃታቸውን ተጠቅመው ተልዕኳቸውን እንዲያስፈጽሙ ዕድል ያገኙበት ነው፡፡ በዚህም ተቋሙ በፍጥነት ለውጥ እንዲያመጣ ትርጉም ያላቸው ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ገናሌ ዳዋና ሌሎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገው በለውጡ ምክንያት ነው፡፡ እነዚህን ለውጦች መዘከር ምንም ዓይነት የሕጋዊነት ጥያቄ  አያስነሳም፡፡