Skip to main content
x
የሩዋንዳ አስከፊ ታሪክ በኢትዮጵያ እንዳይደገም!

የሩዋንዳ አስከፊ ታሪክ በኢትዮጵያ እንዳይደገም!

እሑድ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. የሩዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲዘከር፣ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ይህ አሳዛኝ ታሪክ በኢትዮጵያ ምድር እንዳይደገም ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የዛሬ 25 ዓመት 800 ሺሕ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች በጥላቻ ባበዱ ሰዎች ቅስቀሳ ያለ ምሕረት በሩዋንዳ ምድር ተጨፍጭፈዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጥሪ ያደረጉላቸው የኢትዮጵያ፣ የቻድ፣ የኮንጎ፣ የጂቡቲ፣ የኒጀር፣ የቤልጂየም፣ የካናዳ መሪዎችና የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረት አመራሮች በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1994 በዚህ ሥፍራ ፈጽሞ ተስፋ አልነበረም፣ ዛሬ ግን ከዚህ ሥፍራ ብርሃን ያንፀባርቃል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምክንያቱም ሩዋንዳ ዳግም አንድ ቤተሰብ በመሆኗ ነው፤›› በማለት፣ 250 ሺሕ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ ሩዋንዳውያን በጅምላ የተቀበሩበት ሥፍራ ላይ ሆነው ንግግር አድርገዋል፡፡ ከጭፍጨፋው በኋላ በሩዋንዳ ሰላም ለማስከበር ከኢትዮጵያ የተላከው ሠራዊት ባልደረባ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጠቀሱት ፖል ካጋሜ፣ ሩዋንዳ ከምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደወጣች እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡ የሩዋንዳ ጅምላ ጭፍጨፋ ሲታወስ የሚተላለፈው መልዕክት፣ ይህ ዓይነቱ ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ድርጊት በየትም ሥፍራ እንዳይደገም የሚል ነው፡፡ ምኞት ብቻውን ምንም ስለማይፈይድ፣ አሁን በኢትዮጵያ እየታዩ ካሉ አሳሳቢ ድርጊቶች በመነሳት ሰከን ብሎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ የሩዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ በዚህች ታሪካዊት አገር መደገም የለበትም፡፡

የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ከልዩነቶቻቸው በላይ፣ መጪው ጊዜ ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ በመላ አገሪቱ ከሰላም ይልቅ አለመረጋጋትና ሁከት አድማሱን እያሰፋ ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በጋምቤላ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ግጭቶች ተከስተው ንፁኃን ተገድለዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸው ወድሞባቸዋል፡፡ በአንፃራዊነት ሰላም የነበሩት የሰሜን ሸዋና የወሎ አካባቢዎች ሰሞኑን ጥቃት ተፈጽሞባቸው ንፁኃን ተገድለዋል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ በአንድ አካባቢ የተከሰተ ግጭት ያስከተለው ጥፋት ትምህርት ሆኖ ሰላም መስፈን ሲገባው እየተባባሰ ከሄደ፣ ብዙዎች እንደሚፈሩት የእርስ በርስ ጦርነት ላለመነሳቱ ማስተማመኛ አይኖርም፡፡ የግጭት ሰለባ የሆኑም ሆኑ ሥጋት የገባቸው መንግሥት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ እንዲፈልግ ቢሹም፣ አሁንም ግጭቶች በተለያዩ ገጽታዎች እየተከሰቱ የአገር ህልውናን ጥርጣሬ ውስጥ እየጣሉ ናቸው፡፡ በግጭቶች መባባስ ምክንያት ፍራቻዎች ከመጠን በላይ እየጨመሩ፣ ከተስፋ ይልቅ ሥጋት ብዙዎች የሚጋሩት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲቀባበሉዋቸው የነበሩ የጋራ እሴቶች እየተናዱ፣ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ከፋፋዮች የአንድ አገር ልጆች መሀል የጠላትነት ግንብ እየተገነባ ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ ተከታዮችን ያፈሩ ግለሰቦች የዘር፣ የቋንቋ፣ የእምነትና የባህል ልዩነቶችን ከመጠን በላይ እየለጠጡ ለዘመናት አንድ ላይ የኖረ ሕዝብን እየነጣጠሉ ነው፡፡ ከልዩነቶቹ ይልቅ አንድነቶቹ የሚበልጡበትን፣ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና ስለሚጋራ ተጋብቶና ተዋልዶ ዘመናትን የተሻገረን ሕዝብ በግድ በመለያየት ሆድና ጀርባ እያደረጉ ያሉ እነዚህ ግለሰቦች፣ ሃይ የሚላቸው በመጥፋቱ በየደረሱበት ሥፍራ ሞትና ስደት ይከተላል፡፡ የጽንፈኝነትን መርዝ ኅብረተሰቡ ውስጥ እየረጩ መከፋፈልና ማባላት ልማድ ያደረጉ ልሂቃን ተብዬዎች ማንነት በግልጽ እየታወቀ፣ መንግሥት በሕግ አደብ ማስገዛት አለመቻሉ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ በለውጡ አማካይነት ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ በማስፈን የበደል ትርክትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም ሲገባ፣ በነጋ በጠባ ታሪክና ተረት በመቀላቀል አገር ማሸበር ነው የተያዘው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊያንን በማናቆር ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እየተሸረሸረ ነው፡፡ ይህም እንደ በፊቱ አብሮ የሚያኗኑር ሳይሆን ለዕልቂት የሚያመቻች አደገኛ ጉዞ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቢያንስ ባለፈው አንድ ዓመት ሰላም ሰፍኖባት የዕድገትና የብልፅግና ጎዳና መያዝ ሲገባት፣ በተለያዩ መሥፈርቶች ወደ ቁልቁለት እየተንደረደረች መሆኗን በርካታ አመላካቾች አሉ፡፡ በየቦታው በተሰራጩ የጦር መሣሪያዎች ምክንያት ለቁጥጥር አዳጋች የሆኑ ታጣቂዎች በዝተዋል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት ድንበር መጠበቅ ሲገባው፣ ግጭቶች በተከሰቱባቸው ሥፍራዎች መሰማራት ሥራው ሆኗል፡፡ ዘርን መሠረት ያደረጉ ግድያዎችና ማፈናቀሎች በመብዛታቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ የተጀመረውን ለውጥ ልዩነትን አክብሮ ማስቀጠል ሲቻል፣ የንግግርና የድርድር ባህል ባለመኖሩ ምክንያት አንድ ነገር ሲፈጠር በየጎራው መጋጨት ልማድ ሆናል፡፡ በአገሪቱ ትልልቅ ሰዎች የሌሉ ይመስል የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የመሳሰሉት እዚህ ግባ የሚባል ሚና የላቸውም፡፡ ከእነሱ ይልቅ በርካታ ተከታዮችን ያፈሩ የፖለቲካ አቀንቃኞች እሳት የመለኮሱንና የማባላቱን ድርጊት በስፋት ተያይዘውታል፡፡ የዴሞክራሲና የሲቪክ ተቋማትም እንደሌሉ ስለሚቆጠር መርዝ የሚረጩ በርክተዋል፡፡ አደጋውም የዚያኑ ያህል አስፈሪ ሆኗል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ዓይኑ ሥር አገር እንዳትጠፋ ጠንክሮ መሥራት ካልቻለ መጪው ጊዜ ካባድ ነው፡፡ እነዚህን እየጨመሩ የመጡ ግጭቶች ለማስቆም ግልጽ የሆነ ዕርምጃ ስለማይታይ ሥጋቱ እየጨመረ ነው፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ እንዲሁም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ ግን ከመንግሥት በላይ ራሳቸውን ያጀገኑ ኃይሎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ችግር የሚነሳው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ የሚስተዋለው ልዩነት ነው፡፡ ይህ ልዩነት ቢሸፋፍኑትም በተለያዩ መንገዶች እየተጋለጠ ነው፡፡ ሕዝብ የለውጡን ኢሕአዴግ ተቀብሎ እንዲያሸጋግረው የጠየቀው አገር ያልሆነ እጅ ገብታ እንዳትጠፋ ነበር፡፡ ነገር ግን የሥልጣን ሽኩቻው ያገረሸበት ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል የኢሕአዴግን ክፍተት በሚገባ እየተጠቀሙበት ያሉ ደግሞ ግጭቶችን እያባባሱ ሥልጣን ለመንጠቅ ያደባሉ፡፡ ከእነሱ ለሥልጣን ማድባት በላይ ግን የአገር ህልውና አጠራጣሪ እየሆነ ነው፡፡ አገሪቱንም ከዕለት ወደ ዕለት ወደ መጨንገፍ እየወሰዷት ነው፡፡ የጨነገፈ አገር ውጤት ደግሞ የጦር አበጋዞች የመፋለሚያ ሜዳ በመሆን፣ የለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን ያለው ተስፋ አንድ ብቻ ነው፡፡ እሱም የግልና የቡድን ተራ ፍላጎትን በመግታት አገርን ወደ ትክክለኛው ጎዳና ማስገባት ነው፡፡ ይህ ጎዳና የሚወስደው ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ነው፡፡ ይህ ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ከዚህ ውጪ አገርን አተራምሶ ሕዝብን እርስ በርሱ ማጫረስ፣ የሩዋንዳን አስከፊ ታሪክ መድገም ነው!