Skip to main content
x
በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ እንደሚኖር ተገለጸ
አቶ ፈጠነ ተሾመ

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ እንደሚኖር ተገለጸ

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሊኖር የሚችለውን ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ ግምት ውስጥ በማስገባት ኅብረተሰቡ በዚህ ወቅት የግብርና፣ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር በአግባቡ እንዲያከናውን፣ የኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኤጀንሲ ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በተለይም አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሩ የሚገኘውን እርጥበት በማሰባሰብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡ 

በሚያዝያና በግንቦት ወራት የሚኖረው የአየር ፀባይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲኦሮሎጂ ገጽታዎች ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከሩ ሊሄዱ እንደሚችሉ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰፊ ቦታዎችን ያካተተ እርጥበት አዘል አየር ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በመሆኑም አሁን እየታየ ካለውና ለወደፊቱ እንደሚኖር ከተተነበየው የውቅያኖሶች ሙቀትና የከባቢ አየር ገጽታዎች በመነሳት፣ በበልግ ዝናብ አብቃይና ተጠቃሚ ሥፍራዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተጠናከረ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በተለይም ለረዥም ጊዜ ደረቅ ሆነው የቆዩት የደቡብ ዝቅተኛ ቦታዎች (ቦረናና ጉጂ) አመርቂ ዝናብ እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአንፃሩ በሶማሌ ክልል ዞኖች ግን በአብዛኛው ደረቃማው የአየር ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ከሞላ ጎደል ተጠቁመው የነበሩ ክስተቶች የተስተዋሉ ቢሆንም፣ ከበልግ ወቅት ባህሪ የተነሳ የዝናብ ሥርጭትና መጠን ላይ መዋዠቅ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የወቅቱ ዝናብ በደቡብ ምዕራብ ክፍሎች (ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቤንች ማጂ፣ ከፋ) ላይ ከመደበኛው ጋር በተቀራረበ ጊዜ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ይሁንና ላለፉት ሁለት ወራት (የካቲትና መጋቢት) የነበረው ዝናብ በመጠንም ሆነ በሥርጭት ከፍተኛ መዋዠቅና ያልተስተካከለ ሥርጭት በብዙ ሥፍራዎች ላይ መስተዋሉን አክለዋል፡፡

ደረቃማ ቀናት በብዛት የተስተዋሉበት ወቅት እንደነበር የሚያመለክተው የኤጀንሲው መረጃ፣ የዝናብ መዋዠቅና ያልተስተካከለ ሥርጭት፣ እንዲሁም የደረቅ ቀናት መብዛት በዋነኛነት ምክንያቶች ሆነው የሚቀርቡት ደግሞ በደቡባዊው ህንድ ውቅያኖስ በተለይም በሞዛምቢክ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ከፍተኛ የባህር ላይ ሞገድ (Tropical Cyclone) ነው፡፡ በዚህ ወቅት በመደበኛ ሁኔታ ከባህር ወለል በላይ በአምስት ኪሎ ሜትር ለዝናብ መፈጠር ተጠናክሮ መገኘት የነበረበት የከባቢ አየር አመቺ ሁኔታ አለመገኘት መሆኑም ተገልጿል፡፡

በጥቅል ሲታይ ባለፉት ሁለት ወራት በብዙ የበልግ አብቃይና ተጠቃሚ ሥፍራዎች ዝናቡ በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተዛባ እንደነበር ያመለከተ ነው ተብሏል፡፡ በአንፃሩ በሰሜን ምሥራቅና በደቡብ ትግራይ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ በሰሜን ምሥራቅ አማራ (ሰሜንና ደቡብ ወሎ)፣ በተጨማሪም በኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ከፋና ቤንቺ ማጂ ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ስለመመዝገቡ መረጃው ያመለክታል፡፡ በዚህ ወቅት በተለይም በመጋቢት ወር የተሻለ ዝናብ ማግኘት የነበረባቸው የቦረናና የጉጂ፣ እንዲሁም የሶማሌ ዞኖች ለረዥም ጊዜ (ካለፈው የበጋ ወቅት ጀምሮ) ደረቅ ሆነው በመቆየታቸው፣ ትኩረት እንዲሰጣቸው መደረጉ ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ከበጋው ዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ በእነዚህ ሥፍራዎች የመጠጥ ውኃና የግጦሽ ሣር በበቂ መጠን ያለ መኖር በአርብቶ አደሮች ላይ ተፅዕኖ እንደነበረው ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ከበልግ ዝናብ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ለግብርና ሥራ እንቅስቃሴው አሉታዊ ጎን እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ሆኖም አሁን ያለውን ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ወቅታዊው የግብርና ሥራ በአግባቡ ማከናወን ያስፈልጋል ተብሏል፡፡