Skip to main content
x
የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሥልጣን እንዲለቁ የተጠራው ሠልፍ

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሥልጣን እንዲለቁ የተጠራው ሠልፍ

ለሦስት አሠርታት ያህል ሱዳንን የመሩት ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጠራ ሠልፍ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 ማብቂያ በዳቦ ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዓይነቱን ቀይሮ ፕሬዚደንቱ ላይ ቢያነጣጥርም፣ አልበሽር ሥልጣን ለመልቀቅ ስለመፈለጋቸው የሰጡት ፍንጭ የለም፡፡

የተቃውሞ ሠልፍ አቀናባሪዎችን የዶክተር ዩኒየን ኮሚቴን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በ2018 ማብቂያ ጀምሮ ከተካሄዱ ሠልፎች ሁሉ ይኸኛው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የተሳተፈበት ነው፡፡

የአገሪቱ ከተሞች በሙሉ በተቃዋሚዎች ተጥለቅልቀው መዋላቸውም ተነግሯል፡፡ የዶክተሮች ዩኒየንም፣ ፕሬዚደንት አልበሽር ከሥልጣን እንዲለቁ በሚል አብዮቱን በማቀጣጠል ላይ በነበሩ ንፁሐን ዜጎች ላይ ከዚህ ቀደም ፍትሕ ሲያጓድሉ፣ ሙስና ሲፈጽሙና ነፃነትን ሲደፍቁ የነበሩ የደኅንነት አካላት አፈሙዛቸውን አዙረዋል፣ ንፁሐንን ገለዋል ብሏል፡፡

በንፁሐን ዜጎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ አብዮቱን ያቀጣጥለው እንደሆን እንጂ እንደማይቀለብሰው ያስታወቀው የዶክተሮች ኮሚቴ፣ ፕሬዚደንቱ ከሥልጣን እስኪለቁ ተቃውሞውን እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡

የዶክተሮች ዩኒየን እንደሚለው፣ የደኅንነት አካላት ከተቃዋሚዎች ጋር በፈጠሩት ግጭት 26 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል፡፡

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሥልጣን እንዲለቁ የተጠራው ሠልፍ
ለ30 ዓመታት ሱዳንን የመሩት ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር

 

የየሙያ ማኅበራት ስብስብን የያዘው የሱዳን ፕሮፌሽናል አሶሲየሽን ደግሞ በጠራውና በተለይ የዶክተሮች ዩኒየን ፊት በወጣበት በዚህ የተቃውሞ ሠልፍ፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም በፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ቤተመንግሥትና በአገር መከላከያ ዋና ቢሮ በመገኘት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የደኅንነት አካላት በተለይ ካርቱም ላይ የተጠራውን ሠልፍ ለመበተን ሁለት ጊዜ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም፣ በመቶ ሺዎች ይገመታሉ የተባሉትን የአልበሽር ተቃዋሚዎች መበተን አልቻሉም ነበር፡፡

የደኅንነት አካላት ከሠልፈኞች ጋር ጥቂት ከተጋጩ በኋላ፣ መጋጨቱን ያቆሙ መሆኑን፣ ባሉበት ሆነውም ቤተ መንግሥቱንና የመከላከያ ቢሮውን እየጠበቁ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡

ፕሬዚደንቱ ሥልጣን እስኪለቁ ተቃውሞ አናቆምም ያሉ ተቃዋሚዎች፣ ብርድ ልብስና ፍራሽ በመያዝ በጎዳናዎች ላይ በመቀመጥ ተቃውሞ ሲገልጹ፣ ነጋዴዎች ደግሞ ምግብና ውኃ ሲያድሉ እንደነበር የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በኒውዮርክ የሚገኙ የሱዳን ኮሙዩኒቲ አባላት በዕለቱ ተመሳሳይ ተቃውሞ ሠልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን እንዲለቁም ጠይቀዋል፡፡

‹‹በሽር በዓለማቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መጠየቅ አለበት፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል፣ ሰብዓዊ መብት ጥሷል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በዳርፉርና በሱዳን ለብዙዎች ሞት አልበሽር ተጠያቂ ናቸው የሚሉት ተቃዋሚዎች ዓለማቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ከጎናቸው እንዲቆምም ጠይቀዋል፡፡

በሱዳን ከሦስት ወር በፊት ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሦስት የደኅንነት አካላትን ጨምሮ 32 ሰዎች መሞታቸውን የሱዳን መንግሥት ቢያሳውቅም፣ ዶክተሮችና ወትዋቾች ቁጥሩ ከዚህ በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

አልበሽር ሥልጣን ከያዙበት ካለፈው 30 ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከነዳጅና ከምግብ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ የሱዳን ደኅንነት አካላት የሚወስዱትን ዕርምጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚዩሽነርና አምነስቲ ኢንተርናሽናል አውግዘውታል፡፡

ሶሪያን፣ የመንንና ሊቢያን ለማይወጡት ቀውስ ከዳረጋቸው ዓረብ ስፕሪንግ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የሱዳን አብዮት፣ እንደ ግብፅና ቱኒዝያ ቶሎ ይርገብ አይርገብ ግልጽ ባልሆነበት በአሁኑ ሰዓት አልበሽር የሽግግር መንግሥት ለማቋቋምም ሆነ ሥልጣን ስለመልቀቅ የተነፈሱት የለም፡፡

ሆኖም የአገሪቱ የኋላ ታሪክ እንደሚያስረዳው ለረዥም ጊዜ የተደረጉ ተቃውሞዎች የአገሪቱን መንግሥታት ለመቀየር ኃይል ነበራቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1964 እንዲሁም በ1985 የተደረጉ ሁለት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በየወቅቱ የነበሩትን ወታደራዊ መንግሥታት ለመገርሰስ ችለዋል፡፡

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሥልጣን እንዲለቁ የተጠራው ሠልፍ
ከሦስት ወራት በፊት በጎዳና ላይ የተጀመረው ተቃውሞ

 

የሱዳን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መክሸፍ

የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት አልበሽር የ18 ግዛቶች አስተዳዳሪዎችን መሻራቸውንና ለዓመት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን አሳውቀው ነበር፡፡ ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አልሠራም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወም፣ ከታወጀ ቀናት ሳይቆጠር ለተቃውሞ የወጡት ሱዳናውያን፣ ተቃውሞዋቸውን በመቀጠል ቅዳሜ ዕለትም በርካቶችን አካተው ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

የአዋጁን መውጣት አስመልክቶ ገዥው ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፖለቲካ ስህተቶችን ለማረም ሳይሆን በአገሪቱ የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማረጋጋት እንደሆነ አሳውቆም ነበር፡፡