Skip to main content
x
አዲስ አበባን የፈተኗት አደገኛ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች
የሥጋት ምንጭ የሆኑት የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች

አዲስ አበባን የፈተኗት አደገኛ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች

የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦው እንደ ውኃ ጉድጓድ ክፍቱን ቀርቷል፡፡ በውስጡ እንደ የውኃ ኮዳ፣ ፌስታል የመሳሰሉ ቅራቅንቦዎች ሞልተውበታል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችና አንዳንድ መንገደኞች እንደ መፀዳጃ የሚጠቀሙት ቱቦው የተገኘውን ነገር የሚወረውሩበት ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ፍሳሽ የማስተላለፍ ሚናውን መጫወትም የተሳነው ይመስላል፡፡

አዲሱ ሠፈር ቀጣና አምስት ከሳሪስ ሲኒማ ወረድ ብሎ የሚገኘው መንደር ጎራ ሲሉ መግቢያ ላይ የሚቀበሎት የጉድጓዱ አስከፊ ጠረን ነው፡፡ ዙሪያ ገባውን ወደ ዝንብ መናኸሪያነት የቀየረው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሆነው ቱቦ ፀሐይ ጠንከር ሲል ጠረኑም ይበልጥ ይሰነፍጣል፡፡ በዚህ መንደር እልፍ ሲሉ የዝንብ መንጋ ይበተናሉ፡፡ መለስ ቀለስ ካሉ ደግሞ ጉንፋን ሊያተርፉ ይችላሉ፡፡ በቱቦው ዙሪያ ኑሯቸውን ላደረጉ እንደ አቶ ኑር አህመድ አብደላ ያሉ ግን ያለ ዕረፍት አስከፊውን ጠረን ሲምጉ ይኖራሉ፡፡

አቶ ኑር አህመድ በአካባቢው ጎጆ ቀልሰው ትዳር መሥርተው ሲኖሩ 21 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በቱቦው ከሚወጣው አስከፊ ጠረን በዘለለም ሌላ ሥጋት አጭሮባቸዋል፡፡ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ‹‹ጎርፍ ቤታችን ይገባ ይሆን ብሎ መሳቀቅ፤›› የሁልጊዜም ፍርሃታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በክረምት የሚጥለው ዝናብ ጎርፍ ሆኖ ከተለያዩ ቦታዎች አሸዋና ጠጠር ተሸክሞ ሲወርድ በደረቅ ቆሻሻ የተደፈነውን ቱቦ አልፎ መንደሩ ውስጥ ይተኛል፡፡ አንዳንዴም እስከ ዋናው መንገድ ድረስ አልፎ እንደሚሄድ ይናገራሉ፡፡ በየቤታቸውም ጎራ እያለ አደጋ ያስከትላል፡፡

ዓምና በክረምት ወቅት አካባቢው በጎርፍ መጥለቅለቁን ያስታወሱት አቶ ኑር አህመድ፣ ዘንድሮም ምንም እንኳን መንገዶች ባለሥልጣን ሁኔታውን ለማስተካከል ቢጥርም መፍትሔ አልሆነም፡፡ አሁንም ድረስ በሥጋት እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በተለያዩ ቦታዎች ተቀብረው ይሠሩ እንደነበር፣ በአሁን ሰዓት ግን የየአካባቢው በአንድ ተደርጎ በአቶ ኑር አህመድ ሠፈር በሚገኘው ቱቦ እንዲያልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም የተለመደው የክረምቱ ሥጋታቸው እንዲብስ አድርጓል፡፡ ለሚመለከተው አካል ሥጋታቸውን በተደጋጋሚ ቢናገሩም እስካሁን የተደረገላቸው ነገር እንደሌለ ገለጸው፣ አቤቱታ ማቅረብ ከጀመሩ ሦስት ወራት መቆጠራቸውን አስረድተዋል፡፡

አዲስ አበባን የፈተኗት አደገኛ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች
የከተማ ነዋሪና ድርጅቶች ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ከቻሉ የውኃ ማስወገጃ መስመሮች መደፈናቸው ያቆማል

 

የመንገድ መብራት የማያውቀው ሠፈሩ ክፍቱን ውሎ ከሚያድረው የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ ጋር ተደምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ አካላዊ ጉዳት የሚደርስበት አካባቢ ሆኗል፡፡ ሰዎች በጨለማ ሲደናበሩ ድንገት ቱቦው ውስጥ ወድቀው ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ አንዳንድ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያስታወሱት አቶ ኑር አህመድ ከዚህ ቀደም በቱቦ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ሦስት ሰዎች ሞተው መገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሳሪስ ሲኒማ አካባቢ ሱቅ ተከራይቶ መነገድ ከጀመረ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው አቶ ሀብታሙ አስፋውም፣ ዝናብ በዘነበ ቁጥር በንብረቴ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ሥጋት ላይ ነኝ ይላል፡፡ ‹‹በቅርቡ ቤት መቀየሬ አይቀርም›› የሚለው አቶ ሀብታሙ፣ ተከራይቶ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ የሚገኘው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ወደ ሱቁ ገብቶ ንብረቱን እንዳያበላሽ አፈር እየደለደለ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ያለው አማራጭ ሠፈሩን መልቀቅ ብቻ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ሥጋት የሆነበት ቱቦው ለሕፃናት ደግሞ በህልውናቸው ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፡፡ ቢሆንም በቱቦው ዙሪያ ሕፃናት ይጫወታሉ፡፡

የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሥጋት ምንጭ መሆን በአቃቂ ቃሊቲ አባ ሃና ሰፈርም የሚታይ ነው፡፡ የመንደሩ ነዋሪ ወጣት ጌታቸው ጎሳዬ የሚኖረው ቱቦው ያለበት አካባቢ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የጎርፍ መከላከያ ሥራ ስላልተሠራ ሥጋት ላይ እንደሆነ ‹‹ዓምና ምንም እንኳን እኛ ቤት ባይገባም ጎረቤት ገብቶ ነበር›› በማለት ገልጿል፡፡ በአካባቢው የተሠራው መንገድ ከመንገድ በላይና በታች በኩል የሚኖሩን ያላገናዘበና ለጎርፍ አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው ያስረዳል፡፡

እንዲህ ባለ ሁኔታ ሲኖሩ የጎርፍ አደጋ ላጋጠማቸው የመንደሩ ነዋሪዎች በወረዳና በክፍለ ከተማው ትብብር ጉዳት የደረሰባቸው ተለይተው የኮንዶሚኒየም ቤት እንደተሰጣቸው፣ ቀሪዎቹ ተጋላጭ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሊከሰቱ ከሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች ለማዳን የቅድመ መከልከል ሥራ ግን እንዳልተሠራ ወጣቱ ተናግሯል፡፡

‹‹ይህ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ቅድሚያ የመከላከል ሥራ መሥራት አለበት›› ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በተመለከተ የአዲስ አበባ መንገድ ባለሥልጣን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፣ በከተማዋ በጎርፍ ምክንያት የመንገዶች መጨናነቅና ምቾት ማጣት ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ችግር የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም የውኃ ማፍሰሻ መስመሮች (ድሬኔጅ) በቆሻሻ መደፈን ዋነኛው ነው፡፡ ክረምት በመጣ ቁጥር አንዳንድ መንገዶች በጎርፍ ለመጥለቅለቃቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የውኃ መውረጃ መስመሮች በቆሻሻ መደፈናቸው ከፍተኛ ድርሻን ይይዛል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የዛፍ ቁራጭ፣ ፍራሽና የመኪና ጎማዎች ሳይቀር በውኃ መፍሰሻ ፉካዎች ውስጥ ሲጣሉ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ቆሻሻን የውኃ መውረጃን መስመር ውስጥ በመጣል ቱቦው እንዲደፈን የሚያደርጉ የመዲናዋ ነዋሪዎችና ድርጅቶች ተጠያቂ ናቸው፡፡ ከመስመሮች መጥበብ ወይም ከመንገድ ውኃ ልክ ችግርም ሊሆን ይችላል፡፡ የውኃ መውረጃ መስመሮች በቆሻሻ መደፈን በርካታ ጉዳቶችን ይዞ ይመጣል፡፡ የቱቦው በቆሻሻ መደፈን ጎርፍ መንገዱን እንዲያጥለቀልቅና ውኃ መንገድ ላይ እንዲተኛ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህም ጊዜ መንገዱን በመቦርቦር ለጉዳት ይዳርጋል፡፡ የመንገዱን የአገልግሎት ዕድሜን ያሳጥራል፡፡

በክረምት እየገጠመ ያለው የመንገዶች በጎርፍ መጥለቅለቅ መፍትሔ ያለው በነዋሪዎች እጅ ጭምር ነው፡፡ የከተማ ነዋሪና ድርጅቶች ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ከቻሉ የውኃ ማስወገጃ መስመሮች መደፈናቸው ያቆማል፡፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ የውኃ ማስወገጃ መስመሮችንና ፉካዎችን ቢያፀዳ መንገዱ ላይ ውኃ እንዳይተኛ በማድረግ ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያግዛል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በኩልም ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የውኃ መውረጃ መስመሮች የውኃውን መጠን በአግባቡ ማስተናገድ እንዲችሉ መልሶ ግንባታ እያከናወነባቸው ይገኛል፡፡ በእርጅና ምክንያት ተበላሽተው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የመንገድ ዳር የዝናብ ውኃ መፍሰሻዎችንም ሙሉ ለሙሉ እየቀየረ ነው፡፡

በተጨማሪም የዝናብ ውኃ መንገድ ላይ እንዳይተኛ በአዲስ መልክ የመቀየርና የተዘጉ ፉካዎችን የመክፈት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ በገጹ ላይ ካሰፈረው ጽሑፍ መረዳት ተችሏል፡፡

በተመስገን ተጋፋውና በሔለን ተስፋዬ