Skip to main content
x

ለሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አዲስ የቦርድ አባላት ተሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አዲስ ሰብሳቢና አባላት ሰየሙ፡፡

በዚሁ አዲስ ምደባ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል፡፡

ከቦርድ ሰብሳቢው በተጨማሪ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የቦርድ አባላት እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመደቡት አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ እሸቱ አስፋው፣ አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ፣ አቶ ገለታ ሥዩም፣ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ አቶ ስንታየሁ ደምሴ፣  አቶ ደመላሽ ጌታቸው፣ አቶ ቢርቢርሳ ደምሴ፣ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እና አቶ ጌታቸው ረጋሳ ናቸው፡፡

ከእነዚህ 11 የቦርድ አባላት መሀል ሁለቱ ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች የተካተቱ ሲሆኑ፣ ከአካውንቲንግ ማኅበርም ሙያውን የሚወክሉ አንድ አባል ተሰይመዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አንድ ሰው በቦርዱ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሌሎቹ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከኦዲት አገልግሎት ኮርፖሬሽን የተወከሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡