Skip to main content
x
የፓርኪንሰን ማገገሚያና ማቆያ ማዕከል ሊገነባ ነው
አቶ ታሊሞስ ዳታ

የፓርኪንሰን ማገገሚያና ማቆያ ማዕከል ሊገነባ ነው

ፓርኪንሰን ሕመም መነሻው ያልታወቀ፣ ፈዋሽ መድኃኒት ያልተገኘለት ከባድ የአዕምሮ ነርቭ ሕመም መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ዓይነት በሽታ የተጠቁ ዜጎችን ለመታደግም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ከእንቅስቃሴዎቹም መካከል የፓርኪንሰን ሕሙማን ማገገሚያና ማቆያ ማዕከል የማቋቋም ውጥን ነው፡፡

የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሊሞስ ዳታ እንደገለጹት፣ ማዕከሉን ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት የተቀረፀ ሲሆን፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ የሆነ ቅድመ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

የማዕከሉ ግንባታ የፓርኪንሰን ሕሙማን የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ያለ ምንም ችግር የማግኘት ዕድል እንዲኖራቸው፣ ከዚህም ሌላ በፓርኪንሰንና በሌሎች ተዛማች በሽታዎች ዙሪያ አስፈላጊውን ምርምር ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ የፓርኪንሰን ሕሙማን ዕድሜያቸው የገፋ ስለሆነ ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ያጠቃቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የትም መንቀሳቀስ ሳያስፈልጋቸው ሁሉን አቀፍ የሕክምና አገልግሎት ከማዕከሉ ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት የሚያገኙት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ እንደሆነ ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡

እንደ አቶ ታሊሞስ ገለጻ፣ ማዕከሉ አስታማሚና አስጠጊ የሌላቸው፣ ሕሙማንና ቤተሰባቸው ጠልተዋቸው ለእንስሳ ከሚሰጠው ክብር በታች የሚኖሩ የፓርኪንሰን ሕሙማንን በማሰባሰብ እንዲጦሩበት የሚደረግበት ነው፡፡

ከዚህም ሌላ በፓርኪንሰን ዙሪያ ያተኮሩ ልዩ ልዩ መጻሕፍትና ሌሎች ጠቃሚ የሆነ መረጃዎች የሚገኙበት ማዕከል እንደሚሆን ከዋና ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፒየሮሎጂ ስፔሻሊስቱ ግርማ ዲልታታ (ዶ/ር) የበሽታውን መንስዔ ለማወቅ እንዳልተቻለ፣ ይሁን እንጂ በሽታው አጠቃላይ እንቅስቃሴን የሚያውክ የአንጎል ነርቭ ህዋስ በሽታ እንደሆነ፣ ዋና ዋና ምልክቶቹም የእጅ መንቀጥቀጥ፣ ምራቅ የመዋጥ ችግር፣ የለሃጭ መዝረክረክ፣ የሆድ ድርቀት፣ የመደበር ስሜት፣ እንቅልፍ የማጣት፣ በቀላሉ መበሳጨትና ከፍተኛ የሆነ የመርሳት ችግሮች፣ የመሳሰሉት ተጠቃሾች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

አብዛኞቹ የፓርኪንሰን ሕሙማን ወደ ሕክምና ተቋም እንደማይሄዱ፣ ቢሄዱም የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ተቋም ሲሆን፣ በዚህ ደረጃ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ስለሕመሙ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ ነው ዶ/ር ግርማ የተናገሩት፡፡

ፓርኪንሰን የሚፈውስ መድኃኒት ባይገኝለትም በሽታውን ማስታገስ የሚችሉ ስድስት ዓይነት መድኃኒቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋናዎቹ ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን፣ መድኃኒቶችም የማይገኙበት ጊዜ እንዳለ፣ በዚህም የተነሳ አንድ ፓርኪንሰን ታማሚ በአንድ ጊዜ መጠቀም የሚገባውን መድኃኒት ለሁለት ከፍሎ መጠቀም ግድ እንደሆነበት ነው ያመለከቱት፡፡

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አባስ ሐሰን፣ ‹‹ብዙ ባለሙያዎቻችን ፓርኪንሰን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ በዚህ በሽታ ዙሪያ ለሚሠራው ሥራ ጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ያገባናል የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ይሰጡ የነበረ የማገገሚያ አገልግሎቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁና ችግር ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ፣ ጤና ሚኒስቴር ተረክቦ ለማስተዳደር በሁለቱም መንግሥታዊ አካላት መካከል ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ጤና ሚኒስቴር ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች መረከብና ማስተዳደር ከጀመረ ለፓርኪንሰን ሕሙማን የማገገሚያ ማቆያ ማዕከል ግንባታና አደረጃጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከተወካዩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያና መሥራች ወ/ሮ ክብሯ ከበደ፣ ‹‹በእንክብካቤና ዕርዳታ ሥራችን መድኃኒት መግዛት ለማይችሉ 60 ችግረኛ ሕሙማን በየወሩ 400 ብር ይሰጣቸዋል፡፡ ለእነሱ ምቹ የሆኑ መፀዳጃ ቤቶች ተሠርቶላቸዋል፡፡ ለ200 ሕሙማን የሌሊት ልብስ፣ የመንቀሳቀስ ችግር ላለባቸው ተሸከርካሪ ወንበር (ዊልቸር) ተገዝቶ ተሰጥቷቸዋል፤›› ብለዋል፡፡   

እንደ ወ/ሮ ክብሯ ማብራሪያ፣ በፓርኪንስን የተያዘ ሰው ከሙሉ ጤነኛነት ወደ ሙሉ ሕመምተኛነት ይቀየራል፡፡ የፓርኪንሰን ሕመም ተግዳሮት በአንድ ግለሰብ ጤና ማጣታ ብቻ አያበቃም፤ ተፅዕኖው በቤተሰብ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሕይወታቸው ላይም ከፍተኛ ነው፡፡ ለአንድ የፓርኪንሰን ሕመምተኛ መድኃኒት የሚሰጠው፣ የሚያለብሰው፣ ምግብ የሚያቀብለውና ሌሎች የየቀኑን ውሎውን የሚከታተልለት አጋር ያስፈልገዋል፡፡