Skip to main content
x

የሙያ ተቋማትን እጀ ሰባራ ያደረገው ተግዳሮት

የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተቋቋመ ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በግዮን ሆቴል ተጠሪ ተቋማት በተገኙበት መድረክ የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል፡፡ በመድረኩ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ያሉትን አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡ ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) በተገኙበት በዚህ መድረክ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ የሚታዩት ችግሮችን በተመለከተ ጠለቅ ያለ አስተያየት ከተሳታፊዎች ተሰንዝሯል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ የሥራ ማነቆዎች በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩትም ሆነ ከሥሩ በሚገኙት ላይ የሚንፀባረቅ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ተልዕኮና ያሉበት ተግዳሮቶችን በተመለከተ በውይይቱ ተሳታፊዎች ዝርዝር ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ከመቋቋሙ በፊት የቴክኒክና ሙያ መምህራን ይመለመሉ የነበሩት ከዩኒቨርሲቲዎች ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የነበረው ችግር መምህራኑ ለቴክኒና ሙያ ትምህርት ብቁ የሚያደርጋቸው ክህሎት ሳይኖራቸው፣ እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያተኮረ ዝግጅት ሳይኖራቸው ዘርፉን መቀላቀላቸው ነው፡፡ በዚያው ልክም ተቋማቱን የሚመሩ ብቃት ያላቸው መሪዎች ማግኘትም ላይ ችግር ነበር፡፡ ይኼንን ክፍተት ለመሙላት ሲባል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካይነት የመቋቋሚያ ደንቡ ፀድቆ ኢንስቲትዩቱ ከዓመታት በፊት ተዋቀረ፡፡ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በቅድመና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም የሚያስተምራቸውን መምህራን በየዓመቱ እያስመረቀ ይገኛል፡፡ እስካሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን አስመርቋል፡፡

ይህም በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የነበረውን የመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ የማይናቅ መሻሻል ማምጣት የቻለ አጋጣሚ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ ክፍተት እንዳለ የሚናገሩት በኢንስቲትዩቱ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ኦፊሰር አቶ ሰላሙ ይስሐቅ፣ ‹‹አሁንም ያልደረሰንባቸው ተቋማት አሉ፡፡ በአገር ደረጃ 565 የመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎችን ከደረጃ አንድ እስከ አምስት የሚያሠለጥኑ ናቸው፡፡ ራሳቸውን የቻሉና በክልል መንግሥታት የሚተዳደሩም ናቸው፡፡ የግል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሲታከሉበት ደግሞ በአገሪቱ ያሉት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቁጥር 1,120 ገደማ ይሆናል፡፡ ለእነዚህ ተቋማት ሁሉ አሠልጣኞች የሚያቀርበው የእኛ ኢንስቲትዩት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት 8,714 ተማሪዎችን በስድስት ክልሎች በሚገኙት 15 ካምፓሶቹ ተቀብሎ እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ ካምፓሶቹ የሚያስመርቁት በቅድመ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲሆን፣ ኢንስቲትዩት ደግሞ በድኅረ ምረቃ ያስመርቃል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሁለት ካምፓሶች የአግሮ ፕሮሰሲንግ ትምህርት በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ማስተማርም ጀምሯል፡፡ ሥልጠናውን እየሰጡ የሚገኙ በሆለታና ውቕሮ የሚገኙት ሁለት ካምፓሶቹ ናቸው፡፡ ብዙም ያልተሠራባቸውን ነገር ግን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያቀኑ የሚችሉ የትምህርት ፕሮግራሞችን በኢትዮጵያ እንዲሠጡ ከማድረግ ባለፈም የቴክኒክና ሙያ አመራር (ሊደርሺፕ) ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ ተቋማትን የሚመሩ አካላት ሥርዓቱን አውቀው በብቃት ማስተዳደር እንዲችሉ የሙያና ቴክኒክ በድኅረ ምረቃ ያስተምራል፡፡ በሊደርሺፕ ሥልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመረቀው አምና እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰላሙ፣ ተመራቂዎቹ በየተቋማቱ ተመድበው እየመሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እስከ 76 ሺሕ መምህራን ለማፍራትም ዕቅድ ይዞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰላሙ፣ በዚህ ረገድ አጥጋቢ ሥራ አለመሠራቱን ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡ በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራም እስካሁን ማስመረቅ የተቻለውም ቢበዛ 15 ሺሕ ቢሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን በሙያ የማበልጸግ ራዕይ ያለውን ይኼንን ተቋም ተደራሽነቱን በምሥራቅ አፍሪካም ጭምር ለማድረግ በዕቅድ እየተሠራ ይገኛል የሚሉት አቶ ሰላሙ፣ ኢንስቲትዩቱ ለምሥራቅ አፍሪካ ኢንሺኤቲቭ የልህቀት ማዕከሉ ሆኖ እንዲያገለግል ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር የዝግጅት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል የታቀደው በስድስት ዲፓርትመንቶች ነው፡፡

ተጨማሪ ተልዕኮ ለመሸከም እየተሠራ ቢሆንም ዋነኛ ተልዕኮውን ከመወጣት አንፃር ግን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡ ‹‹እዚህ እየተሠራ ያለው በጀርመን ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ነው፡፡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ተማሪዎች ከእኛ ዘንድ እየመጡ ነው ልምምድ የሚያደርጉት፡፡ እኛ ጋ 70 በመቶ የትምህርቱ አካል የተግባር ልምምድ ነው፤›› ያሉት አቶ ሰላሙ፣ በአገሪቱ የሚገኙ የሙያ ተቋማትን መድረስ የሚችሉ መምህራን ማፍራት ላይ ካለው የአቅም ውስንነት ባለፈ ሌላም ዘርፉን የሚተናነቀው ችግር እንዳለም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ይኸውም በየክልሉ የሚገኙ የሙያና ቴክኒክ  ተቋማት በመምህራኑ የትምህርት ዝግጅት ልክ ማስተማር የሚያስችል ዝግጅት የሚያንሳቸው መሆኑ ነው፡፡ ተቋማቱ ለመማር ማስተማሩ ሒደት ወሳኝ የሚባሉ መሣሪያዎችና ማሽኖች የላቸውም፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት አስተያየት ሰጪዎች እንዳነሱትም፣ ባለው የመሣሪያ ችግር መሰጠት የሚገባቸው የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ሆነው የተቀረፁ የትምህርት ዓይነቶች እየተሰጡ አይደለም፡፡ በብረታ ብረት ትምህርት ዘርፍ ባለው የግብዓት አቅርቦት የግብዓት አቅርቦት ክፍተት የተነሳ ‹‹ብየዳ›› የመሳሰሉት የትምህርት ዓይነቶችን መስጠት ችግር እንደሆነም ተነስቷል፡፡ ባለው የአቅርቦት ችግር ይህንን አንድ ዓመት መሥራት ያልቻሉ ተቋማት እንዳሉም ታውቋል፡፡

የአሥረኛ ክፍል ትምህርት ካጠናቀቁት መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲገቡ የሚል አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ ቢሆንም ተቋማቱን ብቁ ማድረግ ላይ አለመሠራቱ ተወስቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ያጡ ወዳቂዎች የሚሰበስቡበት መሆን የለበትም የሚል ሐሳብም ተነስቷል፡፡ ወደ ሙያ ተቋማት መግባት ያለባቸው ፍላጎቱና አቅሙ ያላቸው የተመረጡ መሆን አለባቸውም ተብሏል፡፡

ተቋማቱን ብቁ ለማድረግ ወሳኝ የሆነው መሠረተ ልማት ሳይሟላ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማድረግ ከባድ ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ቴክኒክና ሙያ ለአገር ብልፅግና ዋነኛ ስትራቴጂ ቢሆንም ትኩረት የሚሰጠው ለቀለም ትምህርት ብቻ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አመዛኙ የትምህርት ክፍል የተግባር እንደመሆኑ በየጊዜው መገዛት ያለባቸው ግብዓቶች አዳዲስ መሣሪያዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይሁንና የሚያዝላቸው በጀት እንኳንስ አዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ጉዳት የደረሰባቸውን አስጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባትም የማይሆን እንደሆነ በመድረኩ ተነስቷል፡፡ መምህራንም መሠረታዊ ዕውቀት በማስጨበጥ ፈንታ የትምህርት አሰጣጣቸው ተማሪዎችን ፈተና ማለፍ እንዲችሉ ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑም ሌላው ጉዳት ነው ተብሏል፡፡ በመምህራን ላይ የሚታየውን የክህሎት ማነስ ለመቅረፍም በየጊዜው ሥልጠና ማግኘት የሚችሉበት አሠራር እንዲኖር ተጠይቋል፡፡

‹‹የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ስለሆነ ነው መንግሥት በስፋት እየሠራበት ያለው፤›› ያሉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም፣ በዘርፉ የራሳቸውን አሻራ ማኖር የቻሉ እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች የ100 ዓመት ታሪክ እንዳላቸው፣ በኢትዮጵያ ግን የሙያ ትምህርት ትኩረት ተሰጥቶት መሥራት ከጀመረ ሁለት አሠርታት እንኳ እንዳልሞላው ገልጸዋል፡፡ የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችም ካለው የልምድ ማነስ አኳያ ዘርፉ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያለው ጨቅላ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ጥንት የነበረው የሙያ ታሪካችን ከዘመናዊው ጋር ተቀይጦ ማደግ አልቻለም፡፡ ባለበት ነው የቀረው ለዚህ ነው የእኛ አገር የቴክኒክና ሙያ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሆነው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላትም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡