Skip to main content
x
በዱር ሰደድ እሳት የሚፈተኑ ፓርኮች
ሰደድ እሳት የተነሳበት የስሜን ብሔራዊ ፓርክ

በዱር ሰደድ እሳት የሚፈተኑ ፓርኮች

ሲያሻው ምድር ለምድር፣ ሲለው ከቋጥኝ ቋጥኝ፣ አሊያም ሣርና ዛፎችን እያያያዘ የመንቀልቀል ባህሪ ያለውን ሰደድ እሳት እንኳንስ በባህላዊ መንገድ በሠለጠነውም ቢሆን መመከቱ ቀናትን የሚፈጅ ነው፡፡ እሳቱ ተረትቶ እጅ እስከሚሰጥም ያገኘውን ሁሉ አመድ ያደርጋል፡፡ በተለይም በዱር የሚነሳ ሰደድ እሳት ጥፋቱ የአየር ንብረት ለውጥን ይቋቋማሉ፣ ለሕዝቡ ሳንባ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁ ደኖችን ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ የሚገኙ አራዊት፣ አዕዋፋትና ሰዎችም ላይ ጭምር ነው፡፡

ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ የካሊፎርኒያ፣ የአውስትራሊያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ታዋቂ ጥብቅ ደኖች ለቀናት ሲቃጠሉ፣ ቃጠሎውን ለመቆጣጠርም ከላይ በሄሊኮፕተር፣ ከታች በመኪና ኬሚካልና ውኃ ሲረጭ ማየቱ ተለምዷል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ላለ የሠለጠነ የዱር ሰደድ እሳት ቁጥጥር ባትታደልም፣ በመልክዓ ምድሯ በሚገኙ ጥብቅ ፓርኮች ውስጥ የዱር ሰደድ በየዓመቱ መከሰቱ ግን አልቀረም፡፡ 2011 ዓ.ም. ከገባ ወዲህ ደግሞ በፓርኮች ውስጥ እየተከሰተ ያለው የዱር ሰደድ እሳት ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የዱር ሰደድ እሳት የሚነሳው ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች የነበረ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ቆላ ከደጋ ሳይል አሉ የተባሉ ፓርኮችን ፈትኗቸዋል፡፡ ከጥብቅ ፓርኮች ውስጥ በመቶዎች ሔክታር የሚገመት ደን አውድሟል፡፡ በየዓመቱ ወቅት እየጠበቀ ክንዱን በፓርኮቹ ላይ የሚያበረታው ሰደድ እሳት፣ በፓርኮች ዙሪያና ውስጥ ለሚያደርሰው ውድመት መንስዔው ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ሰው ሠራሽ ስህተት እንጂ፡፡

ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት እስከ ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን ድረስ በስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ በባሌና አርሲ ተራሮች፣ በሃላይደጌ አሰቦት ፓርኮችና በሌሎችም በአንዳንዶቹ ሁለት ጊዜ፣ በአንዳንዶቹ አንድ ጊዜ የዱር ሰደድ እሳት ተከስቷል፡፡ የብዙዎቹ ከቀናት የኅብረተሰቡ ርብርብ በኋላ በቁጥጥር ሥር ቢውልም በባሌ ብሔራዊ ፓርክ የተዳፈነው እሳት ግን ገና ጢሱ አልነጠፈም፡፡ የባሌውን ሰደድ እሳት ለሞቆጣጠር ኅብረተሰቡ ርብርብ ቢያደርግም፣ ከሌላ አቅጣጫ በገንቦ እሳት ይዘው የሚደፉ ጥቂት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ኢዱልጥባ) አስታውቋል፡፡   

ቆላማ በሚባሉት በማጎ፣ በኦሞ፣ በጋምቤላና በስምጥ ሸለቆ ፓርኮች በጥር 2011 ዓ.ም. በተለያዩ ጊዜያት በተከሰተ ሰደድ እሳት ሙሉ ለሙሉ ባይወድሙም፣ እስካሁን ግምቱ ባልታወቀ መጠን ተጎድተዋል፡፡

በአብዛኛው ቆላማ ቦታዎችን ያጠቃ የነበረው የዱር ሰደድ እሳት፣ ከየካቲት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በደጋማ ሥፍራዎች የሚገኙትን አርሲ ፓርከ፣ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሦስት ዙር፣ በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከመጋቢት 19 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰደድ እሳቱ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፣ በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ አብዛኛውን የደኑን ክፍል አውድሟል፡፡ ይህ ፓርክ ለበርካታ ዝሆኖች መኖሪያ በመሆኑ፣ በእሳቱ ሳቢያ ዝሆኖቹ ወደ ኤርትራ ሊነጉዱ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ጥብቅ ፓርኮች ለሚከሰተው የዱር ሰደድ እሳት ምክንያቱ ምንድነው?

ከአየር ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ሰደድ እሳት በአብዛኛው በተፈጥሮ የሚነሳ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ዘንድሮ አብዛኞቹን የኢትዮጵያ ጥብቅ ፓርኮች ያጠቃውን የዱር ሰደድ እሳት አስመልክቶ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራና ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ሰለሞን መኮንን በሰጡት መግለጫ፣ በሁሉም ፓርኮች ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ መንስዔው ግለሰቦች ናቸው፡፡ በስሜን ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተው ሰደድ እሳት መንስዔ ግን እየተጣራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ‹‹ጥናት ቢያስፈልገውም በኢትዮጵያ ጥብቅ ቦታዎች ላይ ለሚከሰተው እሳት መንስዔ 100 በመቶ ግለሰቦች ናቸው፤›› ሲሉም አቶ ኩመራ ተናግረዋል፡፡

ከማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች በፓርኮች ውስጥና ዙሪያ መኖራቸውና ፓርኮች ውስጥ እርሻና ግጦሽ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ነዋሪዎች ሥራቸውን ለማከናወን ሲሉ የሚጠቀሙት እሳት ለፓርኮቹ ሰቀቀን ሆኗል፡፡

ከሰል ከማክሰል፣ ንብ ከማነብና ከማዕድን ፍለጋ ጋር በተያያዘ እንዲሁም አስታ የሚባለው ዕፀዋት አምስት ዓመት ሲሞላው ከብቶች ስለማይመገቡት እንዲቃጠልና ዳግም እንዲበቅል መደረጉ፣ ማሳ ለማዘጋጀት ሲባል ደንን በእሳት በማቃጠል መመንጠር፣ በሽታን ለመቆጣጠር በተለይ መዥገርና ሌሎች ተባዮችን ለማጥፋትና አደን ለማመቻቸት እሳት ጥቅም ላይ መዋሉ ምክንያቶች ለደኑ ሰደድ እሳት ምክንያት ናቸው፡፡

በፓርኮች ውስጥ እሳት እንዳይከሰት ቀድሞ ምን ተሠርቷል?

ኢትዮጵያ እንደሠለጠኑት አገሮች የቱሪስት መስህብ በሆኑት ፓርኮቿ እሳት ቢከሰት ከባህላዊው አሠራር በተለየ ልትከተለው የምትችለው አማራጭ የላትም፡፡ ስለሆነም በዱር የሚከሰት ሰደድ እሳት የሚሸነፈው የአካባቢው ማኅበረሰብ ለቀናት ያህል ከእሳት ጋር ግብግብ ከፈጠረ በኋላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት፣ የዱር እንስሳቱንና ዕፀዋቱን ሳይነጥቅ አያልፍም፡፡ ከዚህ ቀደም በባሌ ተራሮች ፓርክ እንዲሁም በሌሎች የዱር ሰደድ እሳት ለማጥፋት ሲሉ የተሰው ግለሰቦች መኖራቸውም አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ የዱር ሰደድ እሳትን ለመከላከል ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ የላትም፡፡ በፓርኮች ውስጥ አርብቶ አደሩም ሆነ አርሶ አደሩ እሳት የሚጠቀምና ፓርኮቹም ለእሳት ተጋላጭ መሆናቸው በመንግሥት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ስትራቴጂና ፖሊስ ነድፎ መንቀሳቀሱ ላይ ትኩረት አልተሰጠም፡፡ ይህም ለዓመታት ጥብቅ ፓርኮች እየተባሉ የሚጠሩትን የቱሪስት መስህቦች ለአደጋ አጋልጧል፡፡

በ1980ዎቹ መጀመርያ በተለይ ደግሞ በ1990 ዓ.ም. በአረና ደንን አካባቢ ከፍተኛ የደን ቃጠሎ መነሳቱን ተከትሎ በጥብቅ ደን ውስጥ እሳት እንዳይለቀቅ መመርያ ቢተላለፍም ቀጣይነት አልነበረውም፡፡

በባሌ ተራሮች ቀድሞ፣ በስሜን ተራሮች ደግሞ ዘንድሮ ለሕዝቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ ለእሳት ተጋላጭ የሆኑ ሥፍራዎችን በመለየት፣ እረኞች ምግብ ለማብሰል የሚጠቀሙት እሳት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ፣ አልጣሽ ፓርክ ላይ ደግሞ የእሳት መከላከያ መስመር መዘርጋት የተጀመረ ቢሆንም፣ ከእሳቱ ስፋት አንፃር ቀድሞ የመከላከሉ ሥራ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚገኙ ጥብቅ ፓርኮች በመኖርና አለመኖር መሀል ሠፍረዋል፡፡  

የዱር ሰደድ እሳት በ2011 ዓ.ም. በጥብቅ ፓርኮች ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው?

በአብዛኛዎቹ ጥብቅ ፓርኮች ዘንድሮ ሰደድ እሳት ተከስቷል፡፡ በሰው ሠራሽ ስህተትም ‹‹ኢትዮጵያ ፓርኮች አሏት ወይ?›› የሚል ጥያቄ እስከሚያስነሳ ፓርኮች አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በፓርክ ውስጥና ዙሪያ ከመኖሩና ከማረሱ ባለፈም ደን ከበዛ አራዊት ሕዝቡን ያስለቅቃል፣ ከብቶችም መኖር አይችሉም ከሚል አመለካከት ደኑን ይመነጥራል፣ ሆን ብሎ ይቃጥላል፡፡

ፓርኮች ለስሙ ጥብቅ ተባሉ እንጂ ከኑሮ ንኪኪ የተጠበቁ አይደሉም፡፡ በስሜንና ባሌ ተራሮች ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ሁሉም ጥብቅ ፓርኮች በሚያስብል ደረጃ በአደጋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በተለይ ደግሞ ከእርሻ ሥራ ጋር ተያይዞ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተው ሰደድ እሳት ዘንድሮ በተለያዩ ጊዜያት ተከስቷል፡፡ ባለሥልጣኑ እንደሚለው ደግሞ በጥናት መረጋገጥ ቢኖርበትም ከስሜን ብሔራዊ ፓርክ 342.9 ሔክታር መሬት፣ የቃፍታ ሽራሮ 70 በመቶ ያህል ደን ተቃጥሏል፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይ በአብዛኞቹ ፓርኮች የደረሰውን ጉዳት በገንዘብም ሆነ በዓይነት ለመናገር ቢያዳግትም፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ እንስሳት እንደሚያጠፋ፣ ዕፀዋት እንደሚወድሙ ይታወቃል፡፡ 

ወደፊት ምን ታስቧል?

በኢትዮጵያ በደጋም ሆነ በቆላ የሚገኙት ፓርኮች ለሰደድ እሳት ሙሉ ለሙሉ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በደኖቹ ውስጥ የሚገኙ ብርቅ የሆኑትና ያልሆኑት እንስሳት፣ አዕዋፋትና ዕፀዋትም እንዲሁ፡፡ በመሆኑም የእሳት አደጋ የተጋረጠባቸውን ፓርኮች ለመታደግ የእሳት ቁጥጥርና አያያዝ ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው፡፡

ሥርዓቱ እሳት ቀድሞ እንዳይከሰት፣ ከተከሰተም ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ግብዓቶችን የያዘ ሲሆን፣ የእሳት መከላከያ መስመሮችንና መሠረተ ልማት መገንባትም የሥራው አካል ይሆናል፡፡

ይህ ሥርዓትም ለመፋለም የሚያዳግተውን እሳት ለማጥፋት በየጊዜው ርብርብ የሚያደርጉ የየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ወታደሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎችንም የሚያግዝ ይሆናል፡፡ የሥርዓቱ መዘርጋት እንደ ከዚህ ቀደሙ ‹‹የእሳት አጥፉ ዘመቻና ጥሪ›› ሳይኖር ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ እሳት ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር የሚያስችል ይሆናል፡፡ ፓርኮች የሥራ አመራር ዕቅድ የላቸውም፡፡ ከዚህ ባለፈም የአቅም ክፍተት አለ፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑ በመግለጫው ተነግሯል፡፡

የኢዱልጥባ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በብሔራዊ ፓርኮች በተለይም በስሜን ብሔራዊ ፓርክ ዳግመኛ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት ከደቡብ አፍሪካና ከኬንያ የእሳት መከላከያ አውሮፕላን ለማስመጣት እየተሠራ መሆኑን ሚያዝያ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ለሁለተኛ ጊዜ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩልም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ በተመሳሳይ ዕለት በኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት መግለጫ እሳቱን ለማጥፋት የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሮች ከጎረቤት ኬንያ ለማስመጣት የባህልና ቱሪዝም ኒስቴ ውጭ ጉዳይ ኒስቴርና ጠቅላይ ኒስት ሕፈት ቤት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡