Skip to main content
x

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አዳዲስ የቦርድ አባላት ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን በተመለከቱ ጉዳዮችና በዚሁ ዘርፍ ቁጥጥር ለማድረግ ሥልጣን ለተሰጠው የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ አዲስ ቦርድ ሰብሳቢና የቦርድ አባላትን ሰየሙ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ምደባ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን በማገልገል ላይ ያሉት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው ተመድበዋል፡፡

እዮብ (ዶ/ር) የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ከሰኔ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቦርዱን በሰብሳቢነት ሲያገለግሉ በነበሩት አቶ አህመድ ቱሳ ምትክ ነው፡፡

ከቦርድ ሰብሳቢው በተጨማሪ የቦርድ አባላት እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመደቡት አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ እሸቱ አስፋው፣ አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ፣ አቶ ገለታ ሥዩም፣ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ አቶ ስንታየሁ ደምሴ፣ አቶ ደመላሽ ጌታቸው፣ አቶ ቢርቢርሳ ደምሴ፣ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እና አቶ ጌታቸው ረጋሳ ናቸው፡፡

ከእነዚህ 11 የቦርድ አባላት መሀል ሁለቱ ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች የተካተቱ ሲሆኑ፣ ከአካውንቲንግ ማኅበርም ሙያውን የሚወክሉ አንድ አባል ተሰይመዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አንድ ሰው በቦርዱ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሌሎቹ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከኦዲት አገልግሎት ኮርፖሬሽን የተወከሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡

የቀድሞው ቦርድ ሰብሳቢና የቦርድ አባላት ተሰይመው የነበሩት በሰኔ 2010 ዓ.ም. እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የቀድሞው ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ አህመድ ቱሳን ጨምሮ አቶ በየነ ገብረ መስቀል (የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ)፣ አቶ ዑመር ሁሴን (የግብርና ሚኒስትር) አቶ ሀብታሙ ሲሳይ (የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ)፣ አቶ ኦሌሮ ኦፒው (ኢንጂነር) (የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር)፣ ደግፌ ዱሬሳ (ዶ/ር) (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በአዲሱ ቦርድ ውስጥ ያልተካተቱ ናቸው፡፡

አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አዲስ የቦርድ ምደባ የተደረገው፣ በቦርዱ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው መንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊዎች በተለያየ ምደባ ወደ ተለያዩ ተቋማት በመዘወራቸው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ‹‹የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጃትና አቀራረብ›› አዋጅ ቁጥር 847/2007 መሠረት በቀዳሚነት የሕዝብ ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማን በመያዝ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 የተቋቋመና የመንግሥት ዓላማ አድርጎ የሚሠራ ነው፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካት እንዲችልም በኢትዮጵያ ውስጥ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያን የመምራትና የመቆጣጠር፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ብሔራዊ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችል የሙያ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ የመተግበር ኃላፊነቶች የተሠጡት ተቋም ነው፡፡

በአገር ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆኑ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት አፈጻጸም ደረጃዎችን የማውጣት፣ ባለሙያዎች የሚመሩበትን የሙያ ሥነ ምግባር መመርያ የማውጣት፣ የሙያ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ፈቃድ የመስጠት፣ የመመዝገብ፣ አፈጻጸማቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ ሪፖርት አቅራቢ አካላትን የመለየት፣ የመመዝገብና የሚያቀርቧቸው የፋይናንስ የኦዲት ሪፖርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና የማዘጋጀትና የመስጠት፣ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ ትምህርት ሥልጠና፣ እንዲሁም ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ድጋፎችን የማድረግ፣ የወጡ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመርያዎችና አግባብነት ያላቸው የመንግሥት ፖሊሲዎችን ተከትለው የማይሠሩ ባለሙያዎች፣ ድርጅቶችና ሪፖርት አቅራቢ አካላት ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊ ዕርምጃ የመውሰድና የመሳሰሉት ኃላፊዎችንም የያዘ ነው፡፡

በዚህ ኃላፊነት መሠረት በቅርቡ የፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስና ተያያዥነት ያላቸውን ሪፖርቶች አዘገጃጀትና አቀራረብ ጥራት ማስጠበቅ ‹‹IFSR›› የተባለውን አሠራር እንዲተገበሩ ማድረጉ አንዱ ነው፡፡ ሌሎች ተቋማትም ወደዚህ የሪፖርት አዘገጃጀት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ኦዲተሮችና የሒሳብ ባለሙያዎች የላቀ የሙያ አፈጻጸም ደረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ አገልግሎቶችን የጥራት ደረጃ ማስጠበቅ፣ የሙያው አፈጻጸም የሕዝብን ጥቅምን ለማስጠበቅ መዋሉን ማረጋገጥ፣ የባለሙያዎችን የሙያ ነፃነት ማስከበር ጭምር ኃላፊነት ያለበት ይህ ተቋም ቦርዱ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

በዋናነት ሙያው በአገር ውስጥ እንዲደራጅና እንዲስፋፋ የሚያግዙ አስፈላጊ ተቋማትን አቅም የማጎልበትና የመደገፍ፣ አገር በቀል የሆኑ ጠንካራ የሙያ ማኅበራት እንዲመሠረቱና እንዲደራጁ የማበረታታትና የመደገፍ፣ የአገር ውስጥ ጠንካራ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ እንዲኖር የመደገፍ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ብሔራዊ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ሲፒኤ) የሚሰጥበትን የሙያ ሥርዓተ ትምህርት የመቅረፅና የመተግበር፣ እንዲሁም ሪፖርት አቅራቢ አካላትና ኦዲተሮች ቦርዱ የሚቀበላቸውን ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ተከትለው እንዲሠሩ የመደገፍና የመቆጣጠር ተግባራት ያከናውናል፡፡