Skip to main content
x

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ሒደት የኢትዮጵያ ጉዞ

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በሚተገበርበት ወቅት ያስገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ጠቀሜታ ጎን ለጎን አሉታዊ ተፅዕኖዎችም እንዳሉት እየተገለጸ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይኼንን ስምምነት በተግባር ለመተርጎም በሕግ አፅድቃ መቀበሏንና ይህንኑ ሰነድም ለአፍሪካ ኅብረት ማስረከቧን ተከትሎ ከሚሰጡ አስተያየቶች መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው የሚሉት አመዝነው ተገኝተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ስምምነቱ ሲተገበር ኢትዮጵያን ሊያሳጣት የሚችላቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ አዘዘው (ኢንጂነር)፣ ይህ ስምምነት የጠቀሜታውን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖዎች ይኖሩታል ይላሉ፡፡ ከጠቀሜታው አንፃር ሲታይ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች አስተማማኝና ሰፊ የገበያ ዕድሎች እንዲያገኙ፣ አማራጭ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ ማስገኘቱ፣ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን መጨመርና ሌሎችም ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም ባሻገር የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር፣ ግጭትና አለመግባባቶችን የመቀነስ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡

በአንፃሩ አኅጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ያስከትላቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ አሉታዊ ተፅዕኖዎች መካከል ሲያብራሩም፣ የታሪፍ መቀነስን የሚያስከትል፣ የፖሊሲ ውህደትና የሕጎች መጣጣምን የሚጠይቅ በመሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንደሚያመጣ ያብራራሉ፡፡

የታሪፍ መቀነስ ማለትም የመንግሥት ገቢ መቀነስ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ፣ የፖሊሲ ምኅዳርን ማጥብበ፣ በኢንዱስትሪዎች ላይ የውድድር ጫና ማስከተልን ጨምሮ በርካታ ተፅዕኖዎች ይኖሩታል ይላሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ አሠሪዎች፣ በመንግሥትና በግሉ ማኅበረሰብ በኩል የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን አጠናክሮ መቀጠል፣ ታሪፍን በማንሳት ሒደት ላይ ድርድር ማካሄድ ከወዲሁ የሚጠበቁ ሥራዎች ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡

ይህን በተመለከተ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አገሮች ማለትም ጅቡቲ፣ ዛምቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌና ማላዊ ታሪፍ ማንሳት እንደማይችሉ አቋማቸውን እንዳስታወቁ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች አገሮች የተሰማሙበት በነፃ ቀጣናው ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ በሚገኙ አገሮች ውስጥ የገቢና ወጪ ሸቀጦች ላይ የሚጣለውን ታሪፍ እስከ 90 በመቶ የማንሳት ግዴታ ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያና የተጠቀሱት አገሮች ይኼንን ማድረግ እንደማይችሉ በማስታወቅ፣ ይልቁንም 85 በመቶ የታሪፍ ማንሳት ዕርምጃውን በአሥር ዓመታት ውስጥ ለመተግበር የሚችሉበት አካሄድ እንዲታይላቸው ጥያቄ እንዳቀረቡ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም አሥር በመቶ አሳሳቢ ለሚባሉ ሸቀጦችና አምስት በመቶ ቀረጥና ታሪፍ በልዩ ሁኔታ እንዲጣልባቸው በሚደረጉ ሸቀጦች ላይ እንዲጣል በሚለው ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ልዩነት ለኅብረቱ አስገብታለች፡፡ ሆኖም ከኅብረቱና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ጋር በተደረገ ውይይት፣ 90 በመቶ ሸቀጦች ከታሪፍ ነፃ የሚስተናገዱበት ሒደት በ15 ዓመታት ውስጥ እንዲሆን ለማድረግ ሰባቱ አገሮች ስምምነት ላይ የደረሱበት ውሳኔ ተቀባይነት የሚያገኘውና ውሳኔ የሚሰጥበት በመሪዎች ሰብሰባ ወቅት እንደሚሆን አቶ መላኩ ይገልጻሉ፡፡

የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣናዊ ስምምነት ውስጥ የበለጠ ተጠቃሚ ሆኖ ለመገኘት ኢትዮጵያ የዕቃዎች ሥሪት ምንጭ (Rules of Origin) የድርድር ሒደት ላይ በመሳተፍ በእያንዳንዱ ዕቃ ዝርዝር ላይ የሥሪት ምንጭ መጠንን መወሰን፣ የዕቃዎችና የአገልግሎት ንግድን የአቅርቦት መስጫ ዋጋ ማዘጋጀት፣ የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ጽሕፈት ቤት ማቋቋም ሒደት ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባታል ተብሏል፡፡ የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሪተሪያት ወይም ጽሕፈት ቤት ማቋቋም ሒደቱ ላይ በተለይም በጽሕፈት ቤቱ መቀመጫ አገርና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከወዲሁ ዝግጅትና ምክክር ማድረግ ለኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የተሰጡ የግሉ ዘርፍ አደራዎች መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡ የአፍሪካን የግሉ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚወክሉ የንግድ ምክር ቤት የማቋቋም ሒደት ላይ ተሳትፎ ማድረግ፣ ይህን ስምምነት የሚተገብሩ የተለያዩ ኮሚቴዎችንም ማቋቋሙ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ከሚጠበቁ ዕርምጃዎች መካከል ለአብነት የተጠቀሱት ናቸው፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መፈጠር እንዴት ተጠነሰሰ ስለሚለው መነሻ አቶ መላኩ እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት እ..አ ጃንዋሪ 29 እና 30 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና እንዲመሠረት በመሪዎች ተወሰኗል፡፡ እ..አ በጁን ወር 2015 የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በደቡብ አፍሪካ (ጆሀንስበርግ) 25ኛ መደበኛ ስብሰባው ሲያካሂድ፣ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለመመሥረት የሚረዳው ድርድር በይፋ እንዲጀመር ውሳኔ ተላለፈ፡፡ በተጨማሪም ድርድሩን ቢቻል እ... 2017 ለማጠናቀቅ እንዲሠራ ጉባዔው በመወሰን ሥራው እንዲፋጠን አድርጓል፡፡

አኅጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታ ከድርድር ሒደቱ ጀምሮ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲቻል በሦስት ደረጃዎች የተዋቀረ ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው በመሪዎች ደረጃ የተወሰነ በመሆኑ፣ ይህ ውሳኔ ለድርድሩ የፖለቲካ አመራርና አቅጣጫ ተቀምጦበታል፡፡ ይህም መዋቅር በንግድ ሚኒስትሮች ወይም በአባል አገሮቹ በሚወከሉ ሚኒስትሮች ደረጃ እንዲሆን የሚል ውሳኔም ተላልፏል፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት የንግድ ሚኒስትሮች በተጓዳኝ፣ በንግድ መስክ ኃላፊነት ያለባቸውን አካላት በቋሚ ጸሐፊነት የሚካተቱበትን ጨምሮ በንግድ ዘርፍ ኃላፊነት ያለባቸው ዳይሬክተር ጄኔራሎች ወይም ተመጣጣኝ የሥራ ኃላፊነት ያለባቸውን ይዞ የሚዋቀር የከፍተኛ ኃላፊዎች ኮሚቴ፣ ድርድሩን በዋናነት የሚያከናውኑ ዋና ተደራዳሪዎችንና ተለዋጭ ተደራዳሪዎችን የሚያካትት ዋናው የድርድር መድረክም በመዋቅሩ የሚጠቀሱት ናቸው።

የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታ ድርድር ውጤታማ በሆነ መንገድ ለዕቃዎች ንግድ ድርድር ስድስት የሥራ ቡድኖች እንዲቋቋሙ ተደር የምርት ሥሪት ምንጭ፣ የፀረ ንግድ መከላከያ ዕርምጃዎች፣ የሕግና ተቋማዊ ጉዳዮች፣ የጉምሩክ አሠራርና የንግድ ማሳለጫ ወይም ፋሲሊቴሽን፣ ለሳኒቴሽንና ለፎቶሳኒታሪ (SPS) እንዲሁም፣ ለንግድ ክልከላ የቴክኒክ ዘርፍና ታሪፍ ነክ ያልሆኑ የንግድ ክልከላዎችን የተመለከቱ  ሥራዎችን የሚያከናውኑ ቡድኖች ተመሥርተዋል፡፡

በተጨማሪም ለአገልግሎት ንግድ ድርድር ዘርፍ አንድ የሥራ ቡድን እንዲኖረው ተደርጓል። በዚሁ መሠረት እ.ኤ.አ ማርች 21 ቀን 2018 በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማ  በተካሄደ ስብሰባ፣ የነፃ ንግድ ስምምነቱ እስኪፈረም ድረስ አምስት የንግድ ሚኒስትሮች የተሳተፉባቸው ስብሰባዎች፣ አምስት የከፍተኛ ኃላፊዎች ስብሰባዎችና አሥር የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የድርድር መድረክ ስብሰባዎች እንዲሁም አምስት የቴክኒክ ሥራ ቡድኖች ስብሰባዎች መካሄዳቸውን በመግለጽ፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የእስከዛሬ ጉዞው ምን እንደሚመስል አቶ መላኩ አሳይተዋል፡፡

በተለይም የድርድር መድረኩ ሁለት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም የዕቃዎች ንግድ፣ የአገልግሎት ንግድ፣ የንግድ ግጭት መፍቻና አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተቋማዊ ማዕቀፍ ስምምነቶችን የተመለከቱ አካሄዶች ሲኖሩ፣ የአዕምሮአዊ ንብረት፣ የንግድ ውድድር፣ የኢንቨስትመነት ጉዳዮችም በድርድሩ ሁለተኛ ምዕራፎች ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡

በኪጋሊ የተፈረመው ስምምነትም የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተቋማዊ ማዕቀፍ፣ የዕቃዎች ንግድ፣ የአገልግሎት ንግድና የንግድ ግጭት መፍቻ ስምምነቶች ናቸው፡፡ የአዕምሮአዊ ንብረት፣ የንግድ ውድድር፣ የኢንቨስትመነት ጉዳዮች ከተያዘው ወር ጀምሮ ድርድር እየተደረገበት ይገኛል፡፡

የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ድርድር ላይ የኢትዮጵያ የተሳትፎ ሁኔታ፣ ምቹ ዕድሎች፣ ሥጋቶች፣ ቀጣይ ሥራዎችና የወደፊት አቅጣጫዎችን በሚመለከት አቶ መላኩ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በሁሉም የንግድ ሚኒስትሮችና የከፍተኛ ኃላፊዎች ስብሰባዎች፣ የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የድርድር መድረክ እንዲሁም የቴክኒክ የሥራ ቡድኖች  ስብሰባዎች ላይ ተሳታፊ ነበረች፡፡

ድርድሩ የተመራበት አግባብ በቀድሞው አቶ መኰንን ማንያዘዋል ሰብሳቢነት በአሁኑ ወቅትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ማሞ ምሕረቱ ዋና ተደራዳሪነት፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ አባላት የተሳተፉበት ነው፡፡ እንዲህ ካለው ጉዞ በኋላ ኢትዮጵያ 21ኛዋ አገር በመሆን ሳትወሰን፣ በዚህ ሳምንት በፓርላማ ያፀደቀችውን የስምምነት ሰነድ ለአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ አስረክባለች፡፡